Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርወደ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት ጎዳና ለመግባት ለሀቅ መቆም ያስፈልጋል

ወደ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት ጎዳና ለመግባት ለሀቅ መቆም ያስፈልጋል

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ኢትዮጵያችንን በአንድ ወቅት ወደ ነበረችበት የሥልጣኔ አቅጣጫ እንድታመራ ለማድረግ፣ ለዳግማዊ መንሰራራትና ለዳግማዊ ህዳሴ በአዲስ መንፈስ መነሳሳት ይኖርብናል፡፡ የጠፋንና የተረሳን ዝና እንደገና ለመመለስ የሚደረገው ጥረትም፣ በሌላ አገላለጽ የተናጋውን ማኅበረሰብ ለማረጋጋት፣ የጎበጠውን አመለካከት ለማቅናት፣ ያፈነገጠውን ወደ መስመርና ሥርዓት ለማስገባት፣ ያረጀውን ለማደስ ወይም ለመጠገን፣ አዲስና ጤናማ ሕይወት ለመመሥረት፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን የሚያሳትፍ ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ ይህም በስፋቱና በሁለንተናዊነቱ ቃል ልንገባለት የሚገባ ህዳሴ የአንድነት መሠረቱ የጠበቀ፣ ሁሉንም  ኢትዮጵያዊ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካዊ አመለካከት በየትኛውም ጊዜና ቦታን ያለ ሁሉንም ሕይወት የምታቅፍ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

ከልደተ ክርስቶስ በፊት ከ563 እስከ 483 ዓመተ ዓለም የኖረው ልዑል ጉተማ ሲድሃራታ ቡድሃ ከፍተኛ ልዕለ መንፈሳዊ ደረጃ (ኒርቫና) ትክክለኛ አተያይ፣ ትክክለኛ ውስጣዊ ፍላጎት፣ ትክክለኛ አንደበት፣ ትክክለኛ ድርጊት፣ ትክክለኛ ማኅበራዊ አኗኗር፣ ትክክለኛ ጥረት፣ ትክክለኛ ግንዛቤ፣ ትክክለኛ ጥልቅ ዕሳቤ እንደሚያስፈልግ ያስተማረ ሲሆን፣ ሰላም እንዴት ሊመጣ እንደሚችልም ከ2500 ዓመት በፊት ‹‹ባዶ ከሆኑ በሺሕ በሚቆጠሩ ቃላት ከታጨቀ ግጥም፣ ሰላም የሚያመጣ አንድ ስንኝ ይበልጣል›› ሲል ያስገነዝበናል፡፡ ከጉተማ ቡድሃ 2300 ዓመታት ያህል ዘግይቶ ወደ እዚህች ዓለም የመጣውና ከ1833 ዓ.ም. እስከ 1896 ዓ.ም. የኖረው በኬሚስትሪ ሳይንስ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው፣ በመድረሱም የብዙ ምርምር ውጤቶች ባለቤት የሆነው አልፍሬድ በርናንድ ኖብል የሰላምን አስፈላጊነት እጅግ አጠንክረው ከተናገሩት ታልልቅ ሰዎች አንዱ ሲሆን፣ ዛሬ ‹‹የኖብል ሽልማት›› ተብሎ የሚጠራውን ዕውን እንዲሆን ያስቻለ ነው፡፡

ይህ ታላቅ ሰው የሰላምን አስፈላጊነት በሰፊው የተነተነ ቢሆንም፣ በተለይም ሰላም ከምንም ሊፈጠር አይችልም፡፡ ሰላም ማለት የሰዎች ጦርነት ገጠሙ አልገጠሙ ማለት አይደለም፡፡ በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ መከራቸውን የሚያዩ ሰዎች ዳቦ ወይም ሩዝ፣ መጠለያ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ እንዲሁም ሰብዓዊ ክብራቸው የሚጠበቅበት ነፃነት በመጎናፀፍ ትርጉም ያለውና ቀጣይነት ሕይወት እንዲኖሩ ማስቻል ነው›› ካለ በኋላ፣ ‹‹ለዘመናት ሲሰቃዩ፣ ሲራቡ የኖሩ፣ የተረሱ፣ የተጎዱ፣ የተጎሳቆሉ ሰዎች በአዲስ ሕይወት ውስጥ መኖራቸውን ሲያውቁ ያኔ ሰለም አለ ማለት ይቻላል›› በማለት ይገልጻል፡፡

በእርግጥም ‹‹የእኔን አመለካከት እንጂ የሌላውን አትመን፣ የእኔን ድርጅት አምልክ፣ የሌላው ሁሉ ፋይዳ ቢስ ነው…›› የሚል የግለኝነትና የጠባብነት ጣዖታዊ አስተሳሰብ በ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› አስተሳሰብ ካልተተካ በስተቀር የሰላም ነጋሪት ቢመታ፣ የመቻቻል እምቢልታ ቢነፋ፣ የፍቅር ዋሸትም ቢደመጥ፣ የአንድነት ክራር ቢደረደር ሰላም ደጋግሞ መደፍረሱና ሕዝብ ደጋግሞ መሸበሩ የማይቀር ይሆናል፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ›› መሆኑ ቀርቶ ‹‹የባሰ ሳይመጣ አገርህን ልቀቅ›› የሚያሰኝ የፖለቲካ ውዥንብር እየነፈሰ ነው፡፡ የአሁኑን ክልል በጎጥ ለመከፋፈል ስሜት አለ፡፡ መከፋፈሉን ከጠቀመ ይከፋፈል፡፡ በክልል መሆኑ ቀርቶ በዞን ይሁን፡፡ በዞንም ካልበቃ በወረዳ ይከፋፈል፡፡ ነገር ግን የሚከፋፈለው እንዴት ነው? በታሪክ ነው? በጀግንነት ነው? በእምቢተኛነት ነው? የተከለለበትን ክልል በመጥላት ነው? ግዛት ለማስፋፋት በመፈለግ ነው? በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ነው? ወይስ በምን? መልስ አይኖርም። መተራመስና ማተራመስ ግን ይኖራል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ አከላለል እንደ ዘመኑ፣ እንደ ባለሥልጣኑ አቅም እንደተፈጸመው ፖለቲካዊ ጋብቻ፣ እንደ ለሥልጣን አሥጊነቱ፣ ከአባቱ  እንደወረሰውና እንደ አገሪቱ መሪ ፍላጎት ነበር። ለምሳሌ ጃን አሞራ ዛሬ አንዲት በሰሜን ጎንደር የምትገኝ ወረዳ ናት፡፡ ቀደም ሲል ግን እስከ ሎጋ ሐይቅ የተዘረጋች ነበረች። በጃምድር ከቀይ ባህር መለስ ሱዳንን ጨምሮ ነበር። በጃ ምድርም ከበጌ ምድር ይለያል። የበለዎችና የዶብዓዎች ግዛትም ሰፊ ነበር። የአሁኒቱን ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲን፣ ኤርትራንና ሱዳንን ይጨምራል፡፡

ሌላውን እንተወውና ከአፄ ቴዎድሮስ ወዲህ ያለው አከላለል ይለያያል። ከእነዚህም የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሸዋን ብንወስድ የልዑል ራስ መስፍን ስለሺ ግዛት በምዕራብ እስከ ጊቤ በሰሜን ምዕራብ እስከ ዓባይ፣ በደቡብ እስከ ሐዋሳ ከተማ ድንበር፣ በሰሜን እስከ ጨፋ ድንበር (ወንዙን ረሳሁት)፣ በምሥራቅ እስከ አዋሽ ነበር፡፡ ለራስ መስፍን ስለሺ ጂማም ተጨምሮላቸው ነበር። ደርግ ደግሞ ሸዋን በአራት ሸነሸነው። ስለዚህ ይከለል የነበረው በሹሙ ታማኝነት፣ ለዘውዱ ቀራቢነት፣ ለፀጥታው አመቺነት፣ በተፈጸመ ፖለቲካዊ ጋብቻ፣ ወዘተ ወዘተ ነበር። በዚህ የታሪክ ሒደት የሕዝብ እንቅስቃሴ ነበር። ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ፣ ወይም ከተቃራኒው በመንቀሳቀሱም የሕዝብ ውህደት ተፈጽሟል። ማኅበራዊ ውህደት ተከስቷል፡፡ የባህል ውርርስ አለ።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በዛ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ባላቸው አገሮች የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነት፣ የሥነ ባህርይ፣ የኢኮኖሚ ትስስርና የንብብርነት ሊኖር እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ሒደት የአንዱ ወይም ከአንድ በላይ የሆነ ቋንቋው፣ ባህሉ፣ ሥነ ባህርይው፣ የኢኮኖሚ የበላይነቱ ወይም ጎላ ብሎ የመውጣቱ፣ የማደጉ የመኮስመኑ፣ የመክሰሙ ሁኔታም ይኖራል፡፡

በአንድ አገር የሚገኝ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሥነ ባህርይ፣ የኢኮኖሚ ትስስር ብቻ ሳይሆን የአጎራባች ወይም የድንበር ዘለል አገሮች የቋንቋ፣ የባህል፣ የሥነ ባህርይ፣ የኢኮኖሚ ትስስር እንደ ሁኔታው ተፅዕኖ እንደሚደርስበት ዓለማችን ያለፈችበት ታሪክ ያሳየናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጆርጅ ቤርናንድ ሾ (1856 እስከ 1950 ዓ.ም.) ‹‹ፒግማሊየን›› በሚል ርዕስ ለመድረክና ለኅትመት ያበቃውን ድራማ መጥቀስ ይቻላል፡፡

የዚህ ድራማ መልዕክት የሚያጠነጥነው የነጠረ እንግሊዝኛ ማለትም የቤተ መንግሥቱ አካባቢ እንግሊዝኛ ዘዬ ለመናገር የሚደረገውን ጥረት በሚያመለክት ነው፡፡ አዎን በየአገሩ የቤተ መንግሥት ዘዬ መናገር እንደአስፈላጊ ጉዳይ ይወሰዳል፡፡ ኢንግላንዳውያን ደቾችን እንደ ጥሩ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች አያዩዋቸውም፡፡ አፍሪካውያንን አሜሪካውያንንም ከአውሮፓ የሚመጡ እንግለዝኛ ተናጋሪዎች አይሰሟቸውም ብለን በጨዋ አቀራረብ እንግለጸው፡፡ እኛም ፈረንጅ ቋንቋችንን ሲናገር እንደዚሁ፡፡ ይህ ጥንትም የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡

የጠራ ዘር ለማምጣት የሚያድር ምኞት ግን ከአደጋዎች ሁሉ የከፋ አደጋ ነው፡፡ ጽዮናዊነትን (ሞአ አንበሳ ዘዕምነገደ ይሁዳ እንዲሉ) እና የእነ ጋዳፊና መሰሎቻቸው ጠባብ ዓረብነትም ከዚህ ጋር ማየት ይገባል፡፡ ስለሆነም የጎረቤት ግጭት ከቤተሰብ ይጀምርና እስከ ዓለም አቀፍ ድንበር ይደርሳል፡፡ በዚህም መሠረት በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች በድንበር አካባቢ የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነት፣ የሥነ ባህርይ ልዩነት አለ፡፡ ይልቁንም በአንድ ወቅት ብዙ አገሮችን በአንድ ላይ አድርጋ ስትገዛ የነበረችው አገራችን፣ በሌላ ወቅት ደግሞ በዘመነ መሳፍንትና በሌሎችም ዘመናት ተበታትና ስለነበር፣ በዚህ ምክንያት የሚመጣ የልዩነት ችግር ይኖራል፡፡ ገዥዎች አስተዳደራቸውን ሲያዋቅሩ ለአገዛዝ በሚያመቻቸው መንገድ ሲከልሉ የሚያስከትሉት ልዩነትም
ይኖራል፡፡ በየትኛውም አገርና ሥፍራ ደግሞ ምሉዕ በኩለሄ የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ የአገራችን የክልልም ሆነ የዞን፣ የወረዳም ሆነ የቀበሌ አከላለል ብዙ የሚቀረው ስለሆነ ወደፊት በሒደት የሚስተካከል ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡

ስለዚህ ከጉርብትና ጋር የተያያዘ ችግር በተለያዩ አካባቢዎችና አገሮችም የሚኖር ዕድሜ ጠገብ የጭቅጭቅና የውዝግብ መንስኤ በመሆኑ፣ እንዲህ ያለው ችግር መከሰቱ አይቀርም፡፡ መፍትሔው ለአንድ ወይም ለሌላ ዓላማ ሲባል ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማጋጨት፣ የጎሪጥ እንዲተያይ መገፋፋት፣ የሌለ ችግር መፍጠር ሳይሆን፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተሞላበትን የጋራ መፍትሔ መሻት፣ ማምጣት፣ መላ መምታት፣ መመካከር ነው፡፡ አሉታዊ አመለካከት ግፊቱ ምን እንደፈጠረና የአንዳንድ ግልፍተኛ ስሜትን በመንካት ጎጂ እንቅስቃሴ እንደዳረገም ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡

በጎልማሳነት ዕድሜ ከሚገኝ ሰው በተለይም ሕግ ካጠና ምሁር የሚጠበቀውም ይህ ነው፡፡ ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ ተነስተን ስንመለከተው በአገራችን በብዙ አካባቢዎች ኩሻውያን፣ ኦሟውያንና ሴማውያን እየተፈራረቁ ኖረዋል፡፡ ከኩሻውያን ውስጥም አገዎች፣ አፋሮች፣ ኦሮሞች፣ ሶማሌዎች፣ ሲዳማዎችና ሐዲያዎች ይገኙበታል፡፡ ሴማዊነት ደግሞ አማሮችን፣ ትግሬዎችን፣ አርጎባዎችን፣ ሐረሪዎችን፣ ሥልጤዎችን፣ ጉራጌዎችን (በከፊል) እና ጋፋቶችን (የሉም) ይጨምራል፡፡

ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በአካባቢው በመኖራቸው ምክንያት የአካባቢው ነዋሪ የእነዚህን ብሔር ብሔረሰቦችን ቋንቋ፣ ባህል፣  እምነት፣ ሥነ ባህርይ መያዙ እርግጥ ነው፡፡ የረዥም ጊዜ ታሪኩም የዚህ ነፀብራቅ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡

በመሠረቱ ቋንቋ እንደ ባህል ሁሉ እንደ ጊዜውና እንደ ሁኔታው በልዩ ልዩ ተፅዕኖዎች የሚያድግ፣ የሚለወጥ፣ ቋንቋዎች ከጎረቤቶች ጋር በሚፈጥረው ግንኙነት፣ በንግድ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሃይማኖት ምክንያት የሚዳቀል በሌሎች ቋንቋዎች ተፅዕኖ ምክንያት ቅርፁን ሳይቀር የሚቀይር እንጂ ራሱ ፀንቶ የሚቆም አይደለም፡፡ ቋንቋ እንደ ሁኔታው ሊያድግ እንደሚችለው ሁሉ ሊጠፋም ይችላል፡፡ በአውሮፓ፣ በእስያና በአሜሪካ በዚህ ምክንያት የተወራረሱ፣ የተቀያየሩ፣ ያደጉና የቀጨጩ ቋንቋዎች አሉ፡፡ በዚህም ሰበብ ድርብርብ ማንነት ይፈጠራል፡፡

ድርብርብ ማንነት በአንድ ቤት፣ ጎረቤት፣ ሠፈር፣ ቀበሌ፣ በክልል፣ በአገር፣ በአኅጉርና በዓለም ልንመለከተው እንችላለን፡፡  ለምሳሌ አንድ አውራጃ ወይም ዞን በቀጥታ በፖለቲካዊ ሒደት ተገዶ በመገበርም ሆነ በጉርብትና የትግርኛ፣ የአማርኛ፣ የአገውኛ፣ የኦሮምኛና የአፋርኛ ማንነት እንደ ወቅቱ ጎልቶ ሲወጣና ሲከስም በታሪክ ሊከሰት ይችላል፡፡

በመጀመሪያ የኩሻውያን የበላይነት ገኖ በነበረበት ከ2000 ዓመታት በፊት፣ ኩሽኛ የኩሽ ዘመን በሳባውያን በተተካ ጊዜ ደግሞ በሳብኛ፣ በአግአዚያን ዘመን ግዕዝ፣ በዛጉዌ ዘመን አገውኛ፣ በሸዋ ሰለሞናውያን ዘመን አማርኛ፣ በኦሮሞ ዘመን ኦሮምኛ፣ ከዘመነ መሳፍንት እስከ ዛሬ ደግሞ ትግርኛ ሊስፋፋ ይችላል፡፡ ከእነዚህም ቋንቋዎች አንዱ በአንድ ወቅት የበላይነትን ሲያገኝ የአውራጃው ሕዝብ በአብዛኛው ሊናገረው ይችላል፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ሥርዓት ለመቶ ዓመታት ገኖ በነበረበት ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ እስከ አራ ድረስ፣ በምሥራቅ፣ በምዕራብና በደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ በጥናት መቅረብ ያለበት ሰፊ ግዛት ውስጥ የነበረውን ቋንቋ በመተካት የሕዝቡ መነጋገሪያ ቋንቋ ሆኗል፡፡

በዚህም መሠረት ዛሬ ኦሮሞዎች ከሚባሉት ብዙዎቹ አፋር፣ ሶማሌ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህ ዓይን ሲታይ አገውኛም አፋርኛም በየዘመናቸው ገነው ነበር፡፡

በመሠረቱ ቋንቋ ሊቃውንት እንደሚነግሩን ምንም እንኳን በከፍተኛ ጥረት ዕድሜያቸውን የሚያራዝሙ ቋንቋዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ፣  ከ30 ዓመታት በኋላ 6,000 የሚያህሉ የዓለም ቋንቋዎች እንደሚጠፉ ሲተነብዩ፣ በእነዚህ ሊቃውንት ግምት መሠረት ጥቂት ደርዘን ቋንቋዎች ብቻ ለመኖር ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ ሚሸል ራውስ (Michael Krauss) የተባሉ በአላስካ የአካባቢ ቋንቋ ማዕከል ተመራማሪ በ2100 ማለትም ከ80 ዓመታት በኋላ፣ ከዓለም ቋንቋ 90 በመቶ ያህሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናል፡፡ በእኚህ ተመራማሪ ትንበያ መሠረት በዓለም ካሉ ቋንቋዎች ውስጥ ከአምስት በመቶ እስከ 10 በመቶ ያህሉ ብቻ አንድም መንግሥታዊ ወይም ብሔራዊ ቋንቋዎች ይሆናሉ፡፡

ስለዚህ የብሔራዊ ዕርቅን ጽንሰ ሐሳብን ጉዳይ ስናነሳ ‹‹ኢትዮጵያ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ ብትለያይም አንድ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ልዩነት በአንድነት ላይ የተመሠረተ ነው›› ከሚል መሆን ይኖርበታል እንጂ፣ አንዱ ተነስቶ ሌላው በደለኝ ቢል ፋይዳ የለውም፡፡ በመሠረቱ ቋንቋ ወይም ባህል በራሱ ጨቋኝ አይደለም፡፡ የጨቋኝ ቋንቋ የሚባለውም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡

ስለሆነም እንደ ጂን ኤቺሰን (2003)፣ ‹‹የኅብረተሰብ ሥነ ልቦናንና የቋንቋ መለዋወጥ››፣ ሄኒንግ አንደርሰን (1988)  ‹‹ቋንቋ መለያ ጠርዝ፣ እንደ አመቺነቱ መጠቀም፣አንዱ በሌላው ላይ መስረፅና ሥርጭት››፣ እነ ጀይ ፊሲያክ ‹‹የሥነ ልሳን ጥናት ከአገርና ከሕዝብ አንፃር››፣ ሬይሞ አንቲላ (1989) ‹‹ስለታሪካዊ ንፅፅራዊ ሥነ ቋንቋ››፣ ቻርለስ ጀይ ኬይ ‹‹ስለቋንቋ ልዩነትና መለወጥ፣ ዊልያም ክሮፍት (2000)››፣ ሩዲ ኬለር (1994)፣ ሀንስ ኤች ሆክ 1992)፣  ዊልያም ላቫሮቭ (2001)፣ ሮጀር ላስ (1987)፣ ኤፕሪል ኤስ ማክማሆን (1994)፣ ጀምስ ሚልሮይ (1992)፣  ጆሀና ጀይ ኒኮላስ (1992)፣  ኤድዋርድ ሳፓየር (1921)፣ ወዘተ ስለቋንቋ መለዋወጥ የሰጡትን ትንታኔ ብንመለከት ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ እምብዛም ፋይዳ እንደሌለው እንረዳለን፡፡

የዕርቀ ሰላም ንድፈ ሐሳብ ስለሰላም ስለተዘመረ ሰላም አይኖርም

ሰዎች ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ፣ ቀን ከሰዎች ጋር ሲገኙና ሌሊት ለመተኛት ጋደም ሲሉ የሰላም ቀንና ሌሊት እንዲሆንላቸው ይመኛሉ፡፡ ሰላም የሠፈነበት ቀንና ሌሊት ከሁሉም ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ ነውና፡፡ በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖርና መቻቻል ዛሬም ወደ ፊትም አስፈላጊ ናቸው፡፡ የዕድገታችን ቁልፍ የሚገኘው እዚህ ውስጥ ነውና! ዳሩ ግን፣ ‹‹ስለሰላም የሚሟገቱትን ፀረ ሰላም፣ ስለዴሞክራሲ የሚታገሉትን ፀረ ዴሞክራሲ፣ ስለፍትሕ የሚናገሩትን ፀረ ፍትሕ፣ ስለእኩልነት የሚሞግቱትን ፀረ እኩልነት›› እያሉ በመፈረጅና በማጥላላት ስለሰላም ቢዘፈን፣ ስለሰላም ቢነገር፣ ስለሰላም ቢሣል፣ ስለሰላም ቢገጠም ጥሩ ቢሆንም ሰላምን አያስገኝም፡፡ የሚነገርለት ዴሞክራሲም፣ ፍትሕም እኩልነትም ፈጽሞ ዕውን ሊሆን አይችልም፡፡

ስለዚህ በእርግጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሠፍን ከተፈለገ፣ የፖለቲካው ምኅዳሩ ከዚህ ደፋቂ አዙሪት መውጣት ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለንበት ታሪካዊ ወቅት ዕርቅ፣ መግባባትና አንድነት ሲባል ምን ማለት ነው? ምንስ ዓይነት ቅርፅና ይዘት ይዞ ተከስቷል? እንዴትስ ነው በተግባር የምናውለው? ችግሩን እያድበሰበስነው እንኖራለን ወይስ አንድ በአንድ ፈትሸን መፍትሔ እንዲያገኝ እናደርገዋለን?

የዕርቀ ሰላም ንድፈ ሐሳብ፣ ተቃራኒ አጽናፋትን ረግጠው የቆሙ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ እውነታዎችን ለማቀራረብ የሚጠቅም ጥንታዊና ዘመናዊ መልክ ያለው የብልሆች መሣሪያ ነው፡፡ ዕርቅም በሁለትና ከሁለት በላይ የሆኑ ኃያላን፣ ወይም በአንድ ኃያልና ለነፃነታቸው ቆርጠው በተነሱ በብዙ ደካሞች፣ ወይም በደካሞች መካከል
ሊካሄድ ይችላል፡፡ ስለሆነም ዕርቅ ወደ ፀብ ያመሩ የተለያዩ አመለካከቶችን አቻችሎ፣ አግባብቶና አስማምቶ በአንድ ላይ ለጋራ ዓላማ እንዲሠሩ ያስችላል፡፡

ዛሬ በአገራችን የሚታየው የዕርቅ ገጽታ ሦስት መልክ ሲኖረው፣ አንደኛው በብሔራዊ ዕርቅ ሁለተኛው በታሪካዊ ዕርቅ፣ ሦስተኛው ደግሞ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ የተከሰተው ‹‹ለአገሪቱ የሚበጃት ብሔራዊ መግባባትና አንድነት የሚያመጣ ዕርቅ ነው›› ወይም ‹‹የኢትዮጵያን አንድነት ለማምጣት የሚቻለው በብሔራዊ መግባባት ነው›› የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መሥፈን የሚበጀው የትኛው ነው? ጉዳዩ መሠረታዊ ስለሆነ፣ ሕዝብም የማወቅ መብት ስላለው አንድ በአንድ እንመልከተው፡፡

ይልቁንም አንዱ ኃያል ሲነሳ ሌላውን አስገብሮ ለተወሰነ ጊዜ ሲኖር የሚፈጥረው ውህደት ማንነቱን የበለጠ እንዲዳብር አድርጎታል ብሎ ያምናል፡፡ በመደምደሚያም ‹‹ስለዚህም ግጭቱ የተፈጠረው ባለፉት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ አንዳቸውን ከሌላቸው ጋር ያዋሰባቸውን፣ ያዳቀላቸውን፣ ያዋሀዳቸውን፣ ያስማማቸውን፣ ወዘተ ቋንቋዎች መሠረት በማድረግ በተመሠረተው ፌዴራሊዝም ሥርዓት ምክንያት ስለሆነ፣ ይህ ሕዝብ በልዩነት ላይ በተመሠረተ አንድነት አስተሳሰብ ምክንያት የተበታተነውን ሕዝብ ወደ አንድነቱ እንዲመለስ ብሔራዊ ዕርቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡›› ይላሉ፡፡

የብሔራዊ ዕርቅ ፈላጊዎች ማንነት ጅምላዊ ዳሰሳ

የብሔራዊ ዕርቅ አመለካከት ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት ኢዴሞክራሲያዊ፣ ዘረኛ፣ ጠባብ፣ ወዘተ በመሆኑ መወገድ አለበት›› ከሚል የመነጨ ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማውም በብሔራዊ ዕርቅ አስተባባሪው አማካይነት የሽግግር መንግሥት በማቋቋም ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና ማኅበረሰቡን እንወክላለን የሚሉ ኃይሎች የሚሳተፉበት ሕዝባዊ መንግሥት መመሠረት ነው፡፡ ምንም እንኳ የብሔራዊ ዕርቅ አራማጆች ሐሳብ ቀደም ሲል የተጠቀሰውን ቢመስልም፣ ‹‹እንዴት ነው የሚመሠረተው?›› የሚለው ቴክኒካዊ እንጂ ሜካኒካዊ ባለመሆኑ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ኖረች አልኖረች አንዳችም ደንታ የማይሰጣቸው ሰዎች  በኩል ደግሞ ከፍ ያለ ሰንደቅ ይዘው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በሚያቀነቅኑበት፣ ከእነዚህም ጋር  ባሉት ሁኔታ የኢትዮጵያ ዋነኛ በሽታ የታሪክ መቃወስ፣ የታሪክ ሸፍጥ፣ የታሪክ ቅሚያ፣ የታሪክ ሽሚያ፣ የታሪክ ሕመም ወይስ በብሔራዊ ዕርቅና ድርድር የሚወገድ ቀላል ችግር ነው? ብሔራዊ ዕርቅ በአገሪቱና በሕዝቧ ውስጥ ሥር ተከል ለውጥ የሚያመጣ ወይስ ራስ ምታትን ለማስታገስ ከሚወሰድ ባህላዊም ዘመናዊም መድኃኒት ያልተለየ ፈውስ?

የታሪክ ዕርቅ ምንነትና ተግባራዊነት

የታሪክ ዕርቅ የምንለው ምንድነው? ታሪክን በተፈጸመበት ጊዜ እንደሆነው፣ እንደተደረገው አድርጎ ሀቁን በመቀበል ያን ታሪካዊ ክስተት በበጎም ይሁን በመጥፎ መልኩ በመቀበል በጥሩ መደሰት በመጥፎ ደግሞ እኩል ማዘን ሲሆን፣ ‹‹የእኔ ትክክል ነው፣ ያንተ ግን ስህተት ነው›› በሚል ኅብረተሰብ መካከል እንዲህ ያለውን ሀቅ መቀበል በእጅጉ አስቸጋሪ ነው፡፡

የታሪክ ዕርቅን ዕውን ለማድረግ ግን መተማመንና የፈረሰውን መንፈሳዊ፣  ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ በጋራ ለመገንባት ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት፣ በጠላትነት ሲፈራረጁ የነበሩት ዜጎች በጋራ አገራቸውን አብሮ ለመገንባት የሚያስችል ራዕይ ይዘው ለመጓዝ መዘጋጀት ማለትና በተግባር መፈጸም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው በደቡብ አፍሪካ በማንዴላና በዘረኛው የደቡብ አፍሪካ መካከል የተከናወነው የታሪክ ዕርቅ ነው፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካም እጅግ የመረረ የዘር አድልኦ ስለነበር፣ አንዱ በሌላው ላይ ‹‹አስከፊ›› የሚለው ቃል የማይገልጸው የእርስ በርስ ጥላቻ ነበር፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ፣ በሰሜን ቬትናም፣ በካምቦዲያ፣ በጃፓን መካከል ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል ተብሎ የሚታሰብ የታሪክ ጠባሳ ነበር፡፡ ዛሬ በተደረገው ጥረት የተሻለ በመሆን ላይ ነው፡፡

ለመሆኑ ታሪካችንስ ተጣልቷል? አዎን፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየዩ ምክንያቶች የተካሄደው ጦርነት ኢትዮጵያውያን በክፍለ ሀገር፣ በወንዝ፣ በተራራ፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ ከፋፍሎ የጦርነት ዓውድማ አድርጓታል፡፡ አንዱ ጀግና የጦር መሪ በአንድ አካባቢ ሲፈጠር ሌላውን አካባቢ በሰላማዊም ሆነ ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ በማስገበሩ፣ በመግዛቱ፣ ሕዝቡን ባሪያ አድርጎ በመሸጡ እርስ በርስ ሲቋሰል ኖራል፡፡ በዚህም ምክንያት ሁሉም አንድም ከራሱ ጀግና ወጥቶ እንዲገዛለት ይፈልጋል፣ ካለዚያ አልገዛም ብሎ ይሸፍታል፡፡ ሸፍቶም አንዱ የሌለው ጠላት ይሆናል፡፡

የአክሱም መንግሥት በዛጉዌ፣ የዛጉዌ መንግሥት በሰለሞናውያን በደም መፋሰስ መተካቱ ብዙ ስለሚያስብለን ለጊዜው እናቆየውና ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ለመግዛት ከተነሱት አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስና አፄ ምኒልክ ወዲህ ያለውን ታሪካችንን ብንመለከት ሕዝባዊ የታሪክ ዕርቅን የሚጠይቅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከጎንደር መሪ ቢነሳ ‹‹እንደምን ጎንደሬ ይገዛናል፣ ከትግራይ መሪ ቢነሳ እንደምን ትግሬ ይገዛናል፣ ከሸዋ ቢነሳ እንዴት ሸዌ ይገዛናል፣ ከኦሮሞ ቢነሳ እንደምን ኦሮሞ ይገዛናል?›› የሚል ጠባብ አስተሳሰብ እስካለ ድረስ፣ አገራችንን መበታተን እንጂ አንድ ልትሆን አትችልም፡፡ ለመሆኑ ጠባብነት ምንድነው? እንዴትስ ድል እናደርገዋለን?

ለታሪካዊ ዕቅር ጠባብነትን ተዋግቶ ድል ማድረግ፣ ስለስሜታዊነት የሚለው ቃል ከራሳቸው በስተቀር የተለያዩ አስተሳሰብ፣ አካሄድ፣ ፍልስፍና፣ አስተምህሮት ያላቸውን ባለመቀበል፣ በመጥላት፣ በማጥላላት፣ በዚህም ምክንያት በሚቻል መንገድ ሁሉ ተቀባይነት እንዳያገኙ ተፅዕኖ በማሳደር በአንደበት፣ በገጽታ፣ በድርጊት፣ በጽሑፍ፣ የሚገለጥ ባህርይ ነው፡፡ ይህም ስሜታዊነት በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ሲሆን አንዱ ጠባብነት ነው፡፡ ጠባብነትን ደግሞ ቢገትሪ (Bigotry) ለሚለው ቃል በአማርኛችን ተመሳሳይ ትርጉም ብንሰጠው ጽልመታዊ፣ እቡይ፣ አልኩ ባይ፣ ተመፃዳቂ፣ ‹‹ከእኛ በላይ ጎራሽ ማድ አበላሽ›› የሚል አዋራጅ፣ ክብርን የሚነካ፣ በራሱ ጠባብ አመለካከት የታጠረ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል የማያውቀውን አውቃለሁ፣ የማያደርገውን አደርጋለሁ የሚል አስመሳይ፣ በተገኘው አጋጣሚ የሚጠቀም ልንለው እንችላለን፡፡

አሜሪካውያን ደግሞ ከነጮች ወይም ከጥቁሮች የዘር ጥላቻ ጋር አጥብቀው ያያይዙታል፡፡ እኛ ደግሞ ከጠባብ ብሔርተኝነት፣ ከጎጠኝነት፣ ከሻጉሬነት (ከእኔ ሌላ ሃይማኖት ለቅስፈት ባይነትና ሃይማኖት አጥባቂነት) ጋር እናያይዘዋለን፡፡ ‹ቢገትሪ› የሚለው ቃል ‹ጠባብነት› ብለን ከወሰድነው ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ ‹በሐሳቡ ግትር የሆነ፣ ወይም የራሱ አመለካከት ከሌላ አመለካከት ጋር አቻችሎ ለማካሄድ ፈቃደኛ ያልሆነ፣ የራሱን እንጂ የሌላውን አመለካከት፣ ሐሳብ፣ ዕውቀት፣ ፍልስፍና፣ ሽምግልና፣ ወዘተ የማይቀበል አንድን ወገን፣ ቡድን፣ ዘር፣ ሃይማኖትን፣ ወዘተ አጉልቶ ሌላውን የሚጠላና የሚያጥላላ፣ የመቻቻል ስሜት የሌለው፣ የእኔ ነው የሚለው ሐሳብ ትክክል ባይሆንም እንኳን የሌላውን ላለመቀበል ድርቅ ያለ፣ ‹ድርቅና› በሚለውም
ይተረጎማል፡፡ እኛ ‹ጠባብነት› ያልነውን ‹ቢገትሪ› ‹አክራሪነት›፣ ‹ጽንፈኝነት› በማለት ስለሚተረጉሙትም ይህንንም ሐሳብ ያካትታል፡፡ እነዚህ ደግሞ ለሰላም መደፍረስና የኹከት መከሰት መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ቀደም ሲል የቀረበው ሰፋ ያለ ትንታኔ አንባብያን በተለይም ወጣት አንባብያን ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ ሲሆን ጸሐፊው ስሜታዊነት፣ ሐሳበ ግትርነት፣ ወይም የራሱን አመለካከት ከሌላ አመለካከት ጋር አቻችሎ ለማሳኬድ ፈቃደኛ ያልሆነ፣ የራሱን እንጂ የሌላውን አመለካከት፣ ሐሳብና ዕውቀት፣ ፍልስፍና፣ ሽምግልና፣ ወዘተ የማይቀበል አንድን ወገን፣ ቡድን፣ ዘር፣ ሃይማኖትን፣ ወዘተ እንጂ ሌላውን የማይቀበል፣ ሌላውን የሚጠላና የመቻቻል ስሜት የሌለው፣ የእኔ ነው የሚለው ሐሳብ ትክክል ባይሆንም እንኳን የሌላውን ላለመቀበል ድርቅ የሚል ድርቅና  ከሆነ ያለ ምንም ጥርጥር የአዕምሮ እንከን መሆኑን፣ የአዕምሮ እንከንነቱንም ካገኘው መረጃ በመነሳት ከመግለጹ በፊት ግን ስለጠባብነት አንዳንድ መገለጫዎቹን አስቀድሞ ለማቅረብ ይወዳል፡፡

የሥነ ባህርይ ምሁራን ጠባብነት፣ ራስ ወዳድነት፣ ትምክህተኛነትና ከዚህ ጋር የተያያዘው ጥላቻ የአዕምሮ በሽታ መሆኑን ባደጉት አገሮች እየመሰከሩ ነው፡፡ በዚህም ረገድ ከፍተኛ ጥናቶችና ምርምሮች እየተደረጉ ነው፡፡ በእነዚህ ተመራማሪዎች መሠረት፣ አንጎላችን በብዙ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ኒሮን በተሰኙ መልዕክት የማስተላለፊያ መስመሮች የታጨቀ ነው፡፡ ቁጥሩን ብዙ ተመራማሪዎች ‹‹የትየለሌ ወይም ለመቁጠር የሚያዳግት ነው›› ይሉታል፡፡ በእነዚህም መልዕክት አስተላላፊ መስመሮች አማካይነት የሚመጣለትን መልዕክት አንጎል ከሰውየው  ዕድገት፣ ልምድ፣ ባህል፣ ወዘተ አኳያ ይተረጉማል፡፡ መጥፎና ጥሩ የሚባለው ነገርም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡  ለምሳሌ አንድ ሰው ብሶት፣ ጭንቀት፣ ናፍቆት፣ መከፋት፣ ወዘተ የመሳሰሉ ችግሮች ካሉበት በኒውሮኖች አማካይነት የሚመጣለትን መልዕክት የሚተረጉመው ከዚህ በመነሳት ሊሆን ይችላል፡፡

ስለሆነም አንጎል አንዳች ቀርፆ ያስቀመጠው ግንዛቤ ከሕይወት ልምድ፣ ከትምህርት ቤት፣ ከተረቶች፣ ከሃይማኖቶች፣ በአካባቢው ከሚነገሩ ተረትና ምሳሌዎች፣ ከታሪካዊ ባህላዊ እሴቶች፣ ወዘተ… ተቀርፀው የተቀመጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህም የተቀረፁ ነገሮች አንዳች ነገር ሲፈጠር አንጎል በቅጽበት ይተረጉምና አንዳች ውሳኔ እንድንወስን ያደርገናል፡፡

አብርሃም ሊንከን (ከ1809 እስከ 1864) የተባሉ አሜሪካዊ መሪ፣ ‹‹ይህችን የአንድነት መርከብ ከመስመጥ ከላዳናት በስተቀር ሌሎች ሰዎች በሌላ ጉዞ ይዘዋት ሊሄዱ አይችሉም፡፡ ይህች አገር ከመላው ተቋማቷ ጋር የሚኖርባት ሕዝብ እንጂ የማንም አይደለችም፡፡ ስህተት፣ ስህተት መስሎ ሲሰማኝ ለማረም ጥረት አደርጋለሁ፡፡ አዲስ ሐሳብም ትክክለኛና በተግባር ሊውል የሚችል ሆኖ ሳገኘው እጠቀምበታለሁ፡፡ …ሁሉም ሕዝብ ነፃ ይሁን የሚለው አመለካከቴን ግን ምን ጊዜም ሊያሻሽለው አልችልም፡፡›› ያሉት አብርሃም ሊንከን፣ ‹‹የምንጨቃጨቅበት ትክክለኛ ጊዜ መኖር ካለበት ያ ጊዜ ያለ ጥርጥር አሁን አይደለም፡፡ ዛሬ የምናሳልፈው እጅግ አስቸጋሪ ፈተና የሚቀጥለው ትውልድ እንድንከበርም እንዳንከበርም ሊያደርገን ይችላል፡፡ ዛሬ እኛ ለአገሪቱ የግዛት አንድነት ቆመናል ብለናል፡፡›› በማለታቸውም ይጠቀሳሉ፡፡

ወቅታዊ ግጭትና ጠባብነት ዛሬ አገራችን አንድን ብሔር ወይም ብሔረሰብ በስመ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ወንድማማችነት፣ ወዘተ ማጥላላት፣ ታሪኩን ማጠልሸት፣ ምንም ዓይነት አቅም የሌላቸውን ዜጎች በጠላትነት መፈረጅ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እንደሆነ በሕገ መንግሥትም፣ በሕግም ተረጋግጧል፡፡ በዚህም መሠረት አገሪቱ በቋንቋ የተመሠረተ (ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ) ፌዴራል መንግሥት አቋቁማለች፡፡ ይህም ማለት ሰባት ትውልድ የሚቆጥር እዚያው አካባቢ መወለዱን የሚቆጥር ሳይሆን፣ በሕገ መንግሥቱ በተጠቀሰው መሠረት በዚያ አካባቢ የኖረና ቋንቋውን የሚናገር ማለት ነው፡፡

ሆኖም ይህ ጉዳይ ተወሳስቧል፡፡ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን መሆኗ ማስረዳት ቀላል አልሆንም ብሏል፡፡ ዜጎቿ የትም ሠርተው የመኖር መብታቸው በወቅታዊ ጠባብነት ስሜት ተገርስሷል፡፡ አንዱ ብሔረሰብ የሌላው ጠላት ሆኗል፡፡ ነገሩ ‹‹ከክልላችን ውጡልን›› ከማለት አልፎ መኪኖች ወደ እዚህ ክልል እንዳያልፉ ተብሏል፡፡ መኪኖችም ተቃጥለዋል፡፡

በመሠረቱ አንድ አካባቢ በተነሳ ግጭት መኪኖች መንገዱን አቋርጠው እንዳይሄዱ በቋጥኝ ቢዘጋ፣ ለዘጊዎቹ ከቁጣ ጋር በተያያዘ መልኩ ስናየው ልክ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን መንገድ መዝጋት የተዘጋበትን ክፍል ስለሚጎዳ የሚያስከትለው መዘዝ በቀላሉ መታየት አይኖርበትም፡፡ መንገድ ብቻ አይደለም፡፡ ከዕለት ተዕለት የምንጠቀምበት ምርት የሚገኝበት አካባቢ ምርቱን ቢያቋርጥ የተቋረጠበት ክፍል ዝም ብሎ አይመለከትም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ መኪና ከማቃጠል ታልፎ ወደ ሰው ማቃጠል ሽግግር ተደርጓል፡፡ ይህም በታሪክ ይቅርታ ካልታጠበ በስተቀር እያመረቀዘ የሚኖር ቁስል ይሆናል፡፡

አሁን ያለውን ብሔራዊ ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት?

በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ችግራችን ጽልመታዊ፣ እቡይ፣ አልኩ ባይ፣ ተመፃዳቂ፣ ‹‹ከእኛ በላይ ጎራሽ ማድ አበላሽ›› የሚል አዋራጅ፣ ክብርን የሚነካ፣ በራሱ ጠባብ አመለካከት የታጠረ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል የማያውቀውን አውቃለሁ፣ የማያደርገውን አደርጋለሁ የሚል አስመሳይ፣ በተገኘው አጋጣሚ የሚጠቀም ያጎበጠውን ለማረቅ ከታሪክ ዕርቅ በስተቀር ሌላ አማራጭ አይኖርም፡፡ በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙኃንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ ለጋራ ሰላም፣ ለወንድማማችነት፣ ለመከባበር፣ ለመተባበር፣ ለመቻቻልና ለፍቅር ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከአዎንታዊ አመለካከት ተነስተን ስንመለከተው ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ዛሬም አልመሸም፡፡ ፍትሕ በተጓደለበትና ዴሞክራሲያዊ መብት በተረገጠበት ሥርዓት ሰላም ሊሰፍን እንደማይችል አምኖ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ከሰፋና አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ካለ ሰላም ይሰፍናል፡፡ የሰውን መብት መከበሩን የሚያረጋግጡ ሕጎች ተግባራዊ ሲሆኑ፣ የሰላም መደላድሉ ይሰፋል፣ ሥሩም ይጠነክራል፡፡ ቅርንጫፉ ይለመልማል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው የወጡና በጠላትነት የተፈረጁ ሰዎች ወደ አገራቸው በሰላም እንዲገቡና እንዲኖሩ አመቺ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ውጥረቱ ይላላል፡፡ ሊፈነዳ የተቃረበው ችግር ይተነፍሳል፡፡

በአገር ውስጥ ሰላምን የሚያረጋግጠው ጠንካራ የጦር ኃይልና ደኅንነት ሳይሆን ከአድልዎ፣ ከጠባብነትና ከዘረኛነት፣ እንዲሁም ከሙሰኝነት የፀዳ የአስተዳደር ሥርዓት ነው፡፡ እኛም ቆርጠን ከተነሳንና እንደ አንድ ራሱን ለመስዋዕትነት ያዘጋጀ ወታደር ከውስጣችን፣ ከልባችን፣ ደግሞም በጀግንነት፣ ደግሞም በብልህነት፣ ደግሞም በቀጣይነት፣ ደግሞም በጥንቃቄ፣ ደግሞም ሕዝባዊ አደራ በተመላበት ከሠራን በዚህች አገር ላይ ሥር ነቀል ለውጥንና ዴሞክራሲን ማንገሥ እንችላለን፡፡

በእርግጥም በጎ አመለካከቱ ካለ ከደለበው ባህላዊ እሴታችን የሚመነጭ ‹‹ዕርቀ ሰላም›› የተሰኘ፣ ብሔራዊ መግባባትንና አንድነትን ማምጣት የሚያስችል ባህላዊ እሴት አለን፡፡ ስለሆነም ታሪካችንን እናስታርቅ፡፡ እኛ ይቅርታ ካደረግን ፈጣሪ ይቅር እንደሚለን ማወቃችንም ትልቁ ሃይማኖታዊ ሀብታችን ነው፡፡ አዎን ታሪካዊ ዕርቅ ኢትዮጵያን ያለችበትን የእርስ በርስ መቆሳሰል ታሪክ አውጥቶና ለህሊና ፍርድ አቅርቦ ብሔራዊ መግባባትንና አንድነትን ዕውን እንዲሆን ያደርጋል፣ እንጠቀምበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...