Wednesday, May 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከመኮራመት የመውጣት ጉዞ

ከመኮራመት የመውጣት ጉዞ

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በኢትዮጵያ የታዩት ፅንፈኛ ብሔርተኛ ፖለቲካዎች ባበቃቀላቸው፣ በይዘት ፀባያቸውና ሄደው ሄደውም በአዘቃቀጣቸው ተመሳሳይ ናቸው ባያሌው፡፡ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በአማራ ውስጥ የታዩትን ፅንፈኝነቶች መገንዘብ በሌላው አካባቢም የተከሰቱትን ለመረዳትም ያስችላል፡፡ በኦሮሞም ሆነ በትግራይ ማኅበረሰብ ውስጥ ስለታዩት ፅንፈኝነቶች ከዚህ ቀደም በቀረቡ ጽሑፎቼ ብዙ ስላተትኩ ዛሬ ለንፅፅር ያህል ነካ ነካ ከማድረግ አልፌ አልዘልቅባቸውም፡፡ የዛሬው ዋና ትኩረቴ በአማራ ውስጥ በተከሰተው ላይ ነው፡፡

) የኦሮሞና የሌሎች ብሔርተኞች ብቅ ብቅ ያሉት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ውስጥ ሲሆን፣ የአማራ ብሔርተኝነት የተነሳው ግን ደርግ ከወደቀ በኋላ ነው፡፡ ብዙዎቹ የብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች የበደል ትርክታቸውን ከምኒልክ ጋር ያያይዛሉ፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት መጀመሪያ ደረጃ ላይ በሕወሓት ኢሕአዴግ አገዛዝ መጀመሪያ ላይ ከደረሰበት ጥቃት ጋር ያያያዘ ነበር፡፡ ሁሉም ብሔርተኞች በፀባያቸው ለእውነታዊነት መታመን አይገዛቸውም፡፡ የሕዝቦችን የተወራረሰና ለጋራ ጥቅም የመረባረብ ታሪክን የትርክት ዓይናቸው አያይም፡፡ ከገዥነትና ከገዥ መደቦች ጋር የተያያዘ የታሪክ ገጽታን ይሸሽጋሉ፡፡ የሚያተኩሩት በደል ላይ ነው፡፡ የበደል ትርክት ቢሳሳባቸው በማጋነን፣ በማስፋፋትና በፍልስፋ ያወፍሩታል፡፡ ዘመኑ ቢያንስባቸው ዘመኑን የትናየት ጥንት ድረስ ለመውሰድ ይደፍራሉ፡፡ የ16ኛው ክፍለ ዘመንን ይዞ በየአቅጣጫው የተዛመተው የኦሮሞ እንቅስቃሴ ዘመቻ፣ ጦርነት፣ ማርኮ መቀላቀል፣ የቦታ ይዞታ ማስፋት የነበረበት ሆኖ ሳለ ‹‹መስፋፋት›› በሚል ቃል ክንዋኔውን ለመግለጽ ብዙዎቹ የኦሮሞ ብሔርተኞች አይፈልጉም፡፡ ከዚህ ዘመን አንስቶ ኦሮሞ ያካሄደውን መሠረጫጨት የትልቅ አገር ግንባታ ወሳኝ ማኅበራዊ ንጣፍ አድርጎ ማየትማ እንዴት ሆኖ! ምክንያቱም ለበደል ትርክርትም ሆነ ለፅንፍ ፍላጎት የሚያዋጣው ፍሬ የለም፡፡ ይህን ጉድለት ለመሙላት አንዳንዶቹ የ16ኛውን ክፍለ ዘመን ጦርነት፣ ‹‹በኦሮሞ ላይ የተካሄደ ቀዳማዊ ወረራንና መገፋትን ለመቀየር የተካሄደ የነፃነትና ይዞታን የማስመለስ የድል ታሪክ›› አድርገውታል፡፡

የኦሮሞም የትግራይም ብሔርተኞች በኢትዮጵያ የገዥ መደቦች ታሪክ ውስጥ የነበራቸውን ሥፍራ በብሔር በደል ውስጥ አለባብሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአፄዎች የገዥነት ታሪክ ውስጥ ከአካባቢ ገዥዎች ጋር በጋብቻ መዘማመድ የተለመደ የፖለቲካ ሥልት ነበር፡፡ ከዝቅተኛ መደብ በባለሟልነት አድጎ ወደ መኳንንትነትና ጉልተኝነት መውጣት፣ ብሎም ከመሳፍንትና ከንጉሣዊያን ቤተሰብ ጋር በጋብቻ መቀላቀል ጭምር  ክፍት ዕድል ነው፡፡ አማራነት በጣም ቦርቃቃ ቃል ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ቅልቅል ያለበት ገዥነት ሁሉ መጠሪያው ‹‹አማራ›› ነበር፡፡ አማራ ወታደር ማለት ነበር፡፡ አማራ ክርስቲያን ማለት ነበር፡፡ ገዥዎች በነፍጠኝነት (በወታደርነት) የመለመሏቸው፣ ያዘመቷቸውና የተከሏቸው ሰዎች ከአንድ ማኅበረሰብ ብቻ የፈለቁ አልነበሩም፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከነበሩ ልዩ ልዩ ነገዶች የወጡ ነበሩ፣ እነሱ ሁሉ አማራ ተብለዋል፡፡ ክርስትና የተነሳ የትኛውም ገዥና ባለርስት ወይም ተራ ሰው አማራ በሚል ተጠርቷል፡፡ ክርስቲያን ነው ለማለት አማራ ነው ብሎ መናገር እስከ ቅርብ ጊዜ የነበረ አጠቃቀም ነው፡፡

የአማራ ብሔርተኞችም በስመ ‹‹አማራ›› የተጻፈና የተነገረን ሁሉ በአማራ ማኅበረሰብ ላይ መደፍደፍ እጅግ አሳሳች መሆኑን፣ በስመ አማራ በገዥነትና በገዥዎች መሣሪያነት ከብዙ ማኅበረሰብ የወጡ ሰዎች መሳተፋቸውን፣ በዚያው ዓይነት ከአማራም ማኅበረሰብ ውስጥ ገዥነቱንና የአስገዥነቱን ታሪክ በተከታታይ የተቋደሱ መኖራቸውን፣ ከዚያ ውጪ የአማራ ሕዝብ እንደማንኛውም ሕዝብ፣ ምናልባትም በባሰ ደረጃ፣ በድህነት ውስጥ ሲማቀቅ የኖረ ሕዝብ መሆኑን ማሳየት አልቻሉም፡፡ የብሔርተኝነት በደል የማነፍነፍ ፀባይ አልፈቀዳቸውምና እነሱም የትኛውንም የጭቆናና የምዝበራ ተሳትፎን ሸምጥጠው በአማራ ላይ የደረሰ በደልንና ግፍን ጥንት ድረስ ወስዶ በመከመር ተግባር ተጠመዱ፣ በተለይ ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ በኋላ፡፡

ከወዲህም ከወዲያ በሐሰትና በጡዘት የተሞላ ብሔርተኛ ውስወሳ በደራበት የሰላሳ ሁለት ዓመታት  ጊዜ ውስጥ የነበሩም በጣም ውስን እውነታዊ  የታሪክ ማስታወሻዎች የረባ ተፅዕኖ ማሳደር አልቻሉም፡፡ የታሪክ ባለሙያዎችም ሐሳዊ ግንዛቤን የሚገፉ ሥራዎችን ለሕዝብ ማበርከት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ጭቆና፣ ነፍጠኝነት፣ ገዥነትና በምዝበራ የመሞናሞን ጥቅም አማራ ላይ የተደፈደፈበት ትርክት ደመናውን እንደሞላ ለመቆየት ቻለ፡፡ የታሪክ ባለሙያነት ዱክትርና ደረጃ ቢደርስም፣ መረጃ እያጣቀሱ በመጻፍ ዘይቤ የምርምር ሥነ ምግባርን ለመጠበቅ ‹‹ቢሞክርም›› ለብሔረሰባዊ የማንነት ፖለቲካ በመታመን እስከተሰነከሰ ድረስ ሙያዊ ኃላፊነቱን መወጣት አይችልም፡፡

የፈለገ ሳይንሳዊ የመረጃ አጠቃቀም ቢኖር፣ በታሪክ አጻጻፍ ውስጥ የርዕሰ ጉዳዮችና የክንዋኔዎች መረጣ፣ የአሰዳደርና የአተረጓጎም ልዩነት መኖሩ አይቀርም፡፡ በመረጃ አመራረጥና አሰዳደር ላይ የፖለቲካ አቋምና ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ ጫና የሚያሳርፉበትና የማያሳርፉበትም ጊዜ አለ፡፡ በተረጋጋችና በዳበረች አገር ውስጥ የታሪክ ጽሑፍ እውነትን ለእውነትነቱ ሲባል እስከ መመርመር ድረስ ሊደላው ይችል ይሆናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለች በቅራኔዎችና በፀቦች ተጠምዳ በቆየች አገር ውስጥ ፀቦችንና ጥላቻዎችን እንደሌሉ ቆጥሮ ሙያተኛ ጸሐፊ የታሪክን ሁሉን የእውነት ገጾች ልዘርግፍ አይልም፣ ኃላፊነት የሚሰማው ከሆነ፡፡ መዘርገፍን ከደፈረም የማይታተምና ይፋ የማይሆን አድርጎ አስሮ ማቆየት ይገባዋል፡፡ በብሔተርኛ የጎራ ብሽሽቅ የተጠመደ ሰው ግን ምን ሙያተኛ ቢሆን የሙያና የማኅበራዊ ኃላፊነትን አጣጥም ማስኬድ አይሆንለትም፡፡ ጭራሽ ታሪክን እስከመፈልሰፍ ሊዘቅጥና የብሽሽቅ ረድፍ ውስጥ ገብቶ ሊገኝ ይችላል፡፡ ሀብታሙ መንግሥቴ ተገኘ የተባለና ‹‹በራራ ቀዳሚት አዲስ አበባ (1400-1887)›› የሚል መጽሐፍ የጻፈ ሰው ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም. አፍላ የውርክብ ጊዜ እንዲህ ያለ መጽሐፍ ይመጣል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ ጸሐፊው በርዕሱ ተገድቦ በመካከለኛው ዘመን በራራ የምትባል ከተማ ዛሬ አዲስ አበባ በሚባለው የሥፍራ ይዞታ ግድም ውስጥ ነበረች በሚል ማስረጃና ትንታኔው ተወስኖ አዲስ አበባ የእኔ ብቻ የሚል አንድ አቋምን ቢነቅፍ ኖሮ፣ ምናልባት በሁለት ጥግ ያሉ ግንዛቤዎችን ያናጠረ ግንዛቤ ለመፍጠር ድርሻ በኖረው ነበር፡፡ ሰውዬን ግን ለዚህ ኃላፊነት የሚበቃ አልነበረም፡፡ ፅንፈኛ ቁጣና በቀል ትፍተፋንና ወገራን ተያይዞ በነበረበት ጊዜ፣ የግለሰብ ጥፋት የብሔር ጥፋት ተደርጎ ጭፍን ጥቃት ያስነሳ በነበረበት ጊዜ፣ ፅንፈኛ ትርክትን በአፀፋ ፅንፈኝነት እስከመገዳደር ህሊና አጣ፡፡ የኦሮሞ ፅንፈኞች ‹‹በኢትዮጵያ/በሐበሻ መንግሥት ተወረርን…፣ ቅኝ ተያዝን…፣ ማንነታችን ላይ ጥፋት ደረሰ…›› እንዳሉ ሁሉ፣ እሱ ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ ነገዶችንና የአማራ ርስትን ኦሮሞዎች አስለቅቀውና ህልውና ደምስሰው የሠፈራ ቅኝ ገዥነት አካሄዱ…፣ የባህል ጄኖሳይድ አካሄዱ›› ባይ ሆነ፡፡ ሌሎች የብሔር ርስት እያሉ መሬት እንደቆጠሩ ሁሉ፣ እሱም ‹‹አፅመ ርስት›› እያለ ቆጠረ፡፡ የ16ኛውን ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ሥርጭት አንዳንዶች ‹‹የሐርነት እንቅስቃሴ›› እንዳደረጉት ሁሉ፣ ይኼኛውም ‹‹ሊቅ›› ከገላውዴዎስ ጀምሮ እስከ ምኒልክ ዘመቻ ያለውን ጊዜ ‹‹ይዞታ የማስመለስ›› ብሎ አለው፡፡ ሞጋሳንና ጉዲፈቻንም ‹‹የባህል ጄኖሳይድ›› አድርጎ አቀለመው፡፡ ይህን ሲያነቡ ብዙዎች የሰውየውን ጤንነት ሳይጠራጠሩ አይቀሩም፡፡ የብሔርተኝነት የፅንፍ ለፅንፍ ‹እንካ ሰላንቲያ› ባሪያ እስከ መሆን ድረስ አዕምሮ ሚዛን ሲጠፋው ጤናማነቱን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የአማራን ህሊና ያነቁ መስለው በመርዘኛ ድንቁርና መሙላትና ለጭፍን ጥቃት ማጋለጥ እንደምን ጤናማነትስ ይሆናል!

የዚህ ሰውዬ መጽሐፍ በ2012 ዓ.ም. እስከ ግንቦት ወር ሦስት ጊዜ ታትሟል፡፡ ከዚህ በመነሳት ለሰኔ 20ዎች 2012 ዓ.ም. የበቀል ጭፍጨፋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉ አያጠራጥርም፡፡ በተያያዝነው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ፣ ለኢትዮጵያ እብከነከናለሁ እያለ ኢትዮጵያን የሚበታትን መርዝ በመርጨት ይህንን ሰውዬ የሚስተካከልም ሌላ ጸሐፊ በበኩሌ አልገጠመኝም፡፡ የሰውዬው ሥራ ኢትዮጵያንም አማራንም የማይበጅ ከሆነ፣ ማንን ለመጥቀም ምን ለማግኘት ተለቀለቀ? ለዚህ ጥያቄ  ያገኘሁለት መልስ በብሽሽቅ እንዳበሸቃችሁኝ እኔም አብሽቄ አንጀቴን ላርስ የሚል ጥማትን ማርካት የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሰላምና ኢትዮጵያን ለብሽሽቅ እርካታ መሰዋት እንዲህ ነው!!

) የዚህን ሰውዬ መጽሐፍ በተመለከተ በ2012 ዓ.ም. ግንቦት ወር በማስታወሻዬ ካሠፈርኩት ግምገማ ጥቂቱን ቆንጥሬ ዛሬ ብቅ ያደረኩት፣ የተሻለ ቀን እየቀደደ ነውና ሕዝቦችን  ለማፋጀትና ኢትዮጵያን ለመበታተን መሥራት በብሔረሰብና በጎጥ የማይለይ ከሁሉም ሠፈር የወጡ ጨለምተኞችና ፅንፈኞች የተሳተፉበት መሆኑን ማሳየት ተገቢ መስሎ ስለታየኝ ነው፡፡፡

ከ2010 ዓ.ም. ወደ እዚህ ሌሎችም የአማራን በደል ጥንት ዘመን ድረስ እያጦዙ የጻፉ መጻሕፍት ወጥተዋል፡፡ እንዲህ ላሉ አጥፊ ትርክቶች ታዲያ ሰው እንደምን ልቡን ሊሰጥ ይችላል? ይህንንም ጥያቄ ለመመለስ ብንችል አንዳንድ ነገሮችን እናስቀምጥ፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት ይበልጥ ጨለምተኛ በሆነ አቅጣጫ ጦዞ መስፋፋት የቻለው ከለውጡ ወደ እዚህ በማንነቱ ላይ የደረሱ ጥቃቶች (ጨካኝ ግድያዎች፣ ማፈናቀልና ንብረት ማውደም) እየሰፉና ማቆሚያ እያጡ በመጡበት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ፀጥታና የሰው ደኅንነትን አስከብሩ›› የሚል ጩኸት ሰሚ ያጣ የቁራ ጩኸት መስሎ ነበር፡፡ መንግሥት በየቦታው ይከሰቱ የነበሩ ፀጥታ የመንሳት እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ተቆጣጥሮ ማስቆም የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ አልነበረም፡፡ ማውገዝ እንኳ፣ ‹‹የአማራ ነፍጠኞች አሽከር ሆነ መንግሥት›› የሚል ሾኬ ነበረበት፡፡ ዝም ማለትም፣ ‹‹መንግሥትማ የአማራ ጠሎች አገልጋይ…›› የሚል ውንጀላን ይጠቅም ነበር፡፡ ጥቃቱ ቀነሰ ሲሉት የሚሞቅ፣ በአንድ አካባቢ ተወሰነ ሲሉት ሥፍራዎች እያሰፋ የሚሄድ መሆኑ፣ ለጥርጣሬ አራጋቢዎችና ለሴራ ተንታኞች ፍትፍት ሆኖላቸው ነበር፡፡ የእነሱም ጨለምተኛ ትርጓሜ፣ በማያባራ ብሶት የዛለ ህሊናን ለመውረር ተመችቶት ነበር፡፡ በዚህ ላይ ዱክትርና ያገኘ ምሁር የጻፈው (ምሁራዊ ድምፀቱ የደመቀ) በጥናታዊ አጻጻፍ የተቀሸረ የበደል ትርክት ሲታከል እንዳለ ከመሰልቀጥ ውጪ ምን አማራጭ ይኖራል! ተራ ህሊናና ቀለም የቆጠረ የወጣት መኃይምነት ምሁሩን ልጠርጥር ቢል አቅምን ያላወቀ ከባድ ድፍረት ይሆናል፡፡ በክፍልፋይ ብሔርተኝነት ጎዳና ውስጥ ከነጎዱ ደግሞ ‹‹የደረሰብህ በደል›› ተብሎ የቀረበን ነገር እንዳለ መዋጥ እንጂ መጠየቅና ማበጠር ብሎ ነገር የለም፡፡ ብሔርተኛነት ውስጥ በተለይም ጨለምተኛ ፅንፈኛነት ውስጥ የወደቀ አዕምሮ ከልካይ የሌለበት (ሁሉም ሊጻፍበት የሚችል) ሰሌዳ ነው፡፡ አላፊ አግዳሚ ብቻ ሳይሆን ጠላትህ ነኝ ያለም የፈለገውን ሊቸከችክበት ይችላል፡፡ የሽንት ቤት ‹‹ፖለቲከኛ›› ኃፍረት ሳይሰማው ነውረኛ ነገር እየቸከቸከ ዘወር ይላል፡፡ የዛሬ ዘመን የሽንት ቤት ‹‹ፖለቲከኛ›› መሞነጫጨሪያ ደግሞ የኢንተርኔት ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችና የዩቲዩብ መድረክ ነው፡፡ በእነዚህ ላይ የሚወጡ መረን ነገሮች የቀለብተኛቸውን ህሊና ጥቀርሻ በጥቀርሻ ያደርጋሉ፡፡ ሰብዕና በፅንፍ አስተሳሰብ፣ በጥላቻ፣ በታመቀ ቁጣና የበቀል ጥማት ይታወራል፡፡

በጨለምተኛ ፅንፍ አስተሳሰብ የተወረረ ሁሉ የዚህ ዓይነት ጥቃት ደርሶበታል፡፡ ሁሉም ብሔርተኛ ፅንፈኝነት ሰብዕናን ፈቅፍቋል፡፡ አብሮ መኖር አይቻልም የሚል አስተሳሰብ አባዝቷል፡፡ ሰው ለአብሮ መኖር እንዳይጨነቅና አብሮ መኖርን እንዲያጠቃ አድርጓል፡፡ ሰው፣ ‹‹የእኔ ያልሆነ/ደመኛዬ›› ባለው ሕዝብ ላይ እንዲዘምት አድርጓል፡፡ ‹‹የእኔ›› የተባለ ሕዝብም ተዘምቶበታል፡፡ ወሬ እያቀበሉ፣ መንገድ እየመሩ ማስጠቃት ማስገደል ንብረት ማስወደምና ማዘረፍ ቀላሉ ጥቃት ነው፡፡ በጥቅሉ የእኔ ያሉትን ሕዝብ በጥላቻ እየወሰወሱ ለጥፋት ጦርነት ማስማራትና መላ አካባቢውን የሰላም ማጣት መናኸሪያ ማድረግ ትልቁ በራስ ላይ የመዝመት አብነት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያለማና የሚያጠፋ ጉዞን መለየት እስኪያቅት ድረስ የአስተውሎት መኮማተር ውጤት ነው፡፡ የጥላቻ ዋንጫው የሞላ ሁሉም ፅንፈኝነት አይደረግ እስከ ማድረግ፣ አይሰደብ እስከ መሳደብ ድረስ ጨዋነትን እንደሚበላ አሳይቶናል፡፡ ብሔርተኝነት ህሊናንና ስሜትን እየመዘመዘ የቱን ያህል ሊያብድና ሊቀጣ እንደሚችል ማየታችን ከሠፈርተኛነት ጥበት መውጣት የሚያስችለን ደጃፍ ላይ የመድረስም ጉዳይ ነው፡፡ በብሔርተኛነት ውስጥ ተኑሮ ከእንግዲህ በቃኝ ቢሉት ውስጥ ለውስጥ ለተወሰነ ጊዜ መወዝወዙ አይቀርም፡፡ ከፅንፈኝነትና ከጨለምተኝነት መላቀቅ ግን ከብሔተኝነት የመፋታት አንድ ዕርምጃ መሆን ይችላል፡፡

ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ጋር ኦነግ የሽግግር መንግሥት ተሳታፊ በነበረበት ጊዜ በውስጡ ምን ይፍተለተል እንደ ነበር መናገር ባይቻልም፣ ከሽግግር መንግሥቱ ተገፍቶ ከወጣ በኋላ በግንባሩ ውስጥ የደረሰው ቀውስ የአዎንታዊ ጉዞ አንድ ዕርምጃ ነበር፡፡ የኦነግ መሰነጣጠቅን ተከትሎ ነባር አስተሳሰቦችን የመተቸት ድፍረት መጀማመሩና  ብሎም በኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ የኦሮሞን ጥያቄ ለመፍታት ያለመ ክንፍ ከሌሎች በኢትዮጵያ ዙሪያ ከተሰባሰቡ ቡድኖች ጋር የትግል ቅንብር በባህር ማዶ መከሰቱ ተቀዳሚ የመታደስ ጉዞ ነበር፡፡ በአገር ውስጥም ከኦሕዴድ ሌላ ‹‹ኦሮሞ ከማን ነው የሚገነጠለው? ኦሮሞ የኢትዮጵያ ግንድ ነው!›› የሚሉ ብሔርተኛ ቡድኖች ሕጋዊ እንቅስቃሴ ሆነው መውጣታቸው ሌላው አዎንታዊ ዕርምጃ ነበር፡፡ ፅንፈኝነት ተጭኖት የነበረው የኦሮሞ ልሂቃዊ ትግል በዚህ አኳኋን ከፅንፈኝነት ርቀቱን እየጨመረ የ2010 ዓ.ም. ለውጥ አንዱ ዋና አማጪ እስከ መሆንና በለውጥ መሪነት ውስጥ ሁነኛውን ሚና እስከ መጫወት ይራመዳል፡፡

የለውጡ አምስት ዓመታት በጥቅሉ የኢትዮጵያን በፌዴራላዊ አንድነት መቀጠል የሕዝቦች ህልውና መቀጠል አድርጎ የሚያይ ፖለቲካና  ፅንፈኝነት በመሀላቸው ያሉ ቁርስራሽ አስተሳሰቦችንና ቡድኖችን ወደየ ጎራዎቻቸው የመሳብ ትግል የገጠሙበት ጊዜ ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ትንቅንቅ ኢትዮጵያን ወዳዱ ጎራ አገርን ከሞላ ጎደል ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ፅንፈኝነት በተቃራኒው በሥውርና በግልጽ ተደጋግፎ እየዶለተ ሲንቆራጠጥና ትንንሽ ማዕበሎች ሲፈጥር ቆይቶ የመጨረሻ የሞት ሽረት ግብግቡን አካሂዷል፡፡ በዚህ የሁለት ጎራ ትንቅንቅ ውስጥ ፅንፈኝነት ከተቆጣጠረውና ዋና ማዕከሉ አድርጎት ከነበረው ከአንድ አካባቢ በስተቀር ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ በጥቅሉ ‹‹ኢትዮጵያችን!›› ባለ አርበኝነት ውስጥ ተነቃንቀው ነበር፡፡ አካባቢያዊ ጥቅምና መብት ከኢትዮጵያ ወዳድነት ጋር የነበረው መጣጣምም የሚደንቅ ነበር፡፡ በተለይ አፋሮች ኢትዮጵያዊነትን የሚኖሩት በአፋርነት ውስጥ ሳይሆን፣ አፋርነትን የሚኖሩት በኢትዮጵያዊነት ውስጥ መሆኑ ልዩ ሞገሥ የሚሰጠው ነው፡፡

ፅንፈኝነት ፈሪሃ ፈጣሪን፣ ርኅራኄንና መተሳሰብን ቀረጣጥፎ በጥላቻና በጭካኔ እየሠገረ አይሠራ ነውር ሲሠራ የሚጎዳውና የሚፈራርሰው ንብረት ብቻ አይደለም፡፡ ሰውም ይረግፋል፡፡ ሰውም ሳይሞትም ‹‹ይፈርሳል››፡፡ በጥላቻ ተመንጥሮ ወደ ጨካኝ ግፈኝነት በመዝቀጥ መልክ የሚደርሰው የሰብዕና መንኮትና የግፍ ዕርምጃ ተጠቂዎች በሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ስብራት በአንድ ዓይን የሚታይ አይደለም፡፡ በቀዳሚው ላይ የደረሰው ጉዳት ባለ ሁለት ደረጃ የሰብዕና ጉዳት ነው፡፡ ሁለተኛ ሁኔታ ከግድያ ያመለጡ ሰዎችን ስቃይ የሚመለከት ነው፡፡ ከሁለቱም ጉዳቶች በስተጀርባ ሁኔታዎችን እያካረሩ ወደ እዚህ ያደረሱ የቅርብና የሩቅ ጊዜ ልሂቃዊ ጥፋቶች አይታጡም፡፡ የጀርባ ጥፋተኝነት መኖር ግን የግፍ ሥራን ግፍነት ማሳነሻ አይሆንም፡፡ ወጣም ወረደ፣ በሁለቱም በኩል የደረሱት የሰብዕና ጉዳቶች መፈወስ አለባቸው፡፡ ‹‹የሽግግር ፍትሕ›› የሚባለውና ከእሱ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተከታይ ሥራዎች ባያሌው የዚሁ አካል ናቸው፡፡

) በኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን አካባቢ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በተወራረሰ የብዝኃነት ቅንብር የሚረዳ አመለካከት ከሰረፀ ውሎ አድሯል፡፡ ከ2010 ዓ.ም. መጋቢት ለውጥ አንስቶ እስከዛሬ ያለው ጊዜ ለኦሮሞም ለሌሎች ማኅበረሰቦችም ፅንፈኝነት እየታገሉ፣ እያዳከሙ ኅብራዊ የአተያይ እነፃን የማስፋፋት ጉዳይ ነበር፡፡

ትግራይን በተመለከተም፣ የተደረሰው የሰላም ስምምነት የተሻለ ጊዜን ደቅኗል፡፡ ብሩህ ለውጥ እንደሚመጣም አልጠራጠርም፡፡ ይህንን ለመናገር የደፈርኩት የትግራይ የመከራ ልምድ የሚነግረኝን አምኜ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የሕወሓት ሰዎች ጎምለል ሲሉ ባይም በትግራይ ነባራዊና ህሊናዊ እውነታ ውስጥ መጎማለልን የሚያሞቅ ነገር የለም፡፡ ሲማቅቅ የኖረ ኑሮና ህሊና ከእንግዲህ ሌላ የጦርነትና የእብሪት አታሞ ለመስማት የተረፈ አቅም የለውም፡፡ ለዚያ የሚሆን አቅሙ ሙሉ ለሙሉ ጥንፍፍ ብሏል፡፡ ለእርጥባን መቁለጭለጭ አብሮ የተፈጠረ ይመስል ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ መቀጠሉ ቅስም ድረስ ተሰምቷል፡፡ በጎጠኛ/ብሔርተኛ ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ ሲደቀደቁ መኖርን፣ ለአንድ ቡድን መታመንን የሚያበረታታ ሁኔታ የለም፡፡ መሬቱም ሰውም የናፈቀው በልማትና በነፃ ህሊና መጎልበት ነው፡፡ መከራ መካሪ የሆነበት ጥሬ እውነታ ወደ ተሃድሶ የገባውንም ታጣቂ ከቡድን አገልጋይነት ነፃ ውጣ/ዳግም የቡድን ታጣቂ አትሁን ብሎ የሚቀሰቅስ ነው፡፡ በተሃድሶ ሒደት ውስጥ የቡድን ታማኝነት ውጨፎ እንዳገኘው ያኮፈኮፈ የጭቃ ምርግ ሊቅረፈረፍ ይችላል፡፡ ይህ እንደ አጋም ፍሬ የበሰለ ሁኔታ በደንብ ከተሠራበት፣ በትግራይ ወጣቶች ዘንድ ወደ ሌላ የጠመንጃ ድግስ የሚወስድ ድርጅታዊ ቋጠሮ ውስጥ ከመግባትምና መሣሪያ ሸሻጊ ከመሆን ይልቅ አጋላጭ መሆን ይቀላል፡፡ ለትግራይ ሕዝብ የህሊና ነፃነት የሚበጅ ከቡድናዊ ታማኝነት ነፃ የሆነ መደበኛ ፖሊስና አካባቢያዊ የመንግሥት አውታር ለማዋቀር የሚመቹ ጥሬ ሁኔታዎች ተሟልተዋል፡፡ በአጭር አነጋገር አሁን ያሉ ሁኔታዎች የትግራይን ሕዝብ ነፃ እንቅስቃሴና የለውጥ ፖለቲከኞችን የሚያግዙ ናቸው፡፡ ጥሬ ሁኔታዎቹ እንኳን የለውጥ ፖለቲከኞችን አሮጌዎቹንም ብታውቁ እውቁበት የሚል እንፋሎት የሚያመነጩ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ሁኔታዎቹን አሮጌ ፖለቲካ ለመተክተክ ተጠቀሙባቸው ማለት አይደለም፡፡ የአርባ ምናምን ዓመት ልምድ የተከተከውን ቡድነኝነት አሁን ልተክትክ ማለት ጊዜ ከማጥፋት አይለይም፡፡ ዕድሜ ያለው የሕዝብ ከበሬታ የሚገኘው በአውራጃ ለመበጣጠስ መንገድ መሪ ሳይሆኑ፣ የትግራይን ሕዝብ አንድ ላይ በኢትዮጵያ ግቢ የሚያሰባስብ የለውጥ ትልም ይዞ የሕዝብ ሕይወትን በመለወጥ ላይ ማተኮር ነው፡፡

የአማራ ሕዝብ የነበረበት ሁኔታ ግን ውስብስብ ነበር፡፡ በ1984 ዓ.ም. ብቅ ያለው ብሔርተኝነቱም በብዙ ጎኑ ታክቲካዊ (በደልን ለመቃወም በአማራነት መሰባሰብን በጊዜያዊነት ለመጠቀም የሞከረ) ነበር፡፡ ሞቅ ሞቁ ከበረደም በኋላ በኢትዮጵያዊነት አደረጃጃት ውስጥ ፈዞ ቆይቷል፡፡ በለውጡ ዋዜማ አማሮች በአገዛዙ ላይ የነበራቸውን የተቃውሞ ትግል ከኦሮሞች ትግል ጋር ማዛመድ ችለው ነበር፡፡ ‹‹የሚፈሰው የኦሮሞ ደም የእኔም ነው!›› ባዩ ድምፅ ለጋራ ትግሉ ትልቅ ትርጉም ነበረው፡፡ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን የሚተካ የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫው፣ ለውጥ ወዳሰቡት ሰዎች ሊያዘነብል የቻለውም በብአዴንና በኦሕዴድ ሰዎች ጥምረት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚያም በኋላ ለውጥ ወጣኞቹ ከፋም ለማ አብረው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በብሔር እያለኮሱ ትርምስ ከዩኒቨርሲቲ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከማባዛት አንስቶ በብዙ አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች በተለይ አማራን በማጥቃትና በማፈናቀል ያደርሱት የነበረው ማቆሚያ ያጣ ጉዳት፣ ለአማራና ለኦሮሞ የትግል አጋርነት ቅንቅን ሆኖ ነበር፡፡ የአማራን ሕዝብ በኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያ የመተማመንን ተስፋ አበልዟል፡፡ ‹‹ይህ ሁሉ ማባሪያ ያጣ የጭካኔ ጥቃት ምን በድዬ ምን አጥፍቼ? ከሌላው ጎስቋላ ሕዝብ በምኔ ተለይቼ…?›› በሚሉ ዕንቆቅልሾች ህሊናው ሲበረበር ቆይቷል፡፡ ስሜቱ ሐዘንና እህህን ለብሶ ቆይቷል፡፡ ‹‹ከሕወሓቶች ጋር የኦሮሞ ብሔርተኞች እያሴሩብህ ነው! የዓብይ አህመድ መንግሥት የሴራው አካል ነው!…›› የሚሉ ጨለምተኞችን እምቢኝ ለማለት የሚያበቃ መረጃና የፀጥታ መከታ አልነበረውም፡፡ መንግሥት አንዱ ጋር ዕርምጃ ሲወሰድ በሌላ በኩል ጥቃት ብቅ ይላል፡፡ ዘላቂ ዋስትና ህልም ሆኗል፡፡ በዚህ ግራ አጋቢ ሁኔታ ውስጥ የአማራ ህሊና በጨለምተኞች ትርጓሜ ከመመዝመዝ ማምለጫ አልነበረውም፡፡ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጦርነት ከተከፈተ በኋላ፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ለኢትዮጵያ ሆ ብሎና በነገዪቱ ኢትዮጵያ ላይ ተማምኖ የተጋድሎ ድርሻውን በሚወጣበት ጊዜ እንኳ (ከሞላ ጎደል በጦርነቱ ዓመታት ውስጥ) በስመ አማራ በተለያየ አካባቢዎች ይደርስ በነበረ ጥቃት ህሊናና ስሜቱ ከጊዜ ጊዜ ይቆስል ነበር፡፡ በተለይ በሁለተኛው ጎርፋዊ ወረራ ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት እየመከተ ያፈገፍግ ለነበረበት ሥልት ጨለምተኞች የሰጡት ‹‹አማራ እንዲጨፈጨፍ፣ ኑሮውም የውድመትና የዘረፉ ሲሳይ እንዲሆን ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ›› የሚል ትርጉም የአማራን የአርበኝነት ተጋድሎ በትንሹም ቢሆን ቧጭሯል፡፡ መከላከያን ‹‹የዓብይ ጦር›› ባዩ ፕሮፓጋንዳ የተወሰነ ጆሮ አግኝቶ ጥቂቶችን አቂሏል፡፡ ወሬ ነጋሪና ሽብር አውሪ፣ እንዲሁም መንገድ መሪ ሎሌዎችን ወራሪው ለማግኘትም ችሎ ነበር፡፡

) አሁን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምዕራፍ በሁሉም አካባቢዎች ተኳሾች በሰላም ድርድርም በኃይልም እየተቃለሉ ያሉበትና ሰላም እየሰፋ ያለበት ምዕራፍ ነው፡፡ ይህ ማለት ከእንግዲህ ጨለምተኛ ብሔርተኞች የአማራን ሕዝብ ህሊናና ልቦና በሴራ ትርጓሜዎች ለማመስ የሚጠቀሙባቸው የጥቃት ድርጊቶች የሚደርቁበት ቀን እየቀረበ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ተጨባጭ ሆነ ማለት ደግሞ የጨለምተኞች ኑሮ አፈርና ውኃ ያጣል ወይም ቆብ ቀዶ ወደ መስፋት ያመራል እንደማለት ነው፡፡ የአማራ ሕዝብም ሙሉ ቀልብ መልሶ ግንባታና ልማት ላይ ማተኮሩ አይቀርም፡፡ መልሶ ግንባታው ደግሞ ቁሳዊ ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ሰውንም የሚመለከት ነው፡፡

የሰዎች ግንባታችን ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የምንረዳው ጨለምተኞች አፈርና ውኃ ስለማጣታቸው ያስቀመጥኩት ሐሳብ በጣም ስስ (ሲምፕሊፋይድ) እንደሆነ ካጤንን ነው፡፡ ስለጨለምተኝነት ሳወራ የፖለቲካ አስተሳሰብ አዝማሚያን መሠረት አድርጌ ሳይሆን ጨለምተኛነት አሳምሮ ከበላቸው ሰዎች ጋር በቅርበት ሐሳብ ለመለዋወጥ ሞክሬ ነው፡፡  የትኛውም ብሔርተኛ ጨለምተኝነት በጨለማ ብዕርና በጨለማ ምላስ ምን ያህል የሰውን ህሊናና ልቦና እየደለዘ ሊያጠፉ እንደሚችል የሚገባችሁ ቀርባችሁ ስታዩዋቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው አካል እግራቸው ብቻ ነው፡፡ ጆሯቸው፣ ዓይናቸው አዕምሮና ልቦናቸው የሚኖረው ጨለምተኞች ኢንተርኔት ላይ በሚሥሉላቸው ተስፋ የሌላት፣ ዋይታና ሰቆቃ የቀለጠባት ሌላ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር አውርታችሁ ቅንጣት ታህል በመሀላችን የሚያግባባን ነገር አለ ልትሉ አትችሉም፡፡ የሚሉትን በሰማችሁ ቁጥር እንደ ድንጋይ ያለውን ጠጣር ነገር እንኳ አንድ ላይ ዳስሳችሁ ‹‹ድንጋይ ነው›› የሚል ተመሳሳይ ግንዛቤ ስለመያዛችሁ ትጠራጠራላችሁ፡፡ ዛሬ በአማራ ክልል ውስጥ እየተኮሱ ያሉትን ወጣቶች በተለመደው ‹‹የነፍጠኝነት›› ዕሳቤ ፖለቲከኞቻችን የምታዩዋቸው ከሆነ ብዙ ነገር አልተገለጸላችሁም፡፡ የኢንተርኔት ጨለማ ወሬና ትንታኔ ምን ያህል ኢትዮጵያን እንዳጠቃና ምን ያህል ሰው እንዳፈረሰ አልተረዳችሁም፡፡ አማራ ውስጥ ጨለምተኝነት ያጨረማመታቸው የሚተኩሱትን ብቻ አይደለም፡፡ ጨለማ ወሬ እየጠጡ እህህ የሚሉ በየቦታው በገፍ ናቸው፡፡

መቶ ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ስምንት መቶ ሺሕ ገደማ ቱቲሲዎች በሩዋንዳ ስለመጨፍጨፋቸው ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ጭፍጨፋውን በደወል (የሁቱ ተወላጁን ፕሬዚዳንት አውሮፕላን ተኩሶ በመጣል) ያስጀመሩት ግን የቱትሲ ታጣቂዎች እንደነበሩ የሚያሳየው የእውነቱ ሽራፊ ግን ብዙ ጊዜ እንደዋዛ ይዘለላል፡፡ በእኛ አገር ስለአማራ ጠል ጥቃቶች ሲፈጠር የነበረው ጫጫታ ለጭፍጨፋ ሰበብና ነዳጅ የመስጠት ሚና የነበራቸውን የአማራ ብሔርተኞችን የመገሰጽ አቅም አልነበረውም፡፡ አሁንም የጨለምተኞቹ ረድፈኞች እስከ ስድብ በሄደ ችክቸካና ልፍላፏቸው አማራ ጠልነት እንዲበራከትና በንፁኃን ከልታሞች ላይ ሲፈጸም የነበረውም ጥቃት እንዳይደርቅ እየተለማመኑ ነው፡፡ ቀጣፊው ልደቱ አያሌው በአቅሙ አገር ውስጥ ገብቶ ስለመታገል ከሰሞኑ የቀባጠረውም በአማራ ውስጥ ያሸተተውን ጠመንጃ ሙጥኝ ያለ ሁኔታ ያጋጋለ መስሎት ነው፡፡ በአማራ ደም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚነገደው እስከዚህ ድረስ ነው! የተያዘው አጥፊነት በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ትልቁ ጥፋት፣ ቤታችንን በእሳት አያይዞ እሳት ለመመሞቅ እስከ መራወጥ የከፋ ነው፡፡

የሰው ግንባታችን ዓውዱ በአግባቡ መስፋት አለበት፡፡ የለየላቸውን ተኳሾች ወደ ሰላም ለመሳብ ሳይቦዝኑ፣ ከጥይት ተኩስ በመለስ ያሉ የጨለምተኛነት ሰለባዎችንም ከጨለማ ለማውጣት መሥራት ይኖርብናል፡፡ በኦሮሚያም ውስጥ በፅንፍ ፕሮፓጋንዳ አዕምሮን በመመረዝ የተጠመዱትንና ተመራዦቹን ለያይቶ የሚያተውል ዓይን ሊኖረን ይገባል፡፡ በአካባቢ መንግሥትም ደረጃም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የምንሠራቸው ነገሮች ሁሉ መጥፎ ትዝታዎችንና የብሶት ቋጠሮዎችን ቅንጣት በቅንጣት ቢሆንም እንኳ የማሟሸሽ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት የአመራር ሹመት የትግራይ ሕዝብን የአሁን ልቦና ካለመመጠኑም በላይ የትግራይንና የአማራ ሕዝብን ቅርርብ በመበጀት ረገድ በአግባቡ የተመዘነ አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ክፉ ተንኳሽ ቃላትን በአደባባይ በመወርወር ተግባር ውስጥ እጅግም ያልታየ ሰው በተሾመ ነበር፡፡ ትናንትና ስንት ጉድ የተናገረ አንደበትና ፊት ዛሬ ማር አዝናቢ ሲመስል ልብ ይፍቃል፡፡ ደረቅ በደረቅ የሚካሄድ የፖለቲካ ትቅቅፍ ከፖለቲካ ተውኔትነት አልፎ አንጀትን አይነካም፡፡ በሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ውስጥ የአካባቢ አስተዳደሮች መሪዎች ወደ ትግራይ ሄደው በነበሩበት ጊዜ የሰማነው ዓይነት የአቀባበል ንግግር ደግሞ ጭራሽ ሊያቆስልም ይችላል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ኑሮ ይህን ያህል ለመንኮታኮት የበቃው ትናንትና ናጥጦ በተካሄደ  ጦርነት ያልሆነ ይመስል፣ የዛሬው የጊዜያዊ መንግሥት መሪ የዚያ ተዋንያን ያልነበረ ይመስል፣ በሞራል ማማ ላይ ራሱን አስቀምጦ የትግራይን ሕዝብ ፈገግተኛ አቀባበል ለእግንዶች ተርጓሚ ሲሆን እንደምን አያቆስል!

ለተራው ሕዝብ ‹‹ይቅር ለፈጣሪ!›› ተባብሎ መኗኗር ዓይንና አፍንጫ ናቸው፡፡ የትግራይና የአማራ እናቶችና አባቶች ተገናኝተው የሚባባሉትን እንዲባባሉ ዕድል ቢሰጣቸው፣ በበድን ጨዋታ ተሸነጋግለው የሚለያዩ አይመስለኝም፡፡ ቢያንስ ጊዜ ስለአመጣባቸው ጥሎሽ በመነጋገር ዳር ዳር ብለው በሁለቱም በኩል የደረሰባቸውን እየተረተሩ በዕንባ ሲራጩና አንገት ለአንገት እየተጠማጠሙ ሌሎች ያመጡባቸውን ፀብና አበሳ ሲሻገሩ ባየን ነበር፡፡ ሕዝብ ይህንን በመሳሰሉ ዘዴዎቹ ግጭቶችንና መከራን ሲሻገር ኖሯል፡፡

የፖለቲካ ልሂቃን በሕዝብ ውስጥ ያሉ ብሶቶችን የማሟሸሽ ሚና ለመጫወት ከፈለግን ሁላችንም ከማማችን ላይ መውረድ መቻል አለብን፡፡ ከማማዎቻችን ላይ ወርደን የሁሉንም ሕዝብ ጉዳት ያየ ፀፀትና ይቅር መባባል ሲያብሰከስከን ለማየት ተችሎ ቢሆን ኖሮ፣ መብሰክሰካችን ምን ያህል ሕዝብ ይፈነቅል እንደነበር በታየ ነበር፡፡ የዚያ ዓይነት የአንጀት ሥራ በጎደለበት ሁኔታ፣ አማራ ክልልን ስለመጎብኘት የተሰነዘረው ሐሳብ የጎሸ ስሜትን የበለጠ ከማጎሽ በቀር ፋይዳ የለውም፡፡ በአማራ በኩል የሚያቋርጠውን ጎዳና መከፈት በተመለከተ ሕገወጦች አደጋ እንዳያደርሱ ‹‹የበኩላችንን ዕገዛ ማድረግ እንችላለን›› ተብሎ ከአንድ የትግራይ ጊዜያዊ አመራር አባል የተሰነዘረውም ሐሳብ እንኳን ሊደረግ መታሰቡም አስገራሚ ነው፡፡ በተጓዦች ላይ የጨለምተኞች አደጋ ማድረስ መዘዘኛ የመሆኑን ያህል የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች በመንገድ ደኅንነት ውስጥ አጋዥነትን መሞከርም መዘዘኛ ነው፡፡ የፌዴራሉን ጎዳና ደኅንነት በአሁኑ ደረጃ የፌዴራል ኃይል ቢጠብቅው ይመረጣል፡፡ 

የአማራና የትግራይ ሕዝብ ተሃድሶና ልባዊ ቅርርብ ሌላም ሁነኛ ነገር ይፈልጋል፡፡ ሁለቱም የታሰሩበትን የእነ ወልቃይት ጉዳይን ለሁለቱም ካቴናን የሚበጣጥስ ውጤት በሚያስገኝ መንገድ መፍታትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ከባድ፣ ከባድ ሥራ ይመስለኛል፡፡ ከባዱን ሥራ ቀላል የሚያደርገው ደግሞ በሁለቱም አካባቢዎች የሚቀጣጠለው የልማት እንቅስቃሴና አሮጌ ፀብን የሚጥል ህዳሴ ነው፡፡ ለእኔ የመሬት ጣጣን መፍታት ቀላል ነው፡፡ የመሬት ትንቅንቅ እስረኛ አይደለሁምና፡፡ ያልሆንኩትም ውዝግብ ባለባቸው መሬቶች ውስጥ ሕወሓትና ጣጣው ከመምጣቱ በፊት የሁለቱም ሕዝቦች ክልስ ገጽታዎች እንደነበሩ ስለማውቅ፣ ወደፊትም መሬቶቹ በየትኛውም ዓይነት የአስተዳደር ዘይቤ ውስጥ ቢገቡ የሁለቱ ሕዝቦች ሕይወት የማይነጣጠል፣ እንዲያውም ከመዛነቅ እንደማያመልጥ ስለማምን፣ ከውዝግብ ሥፍራዎች ውጪ ያሉ ክልስ ገጽታዎችም ይህንኑ ስለሚናገሩ ነው፡፡ የተወራረሱ ቋንቋዎቻቸው፣ የተወራረሰ ማኅበረሰባዊ ታሪካቸው፣ የተወራረሱ መንፈሳዊና ዓለማዊ የባህል ቅርሶቻቸው (እስከ አለባበስና ፀጉር አበጣጠር ድረስ) ያላቸውን ቤተሰባዊ ዝምድና የጦርነት አባዜ ምን ያህል እንዳነወረውና ሁለቱም ማፈር እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ አሁን ባለንበት ቁዘማ የተጫነው ሁኔታ ውስጥ እንኳ የአክሱም ፅዮን ማሪያም፣ የላሊበላ ገና፣ የጎንደር ጥምቀት የሁሉንም አካባቢ እንግዶቻቸውን ከአደራ ጋር እየጠሩ ነው፡፡ የ‹አሸንዳ/አሸንድዬ…› የልጃገረዶች በዓል የማዶ ለማዶ ኑሮ አያምርብንም እያለ ነው፡፡ በትግራይና በአገው አማራ ውስጥ ያሉ ፍልፍል መቅደሶችም እየተናገሩ ነው፡፡ ‹‹የዛሬ ትውልዶች ቀደምቶቹ በሠሯቸው ታላላቅ ሥራዎች ውስጥ አልነበራችሁም፡፡ እነሱና ሥራዎቻቸው ግን በእናንተ ውስጥ አሉ፡፡ ስለእነሱ ያላችሁን ትውስታ ከማውራትና ከእነሱ ያተረፋችኋቸውን ቅርሶች እያስጎበኛችሁ እህል ከመጉረስ አልፋችሁ የፍልፈላ/የእነፃ ጥበባቸውን በዛሬ ጥበብ አስመንድጋችሁና ጊዜ የማይሽራቸው ዕፁብ ሥራዎች ሠርታችሁ ለቱሪዝም ማዋልን እወቁበት›› እያሉ ነው፡፡ …የሕይወት መተሳሰር ድምፆች ከሁለቱ አካባቢ ሕዝቦች አልፎ መላ ኢትዮጵያ ድረስ የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡

እርግጥ ነው፣ እነዚህን ድምፆች ለመስማት ጆሮ የሌላቸው፣ ከአሮጌ አስተሳሰባቸው ንቅንቅ ሳይሉ ወደ መቃብር የሚወርዱ እንደማይታጡም አይጠፋኝም፡፡ በእኔ ትውልድ ‹‹ተራማጅ ነኝ›› ባይነት ላይ ዓይቸዋለሁና፡፡ በ1968 እስከ 1969 ዓ.ም. ከደርግና ከእነ መኢሶን ጋር የነበረው የእነ ኢሕአፓ አለመግባባት ሊታረቅ የሚችል እንደነበርና የያኔው የከተማ ነፍስ ገዳይነት ወጣት የማስጨፍጨፍ ፖለቲካዊ ኃጢያት እንደነበር፣ ከአርባ ምናምን ዓመታት በኋላ እንኳ ያልተጤናቸውን ግለሰቦች አስተውለናል፡፡ ያኔ በማኦ ሥልት በአሲምባ ውስጥ ትጥቅ ትግል ማድረግ ነበረብን ብሎ የሚቆጭ፣ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች የረገፉት በኢሕአፓም በ‹ኢማሌድህ›ም ውስጥ እንደነበር ያልተረዳ፣ ዛሬ ላይ ቆሞ የእነ ብርሃነ መስቀልንና የጌታቸው ማሩን ከደርግ ጋር ግንባር የመፍጠር አቋም ከክህደት የሚቆጥር አሮጌ የኢሕአፓ ሰው የሱፍ አበባ በሚል መጽሐፍ ውስጥ ሲብከነከን አንብበናል፡፡

በዚያን ጊዜ የትግል ተሳታፊ በነበሩ አያሌ ርዝራዦች ዘንድም ሆነ ከእነሱ በለጠቀው ሌላ ትውልድ ውስጥ ግን በጥቅሉ ያለው ግንዛቤ በየትኛውም ወገን የነበረውን መካረር የታዘበና በሁሉም ጎራዎች የተሰውትን ውድ ልጆች ያስተዋለ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ በፊት በትግራይ በአማራና በአፋር ዘንድ የደረሰውን ነገር፣ አሁን ባለንበት ደረጃ እንኳ ፈጽሞ መሆንና መደረግ አልነበረበትም ባዩ እጅግ አያሌ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ የዛሬ የሰሜን ኢትዮጵያ ታዳጊዎችም ነገ በጉልምስናቸው ተነጋግሮ መስማማት ሞት የሆነበት መካረር የወለደውን የጥፋት ታሪክ ያፍሩበታል፡፡ ለዚያ ሁሉ ጥፋት መዘዝ የሆነው የመጀመሪያ ኃጢያት መቼና በማን እንደተሠራም ማወቃቸውና ደፍረው መናገራቸው አይቀርም፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...