Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየትራፊክ አደጋና መንስኤው በአዲስ አበባ

የትራፊክ አደጋና መንስኤው በአዲስ አበባ

ቀን:

በዓለም በየዓመቱ 1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ እንደሚሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ ከ50 ሚሊዮን በላይ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ አገሮች ደግሞ ችግሩ የከፋ ስለሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የ13 ዓመት የትግበራ ዕቅድ አውጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው ዕቅድ አፈጻጸም በዘርፉ ለውጥ እንዲመጣ መንገድ ቢከፍትም በየጊዜው በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን ከፍ ብሏል፡፡

የመንገድ ደኅንነትን አስመልክቶ፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ ኢንሼቲቭ ግሎባል የመንገድ ደኅንነት ጋር በመተባበር፣ ለሰባተኛ ጊዜ ያዘጋጀውን የትራፊክ አደጋ መረጃ ትንተና ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

የ2014 በጀት ዓመት የመንገድ ደኅንነት ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ ሲደረግ፣ ንግግር ያደረጉት የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ታረቀኝ እንደገለጹት፣ ዓምና 441 ሰዎች በመንገድ በተፈጠረ የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ሕይወታቸውንም ካጡ ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት እግረኞች መሆናቸውን፣ ላለፉት ተከታታይ አምስት ዓመታት በተመሳሳይ ተጋላጭ እንደሆኑ አቶ አማረ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት 45 በመቶ የሞት አደጋ የተመዘገበው አምራች የኅብረተሰብ ክፍል በሆኑት ሰዎች መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይሄንንም ታሳቢ በማድረግ አሁንም ቢሆን እግረኞችን ከአደጋው ለመታደግ በትጋት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን በሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው የሞት አደጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 50 በመቶ መቀነሱን እዚህ ላይም ተከታታይ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ አክለው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከፆታ ስብጥር አንፃር በዓመቱ ውስጥ ከተከሰተው አጠቃላይ የሞት አደጋ ውስጥ 78 በመቶ የደረሰው በወንዶች ላይ መሆኑን፣ 44 በመቶው የደረሰው ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ባለው ጊዜ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ከተወሰነው የፍጥነት ወሰን በላይ ያሽከረከሩ አሽከርካሪዎች ብዛትም 59 በመቶ ሲሆን፣ ከሌሎች ተሽከርካሪዎች አንፃር ከተፈቀደ ፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ቁጥር መያዛቸውን አቶ አማረ አብራርተዋል፡፡

በከተማዋም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት አቶ አማረ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጭርና የረዥም ጊዜ የመንገድ ደኅንነት ስትራቴጂ ዕቅድ አውጥቶ ውጤታማ የማሻሻያ ሥራዎችን እየተገበረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኤጀንሲው ለአንድ ሳምንት እየተከበረ ያለውን ዓለም አቀፍ የመንገድ ደኅንነት ሳምንት ምክንያት በማድረግ፣ በተሽከርካሪና በድምፅ መሣሪያዎች የታገዘ የትራፊክ ሕግን ለማስከበር የማስገንዘቢያ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት የብሉምበርግ ኢኒሼቲቭ ሰርቪላንስ አስተባባሪ ወ/ሮ ሜሮን ጌታቸው እንደገለጹት፣ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚከሰተው የሞት አደጋ መጠን ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ጊዜ የቀነሰ ቢሆንም፣ የ2014 ግን አሥር በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡  

በ2014 ዓ.ም. በትራፊክ አደጋ ምክንያት የተከሰተ የአካል ጉዳት ከ2013 ጋር ሲነፃፀር በ12 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር የ20 በመቶ ጭማሪን ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ከዕድሜ አንፃር 45 በመቶ የሚሆነው የመንገድ ትራፊክ ሞት የሚከሰተው ከ20 እስከ 39 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሞት አደጋ የሚከሰተው ደግሞ በቅዳሜ ቀን መሆኑን ወ/ሮ ሜሮን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአካል ጉዳት የደረሰው በሐሙስ ቀን  መሆኑን ለሞትና ለአካል ጉዳት መንስዔ የሆኑት አብዛኛዎቹ አሽከርካሪዎች የቤት መኪናና የሕዝብ ማመላለሻ ሚኒባሶች ናቸው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለትራፊክ አደጋ ዋነኛ መንስዔ የሆኑት እግረኞች መሆናቸውን አብዛኛውን ጊዜም አደጋ የሚደርሰው በወንዶች ላይ መሆኑን አስተባባሪዋ አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ በከፍተኛ ደረጃ የትራፊክ አደጋ የሚደርስባቸው ቦታዎች መለየታቸውን በእነዚህም ቦታዎች የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስና ለመከላከል መንግሥት ከሌሎች ተቋሞች ጋር በጋራ መሥራት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...