የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ግብይትን በዲጂታል መንገድ ለማከናወን ከፋብሪካዎች ጋር ውይይቶችንና የክፍያ አማራጮች ልየታ እያደረገ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መስከረም ባህሩ፣ የሲሚንቶ ግብይት በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲፈጸም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በመለየት እየተሠራ እንደሚገኘ አስታውቀዋል፡፡
የሲሚንቶ ግብይት በዲጂታል መንገድ በቴክኖሎጂ ታግዞ መከናወኑ ሲሚንቶ በተተመነለት ዋጋ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ፣ ሥርጭቱ ከፋብሪካው ጀምሮ የት እንሚደርስ? ለመከታተል፣ የዘርፉን የግብይት ሥርዓት በማዘመን የግብይት ሠንሰለቱን ለማሳጠርና ከሕገወጥ ደላሎች የፀዳ የንግድ ሥርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያግዝ ተነግሯል፡፡
ወ/ሮ መስከረም እንዳስታወቁት፣ የሲሚንቶ ግብይት በቴክኖሎጂ ታግዞ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ ከፋብሪካዎች ጋር ውይይቶችን የማድረግ፣ የክፍያ አማራጮችን የመለየትና መሰል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በመለየት እየተሠራ እንደሚገኝ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ጋር የሲሚንቶ ግብይትን ለመቆጣጠር መመሪያ ከማዘጋጀት ጀምሮ የሲሚንቶ የግብይትና ሥርጭት አሠራር ሥርዓትን በመዘርጋት ክትትል ለማድረግ ጥረቶች እንደሚደረግ በተደጋጋሚ ቢገልጽም አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ሲሚንቶ በጥቁር ገበያ መሸጥ የተለመደ ጉዳይ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የግንባታ ባለሙያዎችና ሸማቾች በተደጋጋሚ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
ሲሚንቶን አሁን ከሚሸጥበት አማራጭ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን በኩል ለማገበያየት ጥናቶች እየተደረገ እንደሚገኝ ከዚህ ቀደም መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ የተደረገው ጥናት ተጠናቆ በቦርድ በሚፀድቅበት ሰዓት ሲሚንቶ በባለሥልጣኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግብይት የሚቀርብ የኢንዱስትሪ ምርት ውጤት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡