Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤቱን በአዲስ አበባ አደረገ

ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤቱን በአዲስ አበባ አደረገ

ቀን:

በትምህርት ላይ ለመሥራት የተቋቋመውና ኢትዮጵያን ጨምሮ 26 አገሮችን በአባልነት ያቀፈው ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት (ኦርጋናይዜሽን ኦፍ ኤዱኬሽናል ኮኦፕሬሽን፣ ኦኢሲ) ዋና መቀመጫውን በኢትዮጵያ አዲስ አበባ አድርጎ በይፋ ሥራ ጀመረ፡፡

እ.ኤ.አ በ2020 በጂቡቲ የተመሠረተውና ዋና መቀመጫውን በአዲስ አበባ በማድረግ ሥራ የጀመረው ኦኢሲ ዋና ጸሐፊ ማንሱር ቢን ሙሳላም እንዳሉት፣ በአዲስ አበባ ለዋና ቢሮው ግንባታ የሚውል ስድስት ሔክታር መሬትም ከመንግሥት ተረክበዋል፡፡

ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ሥራ የጀመረው ኦኢሲ ከአፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ፣ ፓስፊክና ከዓረቡ ዓለም የተውጣጡ 26 አገሮች በትምህርት ዙሪያ በትብብር አብረው የሚሠሩበት ነው፡፡

እንደ ሚስተር ቢን ሙሳላም፣ ኦኢሲ የሳውዝ ቱ ሳውዝ ትብብርን በማጠናከር በአባል አገሮቹ ትምህርት ፍትሐዊ፣ አካታችና ተደራሽ እንዲሆን የሚሠራ ይሆናል፡፡

እንደ ዋና ጸሐፊው፣ ድርጅቱ የተቋቋመበት ዓላማ የሚማረውን ሕዝብ ቁጥር መጨመር ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ ማንም ሰው ከትምህርት ተገልሎ እንዳይቀር ሥርዓት የሚዘረጋበትም ነው፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የምርምር ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰለሞን ቢኖር (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ግሎባል ሳውዝ ወይም የደቡብ ዓለም አገሮች የሚባሉት በአብዛኛው በቋንቋ፣ በባህል እንዲሁም በአገር በቀል ዕውቀት የተለያየ ዕምቅ ሀብት ያላቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ይህንን ሀብት በአግባቡ መጠቀም አልተቻለም፡፡

ኦኢሲ ዓለም አቀፍ ኢንተርጋቨርመንታል ድርጅት ለእነዚህ ምላሽ ለመስጠት ተልዕኮ ይዞ የተነሳ በመሆኑ፣ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በሣይንስ፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በአገር በቀል ዕውቀት ላይ በመመሥረት በርካታ ሥራዎችን ለመሥራተ እንደሚቻል አክለዋል፡፡

የኦኢሲ መመሥረትና ሥራ መጀመር ለትምህርቱ ሥራ ትልቅ አጋዥ እንደሚሆንና ዓለም አቀፍ የልማት ግቦችን ለማሳካትም ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

አዲስ ከተመሠረተው ድርጅት ጋር ከሦስት ወራት በላይ በቅርበት እየሠሩ መሆኑን፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር)፣ ከኦኢሲ ዋና ፀሐፊ ማንሱር ቢን ሙሳላም ጋር በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን፣ ድርጅቱ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ሚኒስቴሩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንና የምርምር ክፍሉም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን የኦኢሲ ቀንን በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከኦኢሲ ዓላማዎች አንዱ የሆነው አገር በቀል ዕውቀቶችን ማጠናከር መሆኑን ያስታወሱት ሰለሞን (ዶ/ር)፣ አገር በቀል ዕውቀትን በምርምር አጠናክሮ፣ የግሎባል ሳውዝ አገሮች ያላቸውን ዕምቅ ሀብት በሳይንሣዊ ምርምር አግዞና በቴክኖሎጂ ደግፎ ለማሳደግ እንደሚሠራ፣ ይህ የትምህርት ሚኒስቴር አንዱ ዓላማ ስለሆነም በትብብር የሚሠራበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአሥር ዓመት መሪ ልማት ዕቅድ ቁልፍ የልማት ማሳኪያ ግቦች የሆኑትን ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ማምረትና አይሲቲን በምርምር ለመደገፍ ብሔራዊ የልማት ስትራቴጂና የትኩረት መስክ ተነድፎ ለሁሉም የምርምርና የሣይንስ ተቋማት መሠራጨቱንም አክለዋል፡፡

ከኦኢሲ ጋር በሚኖረው ግንኙነትም እንደ አገር ቅድሚያ በተሰጣቸው ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ውይይቶችም ይህንኑ የሚያጠናክሩ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

የድርጅቱ የግሎባል ሳውዝ አገሮች ዋና ዓላማ በሆነው ትምህርትን በፍትሐዊነት፣ በእኩልነት እንዲሁም ካለው የብሔረሰብ ብዝኃነትና ከአገር በቀል ዕውቀት አንጻር ያሉ ክፍተቶችን አብሮ ለመሥራት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጄኔራል ልዑልሰገድ ታደሰ በበኩላቸው፣ የኦኢሲ በአዲስ አበባ በይፋ መከፈት፣ ዋና ጽሕፈት ቤቱን ኢትዮጵያ ማድረጉና ኢትዮጵያም አባል መሆኗ መንግሥት ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን በጥራት እንዲሰጥ፣ ከፍተኛ ሙያና ብቃት ያላቸው ዜጎች እምቅ ችሎታቸውን እንዲያወጡ ቀርፆ እየሠራበት የሚገኘውን የትምህርት ሥርዓት ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል፡፡

የተመሠረተው ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ ኢትዮጵያ የነደፈቻቸውን የልማት ትልሞች በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ ያሉትን በርካታ ተግባራት የሚደግፍ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ የሰነቀው ራዕይም ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል አገር ለሆኑት የደቡብ ዓለም ወይም ግሎባል ሳውዝ የሚባሉት አገሮችን በሙሉ ትብብር እንዲሠሩ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...