Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበበቆጂ ከተማ እስረኞችን ለማስለቀቅ በተሰነዘረ ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸው ተሰማ

በበቆጂ ከተማ እስረኞችን ለማስለቀቅ በተሰነዘረ ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸው ተሰማ

ቀን:

  • የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በየትኛውም አካባቢ ጥቃት የለም ሲል አስተባብሏል

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በቆጂ ከተማ ማንነታቸው በግልጽ ያልታወቁ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት አራት ስዎችን ሲገድሉ በፖሊስ ጣቢያ የነበሩ የተወሰኑ እስረኞችን ማስለቀቃቸው ተሰማ።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች እንደገለጹት፣ ታጣቂዎቹ ባለፈው ዓርብ ግንቦት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ ለሊቱ ስምንት ሰዓት በበቆጂ ከተማ ከባድ ተኩስ ይሰማ ነበር። 

በማግሥቱ ፌዴራል ፖሊስ በከተማው እንደገባና ተኩሱ እንደቆመ ነገር ግን ለሊቱን በነበረው ተኩስ የሚሊሻ አንድ አሠልጣኝን ጨምሮ ነዋሪዎች መገደላቸውን ያነጋገርናቸው የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ የኦነግ ሸኔ አባላት ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የሚናገሩት የዓይን እማኞቹ፣ በከተማው በከፈቱት ተኩስ አራት ሰዎች መገደላቸውን፣ ከተገደሉት መካከል አንዱ በከተማው የሚገኘው የሚሊሻ ጦር አሠልጣኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ካነጋገርናቸው የዓይን እማኞች መካከል በታጣቂዎቹ የተገደለው የሚሊሻ አሠልጣኝ የቅርብ ጓደኛ መሆኑን የገለጸ አንድ የዓይን እማኝ፣ ታጣቂዎቹ ‹ይህን ቤት ከምናፈነዳው አንተ ብትወጣ ይሻላል ብለው የሚሊሻ አሠልጣኝ ጓደኛውን በለሊት ከመኖሪያ ቤቱ አውጥተው እንደገደሉት ተናግሯል፡፡

ታጣቂዎቹ በከተማው ተኩስ የከፈቱት በእስር ቤት የሚገኙ ታራሚዎችን ለማስፈታት መሆኑንም የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል። የታጣቂ ቡድኑ አባላት በሚሊሻ አሠልጣኙና በነዋሪዎቹ ላይ የግድያ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላም በከተማው በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ሰብረው በመግባት በርካታ ታራሚዎችን ከእስር አስወጥተው መውሰዳቸውንም ገልጸዋል።

በበቆጂ ከተማ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ የተገደሉትን እንዲሁም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በቢሾፍቱና በወለንጪቱ የተፈጸሙትን ተመሳሳይ ጥቃቶች በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ገረሱ፣ የተባለውን ዓይነት የተደራጀ ጥቃት በየትኛውም አካባቢ እንዳልተፈጸመ ተናግረዋል።

ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ሌሊት በቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ዓለማየሁ፣ ጥቃት አደረሱ በተባሉት ታጣቂዎች ላይ፣ ‹‹ምርመራ ላይ ስለሆንን ስለጉዳዩ ብዙ መረጃ መስጠት አንፈልግም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። በታጣቂዎች ማንነት ላይ እየተደረገ ያለው ምን ዓይነት ምርመራ እንደሆነ ሲጠየቁም፣ ‹‹እሱ ላይም ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጥም፡፡ ገና ነው፡፡ መጣራት አለበት፤›› ብለው ጉዳዩን በሒደት እንደሚያስታውቁ ሪፖርተር ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕትሙ መዘገቡ ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ አበበ ገረሱ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ተጨማሪ የማጥሪያ ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹አልፎ አልፎ ሽፍታ ወይም ሌባ ሊኖር ይችላል እንጂ ጥቃት የሚባል ነገር የለም። ሁሉም አካባቢ ሰላም ነው፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...