Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በውጭ ኮንትራክተሮች እየተወረሩ ነው›› አቶ ግርማ ሀብተ ሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በብርቱ ከተጎዱ ዘርፎች ምክንያት አንዱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ነው፡፡ ዘርፉ በርካታ ችግሮች ያሉበት ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ ችግሩ እየባሰ እንደመጣ እየተነገረ ነው፡፡ በተለይ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ህልውና አደጋ ላይ ነው የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚገልጹም አሉ፡፡ በተለይ የቻይና ኮንትራክተሮች ገበያውን በሰፊው መያዛቸው፣ አንዳንድ ሥራዎች ያለ ጨረታ እየተላለፉ መሆኑ ደግሞ ነገሩን በዕንቅርት ላይ ጆሮደግፍ አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሀብተ ሥላሴም ይህንን ሥጋት ይጋራሉ፡፡ አገር በቀል ኮንትራክተሩ አደጋ ላይ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ከወቅታዊ የአገር በቀል የኮንትራክተሮች ችግሮችና በተለይም የውጭ ኮንትራክተሮች ገበያውን መቆጣጠርና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዳዊት ታዬ ከአቶ ግርማ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተርወቅታዊው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ምን ይመስላል፣ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች የሥራ እንቅስቃሴ እንዴት ይታያል?

አቶ ግርማ፡- የአገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተጎድቷል፡፡ ፍጥነቱ ተገትቷል የሚባል ደረጃ ላይ ነው፡፡ ለዚህም አንዱና ትልቁ ምክንያት የአገራችን ኢኮኖሚ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ መጎዳቱ ነው፡፡ በተለያዩ የኢኮኖሚ አሻጥሮችና በመሳሰሉ ችግሮች ምክንያት አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው አደጋ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል፡፡ የኅብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታም ሆነ የትኛውንም የቢዝነስና የንግድ ዘርፍ የሚነካ ነው፡፡ ለምሳሌ የየኮንስትራክሽን ዘርፉን ነጥለን ስናይ ደግሞ በየቀኑ እየጨመረ የመጣው የኮንስትራክሽን ግብዓት ዋጋ የአገሪቱ ዓብይ ችግር ሆኗል፡፡ ኢንዱስትሪው የሚፈልጋቸው ግብዓቶች 300 እና 400 በመቶ፣ አንዳንድ ምርቶችም ከዚህም በላይ ዋጋቸው እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም በአጠቃላይ በግንባታ እንቅስቃሴዎች ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ይህም የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸው መጠናቀቅ የነበረባቸው ፕሮጀክት በወቅቱ እንዲያልቁ ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ የሚያስገድድ ደረጃ ላይ ነው የተደረሰው፡፡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በአብዛኛው የሚመጡት ከአስመጨዎች ነው፡፡ በአገር ውስጥ የሚገኘውም ቢሆን በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋቸው ጨምሯል፡፡ አሸዋ፣ ጠጠር፣ ድንጋይና የመሳሰሉ ግብዓቶች ሳይቀሩ በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋቸው ተሰቅሏል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሠራተኛ የጉልበት ዋጋም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያንቀሳቅሰው መንግሥት በመሆኑ፣ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች የተያዙ በጀቶች በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰበት ስለሆነ፣ አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ ችግር ዓለም አቀፉ ፖለቲካም ሆነ የፀጥታ ሁኔታ ሲደማመር ደግሞ ችግሩን አብዝቶታል፡፡ ስለዚህ በመንግሥት በኩል አስፈላጊ ናቸው ተብለው የታመኑ ፕሮጀክቶች ካልሆኑ በቀር፣ በቀጥታ በሥራ ተቋራጮች እጅ ያሉ ፕሮጀክቶች የችግሩ ገፈት ቀማሾች ሆነዋል፡፡ በተለይ ከውጭ የሚመጡ የማጠናቀቂያ ዕቃዎች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል ማለት ይቻላል፡፡ የሳተሪን የኤሌክትሮኒክስ መካኒካልና የማሽነሪ ገጠማ ያላቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ ከውጭ ምንዛሪና ከበጀት እጥረት ጋር በተያያዘ መግባት ባለመቻላቸው፣ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ የሚያስገድድበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ 

በአገሪቱ ውስጥ የነበረው የጦርነት ችግር የኅብረተሰቡን ሰላም ነስቷል፡፡ የኮንስትራክሽን ግብዓት አምራች የሆኑ ቦታዎች በግጭት ምክንያት ተደራሽ መሆን አልቻሉም። የነዳጅ ጭማሪውና የመሳሰሉት ችግሮች እየተደራረቡ ሲመጡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በራሱ መቆም የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ችግሩ ብዙ ትንተና የሚያስፈልገው ነው፡፡ 

ሪፖርተርበኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታው ችግር ይበልጡኑ አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ጎድቷል የሚል አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፣ ይህ እንዴት ይገለጻል፡፡ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የውጭ ኮንትራክተሮች ገበያውን ይዘውታል፡፡ የአገር በቀል ኮንትራክተሩ ተውጧል የሚሉም አሉ፡፡ የእርስዎ ምልከታ ምንድነው? 

አቶ ግርማ፡- የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በውጭ ኮንትራክተሮች እየተወረሩ ነው። ይህንን ዝም ብሎ የሚነገር ነገር ሳይሆን በተግባር እያየነው ያለነው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዝም ብሎ የሚጋልብ አንድ ቦታ ተነስቶ አገር የሚያዳርስ ወሬ አለ፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ብቃት የላቸውም፣ የውጭዎቹ በከፍተኛ ደረጃ ይሠራሉ የሚል ወሬ አለ፡፡ አዎ በእርግጥ እነሱ በተሻለ ሊሠሩት የሚችሉባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በብዙ ችግሮች የተተበተቡ ናቸው፡፡ የውጭዎቹ ግን ለምሳሌ የቻይና ኮንትራክተሮችን ብናይ በአብዛኛው የቻይና መንግሥት ኩባንያዎች ስለሆኑ፣ ከመንግሥታቸው ድጋፍ ያላቸው ናቸው፡፡ እዚህ ግን የአገር ውስጥ ኮንትራክተሩ በሚገባ ስለማይደገፍና አሁን ያሉት አሠራሮች እነሱን ብልጫ እንዲይዙ የሚያደርግ በመሆኑ ተፅዕኖው እየጨመረ ነው፡፡ 

ሪፖርተርየውጭ ኮንትራክተሮች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይዘዋል ቢባልም፣ በተለየ ደግሞ እንደ ‹‹ሲሲሲሲ›› እና ‹‹ሲሲኢሲሲ›› ያሉ የቻይና ኮንትራክተሮች የሚሰጣቸው ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡ ለምሳሌ ሲሲሲሲ ለብቻው አሁን በእጁ ላይ በመንገድ ውስጥም ሥራ ብቻ 20 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ዋጋ ያለው ሥራ ይዟል፡፡ የኢትዮጵያ አየር  መንገድ ወደ 800 ቢሊዮን ዶላር ሥራ ተረክቧል፡፡ ሌሎች ሥራዎችም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ተጨማሪ ሥራዎች ሲሰጡት ማየት ከፍትሐዊነት አንፃር አግባብ  አለመሆኑ ይገለጻል፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን እናንተ እንዴት ነው የምትከታተሏቸው?

አቶ ግርማ፡- ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በቅርቡ በወጣ ጥናት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ትልልቅ ከሚባሉት የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሦስት በመቶውን ብቻ ነው መያዝ የቻሉት። ይህ ማለት ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ሞኖፖላይዝድ ሆኗል ማለት ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተዳደር አሠራሩ ዘመናዊ ነው፡፡ እናም አገር በቀሉን ለማገዝ የውጭ ኮንትራክተሮች ከሚወስዱት ሥራ አርባ በመቶ ድረስ ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እንዲሰጡ እያስገደዱ ነው፡፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ነገር ግን የመንገድ ፕሮጀክቶች ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች መጫረት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሊጫረቱ አይችልም እያሉ ይናገራሉ፡፡ የዚህ መሠረታዊ ችግር የግዥ ኤጀንሲ ያወጣው ፎርሙላ ነው፡፡ ዓመታዊ ተርን ኦቨርን አሥልቶ የሚወጣ የጨረታ ሒደት የሚጠይቀው ክፍያ በጣም ከፍተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ወደ መንገድ ፕሮጀክት እንዲገቡ የሚያስችል አቅም የላቸውም፡፡ ሕጉ መለወጥ አለበት፡፡ መንግሥት ባወጣው ሕግ ጭምር ነው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እየተዋጡና የውጭ ኮንትራክተሮች የአገሪቱን ሪሶርስ እንዲቀራመቱ በር የተከፈተላቸው፡፡ 

ሪፖርተርበቅርብ የወጣ መረጃ የውጭ ኮንትራክተሮች በአብዛኛው የቻይና ኮንትራክተሮች አሁን በሥራ ላይ ካሉ የፌዴራል የመንገድ ፕሮጀክቶች 80 በላይ ያለውን ሥራ መያዛቸው ይነገራል፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተደምረው የያዙት ሥራ በጣም ዝቅተኛ ነው ይህ ምን ያሳየል?

አቶ ግርማ፡- ይህንን ያህል ደረጃ ላይ መድረሱ ብቻ አይደለም አስገራሚው ነገር፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የተረከቡትን ሥራ በአግባቡ ጨርሰው እንዳያስረክቡ የሚያደርጋቸው ውጭዎቹ የተሻለ ዕድል ስለተመቻቸላቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የክሌምን ጉዳይ ብናይ፣ አገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እንደ ውጭዎቹ አይያዝላቸውም፡፡ የውጭ ኮንትራክተሮች በተለያዩ መልኩ በተለያየ የአገር ችግር ክፍያ ቢዘገይባቸው በፀጥታ ምክንያት ሥራ ቢቆም፣ በአጠቃላይ አስገዳጅ በሆኑ ምክንያቶች ሥራቸው ቢዘገይ ክሌማቸው ይረጋገጥላቸዋል፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ግን በዚህ ደረጃ አይደገፍም፡፡ የበጀት እጥረት ችግር አለ፡፡ ብዙ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ክፍያዎች ቆመዋል፣ በሰዓቱ አይከፈልም፡፡ ከወር በላይ ክፍያ ከዘገየ የባንክ ወለድ ይጠየቃል፡፡ ወይም ለኮንትራክተሩ መክፈል እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህ ግን ተግባራዊ አይሆንም፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር የአገርን ችግር ዋጥ አድርጎ ነው እየሠራ ስለዚህ የውጭ ኮንትራክተሮች ከአገር በቀሉ የተሻለ ምቹ ሁኔታ ስላላቸው ሥራዎቹን እየጠቀለሉ ይወስዳሉ፡፡   

ሪፖርተር፡የዋጋ ማስተካከያ ግን ለአገር በቀል ኮንትራክተሮችም ተፈጻሚ እንዲሆን ይፈቀዳል እኮ

አቶ ግርማ፡- የሚባለው ሌላ ነው፣ የሚሆነው ግን ሌላ ነው፡፡ ለምሳሌ በመንገድ ሥራ ላይ 30/70 የሚል የዋጋ ማስተካከያ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም 15/85 የሚባል አሠራር ነበር፡፡ አሁን 30/70 ሆነ፡፡ በዚህ እሴት ማካካሻ ይሰጥ ነበር፡፡ ይህም በአግባቡ አይተገበርም፡፡ ለምሳሌ የሲሚንቶ ችግርን ተመልከት ከ500 ብር በማይበልጥ ዋጋ ከፋብሪካ የተገዛ ሲሚንቶ መሀል ከተማ ውስጥ እስከ 1,800 ብር ይሸጣል፡፡ መንግሥት ይህንን እያየ ዝም የሚባልበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ እንዲህ መሆኑ የሚያመጣው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ የዋጋ ማስተካከያ ተደርጎልን ነበር፡፡፡ ይህ የዋጋ ማስተካከያ 40 በመቶ ኮንትራክተሩ ይችላል፡፡ 60 በመቶውን መንግሥት ይችልና ይሥራ ተብሎ ነው ማስተካከያው የወጣው፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ግን ኮንትራክተሩ 40 በመቶ አይደለም፡፡ 

ሪፖርተርየውጭ ኮንትራክተሮች ቴክኖሎጂንና ክህሎትን ለማስተላለፍ ይረዳል ተብሎ ታምኖባቸው፣ ይህም መተግበር እንደሚኖርበት ይታወቃልና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ክህሎት እየተደረገ ነው ማለት ይቻላል? 

አቶ ግርማ፡- ይህንን ያህል አፍን ሞልተን የምንናገርበት አይደለም፡፡ ዋና ዋና ሥራዎችን በራሳቸው ዜጎች ዘግተው ነው የሚሠሩት፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚደረገው ተፅዕኖ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ መንግሥት አምኗቸው በሚሰጣቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን እስከ 40 በመቶ እንዲያሳትፉ በውለታቸው ውስጥ ግዴታ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ አይደረግም፡፡ የሚቆጣጠር ማዕከል የለም፡፡ ይኼ ጉዳት አለው፡፡ በመንግሥት በኩልም ራሱ አንዳንድ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሊሠሩ የሚችሉትን ፕሮጀክቶች ካለ ምንም ከልካይ አንስተው ለእነሱ ይሰጣሉ፡፡ መንግሥት ይህንን የሚያደርገው በአጭር ጊዜ ሥራውን አጠናቀው ያስረክባሉ ከሚል ነው፡፡ በዋጋ ደረጃ ሲታይ ግን 300 እና ከዚያም በላይ በሆነ ዋጋ ነው የሚሰጣቸው፡፡ ይህንን እንኳን የሚከታተል የሚቆጣጠር የለም፡፡ የውጭዎቹ ኮንትራክተሮች ማንነታችንን መርምረው አውቀዋል፡፡ ስለዚህ በአገር ውስጥ ገበያ ላይ የበላይነቱን ይዘው እንዲቀጥሉ አድርገዋል፡፡ ሌላው ደግሞ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሊሠሩት የሚችሉን ሥራ ወይም ተርሚኔት የተደረጉ ሥራዎችን በከፍተኛ ደረጃ የእጥፍ እጥፍ በሆነ ዋጋ ለውጭ ኮንትራክተሮች መሰጠቱ ነው፡፡ ከውጭ ኮንትራክተሮች ባልተናነሰ መልኩ ችግር እየፈጠረ ያለው ጉዳይ በየክልሉ የተቋቋመው የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ናቸው፡፡ እነዚህም ቁጥጥር የሌላቸው ሆነዋል፡፡ በደርግ ጊዜ ሁሉ ሥራ ይሰጥ የነበረው ለመንግሥታዊዎቹ ለሕንፃ ኮንስትራክሽን፣ ለበርታ፣ ለናሽናል ኮንትራክተር ለመሳሰሉት ነው፡፡ አሁን ግን በክልል መንግሥታት ለተቋቋሙት የኮንስትራክሽን ድርጅቶች በቀጥታ ነው የሚሰጠው፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ እያለ የአገር በቀል ኮንትራክተር በየት በኩል ይደግ? የአገር ውስጥ ተቋራጭን አቅሙን ገንብተን በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እናደርገዋለን እየተባለ በመንግሥት አካላት እየተነገረ፣ በግልጽ በፖሊሲ ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም ሲተገበር አይታይም፡፡ ለምሳሌ አንድ የአማራ ክልል ውስጥ በዓይኔ ያየሁትን ልንገርህ፡፡ የ400 ሚሊዮን ብር ሥራ የአማራ ኮንስትራክሽን ድርጅት እንዲሠራው ተሰጠ፡፡ ይህ ገንዘብ ትንሽ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ጥቃቅን ሥራ እነሱ ከሠሩ አቅሙን እናሳድግለታለን ደግፈነው ሠርቶ አገር ይደግፋል፣ ሌላውንም ያሳድግለታል የተባለው ኮንትራክተር ከምን የተረፈ ሥራ አግኝቶ ነው የሚያድገው፡፡ በዚህ የውጭ ኮንትራክተሮች በሌላ በኩል ደግሞ የክልል የኮንስትራክሽን ድርጅት ዝም ብሎ ሥራ እየተሰጣቸው ሥራ እንዴት ማግኘት ይቻላል፡፡ ከግዥ ባለሥልጣን የወጣ ሕግ ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ማነቆ መሆኑም ችግር ነው፡፡ 

ሪፖርተርየውጭ ኮንትራክተሮች አሁን እየታየ ባለው ደረጃ የግንባታ ሥራዎችን ጠቅልለው እየወሰዱ ነው ከተባሉ፣ አሁን እየታየ ካለው ችግር ባሻገር ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖ ምንድነው? እንደ ማኅበርስ ምን ለማድረግ ታስባላችሁ?

አቶ ግርማ፡- እንደ ማኅበረሰብ ዝም ብለን አልተቀመጥንም፡፡ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ከመንገዶች አስተዳደር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ጋር በቅርበት እየተነጋገርን ነው፡፡ የሚሻሻሉ ሕጎች እንዳሉ ተማምነናል፡፡ የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ከሥራ እየተገለሉ የበይ ተመልካች መሆናቸውን ተማምነናል፡፡ የውጭ ኮንትራክተሮች ገበያውን በከፍተኛ ደረጃ መቆጣጠራቸውን ደርሰውበታል፣ ጥናቱም ያመለክታል፡፡ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የኮንትራክተሩን አቅም ለመገንባት ለምሳሌ ተቋርጦ የነበረው ማሽነሪዎችና የመሳሰሉ ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ይፈቅድ የነበረው አሠራር አሁን በመጀመሩ ይህንን ማጠናከር አንድ መፍትሔ ነው፡፡ ይህም ቢሆን አሠራሩ ግድፈት ያለበት መሆኑ እንዲታረም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማበረታቻ ከእነ ችግሩ እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አቅማቸውን ገንብቶ በመንገድ ሥራ አለመግባት ምክንያት ለውጭ ሕጉ አግዟቸዋል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሲሲሲሲ››ን ያየህ እንደሆነ ያቆመው ፕሮጀክት አለ፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ቢሆን እየተጨቃጨቀም ቢሆን ሊሠራው ይችላል፡፡ የውጭዎቹ ግን ሕግ ሕግ ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንዳንድ የውጭ ኮንትራክሮች ላይ ያለውን ድክመት ያለባቸውና ብቃት የሌላቸው የተባሉም አሉ፡፡ የእኛ አገር ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ታሪኩ ብዙ ነው፡፡ 

ሪፖርተርቀደም ብለው እንደጠቀሱልኝ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪ ላይ እንደ ችግር እየታየ ያለውና የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ላይ ተፅዕኖ እያሳረፈ ያለው አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ያለ ጨረታ መስጠት ነው፡፡ ይህ ከሕግ አንፃር አግባብ አይሆንምና ይህንን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?  

አቶ ግርማ፡– የግዥ የኤጀንሲ (ባለሥልጣን) አንድ የወጣ ሕግ አለ፡፡ ሦስት ዓይነት የአሠራር ሕጎች አሉ፡፡ ጨረታ ግድ ነው፡፡ የውጭ ኮንትራክተሮች የግንባታ ሥራ ሲገቡ መነሻ ዋጋው 600 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ከዚያ በታች መጫረት አይችሉም፡፡ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ግን በራሳቸው ሥልጣን እንደዚያ የሚያደርጉ አሉ፡፡ በእኛ በኩል አሁን ካለው የዋጋ ሁኔታ አንፃር፣ ይህ እንዲሻሻል ማኅበራችን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ካልኖረ በቀር፣ ወይም የፕሮጀክቱ አስፈላጊነት ታምኖ ልዩ ትዕዛዝ ካልመጣ በቀር፣ ወይም የተለየ ቴክኖሎጂ ድጋፍ የሚጠይቅና በመሳሰሉ ጉዳዮች ካልሆነ በቀር፣ ሥራዎች ያለ ጨረታ ሊሰጥ አይቻልም፡፡ ከዚህ ውጪ ዝም ብሎ የሕዝብን ፕሮፐርቲ አንስቶ መስጠት በሕግ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ከተጠያቂነት ለመዳን በሚል ለአገር ውስጥ ኮንትራክተር ከመስጠት ለውጭ አገር መስጠት ይሻላል በሚል የሚያደርጉ አሉ፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር በፍፁም በሕግ አይደገፍም፡፡ በተለይ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ፕሮጀክት በምንም መልኩ ያለ ጨረታ መስጠት አይቻልም፡፡ በግዥ ባለሥልጣን አሠራርም አይፈቀድም፡፡ 

ሪፖርተርነገር ግን ከዚህ ውጪ ያለ ጨረታ እየተሰጡ መሆናቸው የሚነገርላቸው ፕሮጀክቶች አሉ?

አቶ ግርማ፡- አዎ እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርብ ጊዜ 40 ሚሊዮን ብር፣ 87 ሚሊዮን ብርና የተለያዩ ዋጋ ያላቸው ሥራዎችን ካለ ጨረታ በጥቃቅን ለተደራጁ ሰጥቷል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር ነው ግራ የሚያጋባው፡፡ የብሔራዊ ቴአትር ፕሮጀክት ቴክኖሎጂ ይዘው ወተዋል ተብሎ ነው የተሰጣቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡ ይህ በመንግሥት በኩል ምን ያህል ድጋፍ ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን የምናውቀው ነገር የለም፡፡ የቤቶች ግንባታ ላይም አንድ ፕሮጀክት ጨረታ ሳይወጣ ለውጭና ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተሰጠ ተብሎ ነው የተነገረው እንዲህ ያለ ነገር አለ፡፡   

ሪፖርተርእንዲህ ያለው ሁኔታ ማቆሚያ ከሌለው በተለይ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተጎጂ ይሆናሉ የሚሉ አስተያየቶች በሰፊው ይሰነዘራል፡፡ እርስዎም ይህ ጉዳይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ጠቅሰውልኛልና ተፅዕኖ እንዴት ይገለጻል?   

አቶ ግርማ፡– ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ያለ ምንም ጥርጥር የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ከገበያ የሚያወጣ ነው፡፡ ኮንትራክተሩ ግብር ከፋይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሪሶርስ ላይ መጠቀም መብቱ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ማደግ ለአገር ዕድገት ይጠቅማል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የአቅም ማነስ አለባቸው ይባላል፡፡ አቅም ካነሳቸው አቅማቸውን እንዲያጎለበቱ ማድረግ እንጂ፣ ከጨረታ ውጪ ማድረግ ተገቢ አይሆንም፡፡ ሲስተም ባልተዘረጋበትና ሙስና በነገሠበት አካባቢ በሚታይበት ኢንዱስትሪ ላይ ብዙኃኑን ኮንትራክተር ሥራ ላይ እንዳይሰማራ ማድረግ ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ 

ሪፖርተር፡በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ አሉ የሚባሉ ችግሮች ግን የራሱ የኮንትራክተሩ ስለመሆኑ የተሸሸገ ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሥት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች እንዲበረታቱ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ብዙ ሁኔታዎችን አመቻችቶ አልተጠቀመበትም ይባላል፡፡ ሌላው ቀርቶ የመጫረቻ ዋጋ ከውጭዎቹ እንዲያንስላቸው ተደርጎ እንኳን አልቻሉም ይባላል፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ የቻይና ኩባንያዎች መግቢያ ቀዳዳ እንዲያገኙ ረድቷል ለሚለው አስተያየት ምላሽዎ ምንድነው?   

አቶ ግርማ፡- ችግሩ እሱ አይደለም፡፡ የእኛ ትልቁ ችግር ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ቅድሚያ የመስጠት ቁርጠኛ ያለመሆኑ ነው ሥራ እየተጓተተ ነው፡፡ ሥራዎች በወቅቱ አያልቁም የሚባሉ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ ይህ የኮንትራክተሩ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የጦርነቱ ጉዳይ፣ የነዳጅ መጨመር፣ የውጭ ምንዛሪ ችግር አለ፡፡ እንዲህ ባሉ ምክንያቶች ለተፈጠሩ ችግሮች ኮንትራክተሮች ተጠያቂ አይደሉም፡፡ ከመንግሥት አቅም ውጪ የሆነንና በአስገዳጅ ሁኔታዎች ለዘገዩ ፕሮጀክቶች የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ስላልቻሉ ለውጭ ኮንትራክተር እንሰጣለን ወይም ሰጥተናል የሚለው ነገር ትክክኛ አካሄድ አይደለም፡፡ ችግሮችን ሁሉ ተቋቁሞ፣ እየሠራ ያለውን የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ትቶ ለውጭ ኮንትራክተር ሥራዎችን የመስጠት አካሄድ ሙሉ ለሙሉ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ሊያናጋ ይችላል፡፡ 

ሪፖርተርየአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አሁንም የሚተቹበት ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት አሥር በላይ የሚሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ትልልቅ ሕንፃ ግንባታዎችን ያካሄዱና በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ የእነዚህን ሕንፃዎች ግንባታ በሙሉ በጨረታ አሸንፈው የወሰዱት የቻይና ኩባንያዎች እንዲህ ባሉ ሥራዎች ላይስ አገር በቀል ኮንትራክተሮች የማይሳተፉበት ምክንያት ምንድነው? 

አቶ ግርማ፡– ይኼ እኮ የተለመደ ነገር ነው፡፡ እዚህም አካባቢ ቢሆን ከሙስና የፀዳ ነው የምትለው አይደለም፡፡ የባንኮች ሕንፃዎች በጥራት ተሠርተዋል፡፡ በዋጋ ደረጃ ግን የተጋነነ ዋጋ የወጣባቸው መሆኑን ማየት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተርበእነዚህ የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የተሳተፉ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች ያለመኖራቸውስ እንደ ድክመት አይታይም?   

አቶ ግርማ፡- ይህ ያልሆነበት ምክንያት ዓለም አቀፍ ጨረታ በመሆኑ ነው፡፡ የጨረታ መሥፈርቱም ቢሆን ኢትዮጵያውያን የሚያሟሉት ስላልሆነም ነው፡፡ መሥፈርቱ ወደ ላይ ከወጣና ኮንትራክተሮቻችን ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር ከተጠየቀ እንዴት አድርገው ነው የሚካፈሉት፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ድርጅቶች ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር (የቀድሞ ባለሥልጣን) ላሉን ፕሮጀክቶች በቂ ኮንትራክተር ማግኘት አልቻልንም ሲል ይሰማል፡፡ በዚህም ምክንያት በጀት እየታጠፈብን ነው የሚል አቤቱታ ያሰማሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችልበት አንዱ ምክንያት የመንገድ ሥራ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅና ኮንትራክተሮች በቢሊዮን የሚቆጠር ተርን ኦቨር ስለሚጠይቁ ነው፡፡ በጣም ጥቂዎቹ ናቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ተርን ኦቨር ያላቸው፡፡ ስለዚህ በሚመጣው ዓመታዊ ተርን ኦቨር መመዘኛ ላይ የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች የተጠየቀውን መሥፈርት አሟልተው ሊሳተፉ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ለመሳተፍ ይችላሉ፡፡ በጨረታ ሒደቱ ዶክመንት ውስጥ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮቹን የሚያበረታታ ሪኳርመንት የለም፡፡ አያበረታታም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደ ማኅበር ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ሕጉን የግዥ ባለሥልጣን ካላሻሻለው በቀር እኛ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ መቀየር አንችልም የሚል ነው ያገኘኘው ምላሽ፡፡  

ሪፖርተርእንደጠቀሱልኝ እንዲህ ያሉ ችግሮች እየተጠቀሱ፣ ኮንትራክተሩ ሥራ የሚያገኝበት ሁኔታ ከተፈጠረ ዕጣ ፈንታው ምን ሊሆን ነው?   

አቶ ግርማ፡– የማኅበራችን ዋነኛ ጥያቄና እየሠራንበት ያለነው ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እነዚህ ሕጎች ይሻሻሉ ብለናል፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የወጣ ሕግ 2015 ዓ.ም. ላይ ሊሠራ አይችልም፡፡ በአገር ውስጥ ያለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ባህሪ በዓለም ላይ ያለው የኮንስትራክሽን ባህሪ የግብዓቶች እጥረት፣ የዋጋ ንረቱ፣ ጦርነት ያመጣው ችግር፣ ኮቪድ ያሳረፈው ተፅዕኖ፣ የነዳጅ ዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሪ ችግር ተፅዕኖ አሳርፎበታል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከአምስት ዓመታት በላይ መንግሥት በበጀት እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች ለጨረታ ያወጣቸው ፕሮጀክቶች ስለሌሉ ብዙኃኑ ሥራ ፈትቷል፡፡ በአምስት ዓመታት ውስጥ ተርን ኦቨር ይህንን ያህል ይሁን የሚለው ሕግ አዳዲስ ሥራዎች በሌለበት ሁኔታ እንዴትም ሊሳካ አይችልም፡፡ በሌለ ሥራ አምጡ የሚለው መሥፈርት መስተካከል አለበት፡፡ 

ሪፖርተርጨረታዎች እንደ ቀድሞ ያለመውጣታቸው ዋነኛው ችግር ምንድነው? እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖስ? 

አቶ ግርማ፡- ይህ የአገር ችግር ነው፡፡ ይህንን በደንብ እንረዳለን፡፡ በጀት የለም ዕርዳታ የለም፡፡ ብድር የለም፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ ጨረታዎች በእጅጉ መቀዛቀዛቸው አይቀርም፡፡ ይህንን እንረዳለን፡፡ ሼር ማደረግ አለብን፡፡፡ የሌለውን ውለድ አይደለም የምንለው፡፡ ያለውን ግን በአግባቡ ይሠራ ነው የምንለው፡፡ ብዙ መንግሥት በሚያሠራቸውን ፕሮጀክቶች ክፍያ ማግኘት ተቸግረዋል፡፡ ይህ ጥያቄ በብዛት ወደ እኛ እየመጣ ነው፡፡ ችግሩ ፕሮጀክት እስከ ማቆም ያደረሰ ሆኗል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን መፍታት የሚለውን ነው እንጂ፣ ጨረታ ቀንሷል በእኛ አገር ጨረታውን የሚያወጣው ደግሞ መንግሥት ነው፡፡  

 

 

 
     

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች