Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢንቨስተሮች በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፉ መንግሥት ቢሮክራሲውን ዘመናዊ ማድረግ እንዳለበት ተገለጸ

ኢንቨስተሮች በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፉ መንግሥት ቢሮክራሲውን ዘመናዊ ማድረግ እንዳለበት ተገለጸ

ቀን:

የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው መንግሥት ክፍት ባደረጋቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ ለማድረግ፣ የመንግሥት ትኩረት ቢሮክራሲውን ዘመናዊ ማድረግ ላይ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

 በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አባቢ ደምሴ (አምባሳደር) ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የግሉ ዘርፍ በኢትዮጵያ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፍ ከማድረጉ ጎን ለጎን በዚህ ወቅት የመንግሥት ትልቁ የትኩረት ማዕከል ቢሮክራሲውን ዘመናዊ ማድረግ ነው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፣ መንግሥት በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ሚና እየቀነሰ በብዛት የቁጥጥር (ሬጉላቶሪ) ሚናውን እንዲጫወት፣ በመንግሥት የተያዙ ዘርፎች ቴሌኮምና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለግሉ ዘርፍ በግልና መንግሥት አጋርነት እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ ክፍት በማድረግ ረገድ ትልቅ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል፡፡

‹‹ባለሀብቶች ወደ አገር ቤት ሲመጡ መጀመርያ እምነት እንዲያሳድሩና እምነት እንዲጥሉ በፖሊሲዎቻችን አተገባበር ላይ ፅኑ አቋም እንዲኖራቸው ለማድረግ የቢሮክራሲው ክፍል ትልቅ ሚና አለው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ስለሆነም ቢሮክራሲው ላይ የቢዝነስ ማብራሪያ (ኦሬንቴሽን) እንዲኖር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከተለያዩ አገሮች የሚወሰዱትን ተሞክሮዎችና ልምዶችን በመውሰድ የአገሪቱን ቢሮክራሲ ዘመናዊ ማድረግ እንደሚገባና በአገር ውስጥ ያሉና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ የሚጥሩ ባለሀብቶችን የመደገፍ አመለካከት በጣም በትልቁ መስተካከል እንዳለበት፣ መንግሥትም ይኼንን ጉዳይ የሚያውቀው መሆኑን አባቢ (አምባሳደር) አስታውቀዋል፡፡

ባለሀብቱ በኢኮኖሚው ላይ ዘለቄታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ ትልቅና የማይተካ ሚና አለው በሚል በፖሊሲ ላይ እንደተዘረዘረው ሁሉ መሬት ላይም ተግባራዊ መደረግ አለበት ብሎ ለመሥራት አሠራርን፣ አመለካከትን፣ የድጋፍ ሥርዓቱንና የአገልግሎት አሰጣጡን፣ የተንዛዛውን አሠራር ማስተካከል ይገባል ተብሏል፡፡ ‹‹የማስተካከል ሥራው ባይስተካከል እንኳን በዚህ ምክንያት ነው ብለን የመግለጽ፣ በትህትና የተሞላበት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓታችን እየጎለበተ ከመጣ፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ ያስቀመጠቻቸው አገሪቱን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከልና የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም መዳረሻነት እንዲሁም በዚያው ልክ ንግድን የማስተዋወቅ ሥራዋ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፤›› ሲሉ አባቢ (አምባሳደር) አክለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ሲባል በዋናነት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን፣ ቱሪዝምን፣ የንግድ ማስፋፊያና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማዕከል ያደረጉ መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህ ረገድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመሆን የአገሪቱን ዕምቅ የኢንቨስትመንት አቅም እንዲሁም ደግሞ ኢንቨስትመንትን ለመሳቢያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት  ከባቢ (ኢንቫይሮመንት)፣ ማበረታቻዎችና ፖሊሲዎች የማስተዋወቅ ሥራ አየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

‹‹ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን ሚሲዮኖቻችንን በማሳተፍ ከሳምንታት በፊት ያካሄድነው ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› ትልቅ የፕሮሞሽን ሥራ ማሠሪያ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ በተወሰኑ አገሮች እየተንቀሳቀስን በአሜሪካ፣ በጣሊያን፣ በእንግሊዝ፣ በፓሪስ፣ በቻይና ከፍተኛ ሥራ ይሠራል፤›› ሲሉ ያስረዱት አባቢ (አምባሳደር)፣ ይህም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ከማስፋፋትና ኢንዱስትሪያሊስቶች መጥተው ኢንቨስትመንትን ከማጠናከር ባሻገር የማኅበራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሳካና የአገር ውስጥ የሥራ ፈላጊዎች ሥራ አግኝተው የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን አንድ አገር ያላትን የፖሊሲ ሐሳቦችን፣ አፈጻጸሞችን፣ ፖሊሲዎቹ ለባለሀብቶች የሚሰጡትን ማበረታቻዎችንና ሌሎች አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ አጠቃቀምና የአሠራር ሥርዓት የሚታወቅበት ነው፡፡

‹‹አገር ቤት ያለው ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሮ ኢንቨስትመንት ያለው አመለካከትና ኢንቨስትመንትን አቅም እየተገነባ ካልሄደና የአሠራር ግልፀኝነት እየሰፈነ ካልሄደ፣ የመጣው ባለሀብት ምስክርነት እየሰጠ መሄድ ካልተቻለ የፕሮሞሽን ሥራ ብቻውን ለስኬት አያበቃም፤›› ሲሉ አባቢ (አምባሳደር) አክለዋል፡፡

የቢዝነስ ሥራ አስተዋዋቂው ባሰበው መሠረት የሚያመጣው እንዳልሆነና ኢንቨስተሩ ትርፍና ኪሣራ አይቶ፣ አዋጭነቱን ሌሎች ተወዳዳሪዎችን አይቶ የሚመጣበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ውድድርን ለትርፍ ሊያበቁ የሚችሉ ሥራዎችን አቀላጥፎ በመሥራት እንዲሁም አገር ውስጥ የሚገባውን ባለሀብቱ ይዞ ማቆየትና ድጋፍ በማድረግ ለምርትና ለተፈለገው ዓላማ እንዲችል በተደረገ ቁጥር ፕሮሞሽኑ ውጤታማ እንደሚሆን አክለዋል፡፡

በአሁን ሰዓት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ካሉ ተግባራት ውስጥ ኢትዮጵያ በአኅጉሪቱ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ያለውን ሚና ማስጀመር አንዱ እንደሆነ እንዲሁ ተጠቅሷል፡፡

በአኅጉራዊው የንግድ እንቅስቃሴ ተወዳዳሪ ለመሆን የኢንቨስትመንትና የንግድና አጠቃላይ ጉዳዮች እንዲሳለጥ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው ወደ ሥራ መገባት መቻል ስለሚገባ የኢትዮጵያ መንግሥት አጠቃላይ ፖሊሲዎቹ ከነፃ የንግድ ቀጣናው ጋር የማናበብ (አላይመንት) ተሠርቶ አንድ ወጥ የሆነ አሠራር እንዲኖረው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለቤት በማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት አመቺ ናት የሚል እምነት በውስጥም፣ በውጭም ተፈጥሯል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ፕሮሞሽን ባለሀብቱን ለማስተዋወቅና ለመምረጥ አንዱ የሥራ መሣሪያ ቢሆንም መሬት ላይ የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ አቅልሎ እንዲቆዩ የማቆየት ሥራ መሠረታዊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ በተጨማሪም ኢንቨስተሮች በሥራ ሒደት የሚገጥማቸውን ችግር መፍታት ሌላው ጥረትን የሚጠይቅ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አክለዋል፡፡

ከአጎዋ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የዕድሉ ተጠቃሚ በነበረችበት የኢንዱስትሪ ምርቶቿ በአሜሪካ ገበያ የተሻለ የውድድር ተፈጥሮ እንደነበር፣ ነገር ግን ዕገዳውን ተከትሎ አብዛኛው በኢንዱስትሪ ውስጥ የነበሩትን ችግር ላይ እንዲወድቁ እንዳደረገ፣ ዕርምጃው እውነታውን ተገንዝቦ ያልተወሰደ እንደሆነ ለአሜሪካ መንግሥት በተደጋጋሚ እንደቀረበ ተገልጿል፡፡ በቅርቡም በአሜሪካ በተደረገ የቢዝነስ ፎረም ላይ የአሜሪካ ድርጅቶችን ጨምሮ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የተቀጠሩ በተለይም ሴቶችን ከሥራ ማጣት እንዳደረገ ለማሳወቅ ጥረት ተደርጓል ሲሉ አባቢ (አምባሳደር) ተናግረዋል፡፡

ዕድሉን ለማስመለስ በቅድመ ሁኔታ የተገለጹት ጉዳዮች በዚህ ወቅት በአብዛኛው እንደተሟላና ይህንን የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት መመለስ አለበት የሚለውን የኢትዮጵያ መንግሥት እንደጠየቀና ይመለስ የሚል ዕሳቤ እንዳለ አባቢ (አምባሳደር) ተናግረዋል፡፡

ሌላ ቅድመ ሁኔታ ካልተቀመጠ በስተቀር የአጎዋ ዕድል እንደሚመለስ ተስፋ እንዳለ አክለው፣ አጎዋ እንዳለ ሆኖ ሌሎች የአውሮፓ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የእስያና የአፍሪካ ገበያ ምርቶችን በማቅረብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሁሉም መልክ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...