Monday, July 22, 2024

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት ረቂቅ ማቅረቢያ ስለሆነ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ይገባል፡፡ መንግሥት ያለፈው ዓመት በጀቱ እንዳልበቃው፣ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመሰረዝ መገደዱን፣ በአንዳንድ ክልሎች ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መክፈል እንዳቃተውና የመሳሰሉ የችግር ወሬዎች በስፋት ተሰምተዋል፡፡ መንግሥት የገንዘብ ችግር አጋጥሞታል ሲባል ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት በተቻለ መጠን አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ አለበት፡፡ ከወረዳ እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ የሚከናወኑ የቅንጦት ግዥዎችና አንገብጋቢ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች መቆም አለባቸው፡፡ በጥናት ላይ የተመሠረቱ አዋጭ የገቢ ምንጮችን ማስፋት ይጠበቅበታል፡፡ በከባድ የኑሮ ውድነት እየተደቆሰ ያለውን ሕዝብ ካለችው ከእጅ ወደ አፍ ገቢ ላይ፣ በተለያዩ መንገዶች ጫና በመፍጠር የተለያዩ የግብር ዓይነቶችን መቆለል ተገቢ አይደለም፡፡ መንግሥት የሕዝቡን ኑሮ ማክበድ አቁሞ ጤናማና ውጤታማ የገቢ ምንጮች ላይ ያተኩር፡፡

እየተለወጠ ካለው የዓለም ሥርዓት ጋር አብሮ መራመድ የግድ ነው፣ መሆንም አለበት፡፡ ከተለያዩ አገሮችም ሆነ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በሚኖር የሁለትዮሽም ሆነ የባለብዙ ግንኙነት፣ የራስን የቤት ሥራ በሚገባ አጠናቆ መነጋገርም ሆነ መደራደር ከመንግሥት ከሚጠበቁ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለያዩ መስኮች በተመሰከረላቸው ብቁ ባለሙያዎች መታገዝ አስፈላጊ ነው፡፡ ፖሊሲዎችም ሆኑ ስትራቴጂዎች ወቅቱን የዋጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የጥቂቶችን ፍላጎት ከማስፈጸም በላይ አገራዊ ጥቅም ሊከበር የሚችለው፣ ከማናቸውም ተደራዳሪ አካላት ጋር በብቃት ጥቅምን ለማስከበር የሚያስችል ክህሎት ሲኖር ነው፡፡ መንግሥት የበጀት ጉድለትን ለመሸፈን፣ አማራጭ የገቢ ምንጮችን ለመቃኘት፣ ሕዝብ ላይ ጫና የሚያሳድሩ ዕርምጃዎችን እንዳወይስድና በሌሎች ኃይሎች እጁ እንዳይጠመዘዝ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች ያስፈልጉታል፡፡ በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ የዘፈቀደ ዕርምጃዎች ግን የሕዝቡን ኑሮ ከማክበድና ከማመሰቃቀል የዘለለ ፋይዳ እንደሌላቸው በስፋት እየታየ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብቶችን ከፍተኛ መጠን ካለው የሰው ሀብት ጋር አቆራኝቶ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቅርጫ ማድረግ እየተቻለ፣ እያደር የድህነቱን አዘቅት ማስፋት የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡

መንግሥት ሙሉ ትኩረቱ መሆን ያለበት የቅንጦት ቤተ መንግሥቶችና መናፈሻዎች ላይ ሳይሆን፣ ከፍተኛ የገቢ ምንጭና ሥራ ፈጣሪ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ላይ ነው፡፡ ፕሮጀክቶች ሲታቀዱም የምግብ ችግርን የሚፈቱ፣ ንፁህ ውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል በስፋት የሚያስገኙ፣ የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በብዛት የሚያቀርቡ፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎችን በብዛትና በጥራት የሚያመርቱ፣ የግብርና ዘርፉን በአጭር ጊዜ የሚያዘምኑና የሚያስፈነጥሩ፣ ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ አቅም የሚያስታጥቁና የመሳሰሉ ሀብት ፈጣሪነት ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በተረፈም መንግሥት በከፍተኛ ዲሲፕሊን ከአባካኝነት ወጥቶ ወጪ ቆጣቢ መሆን አለበት፡፡ በደሃ አቅም ደረጃ ሊታሰቡ የማይችሉ ዘመናዊ የቅንጦት ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ውድ ቁሳቁሶችን ግዥ በፍጥነት ማስቆም የግድ ነው፡፡ የቅንጦት ግንባታዎችን እያካሄዱና በቅንጦት ኑሮ ውስጥ እየተቀማጠሉ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለወደሙ መሠረተ ልማቶች መልሶ ግንባታና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የውጭ ዕርዳታ መጠየቅ እርስ በርሱ ይጣረሳል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመታ ቅንጦት ማሰብም ኢሞራላዊ ነው፡፡

በተደጋጋሚ ለማስታወስ እንደምንሞክረው ከዚህ በፊት የነበሩና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ ቅደም ተከተል ያስፈልጋል፡፡ በረጅም፣ በመካከለኛና በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን መለየት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትኩረት ከሚፈልጉ ጉዳዮች መካከል ሰላም፣ የምግብ ዋስትና፣ መጠለያ፣ የሥራ ፈጠራና የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ መንግሥት ሌሎች ጊዜ የሚሰጡ ፕሮጀክቶቹን ገታ አድርጎ መሠረታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩር ከመካከለኛ ኑሮ ወደ ድህነት፣ ከድህነት ወደ ባሰው ፍፁም ድህነት ውስጥ እየተንደረደሩ እየገቡ ያሉ ወገኖችን መታደግ ይችላል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ በተለይ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ወጣት የሰው ኃይል ሊያሰማራ የሚያስችል አዋጭ ፖሊሲ መንደፍ ነው፡፡ በተለመደው መንገድ መንደፋደፍ ከኪሳራ በስተቀር ምንም ዓይነት ትርፍ እንደማያስገኝ በሚገባ ታይቷል፡፡ የሕዝቡ ኑሮ ከዕለት ወደ ዕለት እየከበደ ሲሄድ፣ አዳዲስ አማራጮችን በባለሙያዎች ታግዞ ማየት ይገባል፡፡ 

በጀትን በአግባቡ አቅዶ ከአቅም ጋር የተገናዘቡ ሥራዎችን ማከናወን ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ በጀቱም ለአገር ልማትና ለሕዝብ የኑሮ ዕድገት ፋይዳ ሊኖረው ይገባል፡፡ መንግሥት ከመጠን በላይ እየተበደረ ገበያውን ሲያጨናንቀው ለዋጋ ግሽበት የራሱን አሉታዊ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ መንግሥት የግብር ሥርዓቱ ውስጥ ያልገቡ በርካቶችን ወደ መረቡ ጎትቶ ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡ ከግብር ሰብሳቢዎች ጋር በመመሳጠር የሚሰውሩና የሚያጭበረብሩትን መንጥሮ ለሕግ ማቅረብ አለበት፡፡ በሐሰተኛ ደረሰኝ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት በሕገወጥ መንገድ የሚያግበሰብሱትን በብርቱ ክትትል በቁጥጥር ሥር ማዋል ይኖርበታል፡፡ አገሪቱን በኮንትሮባንድ የሚያስወርሩ እነ ማን እንደሆኑ ስለሚታወቅ ዕርምጃው ጠንካራ ሊሆን ይገባል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው አገርን ለዘራፊዎች የሚያጋልጡ ስግብግብ ሹማምንትን በሕግ አደብ ማስገዛት አለበት፡፡ በተጨማሪም ከአገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ ላይ ጉቦ ከሚቀበሉ ነቀዞች ጀምሮ፣ የመንግሥት ሀብት ዘረፋ ላይ ተሰማሩትን በሙሉ ያለ ምንም ምሕረት ማጋለጥ ግዴታው ነው፡፡ ሕዝብ እንደ ሰደድ እሳት የሚግለበለበውን የኑሮ ውድነት መቋቋም ተስኖት፣ ጥቂቶች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከዕለት ወደ ዕለት ኑሮን እያከበዱ ካሉ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የምግብ ዋጋ ንረት ነው፡፡ የምግብ ዋጋ ከዓመት ወደ ዓመት በጣም እየጨመረ ከመሆኑም በላይ፣ በርካቶች ቤተሰቦቻቸውን በቀን ሦስቴ ቀርቶ አንዴም ለመመገብ ፅኑ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት ብዙዎች ሊቋቋሙት የማይችሉት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ናቸው፡፡ ከምግብ በተጨማሪ የቤት ኪራይና የሕክምና ወጪዎች የማይቀመሱ እየሆኑ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢኮኖሚው በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል፡፡ የነዳጅና ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ከሁለትና ከሦስት እጥፍ በላይ ውድ ሆኗል፡፡ ብሔራዊ ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት በመቀነሱና የሥራ አጥነት ቁጥሩ እየጨመረ በመሆኑ፣ ለብዙዎች ሥራም ሆነ ገቢ ለማግኘት አዳጋች እየሆነባቸው ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ እየከፋ በሄደ ቁጥር ዜጎች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ማግኘት ስለሚያዳግታቸው፣ ለከፋ ድህነት ከመጋለጣቸውም በላይ ማኅበራዊ ቀውስ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ይሆናል፡፡ መንግሥት ሆይ የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ የበለጠ ችግር ፈጣሪ መሆኑን ተገንዘብ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...