Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዩኒቨርሲቲዎች በዋጋ ግሽበት ምክንያት ተማሪዎቻቸውን መመገብ በማይችሉበት ደረጃ ላይ መሆናቸው ተነገረ

ዩኒቨርሲቲዎች በዋጋ ግሽበት ምክንያት ተማሪዎቻቸውን መመገብ በማይችሉበት ደረጃ ላይ መሆናቸው ተነገረ

ቀን:

  • በተማሪ 22 ብር ቢመደብም ወጪው ግን 89 ብር መድረሱ ተጠቁሟል

ለተማሪ ምገባ የሚመደብላቸው ገንዘብ በዋጋ ግሽበት ምክንያት ዝቅተኛ እየሆነ በመምጣቱ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተማሪዎች ምግብ ማቅረብ ላይ እየተቸገሩ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች በትላንትናው ዕለት ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ‹‹አሁን ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር ተማሪዎቻቸውን መመገብ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርቱን በንባብ ያሰሙት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ሲሆኑ፣ ለአንድ ተማሪ ለዕለት ምግብ 15 ብር በጀት ተመድቦላቸው ለረዥም ጊዜ ሲሠሩበት ቢቆዩም በቅርቡ ወደ 22 ብር አድጎ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን አሁን ካለው የዋጋ ግሽበት ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለተማሪዎች ምገባ የሚመደበው ገንዘብ እንደማይበቃ ‹‹ምንም ጥያቄ የለውም›› ያሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ የተማሪዎችን ምገባ በሚመለከት ‹‹ሌሎች አማራጮችን ማጥናትና መተግበር አስገዳጅ›› እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተማሪዎች ምግብ ስለሚመደበው አነስተኛ ገንዘብ ጥያቄዎቻቸውን ለሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ሰንዝረው የነበረ ሲሆን፣ የትምህርት ሚኒስትር ደኤታው ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በምላሻቸው ዝርዝር ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ደኤታው ገለጻ፣ በቅርቡ ጥናት ተደርጎ አነስተኛው ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎቻቸው ምገባ በቀን የሚያወጡት ወጪ 77 ብር ሲሆን ከፍተኛው እስከ 89 ብር ደርሷል፡፡ የትምህርት ተቋማቱም ለአንድ ተማሪ በቀን ምገባ ከ55 ብር እስከ 67 ብር ድረስ ከበጀት ውጪ በማቅረባቸው ለጉዳት እየተዳረጉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

‹‹ዛሬ ላይ በ22 ብር የምግብ ግብዓቶችን በማቅረብ አንድን ተማሪ መመገብ አይቻልም›› ያሉት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ በኢኮኖሚ ገለጻ ከፍ ያለ ቁጥር ላላቸው ተማሪዎች የምግብ ወጪ ትንሽ ነው የሚል ዕሳቤ ቢኖርም፣ በ22 ብር ግን ተማሪዎችን መመገብ እንደማይቻል ‹‹በተደጋጋሚ ጥናት አድርገን አይተነዋል›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ደኤታው ገለጻ በቀን 15 ብር ለአንድ ተማሪ የምግብ ወጪ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሠራበት ቆይቶ በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በተካሄደ ጥናት ከጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር ወደ 22 ብር ያደገው፡፡

‹‹ለዩኒቨርሲቲዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት በየዓመቱ ይመደባል፣ ሰፋ ያለ ወጪውን የሚወስደው ከተማሪዎች ጋር የተገናኙ ወጪዎች ናቸው›› ያሉ ሲሆን ሚኒስትር ደኤታው፣ ወጪውም ለተማሪዎች ‹‹የትምህርት ግብዓት ማቅረብ፣ ተማሪዎችን ለማሳደር፣ ለማስተማር፣ ለመመገብና ለማከም ነው የሚውለው፤›› ብለዋል፡፡

ከምክር ቤት አባላቶች ለተነሱት ጥያቄዎች ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሩ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹በዚህ ጉዳይ ከመስመር ወጥቼም ቢሆን መናገር የምፈልገው ነገር አለ›› ብለው፣ ምክር ቤቱ በጀት በሚጸድቅበት ወቅት አነስተኛ ገንዘብ መጠን ሊፀድቅ ሲመጣ ማስጨመር እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡

‹‹ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመቀለብ 22 ብር ተብሎ ሲበጀት፣ ‹የለም ይኼ አይበቃም መጨመር አለበት› ብሎ መጠየቅ የምክር ቤቱ ሥራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች ከየት ያምጡትና ይመግቡ ተብሎ ነው የሚጠበቀው?›› ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ባቀረቡት ማብራሪያ በዩኒቨርሲቲዎች የሚደረገው የኦዲት ግኝት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችም የዚህ ውጤት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተማሪ ተቀብለው ሊያስርቡ አይችሉም፡፡ ስለዚህ መንገድ መፈለግ አለባቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተማሪውን ቁጥር ከፍ አድርገውም ይናገሩ ነበር፣ እሱንም አሁን በዲጂታል እያያያዝን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ አስተዳደር ሆነው እንዲቋቋሙ ውሳኔ ተወስኖ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ደግሞ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ይተገበራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...