Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊካንሰርን ለመግታት የቆመው አኅጉራዊው ጥምረት

ካንሰርን ለመግታት የቆመው አኅጉራዊው ጥምረት

ቀን:

ካንሰር ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ ሲሆን ኅብረተሰቡን ለስቃይና ብሎም ለሞት የሚዳርግ ቀዳሚ በሽታ ነው፡፡ ካንሰር ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በደምና በጣም ስስ በሆነ ቲዩብ (ሊፍ) ሥርዓት በቀላሉ ይተላለፋል፡፡

 የካንሰር ዓይነቶች በርካታ ሲሆኑ ዋነኞቹና ሴቶችን ለስቃይና ለኅልፈተ ሕይወት እየዳረጉ ያሉት የጡትና የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰሮች ናቸው፡፡ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ካንሰር በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሞት ያስከትላል፡፡

በኢትዮጵያ በዓመት ወደ 78 ሺሕ የሚጠጉ አዳዲስ የካንሰር ሕመምተኞች እንደሚኖሩ፣ በተለይ ደግሞ ሴቶችን የጡት እና የማህፀን በር ካንሰር ሰለባ በማድረግ ለስቃይ እንደሚዳርግ፣ የማኅበረሰብ ቀውስ እንደሚያመጣ በመግለጽ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በ25 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚተገበር፣ የካንሰር በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የምርምር ጥምረት መመሥረቱ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በተገለጸበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሚኒስትር ሊያ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ለካንሰር ክትትል፣ ለውጤታማነት፣ እንዲሁም ተግዳሮቶችን ለመለየትና ለመቅረፍ የጥምረቱ መመሥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኢፒዲዮሞሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የጥምረቱ ዳይሬክተር አዳሙ አዲሴ (ዶ/ር) በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለአምስት ዓመታት በሥራ ላይ የሚቆየውን ይህንኑ ጥምረት የሚያስተባብሩት የጤና ሳይንስ ኮሌጁና ጀርመን የሚገኘው የማርቲን ሉተር ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡

ምርምሩም በይበልጥ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ሴቶችን ለስቃይና ለሞት በሚዳርገው የጡትና የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ለጥናቱ ማከናወኛ የሚውል ከጀርመን መንግሥት የተገኘ 60 ሚሊዮን ዩሮ በጀት የተመደበለት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለተግባራዊነቱም ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ እንደሚሰጥ፣ የተጠናከረ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወን፣ የዶክትሬትና የድኅረ ዶክትሬት ተማሪዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንደሚመቻች ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ አባባል፣ ከፍ ብሎ የተጠቀሱት ሁለት ዓይነቶቹ ካንሰሮች በቶሎ ወይም በጊዜ ከተደረሰባቸው ከስቃይና ከሞት ማዳን፣ ሳይሠራጭም ማጥፋት ይቻላል፡፡ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች የሚገኙ እናቶች ግን ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱት በሽታው ሥር ከሰደደና ምንም ማድረግ በማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ ይህም  ሕክምናውን አስከፊ ከማድረጉም ባሻገር ለኅልፈተ ሕይወት ይዳርጋል፡፡

የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰርን ከምድረ ገጽ የማጥፋት ፕሮግራምን የዓለም ጤና ድርጅት እንደጀመረና ምርምሩም ዓለም አቀፉ ድርጅት ከያዘው ጅማሮ አንፃር እንዴት መድረስ እንደሚቻል፣ ክትባቱን እንዴት መስጠትና ልየታ (ስክሪኒንግ) በምን መልኩ መከናወን እንዳለበት በመጠቆምና አቅጣጫ በማስያዝ ረገድ ጥምረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ዳይሬክተሩ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በአውሮፓና በሌሎችም አገሮች በካንሰር ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት እንዳሉ ሆኖ፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ግን የካንሰር ዓይነት ይለያያል፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ ውስጥና ሌላው አገር ያለው ዝርያ (ጀነቲክ ቫሪዬሽን) አይታወቅም፡፡ ከዚህ አንፃር በምን መልክ ቢያዝ ነው ሕክምናውንና ክትባቱን ተደራሽ ማድረግ የሚቻለው የሚሉት ነጥቦች ሁሉ የጥናቶቹ አካላት እንደሆኑ ነው የገለጹት፡፡

በስተመጨረሻም ለአምስት ዓመታት ያህል የተሠሩት ጥናቶቹ በሚገባ ተሰናድተውና ተዘጋጅተው ለየአገሮቹ የጤና ሚኒስቴሮች እንደሚቀርቡ ከኔትወርክ ዳይሬክተር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹በኢትዮጵያና በቀሩትም የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለውን የካንሰር በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቅንጅታዊ ሥራ ይጠይቃል፤›› ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዱዓለም ደነቀ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አባባል፣ የግንዛቤ ማጣትና የተደራሽነት ማነስ ሲታከልበት ደግሞ ችግሩን በይበልጥ ውስብስብ አድርጎታል፡፡

በአቅም ማነስ ሳቢያ ለሕክምናው አለመድረስ ሌላው ተግዳሮት ሲሆን ታካሚዎች ጤና ተቋማት ቢደርሱም የመድኃኒት እጦትና የታካሚዎች ቁጥር መብዛት በካንሰር ሕክምና ዙሪያ የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ነው የተናገሩት፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2018 ባወጣው ሪፖርት ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በዓመት 751 ሺሕ አዲስ የካንሰር ሕመምተኞች ይገኛሉ፡፡ ይህም በዓለም ውስጥ ከሚገኙት አዳዲስ የካንሰር ሕሙማን አራት ከመቶ ያህል ነው፡፡

ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች የጡትና የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር ከፍተኛ ሊሆን የቻለው ከመጠን በላይ ውፍረት፣ ከፍተኛ የሆነ የኤችአይቪ ኢንፌክሽንና ከዘር ወይም ከቤተሰብ ጋር የሚያያዝ መሆኑንም መረጃው አመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...