ከሁለት ዓመት በፊት በኬንያ በተከናወነው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያዊቷ ሚዛን ዓለም 5,000 ሜትር ማሸነፍ ችላ ነበር፡፡ አሁን በ21 ዕድሜዋ ላይ የምትገኘው አትሌት ስለእሷ እምብዛም የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡ በበርኒንግሃም የቤት ውስጥ 3,000 ሜትር ፍፃሜ ጉዳፍ ፀጋይን በመከተል ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ግን የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በአንፃሩ እምብዛም ያልተወራላትና በጥቂት ውድድሮች ላይ ስኬታማ መሆን የቻለችው የነገዋ ተስፋ ሚዛን፣ እሑድ ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በእንግሊዝ በተከናወነ የዓለም አኅጉራዊ የዙር የብር ደረጃ 10 ሺሕ ሜትር ውድድር 29፡59፡03 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ በግል ምርጥ ሰዓቷን ከማስመዝገቧ በላይ ከ30 ደቂቃ በታች የገባች 12ኛዋ የዓለም ምርጥ ሰዓት ባለቤት መሆን ችላለች፡፡ ሚዛን ቀድሞ በ10 ሺሕ ሜትር ከነበራት የግል ምርጥ ሰዓት በሦስት ደቂቃ ማሻሻሏ ተጠቅሷል፡፡ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ሀዊ ፈይሳ 31፡09፡85 በመግባት አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡