ጉዞ ከሜክሲኮ ወደ ካዛንቺስ። ኑሮ ያጎበጣቸው ወደ ጉዳያቸው ይጣደፋሉ። ከተማው በፍቅርና በጥላቻ፣ በውሸትና በእውነት፣ በመኖርና ባለመኖር መሀል ግራ የሚያጋባ መጋዘን መስሏል። ጨለማ ወሮት ባደረው አውራ ጎዳና ላይ የተስፋ ብርሃን ያለ አይመስልም። እያንዳንዱ ሰው ለመኖር ብቻ ሲል ሳያውቀው ዓላማዬ ብሎ ለሚኖርለት ነገ ሊተናነቅ እነሆ ነግቷል። የጎዳናው መንፈስ ውክቢያ ይባላል። መንገድ ከሰው ልጆች ህላዌ ይህን ይቀምራል። ያላለቁ ቀመሮች ለልመና በተዘረጉ እጆች በኩል ጎልተው ይታያሉ። ለማለቅ የሚጣደፉቱ ደግሞ በዕድሜ ጫፍ የእርጅና አዙሪት ውስጥ ይርመሰመሳሉ። ጅምሮቹና ለጋዎቹ ግን በትኩስነት ኃይል ውስጥ ገና ፅንስ ናቸው። ትኩሳት ይሉታል ይህን የዕድሜ ፌርማታ። በትኩስነት ውስጥ ሁሉም ነገር በግልጽና በቀላሉ ሊነበብ ይችላል። የዛሬን ከባድ የኑሮ ቀንበር እንደምንም አልፈው በትውልድ ሰንሰለት ውስጥ ውር ውር ለማለት ወጣቶች ጎዳናው ላይ በርከት ያሉ ይመስላሉ። እዚህ ያደረሰን መንገድ ነገ ደግሞ በእነዚህ አፍላዎች ትከሻ አሳፍሮን የት እንደሚያደርሰን ማን ያውቃል? አሮጌን አዲስ መተካቱ የግድ ነውና፡፡ እንዲያ ነው!
የታክሲ ሠልፍ ሳይወዱ በሳቅና በተረብ በተዥጎረጎሩ ሰዎች ረዥም መቀነት ሠርቷል። ቀርበው ሲያዩት ግን የምሬት ጎርፍ ይመስላል። ‹‹እውነትም እየሰነበተ ሲሄድ የማይለመድ ነገር የለም…›› ትላለች አንዲት ልጅ እግር ቆንጆ። ‹‹ችግር ወዳጅ ሲሆን የታየባት በአፍሪካ ብሎም በዓለም የመጀመሪያዋ አገር ኢትዮጵያ መሆኗ ነው። አቤት ለክፉውም ለደጉም አንደኝነት ስንወድ?›› ይላል አንዱ ከኋላ እንቅልፍ ያልጠገበ ዓይኑን እንዳይሆን አድርጎ እያሻሸ። ‹‹አሁንማ ቅሬታ ብናሰማም የሚሰጠንን መልስ በህልማችን ስለፈታነው፣ ተናገርን አልተናገርን ምንም ለውጥ አይኖረውም…›› ይላል አንድ ረዘም ያለ ጎልማሳ ዙሪያውን እየቃኘ። ‹‹መንግሥት በሚያዘጋጃቸው መድረኮች ላይ ሐሳብን በነፃነት ከማንሸራሸር ይልቅ፣ እዚህ የታክሲ ሠልፍ ላይ እንደ ልብ መናገር ተሽሎ አረፈው…›› እያለ ከኋላ አንድ ወጣት ለወዳጁ። ‹‹…ለምሳሌ ‘የታክሲ ችግር እንዲህ የተባባሰው ለምንድን ነው?’ ብለን መንግሥትን ብንጠይቅ፣ ‘ከዚህ በፊት ታክሲ የማይጠቀመው የኅብረተሰብ ክፍል ታክሲ ተጠቃሚ መሆን በመጀመሩ ነው። ይህም የኢኮኖሚ ዕድገታችን ምን ያህል በትክክለኛ መስመር እየተጓዘ መሆኑን ያሳያል’ ብሎ እንደሚመልስልን እናውቃለን…›› ብሎ ትንሽ የምፀት ፈገግ ካለ በኋላ፣ ‹‹ይኼ እኮ ማለት ሐኪም ጋ ሄደን ‘ሐኪም ሆይ አመመኝ’ ብለን ስንነግረው፣ ‘ከዚህ በፊት ጤነኛ ስለነበርክ ነው’ የሚል ምላሽ መስጠት ማለት እኮ ነው…›› እያለ ዙሪያ ገባውን መቃኘት ጀመረ፡፡ አይዞህ በሉት!
በስንት ጥበቃ ታክሲ አግኝተን መሳፈር ጀመርን። የሰው ብዛት እየጨመረ መሄዱን ላስተዋለ ከመጓጓዝ ውጪ ጊዜ ተርፎ ሥራ መሠራቱን ይጠራጠራል። መጠራጠር ሳይሆን ያምናል ቢባል ይቀል ይሆን? ‹‹ረገጥከኝ እኮ ቀስ ብለህ አታልፍም እንዴ?›› ያምባርቃል አንድ ጎልማሳ። ‹‹ይቅርታ!›› ይላል የጎልማሳው ግልምጫና ቁጣ ያስደነገጠው ወጣት። ጎልማሳው፣ ‹‹ጫማዬን አስጠርጌ ያበላሽብኛል? ምን ይመስላል?›› ሲል ይቀጥላል። ወጣቱ መልስ አይሰጥም። ፈገግ ብሎ እያየው በዓይኖቹ ይቀልድበታል። ታክሲዋ ሞልታለች። ድፍን የታክሲው ተሳፋሪ ‘ታላቅን ማክበር’ የሚባለው የማኅበረሰብ እሴት መፈራረሱን እየታዘበ ራሱን በአሉታ ይወዘውዛል። ‹‹ጎበዝ በዚህ እንደ ሮኬት እየተወነጨፈ እየደመሰሰን ባለው የኑሮ ውድነት ላይ ጭቅጭቅ ተጨምሮበት ይቻላል እንዴ…›› እያለ አንዱ ከመሀል ወንበር ነገር ሲመዝ፣ ‹‹ያልበላንን እያከክን ያመጣነው ስለሆነ ይበለን…›› ብሎ ከአጠገቡ ይመልስለታል፡፡ ቪፒኤኑን ከፍቶ ፌስቡክ ገጹ ላይ የተደረደሩ ልጥፎችን ሲያነብ የነበረ አንዱ ቀውላላ፣ ‹‹በአንድ ጊዜ ከተማ የሚያካክሉ ሁለት ታልልቅ ቤተ መንግሥቶች እየገነባን፣ እንዴት ሆኖ ነው ኑሮ ከበደን እያልን ጨርቃችንን ጥለን የምናብደው…›› ብሎ ለራሱ ልጥፍ ሐሳብ ሲቃርም፣ ‹‹የእኔ ወንድም አገር በቤተ መንግሥትና በመናፈሻ የምታድግ ቢሆን ኖሮ አንተ እንዳልከው ጨርቃችንን አንጥልም ነበር፡፡ ጨርቃችንን አስጥለው ሊያሳብዱን የፈለጉትን ግን ልትጠይቃቸው ትችላለህ…›› ብላ አንዷ ከጥግ ስትንጣጣ ሰማናት፡፡ በዚያ ቅላቷ ላይ በንዴት ደም የመሰሉት ጉንጮቿ የተቆጣች አክቲቪስት አስመስለዋታል፡፡ ዙሩ ከሯል!
ታክሲያችን መጣደፏን ከጀመረች ቆየት አለች። ሾፌራችን በእርጋታ ነው የሚያሽከረክራት። ለስላሳ የክራር ሙዚቃ ከወደ ‘ስፒከሩ’ እየተሰማ አንጀት ያላውሳል። የአንዳንዶች ቀልብ ጭልጥ ብሏል ወደኋላ ዘመን። ‹‹የትዝታ ኑሮ ማብቂያ ፌርማታው የት ይሆን?›› ይላል ከወደኋላ መቀመጫ በስተግራ በኩል የተቀመጠ ወጣት። በስተቀኝ ያለችው ደግሞ፣ ‹‹ወደፊት እየተጓዙ የኑሮን ከመጠን በላይ መወደድ ባሰቡ ቁጥር፣ ትናንትን እንደ መናፈቅ የመሰለ ሕመም አለ ብዬ አላስብም…›› ትላለች አንገቷን ደፋ አድርጋ። የቁጭት ይመስልባት ነበር። ምንጩ ብዙ የሆነ ቁጭት። ‹‹ወራጅ አለ!›› ሲል አንዱ ተሳፋሪ ወያላው ፈጥኖ ታክሲዋን አስቁሞ ሸኘው። ‹‹ሳበው!›› ብሎ ወያላው መንቀሳቀስ ልንጀምር ስንል ሦስት ወጣት ተሳፋሪዎች ‹‹ታክሲ!›› ብለው ጮኹ። ወያላው ሳይግደረደር ትርፍ ለመጫን እየቋመጠ ግቡ አላቸው፣ ገቡ። ‹‹ጠጋ… ጠጋ… በሉላቸው። አንተ እዚህ ጋ ተቀመጥ…›› እያለ በማጣበብ ቦታ መስጠት ጀመረ። ‹‹አልጠጋም!›› አለ አንድ የተማረረ ድምፅ። ወያላው ተንጠራርቶ አየው። ‹‹ማን ስለሆንክ ነው የማትጠጋው?›› አለው ንዴት እንደ ትኩሳት ደም ሥሩን እየገታተረው። ‹‹አልጠጋም!›› ባዩ ተሳፋሪ ሳቅ ብሎ ‹‹ለመጠጋትና ላለመጠጋት ማንነት መጠየቅ ተጀመረ?›› አለ። ወያላው፣ ‹‹ተጠጋ እባክህ ሰዓታችንን አትግደል። እንኳን አንተ ላይ ያሉትም እየተጠጋጉ አይደል እዚህ የደረሱት…›› አለ ፈርጠም ብሎ። አንዱ ነገር አራጋቢ ግን የወያላውን አቃቂር ተከትሎ፣ ‹‹ከላይ ያሉት በፈረቃ ላያችን ላይ እየወጡ እኮ ነው አሳራችንን የሚያበሉን…›› ብሎ ሲስቅ ተናግሮ አናጋሪ ይመስል ነበር፡፡ በቃ ተጠረጠረ!
ብሔራዊን ስናልፍ፣ ‹‹ዛሬ በስመ ሕንፃ ከቆሙ ሳጥን መሰል ግንባታዎች ይልቅ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተሠሩ የግድግዳ ግርፎችን እያደነቅን፣ በብዙኃኑ መጠቀሚያ ፍልውኃ በኩል ስናልፍ መልክ የሌለውና ውሉ የጠፋው የቤትና የውኃ ችግር ውልብ እያለብን፣ በታላቁ ቤተ መንግሥት ደጃፍ ስንደርስ ደግሞ ባለሥልጣኖቻችንን በሕዝብ ለሕዝብ ተወክለው እንደሚያገለግሉ ሳይሆን ራሳቸውን ብቻ እያዳመጡ ራሳቸውን እንደሚያገለግሉ ኃያላን ቆጥረን እንደ ደጀ ሰላም በራፍ ለመሳለም እየቃጣን ነው…›› የሚል የአንድ ትልቅ ሰው ድምፅ ይሰማል፡፡ አዛውንቱ በትዝታ ውስጥ ሆነው የዛሬው ነገር የጣማቸው አይመስሉም፡፡ ‹‹ይህ ሁሉ በሐሳብ መንሸራሸር ውስጥ የተገለጠ ሳይሆን፣ በአንድ አገር ውስጥ በምንኖር የጋራ ችግር ተቋዳሽ ሕዝቦች መንፈስ ውስጥ የተገለጠ እውነት ሆኖ ለማንም የሚታይ ነው…›› ሲል አንድ ጎልማሳ የአዛውንቱን ሐሳብ ተጋራ። ‹‹ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችማ ምስክር አያስፈልጋቸውም፣ እነሱ ልክ እንደ ውብ ቋሚ ሐውልቶች የብዙዎችን ቀልብ እየሳቡ የዛሬን ትርኪ ምርኪ ያጋልጣሉ…›› በማለት ያች ቀይ ብስል አክቲቪስት መሳይ አከለችበት፡፡ ወጉ ደርቷል!
ወደ መዳረሻችን እየተጠጋን ነው። ከብሔራዊ አካባቢ ያሳፈርናቸው ወጣቶች በእጆቻቸው በያዙዋቸው ሦስት የተለያዩ መጻሕፍት ዙሪያ ማራኪ ጨዋታ ጀምረዋል። የማንበብ ጥማቱን የእንጀራ ጉዳይ አላዳርስ ብሎ እንዳያረካ የተከለከለው በቅናት አስተያየት ሲያያቸው፣ እስከ እነ መፈጠሩም ባህሉ የሌለው አብዛኛው ተሳፋሪ ግን በቁንፅል ሐሳቦች የራሱን ጨዋታ ጀመረ። ‹‹ሰማህ ወዳጄ…›› ይለዋል ጎልማሳው አጠገቡ የተቀመጠውን ተሳፋሪ። ‹‹ለማንበብ እኮ ብዙ ነገር ያስፈልጋል። ለምሳሌ ቤት (ቢቻል የግል)፣ ጭቅጭቅ የሌለበት ትዳር፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ጥሩ ደመወዝ…›› እያለ ሊቀጥል ሲል፣ ‹‹አንተ እሱን ትላለህ፣ ሁሉም ነገር በገንዘብ እንጂ በዕውቀትና በሕጋዊ መንገድ በማይፈጸምበት አገር ለምን ብለን እናነባለን? ዋናው ነገር እንዴትም ብሎ አካብቶ መገኘት ነው…›› ይለዋል አጠገቡ የተቀመጠው። ‹‹ታትሞ የሚነበብ ሊጠፋ አንድ ሐሙስ በቀረባት አገር ውስጥ ሆናችሁ የከሸፈ ወሬ ስታስተጋቡ አታፍሩም አይደል…›› ትላለች ያቺ የቀይ ብስል፡፡ መሯታል!
አዛውንቱና የቀይ ብስሏ ወሬ ጀመሩ፡፡ አዛውንቱ፣ ‹‹አንቺ ልጅ…›› ወጣቷ፣ ‹‹አቤት አባቴ?›› ድምፃቸውን ቀስ አድርገው፣ ‹‹ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከሽፋለች ብለው የጻፉትን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም መጽሐፍ አንብበሽዋል?›› ወጣቷ፣ ‹‹አዎ!›› አለች ጥያቄያቸው እያስገረማት። ‹‹እውነት ነው?›› ሲሏት፣ ‹‹በአብዛኛው እውነት ነው…›› ብላ መለሰች። ‹‹ታዲያ ምኑን ኖርነው?›› ብለው እንደ መተከዝ አሉ። ይኼኔ ታክሲዋ ቆማ ካዛንቺስ ደርሳ ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› አለን። ከወረድን በኋላ የእግር መንገዳችንን ስንይዝ፣ ‹‹ይህችን ዓለም ከመሰናበቴ በፊት ውስጤ ምን ጻፍ ጻፍ እንደሚለኝ ልንገርሽ?›› ብለው ሲስቁ፣ ‹‹የእኛን ሰው የዘመናት ጀግንነት ከዘመናችን ብኩንነትና ፍራቻ ጋር አነፃፅሬ መጻፍ አማረኝ፡፡ ሁሉም ቦታ የምትሰማው አንድ ዓይነት ነገር ብቻ፣ በድሮ ጀግንነት መኮፈስ እንጂ ወኔ ዜሮ…›› ሲሉ እሷ ደግሞ፣ ‹‹አባቴ እኔን መሳይ ስንት ቆራጦች እንዳሉን ብነግርዎት አያምኑኝም? ምንም የሚያሳሳን ስለሌለን ማንንም የማንፈራ ሞልተናል…›› ስትላቸው እየሳቁ ተሰናብተዋት ሄዱ፣ እኛም እየሳቅን መንገዳችንን ቀጠልን፡፡ መልካም ጉዞ!