Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምከአራት ትሪሊዮን ዶላር በላይ ውድመት ያደረሰው የአየር ንብረት ለውጥ

ከአራት ትሪሊዮን ዶላር በላይ ውድመት ያደረሰው የአየር ንብረት ለውጥ

ቀን:

የዓለም ሙቀት መጨመር በመሬት ላይ ያለውን የአኗኗር ዘይቤ ማዛባት ከጀመረ ከአምስት አሥርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም ችግሩ በጣም እየጎላና ትኩረት ያገኘው ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ በጤና፣ በግብርና፣ በደኅንነት፣ በሥራና በተለያዩ ዘርፎች ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም ስትራቴጂ በተለያዩ አገሮች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ ቢሆንም፣ ችግሩን መቀልበስ አልተቻለም፡፡ በተለይ ለደሃና በማደግ ላይ ላሉ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ሆኗል፡፡

የአየር ንብረት ለውጡ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ለሁለት ሚሊዮን ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑንም የተባበሩት መንግሥታት የሚቲሪዮሎጂካል ድርጅት (ደብሊው ኤምኦ) ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት አስፍሯል፡፡

የተዛባ የአየር ንብረት ለውጥ ባለፉት ሀምሳ ዓመታት ውስጥ የሁለት ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚው ላይም ከ4.3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ውድመት አስከትሏል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1970 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ 11,778 አደጋዎች የደረሱ ሲሆን፣ በአደጋዎቹ ከደረሱ ሞቶች 90 በመቶ ያህሉ የተከሰቱት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ነው፡፡

‹‹የአየር ንብረት ለውጡ እያስከተለ ባለው ችግርና ተያያዥ ጉዳቶች እየተጎዱ ያሉት የደሃ ደሃ የሚባሉት ሰዎች ናቸው፤›› ሲሉም የደብሊው ኤምኦ ኃላፊ ፔትሪ ታላስ አስታውቀዋል፡፡

ምንም እንኳን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችና የተጠናከረ የአደጋ ምላሽ አስተዳደር በሰዎች ላይ የሚደርሱ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን ለመቀነስ ቢያስችሉም፣ ከባድ አውሎ ነፋስና ጎርፍ በተለይ በድሆች ላይ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሱ መሆኑንም በባንግላዴሽና በማይናማር የተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ድርጅቱ እስከ 2021 ድረስ የነበረውን ሞትና ጉዳት አስመልክቶ ባቀረበው ሪፖርት፣ ከ1970 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የተከሰተ ሞት በመጀመርያዎቹ ዓመታት ከነበረው እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ከ1970 ጀምሮ ባሉት የመጀመርያዎቹ አሥር ዓመታት በዓመት 50 ሺሕ ሰው ያህል ይሞት የነበረ ሲሆን፣ ይህ ከ2010 በኋላ በዓመት ወደ 20 ሺሕ ዝቅ ብሏል፡፡

የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ ደግሞ የሞት ቁጥር እየቀነሰ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ በ2020 እና በ2021 ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በሚከሰት አደጋ የተመዘገበው የሞት ቁጥርም በድምሩ 22,608 ብቻ ሆኗል፡፡

የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዕቅድና ትግበራ የሚያመጣውን ለውጥ ተከትሎ፣ ተመድ እ.ኤ.አ. በ2027 ሁሉም የዓለም አገሮች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት እንዲኖራቸው ለማስቻል ዕቅድ ቢያስቀምጥም ሥርዓቱን የዘረጉት ከዓለም ግማሽ ያህሉ አገሮች ብቻ ናቸው፡፡

የኢኮኖሚ ውድመት

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚደርሱ አደጋዎች የሚከሰት ሞት ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ቢመጣም፣ በኢኮኖሚው ላይ ያሳረፈው አሉታዊ ጫና ከፍተኛ ነው፡፡ ድርጅቱ እንደሚለውም፣ በኢኮኖሚው ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት ከባድ ሆኗል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ እ.ኤ.አ. ከ1970 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ በኢኮኖሚው ላይ ያደረሰው ውድመት በሰባት እጥፍ ጨምሯል፡፡

በ1970ዎቹ የመጀመርያዎቹ አሥር ዓመታት በቀን የነበረው 49 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ፣ ከ2010 እስከ 2019 በነበሩት ዓመታት በቀን ግን 383 ሚሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ውድመት ተሸጋገሯል፡፡

የአየር ንብረት ለውጡ የሚያስከትለው ሞት በደሃ አገሮች ላይ የሚበረታ ሲሆን፣ ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ የሚመታው ደግሞ ሀብታም አገሮ ናቸው፡፡

ያደጉ አገሮች በአየር፣ ንብረትና ለውጥና በጎርፍ አደጋ ምክንያት በኢኮኖሚያቸው ላይ 60 በመቶ ኪሳራ ይደርሳል፡፡ ከአምስት ከተሰከቱ አደጋዎች አራቱ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ከ0.1 በመቶ ያነሰ መሆኑንም ድርጅቱ ገልጿል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮችን እየጎዳ ይገኛል፡፡ ዓለም ባንክ እንደሚለው፣ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች፣ ከደቡብ እስያና 140 ሚሊዮን ላቲን አሜሪካ ሕዝቦች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

የውኃ እጥረት፣ የግብርና ምርታማነት መቀነስና የውቅያኖሶች ውኃ መጨመር በአብዛኛው እይጎዳ ያለውም ደሃ አገሮችን ነው፡፡

ለአየር ንብረት ለውጡ ይህንንም ያህል አስተዋጽኦ የሌላቸው አገሮች ክፉኛ የሚጎዱ መሆኑን ተከትሎም፣ ሀብታም አገሮች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ስምምነት አድርገዋል፡፡ ሆኖም በተገባው ቃል መሠረት በወቅቱ ሲፈጸም አይስተዋልም፡፡ በኅዳር 2015 ዓ.ም. በተካሄደው የኮፕ 27 ጉባዔም ሀብታም አገሮች ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ አገሮች ለሚደርስባቸው ኪሳራና ጉዳት ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት መደረሳቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...