Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከኑሮ ውድነትና ከሥራ አጥነት ቀጥሎ ሙስና ሥር የሰደደ ብሔራዊ ችግር እንደሆነ ታውቋል›› አቶ ሐረጎት አብርሃ፣ በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የባለድርሻ አካላት መሪ ሥራ አስፈጻሚ

አቶ ሐረጎት አብረሃ በዛብህ በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ከአሥር ዓመታት በላይ አገልግለዋል፣ አሁንም በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪቸውን በሕግ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፕሮጀክት ማኔጅመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በሕዝብ አስተዳደርና ልማት አመራር የመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሠርተዋል፡፡ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በ2000 ዓ.ም. የሥነ ምግባር ባለሙያ ሆነው ሥራ የጀመሩት አሁን በሚሠሩበት የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲሆን፣ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ በኮሚሽኑ ላለፉት 15 ዓመታት በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ አቶ ሐረጎት ከግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የባለድርሻ አካላት ማስተበባሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከኅብረተሰቡ የሚነሱ በሙስና፣ ብልሹ አሠራሮችና በተቋሙ የአደረጃጀት ሥርዓት ላይ ሔለን ተስፋዬ ከአቶ ሐረጎት ጋር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሙስና ደረጃ ምን ይመስላል?

አቶ ሐረጎት፡- ሙስና በአንድ አገር ማኅበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ልማት የሚያደናቅፉ ተብለው ከተፈረጁ ችግሮች ወይም ወንጀሎች አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወንጀልና ማነቆ ለመፍታት በመንግሥት ደረጃ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ኮሚሽኑም ከተቋቋመበት ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል መንግሥት በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት፣ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በክልሎችም በተመሳሳይ መዋቅሮች ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር፡፡ ነገር ግን የሙስና ጉዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እንዳሉበት፣ መቆጣጠርና መከላከል እንዳልተቻለ የሚያሳዩ ጥናቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በ2013 ዓ.ም. ያደረግነው አገር አቀፍ የሙስና ቅኝት ጥናት ሙስና በሦስተኛ ደረጃ አገራዊ ችግር መሆኑን አሳይቷል፡፡ ስለዚህ ይህ የሚያስረዳው ሙስና አሁንም አገራዊ ሥጋትና የመልካም አስተዳደር ጠንቅ ነው፡፡ ማኅበራዊ እሴቶችን በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግና በአገራችን ለሚደረጉ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት እንቅፋት መሆኑን በተጨባጭ መንግሥት አውቆ አቋም እየወሰደበት ነው፡፡ ኮሚሽኑም ያንን ታሳቢ በማድረግ እንቅስቃሴዎች  እያደረግን ነው ያለው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡ ጥናቶች የሚያሳዩትም ሙስና አሁንም በኢትዮጵያ አሥጊ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ሙስና የሚያደርሰውን ጉዳትና የደቀነውን አደጋ ለመቅረፍ የተለያዩ አደረጃጀቶች አሉት፡፡ መንግሥት የወሰዳቸውም ዕርምጃዎች አሉ፡፡ በዚህ መሠረት ተጠያቂነትና ግልጽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ አሠራሮች፣ ሕጎችና ፖሊሲዎችን ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የሚከናወኑ ሥራዎች ሲታዩም ጥሩ ናቸው ብሎ መውሰድ ያስችላል፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት ከጥቂት ወራት በፊት ሙስና ብሔራዊ የደኅንነት ሥጋት ነው ብሎ ነበር፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ቢያብራሩልን?

አቶ ሐረጎት፡-  ሙስና ዘርፈ ብዙ ችግር አለው፡፡ ዘርፈ ብዙ ችግር አለው ስንል አንደኛ ሕዝብ የሰጠውን ኃላፊነትና እምነት ትቶ ለግል ጥቅም የሚሄድ አመራር፣ ሠራተኛ ወይም አገልጋይ ይኖራል፡፡ በዚህ መሠረት ከሕዝብ የተሰጠን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣትና የሕዝብ እምነት የሚሸረሽሩ አሠራሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ማኅበረሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲከሰት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ሁለተኛው የኢኮኖሚ ጉዳት ከውጭ አሊያም ከሕዝብ የሚሰበሰበውን ውስን ሀብት ለተለያዩ አገራዊ ልማት መዋል የነበረበትን የሕዝብን ሀብት የሚነጥቁና እምነት የሚያጎድሉ፣ ያለውን ሀብት ለግል ጥቅም የሚያውሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህም አንድ መገለጫ ነው፡፡ ሦስተኛ የሙስና ጉዳት ከኢኮኖሚ ጉዳይ የላቀ ነው፡፡ የሙስና ውጤት ንብረትን ከመዝረፍ ጋር ብቻ አያይዘን የምናየው አይደለም፡፡ ዘርፉ ብዙ ፖለቲካዊ ቀውስ ያስከትላል፡፡ የተረጋጋ ማኅበረሰብና የፖለቲካ አስተዳደር እንዳይኖር አሉታዊ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ለምሳሌ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የነበሩ ጦርነቶች፣ በዚህም በዚያም በኩል የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከጀርባቸው ሙስና አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ አንፃር ደምረን ብናስቀምጠው ሙስናን መታገል ካልቻልን፣ በእንጭጩ የሚያስከትለውን ጉዳት ካልገታነውና ካልቀነስነው በአገራችን ላይ የሚፈጥረው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ጦርነትና ሌሎች ችግሮች ላይ ዞሮ በነበረበት ጊዜ የሙስና ድርጊቶችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተበራክተዋል፡፡ በመንግሥት አገልግሎት አሳጣጥ ላይ የተፈጠረ ተፅዕኖ አለ፡፡ ኅብረተሰቡም በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች አሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ መንግሥት መቆጣጠር ካልቻለ ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን አገር ሆኖ ለመቀጠል አደጋ አለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ተነስተው የችግሩን ደረጃ ማስቀመጣቸው ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተጠቀሰው ደረጃም ትግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ተነስተን ያሉ ጥናቶችና ምልከታዎችን ብናይ ሙስናን በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር ካልቻልን፣ በአገራችን ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡    

ሪፖርተር፡- ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮችንና ሥጋቶችን በተመለከተ ጥናት ወይም ዳሰሳ አድርጋችሁ በተጨባጭ ያገኛችሁት ነገር አለ?

አቶ ሐረጎት፡- ችግሮች አሉ ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫችን ጥናቶች ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጥናት ማካሄድም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ በዓለም ላይ የሚደረጉ ጥናቶች አገራችን በሙስና ደረጃ የትኛው ተርታ እንደምትገኝ የሚያስቀምጡ ስታንዳርዶች አሉ፡፡ እነሱን እንደ አንድ ግብዓት ብንወስድ ችግሩን ማየት እንችላለን፡፡ ነገር ግን በመሠረታዊነት እኛ ከራሳችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመነሳት ግልጽ የሆኑ ስታንዳርዶችን አዘጋጅተናል፡፡ አገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጉዳይ በአገር ውስጥ ከሚነሱ ብሔራዊ ችግር ውስጥ በሦስተኛ ደረጃነት ተቀምጧል፡፡ ከኑሮ ውድነትና ከሥራ አጥነት ቀጥሎ፣ ሙስና ብሔራዊ ሥጋት እንደሆነና ሥር የሰደደ ችግር መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የችግሩ መገለጫ ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህንን ለመመለስም በጥናት ማስደገፍ አለብን፡፡ ከዚያ ውጪ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ጀርባ ደግሞ አንዱ የሙስና ችግር ሊኖር ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እዚህ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱም በተለያዩ ጥናቶች ላይ ተመሥርተው ነው፡፡ እኛም የዚህ ዕሳቤ አካል ነን ብለን እናስባለን፡፡ በኮሚሽናችን ሙስናን መከላከል ሥራችን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የሚከሰቱ ችግሮች ካሉ ትኩረት ሰጥተን እንሠራበታለን፡፡ ችግሩ ሰፊ በመሆኑ በብሔራዊ ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ችግሩን መቅረፍ አለብን ተብሎ የተሄደበት ዕርምጃ አለ፡፡ ይህም በጥናትም የተደገፈ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡        

ሪፖርተር፡- ስለብሔራዊ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ካነሱ አይቀር፣ በፌዴራል መንግሥት የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ድምፁ ጠፍቷል ይባላል፣ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ሐረጎት፡- ድምፁ ጠፍቷል የሚባለው ትክክል አይመስለኝም፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴው በዚህ ዓመት ነው የተቋቋመው፡፡ ከተቋቋመ በኋላ ኮሚቴው እየተገናኘ ያከናወናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በአገር ደረጃ የተቋቋሙ የፀረ ሙስና ኮሚቴዎች እስካሁን የሠሩትን ገምግመው ለሕዝብ አቅርበዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ የተሠሩ ሥራዎች ለሕዝብ ይፋ ተደርገዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኮሚቴው ራሱን የማስተዋወቅ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የተለያዩ ጥቆማ መቀበያ ዘዴዎች መቋቋሙን፣ ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥቆማና ቅሬታዎች በመቀበል ስለኮሚቴው ግንዛቤ ሲሰጥ ነበር፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች መግለጫ ሲሰጥ ነበር፡፡ ከዚህ በመነሳት ብዙ ጥቆማዎች ቀርበዋል፡፡ በዚህ ላይ በመመሥረት ግምገማ ተደርጎ በየጊዜው ይፋ የሚደረግበት አግባብ አለ፡፡    

ሪፖርተር፡- ከኅብረተሰቡ የደረሷችሁ ጥቆማዎች ምን ያህል ናቸው? በየትኞቹ ዘርፎች ላይ ነው ጥቆማዎች የሚበዙት?

አቶ ሐረጎት፡- የሚቀርቡ ጥቆማዎች በቀጥታ ለኮሚቴው የሚቀርቡና የማይቀርቡም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ጥቆማዎቹ ቀርበው ባለፈው በተደረገው ግምገማ በመጋቢትና በሚያዝያ አፈጻጸም ሳይገባ፣ ከኅዳር እስከ ጥር የነበሩ አጠቃላይ አገራዊ ጥቆማዎች ከ1,000 በላይ ናቸው፡፡ በሒደት ላይ ያሉ ውሳኔ የተሰጠባቸውና በማጣራት ሒደት ላይ የሚገኙ ጥቆማዎች አሉ፡፡ የጥቆማ ዘርፎች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሬት፣ በግዥ፣ በኮንስትራክሽንና በሌሎችም ዘርፎች ጥቆማዎች እየቀረቡ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ኮሚቴው ሥራዎችን እየገመገመ የሚሄድበት አግባብ አለው፡፡ ይሁን እንጂ በሒደቱ የኅብረተሰቡና የሚዲያ ተሳትፎ በሚፈለገው ደረጃ አልተጠናከረም፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ስብሰባ ብሔራዊ ኮሚቴው ከማኅበረሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች በየወሩ እየተገናኘ ለመገምገም ውሳኔ አሳልፏል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅቶች የሚደገፉ ፕሮጀክቶች ከሙስናና ከብልሹ አሠራሮች የፀዱ መሆናቸውን ለማወቅ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በዓለም ባንክ ትብብር የሚከናወኑ ሰባት ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከሙስናና ከብልሹ አሠራሮች የፀዱ ናቸው ወይ? ችግሮች ሲታዩ ምን ዓይነት ዕርጃዎች ተወስዶባቸዋል?

አቶ ሐረጎት፡- ወደ ፕሮጀክቶች ከመሄዴ በፊት አጠቃላይ መንግሥት እየተከተለ ያለው የሙስና መከላከል አሠራርን ላብራራ፡፡ አሁን እየሠራን ያለነው በዋናነት አሳታፊ የሆነ የፀረ ሙስና ትግል ለመምራት የሚያስችል ሥርዓት ተከትለን ነው፡፡ ይህም ከአሁን በፊት የነበረን ጣልቃ ገብነት በተወሰኑ ተቋማትና አሠራር ላይ ትኩረት አድርገን ነው፡፡ የመፍትሔ ሐሳብ ሰጥተን ነበር ሥራዎችንም ስንከታተል የነበረው፡፡ ነገር ግን አሁን ካለው ችግርና ከውጤታማነትም አንፃር ዘርፍ ተኮር አድርገን ብንሄድ የተሻለ ውጤት እናመጣለን ብለን እየሠራን ነው፡፡ ዘርፍ ተኮር የሙስና መከላከል አሠራር ተከትለን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ዘርፍ ተኮር ምንድነው ብለን ካየን፣ መዋቅሩ እስከታች የወረደ ነው፡፡ ለምሳሌ ግብርናን ካየን ከፌዴራል እስከ ወረዳ መዋቅር ድረስ ይዘልቃል፡፡ ሌሎችም ዘርፎች በየተዋረዳቸው ብዙ መዋቅሮች አሏቸው፡፡ በእነዚህ ዘርፎች ላይ የምናደርገው የሙስና መከላከል በፌዴራል አሊያም በክልሎች ብቻ የሚገደብ ሳይሆን፣ ሁሉን አቀፍና መዋቅሩን ሊዳስስ በሚችል ጥናት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ዘርፎች ላይ የሙስና ሥጋት ጥናቶችን እናደርጋለን፡፡ ጥናቱ ከተሠራ በኋላ ዘርፉን ለሚመራው ሕጋዊ ኃላፊነት ላለው አካል እንሰጣለን፡፡ በጤና ላይ ከሆነ ለሙስና የሚያጋልጥ የሥራ ዓይነትና ሥጋት የሆኑ ምንጮችን አጥንተን ለዘርፉ እንሰጣለን፡፡ በዚህም ለዘርፉ ከሰጠነው ምክረ ሐሳብ ላይ ተነስቶ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ይዘረጋል፡፡ በዚህ መሠረት ኮሚሽኑ በሁሉም ዘርፎች ላይ ጥናቶችን እያደረገ ነው፡፡ እነዚህ ውስጥ ፕሮጀክቶች፣ በመንግሥት የሚሠሩ ተግባሮችና የሚታዩበት አካሄድ አለ፡፡ በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ በ19 ዘርፎች ከሙስና ሥጋት አንፃር ጥናት አጥንተን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ውስጥ ከዓለም ባንክ ጋር ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ስምምነት አለን፡፡ ስምምነታችን ባንኩ በሚደግፋቸው ፕሮጀክቶች ላይ አስቀድሞ ሙስናን የሚከላከልበት የራሱ የሆነ አሠራር አበጅቷል፡፡ ለአሠራሩ ብለው የሚዘጋጁ ስታንዳርዶች አሉት፡፡ በእኛ አገርም ባንኩ በሰባት ፕሮጀክቶች ላይ ድጋፍ ሲሰጥ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተስማማው ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሲደረጉ ከሙስናና ከብልሹ አሠራሮች በፀዳ መንገድ እንደሠሩ ኮሚሽኑ ያጣራል ብሎ የስምምነቱ አካል ሆኗል፡፡ ኮሚሽኑ በዚህ ላይ ተመሥርቶ በፕሮጀክቶቹ ለሙስናና ለብልሹ አሠራር ጥቆማ ሥርዓት እንዲዘረጋ የሚያረጋግጡ፣ ጥቆማና ቅሬታ የሚቀበሉና ለሚመለከተው አካል የሚያስተላልፉ ኦፊሰሮችን እንዲመድቡ የመከታተል ኃላፊነት አለብን፡፡ ሌሎች ከዚህ ስምምነት ጋር የተያያዙ የመረጃ መለዋወጫ ሥርዓቶች በአግባቡ ተግባራዊ መሆኑን በዓመት ሁለት ጊዜ አጣርተን እንልካለን፡፡ በዚህ አሠራር ሌሎች ፕሮጀክቶችን ስናይ በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚከናወኑ በተቻለ መጠን የሙስና የመከላከል ሥርዓት ያላቸው ናቸው፡፡ አስቀድሞ ስታንዳርድ አላቸውና በስታንዳርዱ መሠረት እንሠራለን፡፡ በእኛ እምነት የዓለም ባንክ አሠራሮች በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ ተግባራዊ እንዲሆኑ እንደ ልምድ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ከሙስና ተጋላጭነት አንፃር እንኳን ከሌሎች ፕሮጀክቶች ጋር ቢነፃፀር ያን ያህል የከፋ ሙስና የሚታይበት አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደ ማናቸውም ፕሮጀክቶች የሚነሱ ቅሬታዎችና ጥቆማዎች ካሉ እናጣራለን፡፡           

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቶቹ አንዳንዶቹ ሊጠናቀቁ የደረሱ ናቸው፡፡ እርስዎ በሰጡት ማብራሪያ ጥናት የምታደርጉባቸው ዘርፎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህ ዘርፎች የትኞቹ ናቸው ለሙስናና ለብልሹ አሠራሮች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት?

አቶ ሐረጎት፡- በዓለም ባንክ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ሙስና አይፈጽምባቸውም ለማለት አይደለም፡፡ ጥቆማና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችም አይነሱም ማለት አይደለም፡፡ ጥቆማዎችም፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችም ይነሳሉ፡፡ ነገር ግን ምንድነው ከሌሎች ፕሮጀክቶች የሚለያቸው? አስቀድመው የተዘረጉላቸው የሙስና መከላከያ ሥልቶች መዘጋጀታቸው ነው፡፡ ኮሚሽኑም የተዋዋለው ቀድሞ ፕሮጀክቶቹ ከመጀመራቸው በፊት የሚከናወኑ ሥራዎች ለሙስና ተጋላጭ እንዳይሆን መከላከል ነው፡፡ አስቀድሞ በሚሠሩ ሥራዎች ሙስና ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል ይጠቅማሉ፡፡ ወደ 20 ዘርፎች ስንመለስ ዓላማው ዘርፎችን የማወዳደር አይደለም፡፡ በእርግጥ ሁሉም ዘርፎች ለሙስና ያላቸው ተጋላጭነትና ዕድል ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡፡ ግን እኛ ያኛው ዘርፍ ከእዚህኛው ሙስና ተጋላጭ ነው ለማለት ሳይሆን፣ በዘርፉ ወይም በተቋሙ ውስጥ  የትኛው ነው ተጋላጭ የሚለው ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ ጤናን ብናይ የመድኃኒት አቅርቦት፣ የዕቃ ግዥ አቅርቦት አገልግሎትንና ሌሎችም አገልግሎቶችን ሰብስቦ በማጤን፣ ስታንዳርድ ተዘጋጅቶላቸው ለሙስና ተጋላጭ የሆኑትን በጥናትም ጭምር በየደረጃቸው እናስቀምጣለን፡፡ ያም ሆኖ ግን ብዙ ሀብት የሚንቀሳቀስባቸው፣ ከተፈጥሮ ባህሪያቸው አንፃር ውስብሰብ የሆኑና ሙስናን በቀላሉ ሊስቡ የሚችሉ ዘርፎች አይኖሩም ማለቴ አይደለም፣ ይኖራሉ፡፡ በተለምዶ በኅብረተሰቡ የሚገለጹ ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚያ ትኩረት የምንሰጥባቸው ናቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- በኅብረተሰቡ ጥቆማ የደረሳችሁባቸው ቦታዎች አሉ?

አቶ ሐረጎት፡- ሁሉንም እናያለን፡፡ በየዘርፎች ያሉት በሙሉ ይታያሉ፡፡ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚገናኙ ለምሳሌ ከውኃ፣ ከኤሌክትሪክ፣ ከመታወቂያ ከአገልግሎትና ከሰነዶች ማረጋገጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥቆማዎች አሉ፡፡ እነዚህ የተነሱ ጉዳዮችና ሌሎቹም በየዘርፋቸው ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ በልማት ድርጅቶች ትልልቅ ግዥዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ኮንስትራክሸን ጭምር የሚፈተሽበትና የሚታይበት አካሄድ አለን፡፡ ሁሉም ዘርፎች ያሉበትን የሙስና ተጋላጭነት ፈትሸናል፡፡ በዚህ ረገድ ቅድሚያ የሚጣቸው ዘርፎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አምና ያጠናነውን እንደ ናሙና ላንሳው፡፡ ገቢዎችና ጉምሩክ ዘርፍ በዚህ ውስጥ የትኞቹ የሥራ ዘርፎች ናቸው በሙስና በእጅጉ የተጋለጡ ብለን አጥንተን 14 ዘርፎችን በቅደም ተከተል አስቀምጠን ለተቋሞቹ ለበላይ አካላት ሰጥተናቸዋል፡፡ ከዚያም ዘርፉን የሚመሩ አካላት የወሰዷቸው ዕርምጃዎች አሉ፡፡ በ14 የሥራ ዘርፎች ቅርንጫፎች ያሉ ተቋማት ትኩረት ተሰጥቶባቸው መፍትሔ ተገኝቷል፡፡  

ሪፖርተር፡- ኮሚሽነሩ አባል የሆኑበት ብሔራዊ የፀረ ሙስና ግብረ ኃይል የታሰበውን ያህል ማሳካት ችሏል ብለው ያምናሉ?

አቶ ሐረጎት፡- መንግሥት በጦርነትና በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ትኩረት አድርጎ በነበረበት ወቅት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የሙስና ጉዳዮች ጎልተው ወጥተዋል፡፡ በዚህም መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ችግሩን ለመፍታት በማሰብ ያቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴውን ነው፡፡ በተለያዩ ተቋማት ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡ አገልግሎቶች በሙስና እየተሸጡ ነው፣ እንዲህ ዓይነት እንግልት እየደረሰብን ነው፣ እዚህና እዚያ አካባቢዎች የሚታመኑ አመራሮች የሉም፣ ለግላቸው ትኩረት የሚሰጡ አመራሮች አሉ ለሚሉ ጥያቄዎች መፍትሔ መስጠት ስላለበት ነው መንግሥት ኮሚቴውን ያቋቋመው፡፡ ከዚህ በመነሳት በአጭር ጊዜ ሙስናና ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መቋቋም የሚያስችል ዕርምጃ መውሰድ አለብን በሚል ዕሳቤ የተጀመረ ነው፡፡ ይኼ ከችግሩ ስፋት አኳያ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ያም ሆኖ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ለረዥም ጊዜ ይቆያል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉ በኮሚቴ ብቻ የሚከናወን አይደለም፡፡ ለረዥም ጊዜ በሚሠራ፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና ሌሎችም አሠራሮችን ታሳቢ ተደርጎ ተቋማዊ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡ ያንን ደግሞ መንግሥት ታሳቢ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ ተነስተን ኮሚቴው በዚህ ደረጃ መሥራቱ ተጨማሪ አቅምና ጉልበት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ የሥልጣን ሽሚያና የሕግ ግጭት አለበት አልልም፡፡ ሁለተኛ ኮሚቴው ለረዥም ጊዜ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የሙስና ሥጋት ከቀነሰ መንግሥት መደበኛ ተቋማዊ አሠራሩን አጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ግብረ ኃይል በማቋቋም በሌሎች አገሮች ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ አገሮች በተቸገሩ ጊዜና ጎላ ያለ ችግር ሲገጥማቸው የተለየ አሠራር ተከትለው ችግሩን ለመቆጣጠር የሚሄዱበት አሠራር ያበጃሉ፡፡ ይህም ከአሠራር አንፃር አዲስ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ፀረ ሙስና ኮሚሽን ቀደም ሲል በሙስና ጉዳዮች ላይ የነበረው የዓቃቤ ሕግነት ወይም የከሳሽነት ሥልጣን ወደ ሌላ ተቋም በመተላለፉ፣ ሙስናን በመከላከል ተግባር ላያመጣው ተፅዕኖ የለም፡፡ አንዳንዶች በዚህ ጉዳይ ተቋሙን ‹‹ጥርስ የሌለው አንበሳ›› አድርጎታል ይላሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ሐረጎት፡- በኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ትግል ላይ የተለያዩ ሁነቶች አሉ፡፡ በመጀመርያ አካባቢ የፀረ ሙስና ትግሉ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የሙስናን መከላከልና የሕግ ማስከበር ሥራዎች አንድ ላይ ተደራጅቶ መሥራት አለባቸው የሚል ዕሳቤ ተይዞ፣ በአደረጃጀትም በሕግም እስከ 2008 ዓ.ም. ተሄዶበት ነበር፡፡ በዚህ ደረጃ የራሱ የሆነ አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖዎች ነበሩት፡፡ ከዓለም አቀፍ ልምድ አንፃር ብናየው አገሮች የተለያዩ ሞዴሎችን ይከተላሉ፡፡ አንደኛው ሙሉ ለሙሉ ግንዛቤ በመስጠት፣ በመከላከል፣ በሕግ ማስከበርና በተጠያቂነት ላይ እንዲሠሩ የሚሰጣቸው ኃላፊነት አለ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ የመከላከል ሥራው ለብቻው፣ የሕግ ማስከበር ሥራው በመደበኛው ይሠራ በሚል ዕሳቤ ለሁለት ተከፍሎ የሚሠራበት ሁኔታ ደግሞ አለ፡፡ የተቀረው ዝም ብሎ የሕግ ማስከበሩን ሥራ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ብቻ ይሥሩ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን አያስፈልግም የሚል ዕሳቤ ያላቸው አሉ፡፡ እነዚህ ልምዶች እንደ አገሮቹ የተለያዩ ናቸው፡፡ ልምድና ውጤታማነታቸውም በዚያው ልክ ይለያያሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ስናየው የእኛ አገር ቅድም ለማንሳት እንደሞከርኩት እስከ 2008 ዓ.ም. ይህንን ሥራ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ከ2008 ዓ.ም. በኋላ ግን የምርመራ ሥራዎች ለፖሊስ፣ የክስ ሥራዎች ደግሞ ለዓቃቤ በሕግ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ኮሚሽኑ ደግሞ አጠቃላይ የመከላከል ሥራዎችን ማለትም የሀብት ምዝገባን፣ የጥቅም ግጭት መከላከልን፣ የጥናትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ‹‹ኮሚሽኑ የተዳከመው በእነዚህ ሥራዎች ሥልጣን ስለሌለው ነው፣ አጠቃላይ የፀረ ሙስና ትግል የተዳከመውም እነዚህ ኃላፊነቶቹ ወደ ተለያዩ ተቋማት በመሄዳቸው ነው›› የሚለውን ጉዳይ በጥናት ማስደገፍ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ጉዳዩን በጥናት ካላስደገፍነው በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ እንደተባለው ኅብረተሰቡ ጥያቄዎችን ያነሳል፡፡ እንደዚህ ቢሆንና እንደዚያ ቢደረግ ይላል፡፡ እነዚህን ዕሳቤዎች በጥናት ተደግፈው መታየት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ መንግሥት አደረጃጀት የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡ መንግሥት እኔ የአገራችንን የፀረ ሙስና ትግሉ የምመራው በዚህ መንገድ፣ አደረጃጀትና ፖሊሲ ነው ብሎ የመወሰን ኃላፊነት አለበት፡፡ በዚያ ደረጃ ነው በመንግሥትም እንቅስቃሴ ሲደረግ የነበረው፡፡ ይህ ውጤት አምጥቷል? አላመጣም? ለሚለው በጥናት በተጨባጭ አስደግፈን ብናየው ባይ ነኝ፡፡    

ሪፖርተር፡- እንደ ባለሙያ ኮሚሽኑ የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣኑ ከተነሳ በኋላ ያለው ኃይል አልተዳከመም ይላሉ?

አቶ ሐረጎት፡- በዚህ ውስጥ እንዳለፈ ባለሙያና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ልምዶች አንፃር ስመለከተው፣ በተለይ በአፍሪካ አገሮች በጣም ጠንካራ የሆነ የተጠያቂነት ሥርዓት ባልጎለበተበት፣ ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ባሉበት፣ የሕግ ተጠያቂነት ባላደገበትና ባልዳበረበት አገር ሊኖሩ የሚገባቸው የፀረ ሙስና ተቋማት የተሟላ ሥልጣንና ኃላፊነት ያላቸው እስከ መጨረሻው የሚሠሩ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ሳይንሱና ንድፈ ሐሳቡም የሚሰጠው ምክረ ሐሳብ ይህንን ነው፡፡ ነፃነትና የተሟላ ሀብት ተሰጥቷቸው፣ ኃላፊነትና አቅም ኖሯቸው ቢሠሩ የተሻለ ነው የሚል ነው፡፡ እኔም በግሌ ብጠየቅ እንደዚያ ነው የማስበው፡፡ ያም ሆኖ ግን ይህ ሥልጣን ሳይሰጣቸው ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ ጋር ሆነው ለውጥ ያመጡ አገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ የአፈጻጸምና የጥናት ጉዳይ ይመጣል፡፡ በሌሎች አገሮች ተግባራዊ እየተደረገ ያለው አደረጃጀት ውጤታማነቱ በጥናት ታይቶና ተረጋግጦ የሚቀየር ካለ፣ መንግሥት በፈለገው ጊዜ የመቀየርን ሐሳብ ሊወስድ ይችላል፡፡ እንዲህ የሚነሱ ጉዳዮች በሒደት የሚታዩበት ዕድል ይኖራል፡፡ የኅብረተሰቡ ጥያቄ ከሆነ አደረጃጀቱ በድጋሚ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡   

ሪፖርተር፡- የኮሚሽኑ ሥልጣን ወይም አደረጃጀት እንዲስተካከል ጥያቄ አላነሳችሁም?

አቶ ሐረጎት፡- እኛ በአፈጻጸም ደረጃ የምናነሳቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በሀብት ምዝገባ አሠራር ላይ፣ በምናደርጋቸው ጥናቶች ላይ፣ በጥቅም ግጭት መከላከል ላይና በሙስና መከላከል በሚነሱ ጥቆማዎች ላይ ሥልጣንና ኃላፊነት ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሮችን በቅንጅት መፍታት አለብን ብለን እናስባለን፡፡ እነዚህን ችግሮችን ለመፍታት ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ ጋር በቅርበት ችግሩን መፍታት እንችላለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ በቅንጅት የመሥራት ክፍተቶችና ችግሮች አሉ፣ ይህንንም ሁሌ እናነሳለን፡፡ በዚህ ላይ መፍትሔ ቢገኝ የተሻለ ሥራ መሥራት ይቻላል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት እስካሁን ድረስ ሀብታቸውን እንዳላስመዘገቡ ይታወቃል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ያለፈ ዕርምጃ መውሰድ ያልቻለው ለምንድነው?

አቶ ሐረጎት፡- በሕጉ መሠረት አያንዳንዱ ተመራጭ፣ ተሿሚና ሠራተኛ ሀብት ማስመዝገብ እንዳለበት በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በዚህ ላይ ተመሥርተን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንሠራለን፡፡ በዚህ መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችና አመራሮች ሀብት አስመዝግበዋል፡፡ የሀብት ምዝገባ ቅሬታ የሚያስነሳ አይደለም፡፡ ቅሬታ ሲነሳም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው፡፡ በቦታ በዝውውርና ባለመመቻቸት የሚነሱ ቅሬታዎች እንጂ፣ ሀብት አላስመዘግብም የሚል አካል አላጋጠመንም፡፡ ነገር ግን በሕጉ መሠረት በጊዜው አለማስመዝገብ፣ የመዘግየትና እኛም ኦን ላይን ለማድረግ ጥረት ስናደርግ ዘግይተናል፡፡ በማኑዋል ለማስመዝገብ ብዙ ወጪ የሚያስወጣ በመሆኑ ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በመሆን በኦንላይን የሚመዘገቡበትን ዕድል ለመፍጠር እየሞከርን ነው፡፡ ያም ሆኖ በማኑዋል የሚደረገው ምዝገባ እስካሁን አልተቋረጠም፡፡ በዚህ ደረጃ ግዴታቸውን ያልተወጡ ሲኖሩ መፍትሔ እንዲሰጥ ለሚመለከተው አካል (ዓቃቤ ሕግ) በየጊዜው እንልካለን፡፡ የተመዘገበውም ሀብት ሁሉ ለሕዝብ ይፋ አይደረግም፡፡ ይፋ የሚለው ቃል በራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ እኛ ሁሉም የመመዝገቢያ ዘዴዎች መሠረቱን መከተላቸውንና አለመከተላቸውን ነው የምናረጋግጠው፡፡ አቶ እከሌ የሚባል ባለሥልጣን (ሠራተኛ) ሀብቱን አስመዝግቧል ወይስ አላስመዘገበም ተብለን ስንጠየቅ መረጃ እንሰጣለን፡፡ በግለሰብ ደረጃ ጥያቄ ሲቀርብ እናሳያለን፡፡ ይህንን ያህል ተሿሚና ሠራተኛ ሀብት አስመዝግቧል፣ አላስመዘገበም የሚለውን ይፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የተመዘገበውን ሀብት በግለሰብ ደረጃ ጠይቆ ካልቀረበ በስተቀር፣ እንደ ማንኛውም ማስታወቂያ ይህንን ያህል ተመዝግቧል ይህን ያህል ቀርቷል ብለን የምንለጥፍበት ሥርዓት የለም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ዜጋ አቶ እከሌ ያስመዘገበውን ሀብት የማወቅ መብት አለው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...