Sunday, June 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ተበዳይ በምስክር ዕጦት ፍትሕ ቢነፈግ በምን ይካሳል?››

በያሬድ ነጋሽ

በዳይ ለግብሩ ተገን ይሆነው ዘንድ በኅቡዕ ይደራጃል። ከጊዜያትም መርጦ ውድቅትን፣ አልያ በጠራራ ያደፍጣል። የሕግ ጆሮ መስማት በማይችልበት፣ ዓይኑ ማማተር ከሚያዳግተው ርቀት የጥቃቱን ሥፍራ ይመርጣል። በሕቡዕ ተደራጅቶ፣ ውድቀቱ ላይ አድብቶ፣ ሰወርዋራውን መርጦ ለጥቃት የተዘጋጀው አካል ወንጀሉን ይፈጽማል። ለወንጀሉ ማስረጃ የሚሆኑ የሰነድ ይሁን የሰው እማኞች ሊገኙ በማይችሉበት ሁኔታ ተከልሎ ወንጀሉን ቢፈጽምም፣ ነገር ግን ቅሪት መሳይ ተርፎ ከወጣም፣ የሰነድ ማርስረጃዎችን ይደብቃል፣ ያርቃል ወይም ያቃጥላል። የዓይን እማኞችን በሐሰት እንዲመሰክሩ ያደርጋል፣ ያስፈራራል ወይም ነፍስ ይነጥቃል፣ አልያ የሕግ ሰዎችን ይደልላል ወይም መታያውን አቅርቦ ከጎኑ ያሠልፋል። በዚህ መልኩ ለተፈጸመ ወንጀል፣ ተበዳይ በሁለት መንገዶች ፍትሕን ይነፈጋል።

አንድም ሕይወቱ ቢቀጠፍ፣ ገንዘቡን ቢነጠቅ፣ ርስቱን ቢቀማ ቤተሰብ ዘመዱን ቢያጣ፣ ማስረጃ የሚሆነው ሰነድ፣ ምስክር የሚሆነው ግለሰብ ማቅረብ አይችልምና ላይ እታች ቢል፣ አምርሮ ቢያነባ፣ የደረሰበትን በዋይታ ቢያሰማ፣ የሚያደምጠው ወይም ፍትሕን የሚቸረው የዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት የለም። በዚህም ሳቢያ፣ ማስረጃና ምስክር በማጣት፣ አያሌዎች ሐቃቸውን ተነጥቀዋል፣ ከእናት ከአባት ውርስ ተነቅለዋል፣ ከርስታቸው ተነስተዋል፣ ደማቸው ደመ ከልብ ሆኗል፣ የወላጅነት መብት ተነፍገዋል፣ ከመሶብ ሙሉ እንጀራቸው ላይ ቁራሽ ተጥሎላቸዋል።

ሁለተኛው፣ የሰውም ይሁን የሰነድ ማስረጃ ቢኖረው እንኳን በበዳይ ጥቅማ ጥቅም የተተበተቡት የምስክርና የሕግ አካላት ጡንቻን የማይችለው ባላጋራ ይሆንበትና እውነቱን ከመነጠቅ፣ ሲያልፍም ጭራሽ ራሱ ተጠያቂ ሆኖ የሚቀርብባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም ተስተውሏል። በዚህ መልኩ በጥቅም የተያዙ የሕግ አካላት፣ በንጹኃን ላይ ፈርደዋል፣ ሐቁን ነጥቀዋል፣ ተጎጂውን ተበድሎ ሳለ በዳይ ነህ ብለዋል፡፡ እውነት፣ ርትዕ፣ ፍትሕ አዛንፈዋል ወይም ነፍገዋል።

ይህ ጉዳይ ሦስት ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድደናል። ‹‹ተበዳይ በምስክር ዕጦት ፍትሕ ቢነፈግ፣ በምን ይካሳል? ሰማይ ቤት እንባውን ከመርጨት ባለፈ፣ ገላጋይ የሚሆን ምድራዊ ሥርዓት የለም ወይ?›› የሚሉት በጥንድ እንደ አንድ የምናነሳው ጥያቄ ነው። ‹‹በዳይ አድራሻውን ቢያጠፋ በምን ይያዛል ወይም በፋንታው ማን ይጠየቃል?›› የሚለው ተከታዩ ጥያቄ ነው። ‹‹ዳኞች ተበዳይን ሲበድሉ ወይም በቀጥታ ባይበድሉ እንኳን የሕግ ክፍተቶች ተጠቅመው ፍትሕ ሲያጓድሉ ሕጉ ቢደግፋቸው እንኳን የሰማይ ቤቱ ተጠያቂነታቸው እስኪደርስ ድረስ፣ ለድርጊታቸው መቀጣጫ የሚሆን ምድራዊ ሥርዓት የለም ወይ?›› የሚለው በሦስተኝነት ይጠየቃል። ሦስቱንም ጥያቄዎች በዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ለመመለስ መሞከር ትርፉ ድካም ነው።

ነገር ግን ባህላዊ የአስተዳደር፣ የሕግና የፍትሕ ሥርዓት ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ በርካታ ሥራዎቹን በመጽሐፍ መልክ ያበረከተው የሕግ ባለሙያው አብድልፈታ አብደላህ ለመጀመሪያውና ለሁለተኛው ጥያቄዎቻችን መልስ የሚሆን አለው።

 ለመጀመሪያው ጥያቄያችን መልስ ሲያበጅ፡- ‹‹በዘመናዊ ሕግ ማስረጃ የሌለው ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት አይቀርብም። ቢቀርብም ፍትሕ አያሰጥም። ሕጉ በመረጃና ማስረጃ ብቻ የታጠረ ነው። ቁንጽል ነው። አቅም ደካማነቱን ነው የሚያሳየው። ጉዳዩ የትኛውም ያህል እውነትነት ቢኖረውም፣ ማስረጃዎችን ማቅረብ ካልቻልክ ‹እኔ ምን ላድርግ?› ነው የሚልህ። በባህላዊ የሕግ ሥርዓት (ሽምግልና) ግን ማስረጃ ስለሌለህ ፍትሕ አታጣም። ‹ማስረጃ የሌለው ጉዳይ እንዴት ሊከናወንና እውነታው ሊወጣ ይችላል› የሚል አሠራር አለው›› (የአብድልፈታ አብደላህ ቃለመጠይቅ፣ ፍልስምና ፬ ከገጽ 127-128 በቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ)።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም (ነፍስ ይማር)፣ ይህንን የባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት ሲገልጹ፡- ‹‹በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሽምግልና አድባር ነው፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ በትንሽም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት አይጠፋም፣ የሚፈጠረውን ማናቸውም ዓይነት ግጭት ለማለሳለስና በስምምነት ለመተካት የሚደረገው ባህላዊ ሽምግልና በመልኩም በባህርዩም ዛሬ በሽምግልና ስም ከምናየው በጣም የተለየ ነው። በኢትዮጵያ ባህል ሽምግልና የሚነሳው ከመንፈሳዊ መሠረት ላይ ነው። ሽምግልና የአምላክ ተግባር ነው። ሽምግልና ለዕርቅ፣ ለፍቅርና ለሰላም የቆመ መንፈሳዊ አድባር ነው፡፡ ይህ አድባር ሕንፃ የለውም፣ ለሽምግልና የበቃው ሰው በአዕምሮው፣ በልቡና በመንፈሱ ይዞት የሚዞርና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ ነው፤›› ይሉታል (ኢትዮጵያ ዛሬ፣ ጥር 2001 ዓ.ም.)።

በዚህ የፍትሕ ሥርዓት ተበዳይ ያለማስረጃ በምን መልኩ ይካሳል ያልን እንደሆን፣ አብድልፈታ አብደላህ ይህንን ይለናል፡- ‹‹ተከሳሹንም ምስክር አድርገህ ማቅረብ ትችላለህ። ተከሳሹ ያደረገውን አላደረኩም ብሎ በድፍረት አይምልም። ለመሐላ ያለው ቦታ ትልቅ ነው። መሐላው ይደርሳል። በሐሰት መማል ራስን፣ ዘርን አካባቢውን ያጠፋል። ስለዚህ ማንም ሰው በሐሰት ደፍሮ ወደ መሐላው አይገባም። መረጃና ማስረጃ ባይኖርም ዳኝነቱ ይካሄዳል፣ ፍትሕም ይገኛል፡፡›› (የአብድልፈታ አብደላህ ቃለመጠይቅ፣ ፍልስምና ፬ ከገጽ 127-128 በቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ)፡፡

እውነት ነው! በዚህ ሥርዓት በዳይ ‹‹ማስረጃ አይገኝብኝም›› በሚል ደረቱን የሚነፋበት አይደለም። ሽማግሌዎች መስቀልኛ ጥያቄውን ያቀርባሉ። ወንጀሉን አልፈጸምኩም ያለ እንደሆን ስሙ ሲጠራ በሚደነግጥበት በቆሌው፣ በአድባሩ፣ በቦዠ (በጉራጌ አካባቢ የሚታወቅ ሥርዓት ነው)፣ ሤራ ኸታ (ኮንሶ)፣ አበጋር ሥርዓት (ወሎ) እና በሌሎች (በመላ አገሪቱ በጥናት የተደረሰባቸው 130 የአስተዳደርና የፍትሕ ሥርዓቶች አሉ) የጋራ በሆነ የመስማሚያ ሥርዓት ያስምሉታል። ያኔ ልቡ ተርከክ ይላል። ወንጀሉ አልፈጸምኩም የሚለው ቀርቶ ወንጀሉን ያምንና ይህንን እንዲያደርግ የገፋፋውን አስገዳጅ ምክንያት ይዘረዝራል። በፍርድ ቤት ቁርዓን ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ተጭኖ በበዳይና ተበዳይ ዙሪያ የሐሰት ምስክሩን የሰጠ ግለሰብ፣ አሁን ግን ሐሰተኛነቱ እዚህ ጋ ያከትማል። ለመማማያ የቀረበው ኃይል ወይም ሥርዓት፣ ‹‹በሞትኩ ጊዜ እወጣዋለሁ›› የሚሉት አይደለም። ውሎ የማያድርና ሐሰተኛውን በተጨባጭ ሲቀጣ ማኅበረሰቡ ተመልክቷል።

በሰባት ቤት ጉራጌ አካባቢ በተለያየ ሥፍራ ተዘዋውሮ የሠራና ለእኔም የቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ የነበረ ጴጥሮስ የሚባል ወዳጄ ያጫወተኝን ገጠመኝ አስታውሳለሁ።

በአንድ አካባቢ የሚገኝ የጤና ኬላ ባልታወቁ ሰዎች ይዘረፋል። የጤና ኬላው አስተዳዳሪዎች ለፖሊስ ከመክሰስ ይልቅ ለአካባቢ ሽማግሌዎች አቤት ይላሉ። የአገር ሽማግሌዎቹ ሠራተኛውና መላው የአካባቢው ነዋሪ በአንድ የዛፍ ጥላ ሥር እንዲሰባሰቡ አደረጉ። በመጀመሪያ ንብረቱን የወሰደው አካል ራሱን እንዲያጋልጥ ጥያቄ ቢያቀርቡም ዝምታው ሰፈነ። በመቀጠል ወደ ሁለተኛው መፍትሔ ተሻገሩ። ይኼውም መሐላ ነው።  በሥፍራው የተለያዩ የስለት መሣሪያዎች (ጦሩ፣ ጎራዴው፣ አንካሴው…) መሬት ላይ እንዲደረደሩ ተደረገ። መሐላው ወደ ስለቶቹ እየጠቆሙ ‹‹ከዚህ ባልፍ ከዚህ አልለፍ፣ ከዚህ ባልፍ ከዚህ አልለፍ፣ ከዚህ ባልፍ ከዚህ አልለፍ…) የሚል ነበር። ሁሉም ይህንን መሐላ ፈጸሙና ሸንጎው ተበተነ። በቀጣይ ቀናት ግን ንብረቱን የዘረፉት አካላት በክፍፍል ወቅት አንደኛው የሌላኛውን ነፍስ በስለት እንዳጠፋ ተሰማ። ዘራፊውም ከዝርፊያው በተጨማሪ ነፍስ በማጥፋት ክስ በሁለት ወንጀል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ። (በርካታ የከተማ ልጆች ይህንን እንደተረት ይቆጥሩት ይሆናል። ነገሩን የሚያውቀው ያውቀዋል።)

ሥርዓቱ ወንጀለኛው ራሱን እንዲያጋልጥ ያደርጋል፣ አልያ ከላይ ባየነው መልኩ ከሰማይ ቤቱ የወደፊት ቅጣት በፊት ሳይውል ሳያድር በምድር ብይኑን ያገኛል። ተገቢው ፍትሕ፣ ለሌሎች ማስተማሪያ በሆነ መልኩ ይሰጣል። በሒደቱ ምስክር የሌለው ተበዳይ ይካሳል።

‹‹ወንጀለኛው ቢያመልጥ በምን ይያዛል? ወይም ኃላፊነቱን ማን ይወስዳል?›› ለሚለው ጥያቄያችን፣ ‹‹የአገር በቀሉ የፍትሕ ሥርዓት ዘመናዊ ካልነው ለመሻሉ አንድ ምሳሌ ብጠቅስ በመደበኛው ፍርድ ቤት በሕግ የሚፈለግ ተጠርጣሪ ሊያመልጥ ይችላል። በባህላዊው የፍትሕ ሥርዓት ግን፣ አንድም ሰው አምልጦ ወይም ለመሰወር ሞክሮ አያውቅም፤ ጎሳው ነው ኃላፊነት ያለበት። እሱ ቢጠፋ ጎሳውና ቤተሰቦቹ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ያውቃል። ለራሱ ጎሳ እጁን ሲሰጥ ምንም እንደማይደርስበት ያውቃል። ጎሳው ገዳይን ደብቆ የለም አይልም። ለምሳሌ ያህል ‹በጎርደነ ሤረ› የፍትሕ ሥርዓት አንድም ሰው በታሪክ ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ አመለጠ የሚባል ሰው የለም። ጠፋ ተብሎ ፍትሕ የማይተገበርበት ሰው የለም፡፡›› (የአብድልፈታ አብደላህ ቃለመጠይቅ፣ ፍልስምና ፬ ከገጽ 115-116 በቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ። (በገዳ ሥርዓትም ወንጀለኛው ከነጎሳው የሚጠየቅበት አካሄድ አለ፡፡)

‹‹በዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት በቀጥታም ፍርድ የገመደለ ይሁን በተዘዋዋሪ የሕግ ክፍተትን ተጠቅሞ ፍርድ ያጎደለ ዳኛ፣ በተለያየ መልኩ ከሕግ ተጠያቂነት ሊያመልጥ ይችላል። ሆኖም ‹‹የሰማይ ቤቱ እስኪደርስ በምድር ያለው መቀጣጫ ምንድነው?›› ለሚለው ሦስተኛው ጥያቄያችን ምላሽ የሚሰጠንም የባህላዊው የፍትሕ ሥርዓት ነው። ለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ወላጅ አባቴን ቃለ መጠይቅ አቅርቤለት ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶኛል። ‹‹ማኅበረሰቡ የሚገዛለት መማማያ ዳኞችንም የሚገዛ ነው። በሐሰት የማለው ሰው ቤት የወደቀው ቦዠ (መብረቅ) ፍርድ ያጓደለው ሽማግሌን የሚምር አይደለም›› የሚል ምላሽ አካፍሎኛል። ይህ ነገር ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓትን ለአገር ሽማግሌ ዳኞች ዓይናቸውን ጨፍነው ስለእውነት ብቻ እንዲፈርዱ የሚያስገድድ የህልውናም ጥያቄ ያደርገዋል።

ከላይ የተመለከትነው ሁሉ፣ ጽንሰ ሐሳባዊ ሊመስል፣ ከአሁናዊ ይልቅ እንደ ታሪክ ሊቆጠር፣ ‹‹በዚህ ዘመን የሥርዓቱ ገላጋይነት፣ ለሥርዓቱ የሚገዛ ከሳሽ፣ ተከሳሽ፣ ምስክርና አገላጋይ ሽማግሌ አለ ወይ? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። በተለይም በአገራችን አብዛኛው ኅብረተሰብ ከሚኖርበት ክፍለ አገሩ በራቀውና ጥቂት በሆነው የከተማው ነዋሪ ዘንድ፣ በሐሰት መማሉ፣ በጉቦ መደለሉ፣ በአቋራጭ መክበሩ፣ እኩይ ተግባራት ከማስኮነን ይልቅ ክብርን ሲያጎናጽፍ ከማየቱና ሌሎችም በአካባቢው ከሚመለከተው ጉዳዩች በመነሳት ነገሩ ላይዋጥ ወይም ለተረትም የቀረበ መስሎ ሊሰማው ይችላል። በርካታ ጉዳዩች በምሳሌነት መነሳት እንደሚችሉ እንዳለ ሆኖ፣ የዚህ አንቀጽ አዘጋጅ ተጨባጭ ምልከታ የሆነ ጉዳይ በእማኝነት እናንሳና ጉዳዩን መሬት እናስረግጥ።

ሥፍራው የጊቤ ወንዝ ድንበርተኛ ነውና ያዘቀዘቀችውን ፀሐይ ለምንመለከት፣ የመጥለቂያ ሥፍራዋ ላይ የቆምን ያክል በተሰማን ሰዓት፣ ከሰባት ቤት ጉራጌ፣ እነሞር ወረዳ፣ ‹‹አጋሬ›› ከሚባል አካባቢ ተነስቶ የኮንትራት ተሳፋሪዎቹን ይዞ ወደ አዲስ አበባ በሚጓዝ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ተሳፍሬያለሁ። አቀማመጤ ቀኝ ትከሻዬ ከሚኒባስ ታክሲው ረዳት ጋር እንድጎራበት አስገድዶኛል። በስተግራዬ አንድ ወንበር ተጋርቶኝ የተቀመጠው ሰው ወዳጄ ሲሆን፣ አንድ ሁለት ቀን አብሮኝ የከረመ ነውና እሱን ገሸሽ በማድረግ፣ ከመላው ተሳፋሪ ጋር ቀልድ ለሚወራወረው ረዳት ቀልቤን ቸርኩት። በጉንጩ የምሱን ይዟል። ይህም ይመስለኛል፣ ከተሳፋሪው የበለጠ ኃይል ተሞልቷል። ድካም አይታይበትም። ወልቂጤን እንዳለፍን ጀምበር ጠለቀች። ቀልድና ሳቁ አብቅቶ ዝምታ ሰፍኗል። በተመስጦ ላይ ለሚገኘው ረዳት ማለፊያ የሚሆነኝን ጥያቄ አቀረብኩ። እንደጥያቄዬ ቅደም ተከተል በአግባቡ ምላሹን ሰጥቶኛል። አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ ቢሆንም፣ ባህል ሥርዓቱን ጠንቅቆ ያወቀ ነበር። በጉራጌ ሕዝብ መሐል ስላሉ በርካታ ጎሳዎች ሳይቀር ማብራራት መቻሉ አስገረመኝ። ለዚህ አንቀጽ ዝግጅት ተጨባጭ ምልከታ (Empirical Review) ያልኩት ጉዳይ ያጫወተኝ በመቀጠል ነበር።

ለአባቱ ብቸኛ ልጅ ነው። አባቱ ከትዳር ውጪም ቢሆንም አዲስ አበባ ከተዋወቋት ቆንጆ እሱን ከወለዱ ከጥቂት ዓመታት በኋላ አቅሙ ሳይደረጅ ከቤት እንደወጡ አልተመለሱም። ዕድገቱ ከአባቱ ቤተዘመዱ ዕውቅና ተለይቶ ነበር። እናቱም ብዙም በሕይወት ሳትከርም በሞት ተለይታዋለች። ይኸው ልጅ በፈጣሪ ቸርነት አድጎ ለወጣትነት ከደረሰ በኋላ አያቱ አዲስ አበባ፣ ልደታ በሚባል ሥፍራ፣ ይዞታው የራሳቸው የሆነ የእንጨት መደብ እንደነበራቸው መረጃው ይደርሰዋል። አያቱ ከሞቱም በኋላ፣ አጎቶቹ ሥፍራውን በባለቤትነት እያስተዳደሩ እንደሆነም አክሎ ተገነዘበ። ምቹ ነው ባለው ወቅት ወደ አጎቱቹ በመሄድ የወንድማቸው ልጅ መሆኑን አስረድቶ፣ ለማቀፍ ክንዱን ዘረጋ። ሆኖም የገጠመው ምላሽ ያልጠበቀውና ከመታቀፍ ይልቅ ግልምጫን ያተረፈ ነበር። አጎቶቹ ወንድማቸው ልጅ ሳይወልድ እንደሞተ አበሰሩት። ይኸው ልጅ ዙሪያ ቃኘ፣ ሕግ አዋቂዎች አማከረ። በዘመናዊ ፍርድ ቤት ፍትሕ እንዲያገኝ የሚያደርገው ምንም ዓይነት ማስረጃ እንደሌለው ሕግ አዋቂዎች አበክረው ነገሩት። በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሰጥሞ የነበረው ይኸው ልጅ፣ እንዲህ ያለ ነገር ግልግል የሚያገኝበትን፣ እውነት ያለው ተበዳይ ያለማስረጃ ሊካስ የሚችልበትን ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት እንደሆነ በቅጡ የተረዱ ሰዎች ይገጥሙትና ሐሳባቸውን ያጋሩታል። ወጣቱም አካሄዱን እንዲያብራሩለት በጠየቀው መሠረት፣ ወደ አንድ ትልቅ የአገር ሽማግሌ ዘንድ መሩት።

በማስረጃ ዕጦት ፍትሕ ተነፍጎ የነበረው የታክሲው ረዳት፣ የእኚህን የአገር ሽማግሌ ስም ሲያነሳልኝ፣ በቅርቤ በማውቀው የቤተሰብ ሽምግልና ተገኝተው፣ የተዘበራረቀውን መስመር አሲዘው፣ የተቆጣውን አብርደው፣ የተከፋውን አጽናንተው፣ ትርፍ የጠየቀውን በቂውን አሲዘው፣ የተጋጨው ቤተሰብ ከሽምግልናው በኋላ አብሮነቱ እንዳይነጥፍ አማምለውና መላ ላጣው ችግር እልባት ሰጥተው መሄዳቸውን አስታወስኩ። በቀጣይም በተቻለኝ አቅም ስለሳቸው የተለያየ መረጃዎችን ሰበሰብኩ። ‹‹ትልቅ ነገር አዋቂ፣ ሽምግልናውም የሰመረላቸው ናቸው›› ይሏቸዋል። ከሕመም ጋር እየታገሉ የበርካታ ፍትሕ ናፋቂ ምስኪኖችን እንባ፣ በአገር ሽማግሌ ደንብ፣ ያለ አንዳች ክፍያ አብሰዋል። በዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ለመፍታት እጅግ የከበዱ ጉዳዩችን፣ በሚሊዮን ብር ይሁን በጥቂቱ እስከሚፈላለጉ በዳይ ተበዳዮችን፣ የቤተሰብ፣ የትዳር፣ …ወዘተ ግጭቶችን ገላግለዋል፣ በሽምግልና በተሰባሰቡበት ቦታ የምግብ መጠጡን ክፍያ ሳይቀር በራሳቸው ወጪ በመሸፈን ሽምግልናውን መርተዋል። ይህቺን ታህል ስለሳቸው በመናገር በዕድሜ ዘመናቸው በባህላዊ ሽምግልና ረገድ የነበራቸውን ግዙፍ ገጽታ ማሳየት አይቻልምና የሕይወት ታሪካቸው በመጽሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ቢቀርብ፣ ላለንበትም ይሁን ለሚመጣው ትውልድ፣ ባህላዊ ሽምግልናን ለትምህርት ዘርፍ ማዋል የሚያስችል በቂ የመግባቢያ ሰነድ እንደሚሆን አምናለሁ (የመጽሐፉን ዝግጅት ለመሰነድ ዕድል ባገኝ፣ በበጎ ፈቃደኝነት ሚናውን ልወጣው እንደምችል ላወሳ እወዳለሁ)። እኚህ የአገር ሽማግሌ አቶ አሰፋ አይጎዳ (የስኩል ኦፍ አይጎዳ ባለቤት) ናቸው። ወደቀደመ ነገራችን እንመለስ።

የታክሲው ረዳቱ የአባቱን ንብረት ድርሻ የማግኘት ጥያቄ፣ አቶ አሰፋና ሌሎች ሽማግሌዎች በተገኙበት አጀንዳ ሆኖ ቀረበ። የወጣቱ አጎቶች ‹‹ወንድማችን ልጅ ሳይወልድ ነው የሞተው›› የሚለው ላይ እንደጸኑ ናቸው። በእንዲህ በተካረረ ሁኔታ በዕለቱ እልባት መስጠት ስላልተቻለ፣ ሽምግልናው በሌላ ቀን እንዲሆን ተወሰነ። ሽማግሌዎች እስከቀጣዩ ሽምግልና ድረስ፣ ባህላዊ ሽምግልናን ለየት የሚያደርገውን ግብር መከወን ጀመሩ። በአገር ባህል የፍትሕ ሥርዓት ብቻ የሚገኘውን ይህንን ልዩ ግብር የሕግ ባለሙያው አብድልፈታ እንዲህ ይገልጸዋል፣ ‹‹በአገር በቀሉ ሽምግልና ማስረጃ የማቅረብ ሸክም የሁሉም ነው። በዋነኝነት ከሳሽ ይጠበቅበታል። እሱ እንኳን ቢያቅተው እንኳን ዳኞቹ ‹በእርግጥ ግን ይህ ጉዳይ ተፈጽሟል አልተፈጸመም› ብለው በራሳቸው መንገድ ይጥራሉ። እውነት መፈለግ ነው እንጂ እነሱ ጋ ያለው፣ ለአንተ መፍረድና በአንተ ላይ መፍረድ አይደለም።

በቀጣዩ ሽምግልና፣ ሽማግሌዎቹ ያገኙትን መረጃ የወጣቱ አባት ታላቅ ወንድምን ለብቻው በመለየት አነጋገሩት። መረጃው ‹‹ልጁ ጨቅላ ሳለ አባቱ ለታላቅ ወንድሙ አሳይቶታል›› የሚል ነበር።  ከትንሽ ማንገራገር በኋላ መረጃው እውነት እንደሆነ በማመን፣ ‹‹ያኔ ያየሁት ልጅ እሱ መሆኑን በምን አውቃለሁ›› የሚል መከራከሪያውን አቀረበ። ነገሩ ግማሽ ያህል እንደተቃለለ የገባቸው ሽማግሌዎች የልጁን አጎቶች አንድ ላይ በመሰብሰብ ወንድማቸው ያመነውን ያህል አስረዱ። አሁንም ከጥቂት ማንገራገር በኋላ፣ ‹‹እሱ መሆኑን…›› የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ አነሱ። ሽምግልናው ለሦስተኛ ሳምንት ተራዘመ። የወጣቱን ማንነት እውነታውን ማወቅ ላይ አተኮሩ። ሽማግሌዎች በራሳቸው መንገድ ተጉዘው ለእውነታው የቀረቡ ፍንጮች አገኙ። በዘመናዊ ፍርድ ቤት ያልተረቱት የወጣቱ አጎቶች፣ ለሽምግልናው ገላጋይነት እጅ ሰጡ። ሽምግልናውም ለወጣቱ የአባቱን ድርሻ እንዲደርሰው ሆኖ ተጠናቀቀ።

ሲጠቃለል

ከላይ የተመለከትነው፣ ‹‹ከሳሽ ያለ ማስረጃ የሚካስበት አሁን ሥርዓት አለ? ለዚህ የሚገዛ ተከሳሽ አለ? ሽማግሌስ አለ?›› ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል። በአገራችን አብዛኛው በሚኖርበት ከከተማ ውጪ ባሉ ማኅበረሰብ ውስጥ (በከተማ ውስጥም ግልጋሎቱን ያስቀጠሉ አሉ) ለገላጋይነት ሥርዓቱ ግልጋሎት ላይ እየዋለ ከመገኘቱና ወደፊትም እያገለገለ እንዲቀጥል ከማስቻል አንጻር፣ ሥርዓቱ ይጠበቅ ዘንድ፣ ከዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ጋር ይጣመር ዘንድ፣ የሽማግሌዎቹ ተሞክሮ ይሰነድ ዘንድ እያበከረን በዚሁ እናብቃ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡                     

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles