Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየትምህርት ማስረጃቸው እንዲጣራ ከተደረገባቸው 225 ሠራተኞች ውስጥ 40 በመቶዎቹ ሕገወጥ መሆናቸው ተገለጸ

የትምህርት ማስረጃቸው እንዲጣራ ከተደረገባቸው 225 ሠራተኞች ውስጥ 40 በመቶዎቹ ሕገወጥ መሆናቸው ተገለጸ

ቀን:

የትምህርት ሚኒስትሩ 4.3 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው አሉ

ቀጣሪ መሥሪያ ቤቶች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የ225 ተቀጣሪ ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃዎች ትክክለኛነት ሲመረመር፣ 40 በመቶ የሚሆኑት (90 ማስረጃዎች) በሕገወጥ መንገድ የተገኙ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡትን ሕገወጥ የትምህርት ማስረጃዎች በቁጥር አስደግፈው አቅርበዋል፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ሪፖርቱን ያቀረቡት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በወጡት 18,128 የትምህርት ማስረጃዎች ላይ የማረጋገጥ ሥራ ተከናውኖ አምስት በመቶ (921) የሚሆኑት ሕገወጥ ሆነው መገኘታቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን ለማስጀመርና እያስተማሩ ያሉትንም መርሐ ግብሮች ፈቃድ ለማደስ ጠይቀው፣ በሚኒስቴሩ ፈቃድ የተሰጣቸውንና የተከለኩሉትን በአኃዝ አስደግፈው ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት 35 ካምፓሶች በ71 የትምህርት መስኮች የትምህርት መርሐ ግብር የማስጀመር ፈቃድ ጠይቀው የተፈቀደላቸው መሆኑን፣ ሌሎች 67 ካምፓሶች ደግሞ በ60 የትምህርት መስኮች ለማስተማር ጠይቀው እንዳልተፈቀደላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹የፈቃድ ዕድሳት ጥያቄ አቅርበው መሥፈርት ባለሟሟላታቸው ዕድሳት ያልተፈቀደላቸው በ129 የትምህርት መስኮች 66 ካምፓሶች ናቸው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ 38 ካምፓሶች ግን በ190 የትምህርት መስኮች የዕድሳት ፈቃድ ጠይቀው እንደተፈቀደላቸው አስረድተዋል፡፡ በ132 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በ82 ካምፓሶች ድንገተኛ ፍተሻ ተካሂዶ፣ ዘጠኝ ተቋማት ባልተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት እየሠሩ ተገኝተው ‹‹የማስተካከያ ዕርምጃ›› እንደተወሰደባቸውም አክለዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን በሚመለከት ከ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ካስመዘገቡት ውጤት በተጨማሪ፣ አጠቃላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ውጤት ዝቅተኛ እንደነበር በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቀረበው ሪፖርት አሳይቷል፡፡ በ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተፈተኑት ከ900 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ያመጡት 3.3 በመቶ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ከአራተኛ ክፍል 20 በመቶ፣ እንዲሁም ከስምንተኛ ክፍል 12 በመቶ ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹በሁለቱም የክፍል ደረጃዎች በትምህርት ፖሊሲ ግባችን ካስቀመጥነው ከ50 በመቶ በታች ነው፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ በሚመለከት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በፀጥታ፣ በድርቅና በተያያዥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት 4.3 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፤›› ብለዋል፡፡

በተያዘው የትምህርት ዘመን በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች በአገሪቱ ትምህርት ቤቶች 29.2 ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግበው እንዲያስተምሩ ቢታቀድም፣ በትምህርት ገበታቸው ሊገኙ የቻሉት ግን 24.9 ሚሊዮን (85.2 በመቶ) ብቻ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ሴቭ ዘ ቺልድረን የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ባለፈው ወር አውጥቶት የነበረው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ ሰላም ቢሰፍንም 2.3 ሚሊዮን ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፡፡

በግጭት ምክንያት ትምህርት አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት መመለስ በመንግሥት በኩል ከተያዙት የትኩረት አቅጣጫዎችም አንደኛው እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት በታቀደው መሠረት፣ 1,335 ትምህርት ቤቶችን መገንባት የቀጣይ ዓመታት ዕቅድ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...