Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሸገር ከተማ ቤት ለሚፈርስባቸው ዜጎች ካሳና ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጥ ማሳሰቢያ ተሰጠ

በሸገር ከተማ ቤት ለሚፈርስባቸው ዜጎች ካሳና ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጥ ማሳሰቢያ ተሰጠ

ቀን:

  • በስድስት አቅጣጫዎች የተፈናቀሉ8 ሚሊዮን ሰዎች የከፋ ችግር ላይ ናቸው ተብሏል

በሸገር ከተማ ‹‹ሕገወጥ ግንባታ ነው›› ተብለው ቤት እየፈረሰባቸው ላሉ ነዋሪዎች መንግሥት ካሳና ተለዋጭ ቦታ መስጠት እንዳለበት የኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡

ቤት እየፈረሰባቸው በመሆኑ ያለ ማቋረጥ አቤቱታ ለሚያቀርቡ ሰዎች መንግሥት ካሳና ተለዋጭ ቦታ መስጠት እንዳለበት፣ የተቋሙ የአስተዳደር በደል መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከአቤቱታ አቅራቢዎች ከ100 ሺሕ በላይ ቅሬታዎች ተቋሙ እንደደረሰው ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ የሚፈርሱት ቤቶች ሕጋዊም ሆኑ ሕገወጦች፣ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ካሳ ሊከፍላቸውና የሚያለሙበት ተለዋጭ ቦታ ሊሰጣቸውም እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ መግባባት ቢኖርም፣ በተጨባጭና በተግባር የተደረገ ነገር ባለመኖሩ አሁንም ቅሬታዎቹ እንዳልቆሙና እንዳልተፈቱም አቶ አዳነ ተናግረዋል፡፡

የቀረቡትን ቅሬታዎች በተመለከተ ዕንባ ጠባቂ ተቋማት ያቀደው ነገር እንዳለ  ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ተቋማችን የዜጎች ቅሬታ እስኪፈታ ድረስ እስከ መጨረሻው ለመሄድና ለመከላከል ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት ያደርጋል፣ መፍትሔ እንዲሰጥም እየሠራ ነው፤›› በማለት አቶ አዳነ ገልጸዋል፡፡

ዕንባ ጠባቂ ተቋም በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት የተከሰተው ቀውስና ከደረሰው ጉዳት ለመውጣት በአሁኑ ጊዜ ለተጎጂዎች የሚደረግ ድጋፍን፣ መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን፣ የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሒደትን አስመልክቶ ከሚያዝያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. አደረግኩት ያለውን የዳሰሳ ጥናት ሐሙስ ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

በጦርነቱ በትግራይ ክልል ብቻ 2,146 ተማሪዎች፣ 1,700 መምህራን፣ በአጠቃላይ 3,846 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ተቋሙ አደረግኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት እንደተረጋገጠ አቶ አዳነ ገልጸዋል፡፡

ከሞቱት ሰዎች ባሻገር በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ ስድስት አቅጣጫዎች ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ተፈናቃዮቹ በየወሩ ድጋፍ ሊደረግላቸው ቢገባም ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ድጋፍ ያገኙት ሦስት ጊዜ ብቻ በመሆኑ በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ መቀሌ ከተማን ጨምሮ በሌሎች በክልሉ በሚገኙ ከተሞች፣ በትምህርት ቤቶችና በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ተቋሙ ከትግራይ ማኅበራዊ ጉዳይና መልሶ ማቋቋም ቢሮ አገኘሁት ያለውን መረጃ ጠቅሷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት በተቋማት ላይ የደረሰውን የውድመት መጠን በጥናት ማረጋገጡ ተገልጿል፡፡ በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት 96.5 በመቶ የተማሪዎች መቀመጫ ዴስኮች፣ 95.9 በመቶ ጥቁር ሰሌዳዎች፣ 88.3 በመቶ የመማሪያ ክፍሎች፣ 63.5 በመቶ የመማሪያ መጻሕፍት፣ 31.7 በመቶ የአስተዳዳር ሕንፃዎች ሙሉ ለሙሉና በከፊል መውደማቸው በጥናት መረጋገጡን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በተቋማት ላይ ደረሰ የተባለውን ውድመት ሲገልጹ፣ የትምህርት ተቋማት ከመውደማቸው በፊት ተማሪዎች በቅርበት ተጉዘው ያገኙት የነበረን ተቋም ማግኘት እንዳይችሉ በማድረግ በትምህርት ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ እንደሆነ አክለዋል፡፡

በተቋማት ላይ ውድመት ከመድረሱ በፊት ለአንደኛ ደረጃ የትምህርት ተደራሽነት 2.5 ኪሎ ሜትር ይጓዙ የነበሩ ተማሪዎች፣ ከውድመቱ በኋላ 7.3 ኪሎ ሜትር፣ በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተደራሽነት ደግሞ ቀድሞ ሰባት ኪሎ ሜትር ይጓዙ የነበሩ ተማሪዎች፣ አሁን 17 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ መገደዳቸውን ሪፖርተር የተመለከተው የዕንባ ጠባቂ ተቋም የዳሰሳ ጥናት ያሳያል፡፡

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በመንገድ፣ በመብራት፣ በውኃ፣ በባንክ፣ በቴሌና በሌሎች ተቋማት ላይ ደረሰ የተባለው ውድመት በተገልጋዮች ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑ በዳሰሳ ጥናቱ ተመልክቷል፡፡

በጤና ተቋማት ከ65 ቢሊዮን ብር በላይ፣ በኤሌክትሪክ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ፣ በቴሌ ኮሙዩኒኬሽን ከ1.3 በሊዮን ብር በላይ፣ በውኃ ተቋማት ላይ 489 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በአጠቃላይ ከ69 ቢሊዮን ብር በላይ የመሠረተ ልማት ውድመት መድረሱን የዳሰሳ ጥናቱ ያትታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...