Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አምስተኛው ዓለም አቀፍ የአግሮፉድ ዓውደ ርዕይ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በግብርና ማቀነባበሪያ ላይ ያተኮረው አምስተኛው ዓለም አቀፍ የአግሮፉድና ፕላስትፕሪንትፓክ (የፕላስቲክ፣ የህትመትና የማሸጊያ) ዓውደ ርዕይ ከሰኔ 1 እስከ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ እንደሚከናወን የሁነቱ አዘጋጆች የጀርመኑ ፌርትሬድና ፕራና ኢቨንት አስታውቀዋል፡፡

ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የአግሮፉድና ፕላስትፕሪንትፓክ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይ፣ በግብርና፣ በምግብና መጠጥ ግብዓቶች፣ በግብርና ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች በማሽነሪዎችና በፕላስቲክ ዘርፍ የተሰማሩ ከ12 አገሮች የተውጣጡ ከ130 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡

የግብርና ምርቶችን ማቀነባበር፣ ጠብቆ ማቆየት፣ ማዘጋጀትና አሽጎ ማቅረብ (አግሮፉድ)፣ ኢትዮጵያ በአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዷ ካስቀመጠቻቸው ግቦች አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ ከተጀመሩ ሥራዎች ውስጥም የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪው ይጠቀሳል፡፡

በግብርና ላይ ያተኮረው አግሮፉድ ኢትዮጵያ የንግድ ትርዒትና ኮንፈረንስ፣ በምግብና መጠጥ ቴክኖሎጂ፣ በምግብና በምግብ ግብዓቶች ዙሪያ የሚደረግ ሲሆን፣ በዓውደ ርዕዩ የግብርና ማሽኖች፣ የእርሻ ትራክተሮች የማጨጃ ቁሳቁስ፣ የዶሮ ዕርባታ ዕቃዎች፣ መፍጫ፣ የማዋሃጃ ዕቃዎች፣ የዓሳ ግብርና ቁሳቁሶች፣ የመስኖና የምግብ ግብዓቶች፣ የማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችና ቁሳቁሶች እንዲሁም ያለቀላቸው የምግብ ዓይነቶች የሚቀርቡበት፣ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር የሚደረግበት እንደሆነም አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡

በምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ የጥናትና ልማት ማዕከል የምግብ ዘርፉ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ታዬ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ያለባት ችግር የምግብ ሳይሆን ለምግብ የሚሆኑ ሀብቶችን በአግባቡና በዘመናዊ ኢንዱስትሪ ተጠቅሞ በተያዩ አማራጮች ለኅብረተሰቡ ማቅረብና ጠብቆ የማቆየት ነው፡፡

ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህ ደግሞ በአግሮፉድ ዓውደ ርዕዩ ከሚሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች ዕውቀትና ቴክኖሎጂን እንዲሁም ግብዓትን ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተደረጉት አራት ተመሳሳይ ዓውደ ርዕዮች ተቋማቸው መሳተፉን፣ በዚህም ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉት ማምረት ብቻ ሳይሆን ምርትን መሸጥና ለዚህ የሚሆን መረጃ ማግኘት እንደሆነ መታዘባቸውን፣ ዓውደ ርዕዩ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የግብርና ሀብት አለ ያሉት አቶ ሀብታሙ፣ ሀብቱን በኢንዱስትሪ አምርቶና አቀነባብሮ ለአገር ውስጥና ውጭ ገበያ ለማቅረብ ወሳኝነት ያለውን ማሸጊያ (ፓኬጂንግ) ለማምረት የሚያስችል ዕውቀትና ቁሳቁስ ይዘው በኤግዚቢሽኑ የሚሳተፉ ኩባንያዎች እንደሚኖሩና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም የሚፈልጉትን መረጃና አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

ከሳምንት በፊት በተካሄደው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በርካታ ተሳታፊዎች እርስ በርስ የሚመጋገቡበትን አጋጣሚ መፍጠራቸውን የአግሮፉድ ዓውደ ርዕይም ለኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጠቃሚ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡

እንደ ምርምር ተቋምም፣ ኢትዮጵያ የራሷን ቴክኖሎጂ ማመንጨት እንድትችል ለጀመሩት ምርምር ከዓውደ ርዕዩ የልምድ ልውውጥና የዕውቀት ሽግግር እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

ከሰኔ 1 እስከ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚካሄደው አምስተኛው አግሮፉድና ፕላስትፕሪንትፓክ ዓውደ ርዕይ ቻይና፣ ጀመርን፣ ህንድ፣ ጣሊያን፣ ኩዌት፣ ቱርክ፣ ኢትዮጵያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ታይላንድን ጨምሮ ከ12 አገሮች የሚመጡ ከ130 በላይ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ የጀርመኑ ትሬድፌር አስታውቋል፡፡

የቀድሞው የምግብ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ በ2013 በጀት ዓመት ሪፖርቱ፣ 14.7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ካስመዘገቡ አዲስ ኢንቨስትመንቶች መካከል የአገር ውስጥ አግሮፉድ ፓርክ 3.1 ቢሊዮን ብር እንደነበር ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች