Monday, June 24, 2024

የአገራዊ ምክክሩ መዘግየትና ጥያቄ ያስነሱ ጉዳዮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እንዳስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ጊዜ በርካታ የምክክር መድረኮች ይታዩ እንደነበር ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡ የጊዜ አጠቃቀም ደካማነትና አርፋጅነት ባህል በሆነበት አገር ግን እጅግ ብዙ የተጠበቀው አገራዊ ምክክርም ከዛ የተለየ ዕጣ የገጠመው አይመስልም፡፡ ከሰሞኑ ለፓርላማው የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረበው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋናነት ሲቀርብለት የነበረው ጥያቄ ምክክሩን ከምን አደረስከው? የሚል ነበር፡፡

ስለምክክር ጥራት በሰፊው ሲተነትን የዋለው ኮሚሽኑ፣ ጥራት ያለው የምክክር ሥራ ለማካሄድ የሚያስችል ጥንቃቄ የተሞላበት ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወን ጊዜ እንደወሰደበት ለማሳመን ሞክሯል፡፡

በሌላም በኩል ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍሎች ለማዳረስና ሁሉን ያካተተ ውይይት ለማድረግ መሠራት ያለበት ሥራ ሰፊና ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑም፣ ሌላው ወደ ምክክሩ በቶሎ ለመግባት እንቅፋት እንደሆነበት ኮሚሽኑ ሲያስረዳ ተደምጧል፡፡

አሥራ አምስት አባላት ያሉት የፓርላማው የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግን ደጋግሞ ካነሳቸው ጥያቄዎች ቀዳሚው ‹‹ምክክሩ የት ደረሰ?›› የሚለው ጥያቄ አንዱ ነበረ፡፡ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮቹ ኮሚሽናቸው በሚሠራቸው በርካታ ሥራዎች ጥሩ እመርታ ማስመዝገቡን በሰፊው ቢያስረዱም፣ ምክክሩ ለዘገየበት ግን ለቋሚ ኮሚቴው አሳማኝ አመክንዮ ያቀረቡ አይመስሉም፡፡ ያም ቢሆን ግን በዘጠኝ ወራት ተሠሩ ብለው ካቀረቧቸው ጉዳዮች መካከል ውይይቱ የሚመራበትን ሒደትና ቅደም ተከተል ያስቀመጡበት መንገድ በርካታ አዳዲስና ትኩረት የሚስቡ ነጥቦች የተነሳበት ነበር፡፡

መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ባቀረቡት ሪፖርት፣ የምክክሩ ቅደም ተከተል የሚመራበት ሒደት የሚከተለው መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በአገሪቱ 1,300 ወረዳዎች እንዳሉ፣ በእያንዳንዱ ወረዳ ደግሞ በምክክር መድረኮች ሊወከሉ የሚገባቸው ተብለው ዘጠኝ ባለድርሻ አካላት መለየታቸውን፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ዘጠኝ ባለድርሻ ተብለው የተለዩ አካላት በየወረዳው መኖራቸውን፣ ከእነዚህ ከእያንዳንዳቸው ከዘጠኙ ባለድርሻ አካላት ደግሞ 50 ሰዎች እየተመረጡ ተሰባስበው እንደሚመክሩ፣ ለምሳሌ ሴቶችን የሚወክሉ 50 ሰዎች ለብቻቸው ተሰብስበው ይወያያሉ ተብሏል፡፡

ተሰብስበው ከሚወያዩት 50 ሰዎች መካከል ደግሞ ከዘጠኙም ባለድርሻ አካላት ሁለት ሰዎች ይመረጣሉ፡፡ እንዚህ ሁለት ሰዎች የእያንዳንዱን ባለድርሻ አካል አጀንዳ (ጥያቄ) ይዘው የሚመጡ ናቸው፡፡ በወረዳ ደረጃ የሚካሄደው ውይይት በስተመጨረሻ እነዚህን ሰዎች ጨምሮ ከ450 ያልበለጡ ሰዎች የሚካፈሉበት ይሆናል ማለት ነው፡፡

በዞን ደረጃ የሚካሄደው ውይይት ደግሞ ከእያንዳንዱ ወረዳ በየውይይቱ ተመርጠው የሚመጡ ሁለት ተወካዮችን ያካተተ ነው የሚሆነው፡፡ በዞን ደረጃ የዞን ጉዳዮችን አጀንዳ ያደረገ የተለያዩ የዞን ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ውይይትም ለብቻው ይኖራል፡፡ ከእያንዳንዱ ዞን በውይይቶች የሚመረጡ ተወካዮች ወደ ክልል ያመራሉ፡፡ በክልል ደረጃ የሚደረገው ውይይትም ሁለት ዓይነት መልክ ያለው ሲሆን፣ አንዱ ከየዞኑ የተወከሉ ተወካዮች የሚሳተፉበት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የማኅበረሰብ ወኪሎችና ሌሎች የሚሳተፉበት ነው፡፡

ከእነዚህ ሁለት ዓይነት የየክልሉ ውይይቶች የተመረጡ ተወያዮች ናቸው፣ በፌዴራል ደረጃም ለሚካሄደው ዋናው የምክክር መድረክ ተሳታፊ የሚሆኑት፡፡

ዋና ኮሚሽነር መስፍን (ፕሮፌሰር) በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት በየትም አገር በሚደረጉ አገራዊ ምክክሮች በዋናው የውይይት መድረክ የሚወከሉ ሰዎች ቁጥር ከ2,000 እስከ 2,500 በልጦ አያውቅም፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ በፌዴራል ደረጃ በዋናው ውይይት ላይ የሚካፈሉት ከ2,500 የማይበልጡ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡

አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከውይይቱ ሒደት ቅደም ተከተል በዘለለም፣ የአማካሪ ኮሚቴን መቋቋምን በተመለከተ በሪፖርቱ አዲስ ነገር ይፋ አድርጓል፡፡ ኮሚሽኑ መጀመርያ ሲዋቀር ከመላ አገሪቱ 75 ሺሕ ሰዎች ተጠቁመው ከእነዚህ ወደ 3,000 ተለይተው፣ ከዚያም 42 መቅረታቸውንና በስተመጨረሻ 11 ሰዎች በኮሚሽነርነት መሰየማቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ጠቃሚ ሒደት መሆኑን አውስተዋል፡፡ ከእነዚህ 75 ሺሕ  ተጠቋሚ ሰዎች መካከል ግን በአማካሪነትና በተለያዩ ሥራዎች ኮሚሽኑን ማገልገል የሚችሉ ሰዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ በአማካሪ ኮሚቴነት የተወሰኑት መምጣታቸውን ያመለከቱት መስፍን (ፕሮፌሰር)፣ በሌላ በኩል በአመቻችነትና በአወያይነት የሚመረጡ ሰዎችም ልክ እንደዚሁ ማኅበረሰቡን የሚወክሉ ሰዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከሪፖርቱ በኋላ በሰጠው መግለጫ 35 አባላት ያሉት አማካሪ ምክር ቤት መመሥረቱን አስታውቋል፡፡

‹‹አመቻቾች በየሠፈሩና በየአካባቢው የተከበሩና ኅብረተሰቡን በቅጡ የሚያውቁ የአገር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰብ ወኪሎች ናቸው፡፡ አወያዮች ደግሞ በገለልተኝነት የሚመረጡ በውይይት መምራትና ምንነት የተሻለ ዕውቀት ያላቸውና በኅብረተሰቡ ዘንድ የተከበሩ ሰዎች ናቸው፤›› በማለት በሪፖርታቸው በቀጥታ የተረጎሙት ዋና ኮሚሽነሩ፣ እነዚህን የምክክር መድረኮች ቁልፍ ባለድርሻዎች የመምረጥና የማደራጀት ሥራ በተለያዩ መንገዶች እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ ኮሚሽናቸው ከኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ ከአገር አቀፍ ዕድሮች ማኅበራትና ጥምረት፣ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን አስረድተዋል፡፡ ይህ ደግሞ አወያዮችንና አመቻቾችን የመለየት ሥራቸውን እንደሚያቀለው ነው የተናገሩት፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ መዋቅር የመዘርጋትና ራሱን የማደራጀት ሥራ እጅግ የከበደና ጊዜ የወሰደ እንደሆነበት ገልጿል፡፡ ከቀደሙት ሁለት ኮሚሽኖች የተረከባቸውን ሠራተኞች ቋሚ ለማድረግ ዘጠኝ ወራት እንደፈጀበት ይፋ አድርጓል፡፡ እጅግ የበዛ የመስክ ጉዞ ለሚጠይቅ ሥራ በ2,500 እና በ4,000 ብር ወርኃዊ ደመወዝ ሠራተኛ ቀጥሮ በመንግሥት የውሎ አበል ሕግ ማሠራቱ ፈታኝ እንደሆነበት አመልክቷል፡፡ ወደ 30 የሠለጠኑ ሠራተኞችን ጨምሮ አሁን ወደ 60 ሠራተኞች መቅጠሩን አስታውቋል፡፡

እስከ 3.2 ቢሊዮን ብር በጀት ያስፈልገኛል ሲል ይፋ ያደረገው ኮሚሽኑ፣ በአንድ ዓመት ጉዞው ሥራ ላይ አውየዋለሁ የሚለው በጀት 88 ሚሊዮን ብር  ብቻ መሆኑ ምክር ቤቱን ግራ አጋብቶ ነበር፡፡ በመንግሥት የተመደበለት 148 ሚሊዮን ብር ቢሆንም ከዚህ ውስጥ ግን የተጠቀመው 25 ሚሊዮን ብር (18 በመቶ) ብቻ መሆኑን መግለጹ፣ ውጤታማ ቁጠባ ሳይሆን ዝቅተኛ በጀት አጠቃቀም ተብሎ በቋሚ ኮሚቴ አባላት ተወስቷል፡፡ በዋናነት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) 80 ሚሊዮን ብር ልገሳ ማግኘቱን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፣ በሥራ ላይ ያዋለውም አብላጫ ገንዘብ ከዚሁ ምንጭ የተገኘ ነው ብሏል፡፡

ቅርንጫፍ በመክፈት በኩል ከፌዴራል ዩኒቨርሲቲዎች ኮንሶርቲየም ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም፣ በየዩኒቨርሲቲዎች ቅርንጫፍ የመክፈት ስትራቴጂን እንደሚከተል ጠቁሟል፡፡ ይህ ወጪ ከመቆጠብ አንፃር ብቻ ሳይሆን ለደኅንነት ጥበቃም አዋጪ መሆኑን፣ የዩኒቨርሲቲዎችን የሠለጠነ የሰው ኃይል ለመጠቀምም አዋጪ መሆኑን እንደሆነ ጠቅሷል፡፡

በእስካሁን ሒደት ሠራሁት ያላቸውን ጉዳዮች በአኃዝ አስደግፎ ያቀረበው ኮሚሽኑ በፌዴራል የተካሄዱትን 217 ጨምሮ 1,711 ስብሰባዎችን ማካሄዱን ገልጿል፡፡ ሦስት ያህል መመርያዎች ማፅደቁንና አራት ደግሞ ለመፅደቅ በሒደት ላይ እንዳሉ አመልክቷል፡፡ ከስምንት ባላነሱ ቋንቋዎች መመርያና አዋጁን ማስተርጎሙን፣ ከ40 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር፣ ከኢንተርናሽናል ኮሚዩኒቲ ጋር፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠራም አብራርቷል፡፡

ይሁን እንጂ በአገሪቱ በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችና ያልተጠበቁ የፀጥታ መደፍረሶች እክል መሆናቸውን ሳይገልጽ አላለፈም፡፡ የኦሮሚያ ሰባት ዞኖች ጉዳይ  (በዋናነት ምዕራብ ኦሮሚያ) ብዙ መሻሻሎች ቢኖሩም ገብቶ ለመሥራት ገና አመቺ ሁኔታ አለመፈጠሩን አመልክቷል፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው ሁኔታም አስተማማኝ የሚባል አለመሆኑን ተናግሯል፡፡ በትግራይ ክልል ግን አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል ብሎ በማመኑ ገብቶ ለመሥራት ለጊዜያዊ የክልሉ መስተዳድር ደብዳቤ መጻፉን ይፋ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ በኮሚሽነሮቹ በኩል እነዚህና ሌሎችም በርካታ የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውኖችን ለፓርላማው የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከማቅረብ ባለፈ፣ በርካታ ጥያቄዎችም ቀርበውለት ነበር፡፡ በተለይ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ወደ ውይይት ለምን መግባት አልተቻለም የሚለው ጉዳይ ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ጠንከር ብሎ ነው የተነሳው፡፡ የአወያዮችና የአመቻቾች፣ እንዲሁም የውይይት አጀንዳዎች መረጣ ጥንቃቄ ይደረግበት ከሚለው ባለፈ፣ ኮሚሽኑ ዳያስፖራውን በተመለከተ በምን ሁኔታ እንደሚያሳትፍ ጠንካራ ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡ ከሽግግር ጊዜ ፍትሕ ጋር በተገናኘ፣ ከሴቶች አካታችነትና ከሚዲያዎች ትብብር ጋር በተገናኘም ኮሚሽኑ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውለታል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ‹‹የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ፣ ከሽግግር ጊዜ ፍትሕ ጋር ያለው ቅንጅት ምን ይመስላል?›› የሚለው ይገኝበት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እጅግ በርካታ የሰብዓዊና የጦር ወንጀሎች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን ያነሱት አንዳንድ የኮሚቴው አባላት፣ እነዚህ ዝም ተብለው ሊታለፉ እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡ በየትም አገር ቢሆን ከዕርቅና መግባባት በፊት የሽግግር ጊዜ ፍትሕ እንደሚከናወን ያስረዱ የምክር ቤት አባላት፣ ከምክክር በፊት በኢትዮጵያ ለተፈጸሙ ወንጀሎችና ግፎች ፍትሕ መስጠት ጠቃሚ ዕርምጃ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በአንዳንድ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ኮሚሽኑ ከሚዲያዎች ጋር የፈጠረው ቅንጅት ተጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመሳሰሉ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን በቂ ዕገዛ እያደረጉላችሁ ነው ወይ ተብሎም ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ከዚህ  ጎን ለጎንም በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በተለያዩ ኢመደበኛ መገናኛ ብዙኃን እጅግ የገዘፈ ተደማጭነት የገነቡ ግለሰቦችና አካላት መኖራቸውን የኮሚቴ አባላት ተናግረዋል፡፡ የምክክር ኮሚሽኑ እነዚህን ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችንም ሆነ ተቋማትን በመቅረብ ሕዝብ ዘንድ ተደራሽ ለመሆን ሊሠራ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

የአጀንዳ መረጣ፣ የአወያዮችና የአመቻቾች ልየታን በተመለከተም ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች ሳይቀሩ ሕዝብ ዘንድ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት መሰናክል እንደሚገጥማቸው የኮሚቴ አባላቱ በማሳያነት አስረድተዋል፡፡ ወደ ኅብረተሰቡ በሚወረድበት ጊዜ ታች ያሉ መዋቅሮች በሴፍቲኔት፣ በጥቅምና በግዳጅ የሕዝቡን ችግር ከማንሳት ይልቅ ውዳሴ ከንቱ የሚያቀርቡ ሰዎችን እንደሚሰበስቡ ተናግረዋል፡፡

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከዚህ ልምድ በመቅሰም ብሶት ላላቸውና ሀቀኛውን የኅብረተሰብ ችግር መናገር ለሚችሉ ወገኖች ቅድሚያ እንዲሰጥ ምክረ ሐሳቦች ሰጥተዋል፡፡

አወያዮችና አመቻቾች የሚመረጡበት መንገድ፣ እንዲሁም ለውይይት የሚቀርቡ አጀንዳዎች የሚለዩበት መንገድ ጥንቃቄ የተሞላበትና አሳማኝ መሆን እንዳለበት ነው የኮሚቴው አባላት ያሳሰቡት፡፡

የሴቶች ተሳትፎ 20 በመቶ ነው ተብሎ የተቀመጠው መነሻ አኃዝ በቂ አለመሆኑ የተመላከተ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በጀት እያለውና ሥራውም የበዛ ሆኖ ሳለ በጀት ቆጥቦ ለመጠቀም መሞከሩ አግባብ አለመሆኑም ተነግሮታል፡፡

እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎችን በተመለከተ ምላሽ የሰጡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮችም ስለምክክር ጥራትና አካታችነት በሰፊው አውስተዋል፡፡ ‹‹ጥራት ያለው ውጤታማ ምክክር ለማካሄድ ስለምንፈልግ ነው ጊዜ የወሰድነው፡፡ በሌላ በኩል አንዱን ትተን ሌላውን ይዘን ብቻ ምክክር ማድረግ ስላልፈለግን ሁሉንም አካታች የሆነ ሥራ ለመሥራት ነው የዘገየነው፤›› የሚል ምላሽ በዋና ኮሚሽነሩ መስፍን (ፕሮፌሰር) ተሰጥቷል፡፡

‹‹እኛ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ እንድንሠራ ሕጉ አልፈቀደልንም፡፡ መንግሥት ልሠራ ነው ካለ እኛም ከመንግሥት ውጪ አይደለንም፡፡ የፍትሕ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የካሳና የዕርቅ ጥያቄም አለ፡፡ የእኛ ተሳትፎና ልምድ ከተፈለገ ግን አለን፤›› በማለት ነበር ዋና ኮሚሽነሩ ምላሽ የሰጡት፡፡

ኮሚሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት፣ የኮሚሽኑ ሥራ የመጀመር ጉዳይ ነው ከሁሉም ነጥሮ የወጣው፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡ ጉጉት ከፍተኛ መሆንን እንደ አንድ መሰናክል እንደሚመለከተው ነበር ኮሚሽኑ ያስታወቀው፡፡

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሚያከናውነው የምክክር ሥራ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ላሉባት አገር ፈውስ ይሆናል ብሎ የሚገምተው ኅብረተሰብ በርካታ መሆኑ ጫና እንዳለው ነው ኮሚሽኑ ያመለከተው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በቶሎ ወደ ውይይት መግባቱ የእኛም ፍላጎት ነው በማለት ነበር ኮሚሽነሮቹ ማብራሪያቸውን ያሳረጉት፡፡

ኮሚሽኑ ይህንን ሪፖርት ካቀረበ በኋላ በነበሩት ተከታታይ ቀናት በአራት ክልሎች ተወያዮች መምረጥ መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡ ለውይይት የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ሕዝቡ በነፃነት ያቅርብ ሲልም የአጀንዳ መስጫ አድራሻዎችን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ ወቅት አማካሪ ኮሚቴ መመሥረቱን ይፋ ያደረገው ኮሚሽኑ፣ ከሰሞኑ የነቃ ሥራ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ለማሳየት በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ታይቷል፡፡ ዋና ኮሚሽነር መስፍን (ፕሮፌሰር) በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር እንዴት ማድረግ እንደሚቻል በናሁ ቴሌቪዥን ከሰሞኑ ቀርበው ሰፊ ማብራሪያ ሲሰጡም ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ኮሚሽኑ መቼ ነው በተጨባጭ ተግባራዊ የውይይት መድረኮችን የሚጀምረው የሚለው ጉዳይ ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡

ለአብነት ከሰሞኑ መግለጫ ሰጥቶ የነበረው ኅብር ኢትዮጵያ ፓርቲ ‹የኮሚሽኑ ህልውና በራሱ ይቀጥል ወይም አይቀጥል አይታወቅም› በማለት ነበር ጠንካራ አስተያየት የሰጠው፡፡

ኅብር ኢትዮጵያ በመግለጫው የምክክር ኮሚሽኑ ከምሥረታው ጀምሮ አሳታፊነትና አካታችነት የሌለው መሆኑን ተችቷል፡፡

‹‹ሳይወለድ የጨነገፈ›› ሲል የተቸውን የምክክር ኮሚሽንም መንግሥት ወጥሮ የያዘው የሕዝብ ጥያቄ ለማስተንፈስ ወይም አቅጣጫ ለማስለወጥ ይጠቅመው ካልሆነ በስተቀር፣ በተጨባጭ ሕዝብ አወያይቶ ለአገራዊ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ይረዳል የሚል እምነት እንደሌለው ነው ያስታወቀው፡፡

በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራና እንቅስቃሴ ላይ ተስፋ ያጡ እንዳሉ የሚናገሩ አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የኮሚሽኑ ወደ ተግባር ለመግባት መዘግየት ተጨማሪ ትችቶችን የሚጋብዝ መሆኑም ያክላሉ፡፡

 ኮሚሽኑ የተለያዩ አመክንዮዎችን ለመዘግየቱ ይሰጣል፡፡ ‹‹ውግንናችን ለሕዝብ ነው›› በማለት የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ሲናገሩም ይደመጣል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ኮሚሽኑ በተግባር የሚፈተሽበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ የቀረበ ነው የሚመስለው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -