Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለመረጃ ምንጭነት የሚያገለግለው የሴት ባለሙያዎች ገጸ መዘርዝር

ለመረጃ ምንጭነት የሚያገለግለው የሴት ባለሙያዎች ገጸ መዘርዝር

ቀን:

በኢትዮጵያ ሴቶች ታሪክ፣ በየዘርፉ አርአያ የሆኑ ባለሙያዎችን ማንነት ከገለጹ መጻሕፍት በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው “ክዋኔ እና ርዕይ” የተሰኘው መጽሐፍ ነው። በሽግግር መንግሥቱ ዘመን የተዘጋጀው ታሪካዊ መጽሐፍ በዘውዳዊው፣ በደርግና በኢሕአዴግ ዘመናት ጎልተው የወጡ አትሌቲክስን ጨምሮ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በወታደራዊ ዘርፎች ስመ ጥር የሆኑ ሴቶች ታሪክን ባጭሩ ይዟል። የቅርብ ዘመኖቹ ህንደኬና ተምሳሌትም ተጠቃሽ ናቸው።

ይሁንና በርካታ ሴት ባለሙያዎች በተለያዩ የህትመት ውጤቶችም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን አይታዩም፡፡ ሴቶች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንዲሁም የሥልጣን እርክን ላይ ቢገኙም፣ ለመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ምንጭ ሲሆኑ እምብዛም አይስተዋሉም፡፡

የጉዳዩ ባለቤት ለሆኑበት ጉዳይ እንኳን ለሚዲያ መረጃ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ጉዳዩን ወደ ሌላ መግፋት አሊያም ምክንያት አስቀምጦ ፈቃደኛ አለመሆናቸውም በበርካታ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንደ ቅሬታ ከሚነሱ ጉዳዮች ይጠቀሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በምታዘጋጇቸው ዜናዎችና ሌሎች ትንታኔዎች  የመረጃ ምንጭ ሆነው በብዛት የሚያገለግሉት ወንዶች ናቸው፣ ለምን ሴቶችን አታሳትፉም? ሲባሉም ‹‹ብዙ ጊዜ ሴት ባለሙያዎች ቃለመጠይቅ ለመስጠት፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣና በሬዲዮ ለመቅረብ ፍላጎት የላቸውም›› የሚል መልስም ይሰጣሉ፡፡

ሴቶች ለመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ምንጭ ሆነው ቢሳተፉ፣ በሴቶች ላይ ያለው አመለካከት ይቀየራል፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሉ ሴቶችም ተበረታትተው በሚያውቁት መስክ ሁሉ ሐሳባቸውን ለመስጠት በር ይከፈታል ተብሎ ቢታሰብም፣ ይህ እስካሁንም ቢሆን ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ልምዳቸውን ያካፈሉን ጋዜጠኛም፣ ‹‹ብዙ ጊዜ ሴቶች በተለይም በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉት የሚያውቁትን እንኳን ለመናገር ይሸሻሉ፡፡ ይህ በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ እርከን ላይ ባሉት ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ የሙያ ማኅበራት በመሪነት ደረጃ ባሉትም ይስተዋላል››፡፡ ይላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የገጠማቸውንም ያስታውሳሉ፡፡

አንድ አንጋፋ የሙያ ማኅበርን የሚመሩ ዶክተር፣ ስለማኅበሩ፣ ስለደረሰበት ስኬት፣ የገጠሙ ፈተናዎችና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ በኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ በኩል ቀጠሮ አስይዘው ይሄዳሉ፡፡

በሥፍራው ሲደርሱ ዶክተሪቷ እየጠበቋቸው ነበር፡፡ ጋዜጠኛው ለቃለመጠይቅ ሲዘጋጁ ‹እኔ በማኅበሩ ዙሪያ ምንም መናገር አልፈልግም፣ በእናንተ ሚዲያ እንዲወጣ የምፈልገው ወደፊት ሥለምናደርገው ጠቅላላ ጉባዔ ብቻ ነው፤› ብለው እንደመለሷቸው ይገልጻሉ፡፡

ሴት ባለሙያዎች የጉዳዩ ባለቤት ሆነው ለሚዲያ መረጃ ለመስጠት ብዙም ፈቃደኛ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ መድረኮች የሚገኙት ወንዶች በመሆናቸው ሴቶች በሚዲያው ላይ ሐሳባቸውን በስፋት ለመግለጽ ዕድሉን እንዳያገኙ ማድረጉንም ያክላሉ፡፡ በተገኙበት ቦታ ደግሞ ‹እሱን አናግሩ› ብለው ዞር ማለት የሚመርጡም ጥቂት አይደሉም ይላሉ፡፡

ይህ ሴቶች ዕውቀት ስላጡ ወይም ጉዳዩን ስለማያውቁት ሳይሆን፣ ‹‹ይህን ብናገር ምን እባላለሁ›› ‹‹ሕዝቡ ምን ምላሽ ይሰጣል›› የሥራ ባልደረቦቼ ይነቅፉኝ ይሆን? የሚሉና ሌሎች አሉታዊ ነገሮችን በአዕምሮአቸው ከማስቀደም ሊመነጭ እንደሚችል የነገሩን ጋዜጠኛ፣ ዕድሉ ያላቸው ሴት ባለሙያዎች በመገናኛ ብዙኃን ወጥተው ሐሳባቸውን መግለጽ ካልቻሉ በሚዲያ ላይ ሴቶች የሚኖራቸው የመረጃ ምንጭነት ዝቅተኛ ሆኖ እንደሚቀጥልም ያምናሉ፡፡ ከወንዶች ይልቅ የሴት ባለሙያዎችን አድራሻ ማግኘት ከባድ መሆኑንም ያክላሉ፡፡

ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን ሐሳባቸውን በስፋት እንዲገልጹ ማሳመን፣ ማስቻልና የሚገኙበትን አድራሻ ማሳወቅ ቀላል ሥራ ባይሆንም፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ለዜና ምንጭነት ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ 197 ሴት ባለሙያዎችን የያዘ መዘርዝር በመጽሐፍ አሳትሟል፡፡ ከመጽሐፉ በተጨማሪም ሙያቸውንና አድራሻቸውን በማከል በድረገጹ ላይ አስገብቷል፡፡

ማኅበሩ ለኅትመት ያበቃውን የሴት ባለሙያዎች መዘርዘርም (Woman Experts Directory) ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

የማኅበሩ የቦርድ ሊቀመንበር ርብቃ ታደሰ እንዳሉት፣ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ባለሙያዎች ለመገናኛ ብዙኃን በመረጃ ምንጭነት በማገልገል ያላቸው ምጣኔ ከ12 በመቶ ያነሰ ነው፡፡

ይፋ የተደረገው የሴት ባለሙያዎች መዘርዝር፣ በዘርፉ የሚታየውን ችግር በተወሰነ መልኩ ለማቃለል የሚያግዝ ሲሆን፣ በግብርና፣ በመሬት አስተዳደር፣ በእንስሳት ሕክምና፣ በገጠር ልማት፣ በአካል ጉዳት፣ በቱሪዝም፣ በመገናኛ ብዙኃንና በሌሎችም ዘርፎች ለሚዲያው የመረጃ ምንጭ ሆነው ሐሳብ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ሴቶች ተካተውበታል፡፡

ለመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ የሴት ባለሙያዎች መዘርዝር ማውጣት ያስፈለገበትን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የማኅበሩ የቦርድ አባል መሠረት ከበደ በበኩላቸው፣ ሴቶች በተለይ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በቴክኖሎጂና በፋይናንስ ዘርፎች የዜናና የመረጃ ምንጭ ሲሆኑ እንደማይታዩ ገልጸዋል፡፡

የሴቶች ድምፅ በሚዲያ እምብዛም የማይሰማ ሲሆን፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ ሴቶች ቁጥር አናሳ መሆኑ ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

መዘርዝሩን በማዘጋጀት ወቅት ከታዩ ችግሮችም፣ ሴት ባለሙያዎች በመዘርዝሩ ለመካተት ያላቸው ፍላጎት አናሳ መሆን፣ በሴት ላይ የሚሠሩ ሙያዊ ማኅበራትና ድርጅቶች በአባልነት የያዟቸውን ሴት ኤክስፐርቶች መረጃ ለመስጠት የነበራቸው ፈቃደኝነት ዝቅተኛ መሆን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በመዘርዝሩ በርካታ ሴት ባለሙያዎች እንዳይካተቱ ካደረጉ ምክንያቶች እንደሚጠቀሱም አክለዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...