Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቅድመ ምርመራ የተደረገላቸው 133 ሺሕ የቁም እንስሳት ዕርድ ውድቅ ተደረገ

የቅድመ ምርመራ የተደረገላቸው 133 ሺሕ የቁም እንስሳት ዕርድ ውድቅ ተደረገ

ቀን:

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው የቅድመ ዕርድ ምርመራ ከ133 ሺሕ በላይ የቁም እንስሳት ተገቢውን ደረጃ ሳያሟሉ እንደተገኙ ታወቀ፡፡

በእንስሳት ልየታና ምዝገባ ሥርዓት ሥር የሚያልፉ ለኤክስፖርት የሚቀርቡ እንስሳቶችን የቅድመና ድኅረ ዕርድ ምርመራ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን፣ በተያዘው በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ቅድመ ምርመራ ከተደረገላቸው 1.3 ሚሊዮን የቁም እንስሳት መካከል በአጠቃላይ 133,087 የሚሆኑት በምርመራው ውድቅ መደረጋቸውን አስታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከሚላኩት የቁም እንስሳት በግ፣ ፍየል፣ የዳልጋ ከብትና ግመልን የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም እሴት ሳይጨመር የሚላኩትን ይመለከታል፡፡

የባለሥልጣኑ የእንስሳት ሬጎላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ሀሚድ ጀማል (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ እንስሳት ለዕርድ  ወደ ቄራ ከመግባታቸው በፊት የቅድመ ዕርድ  እንዲሁም ከታረዱ በኋላ የድህረ ዕርድ ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡

ልየታው ከሚደረግባቸው መንገዶች አንደኛው ዕይታ ሲሆን፣ እንደ መፍዘዝ፣ መንቀጥቀጥ፣ ማነከስና መተኛት ዓይነት የጤና እክል ችግሮች የሚለዩበት ነው፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጨነቀና የታመመ እንስሳ በየትኛውም መንገድ ለዕርድ አይፈቀድም፡፡

በቅድመ ምርመራው ከክብደት ጋር በተያያዘ ውድቅ የተደረገ የቁም እንስሳት ለአገር ውስጥ ገበያ አሊያም እንዲወገድ ከማድረግ ውጪ የታመሙት ከኤክስፖርት ሒደት ውጭ ይደረጋሉ ተብሏል፡፡

እንስሳት ጤነኛም ሆነው ለአብነትም እንደ በግና ፍየል ዓይነቶች ዝቅተኛና ከፍተኛ ክብደት የሚባል ነገር እንዳለና፣ ይህንንም ከተስተዋለባቸው እንደሚወገዱና አሊያም ለአገር ውስጥ ገበያ እንደሚቀርቡና ዝቅተኛም ሆነ ከፍተኛ ክብደት ከሥጋ ጥራትና ጤንነት ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለው ተጠቅሷል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ያለው የዕርባታ ሥርዓት ዘልማዳዊ ከመሆኑ አንፃር፣ የትኛው እንስሳት ለቄራዎች ዕርድ ነው መቅረብ ያለበት?፣ የትኛው እንስሳት ለቁም እንስሳት ገበያ የሚለውን ተለይቶ ባለመሠራቱ? እንስሳት ከተለያየ አካበቢዎች በተገቢው መንገድ ተሰባስበው ለገበያ ስለሚቀርቡ በቅድመ ዕርድ ወቅት ለሚስተዋሉት ችግሮች ዓይነተኛ መንስዔ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ከሰሞኑ የግብርና ሚኒስቴርና ተጠሪ የሆኑለት ተቋማት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም በግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሲገመገም፣ ከቀረቡ ጉዳዮች ውስጥ ከቅድመ ዕርድና ድኅረ ዕርድ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

በዘጠኝ ወራት በእንስሳት ጤና ዘርፍ የቅድመ ዕርድ ምርመራ አፈጻጸም 68.7 ከመቶና፣ የድኅረ ዕርድ ምርመራ አፈጻጸም 65.6 ከመቶ፣ እንዲሁም የቄራዎችን ሃይጅንና ሳኒቴሽን እንዲጠበቅ ለመቆጣጠር የኢንስፔክሽን አገልግሎት የበግ፣ የፍየልና የዳልጋ ከብት ሥጋ ምርት  58 በመቶ ሥጋና ተረፈ ሥራ ደኅንነቱ ተረጋግጦ እንዲላክ ተደርጓል የሚለውን በመግለጽ፣ ስለአፈጻጸሙ ማብራሪያ እንዲሰጥበት በቋሚ ኮሚቴ አባላት ተጠይቆ ነበር፡፡

የግብርና ባለሥልጣን ከዕርድና ከቅድመ ዕርድ ልየታና ምርመራ ጋር በተያያዘ፣ በዘጠኝ ወራት የነበረው አፈጻጸም ዝቅተኛ እንዲሆን ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ የእንስሳት አቅርቦት ችግር ዋነኛው ነው ተብሏል፡፡ ይህም በአገሪቱ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ፣ እንዲሁም የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያለው ሕገወጥ ንግድና ሌሎች የተወሳሰቡ ነገሮች ምክንያት እንደሆነ፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ኩማ (አምባሳደር) ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት አስረድተው ነበር፡፡

በዘጠኝ ወራት ውስጥ በተደረገው የቅድመ ዕርድ ምርመራ ከ133 ሺሕ በላይ የቁም እንስሳት ተገቢውን ደረጃ ሳያሟሉ ቀርተው ዕርዱ ውድቅ እንደተደረገና ይህም ከእንስሳት  አመጋገብ፣ ከጤናና ከመሳሰሉት ጋር እንደሚያያዝ ተጠቁሟል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በተጠቀሰው ጊዜያት ግመሎችንም በተመሳሳይ በቀረበው ልክ ምርመራ እንዳደረገ፣ ከድርቁ ጋር ተያይዞ አርብቶ አደሩ ግመሎች ከየአካባቢው ይዞ ስለሚንቀሳቀስ ኤክስፖርተሮች ገበያዎች ላይ እንስሳቱን ለማግኘት እንደተቸገሩና በዚህም እጥረት የተነሳ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አገሪቱ ካላት የእንስሳት ሀብት አንፃር ወደ ውጭ የምትልከውና የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡ በቅድመ ዕርድ፣ በዕርድ፣ እንዲሁም እንስሳቶች ተመርምረውና ተከትበው ወደ ውጭ ከመላክ አንፃር ያለው አፈጻጸም አነስተኛ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታ  አክለዋል፡፡

በደቡብ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የነበረው ድርቅ እንስሳቶችን እንደጎዳና እንስሳት ሞት ብቻ ሳይሆን የክብደት መቀነስና ለበሽታ የመጋለጥ ሁኔታዎች እንስሳቶቹ ታርደው ሥጋቸው ብቁ የማይሆንበት ዕድል እንዳለ፣ ከቅድመ ዕርድ በፊትም ሲመረመሩም ሆነ ታርደው ለማለፍም የማይቻልበት ሁኔታ እንዳለ ፍቅሩ (ዶ/ር)  ጠቅሰው ነበር፡፡        

ከላይ የተገለጹት ጉዳዮች የአየር ፀባይ ለውጥ ያመጣው ተፅዕኖ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

የአገሪቱ ድንበሮች በሁሉም ማዕዘናት ክፍት እንደመሆኑ፣ እንስሳቶች ተጓጉዘው ሊወጡ እንደሚችሉና ሕገወጥ ንግዱ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ሶማሊያ፣ ጂቡቲና ወደ ሌሎችም ጎረቤት አገሮች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት እንስሳቶች አብዛኛዎቹ ከኢትዮጵያ የሚመነጩ ናቸው ተብሏል፡፡

የግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች የሚኒስቴር ተቋማት በጋራ በመሆን የማስተካከል ሥራዎች እንደተጀመረ፣ ዲፕሎማሲን ጨምሮ የገበያ ተደራሽነትን ከማስፋት አንፃር ከሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ ፍቅሩ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...