ኢትዮጵያ የሁለተኛውን የፋሺስት ጣሊያን ወረራ (1928-1933) በድል ከተወጣች በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ አገሪቱን በተለያዩ ዘርፎች ለማዘመን በየዓረፍተ ዘመኑ ካከናወኗቸው ዓበይት ተግባራት መካከል የጦር ኃይሉን በልዕልና ማጠናከር ነበር፡፡
በዋና ዋና ጠቅላይ ግዛቶች የማሠልጠኛ ተቋማት በመመሥረት በተለይ የጦር መኰንኖች ተመርቀው ይሰማሩ ነበር፡፡ በተለይ 1950 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጦር ኃይል ዘንድ ታሪካዊት ዓመት ነበረች፡፡ ስመ ገናናውና በውጩ ዓለም ታዋቂ የነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐረር ጦር አካዴሚ ዕውን የሆነበት፣ በዘመናት ጉዞው በተለይ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዘመን ለአገር መኩሪያ የሆኑ ታላላቅ መኰንኖችን ለማፍራት በቅቷል፡፡
ከነዚህ መኰንኖች መካከል አንዱ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ዘመን፣ ከሰማንያ አምስት ዓመታት በፊት በወርኃ የካቲት ወደዚህ ዓለም የመጡትና በዘመናት ጉዞ ከንጉሣዊው ሥርዓት በፍኖተ ደርግ በኩል እስከ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) መንግሥታት ድረስ ለ33 ዓመታት በቁርጠኝነት አገራቸውን ያገለገሉት ሜጀር ጄኔራል ሁሴን አህመድ ይገኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊትን ታሪክ ‹‹የወገን ጦር›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ያሳተሙት ሻለቃ ማሞ ለማ እንደገለጹት፣‹‹ጄኔራል ሁሴን ኢትዮጵያ አሏት ከሚባሉት ምርጥና ታዋቂ የጦር ጄኔራሎች ውስጥ አንዱ ነበሩ፡፡ ጄኔራል ሁሴን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐረር ጦር አካዴሚ 1ኛ ኮርስ ተመራቂ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ታዋቂና ምርጥ የጦር ጄኔራል ያደረጋቸው በሰሜኑ የጦር ግንባር ከክፍለ ጦር እስከ አርሚ ድረስ ያለን ግዙፍ ሠራዊት በከፍተኛ ብቃትና ችሎታ በመምራት ታዋቂና ተደናቂ የነበሩ ስለሆኑ ነው፡፡››
የ1969 ዓ.ም. የሶማሊያ ወረራን ተከትሎ በምሥራቅ ጦር ግንባር እስከ ወርኃ ሐምሌ በአዛዥነት የከተቱት ከፍተኛ መኰንኑ፣ በሰሜን ጦር ግንባር የኤርትራ ሽምቅ ተዋጊዎችን ለመግታት የተሰማራውን ሠራዊት ለመምራት በማቅናት ለአሥራ አራት ዓመት ሲያዋጉና ሲዋጉ ኖረዋል፡፡ ከግብረ ኃይል እስከ ዕዝ አዛዥነት፣ ከ1981 ዓ.ም. የግንቦት 8 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ከነበሩበት የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት (ሁአሠ) ምክትል አዛዥነት ወደ ዋና አዛዥነት በመሻገር ሠራዊቱንና አገሪቱን ማገልገላቸው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በወሎ ደሴ የካቲት 21 ቀን 1930 ዓ.ም. የተወለዱት ሜጄር ጄኔራል ሁሴን አህመድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንጉሥ ሚካኤልና በወይዘሮ ስሒን ትምህርት ቤቶች፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትና ሐረር መድኃኔ ዓለም አጠናቀዋል። የኮሌጅ ትምህርታቸውን ከቆይታ በኋላ ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ባደገው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እየተከታተሉ ሳለ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሐረር ጦር አካዴሚ በመከፈቱ እዚያ በመግባት በዲፕሎማና በምክትል መቶ አለቅነት ማዕርግ ተመርቀዋል፡፡
በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በአሠልጣኝነት ለሦስት ዓመት አገልግሎት በኋላ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመመለስ በማኔጅመንት በመጀመርያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ለከፍተኛ መኰንነት የአስተዳደር ትምህርት ለመማር ወደ አሜሪካም ዘልቀዋል፡፡
አብዮታዊው ሠራዊት በተሰኘ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንደተጻፈው፣ በ1950ዎቹ መገባደጃ ለተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ የሰላም ተቆጣጣሪ ልዑክ አባል በመሆን ሕንድ፣ ፓኪስታን በመሄድ ለስድስት ወራት በመቆየት የሰላም ጥበቃ ግዳጃቸውን ተወጥተዋል።
የሰሜኑ ጦርነት ወደ ማዕከል መግፋቱን ተከትሎ፣ የኢሕዲሪ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም. አገር ለቅቀው መሄዳቸውን፣ የኤርትራ ጉዳይም ማብቃቱን ተከትሎ፣ ጄኔራል ሁሴን ከነበሩበት ሁአሠን ይመሩበት ከነበረው ኤርትራ ግንቦት 15 ቀን 1983 ዓ.ም. ወደ የመን ተሻግረዋል፡፡ ቀጥሎም በሳዑዲ ዓረቢያ ለአራት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ኑሯቸውን ለቀጣዮቹ ሦስት አሠርታት ኅልፈተ ሕይወት እስካጋጠማቸው ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ኑሮአቸውን በአሜሪካ አድርገዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም በዚያው ግንቦት 18 ቀን ተፈጽሟል፡፡
ጄኔራል መኰንኑ በ55 ዓመት የትዳር ሕይወታቸው ሦስት ልጆች ወልደዋል፡፡ የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡ ሜጄር ጄኔራል ሁሴን አህመድ ሁለት መጻሕፍት ‹‹መስዋዕትነት እና ፅናት›› እንዲሁም ‹‹ማር እና እሬት›› የተሰኙ አሳትመዋል፡፡
‹‹የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት አባል የነበረ ሁሉ ጄኔራል ሁሴንን የማያውቅና የጦር አዛዥነታቸውን የማያደንቅ ከቶ ማን ነበር? ጄኔራል ሁሴን በሁአሠ አባላት ዘንድ ከስማቸው ሌላ በስፋት የሚታወቁበት ፋዘር ወይም ሆቴል በሚል መጠሪያ ነበር፡፡ የዚህም ትርጉም ‹ፋዘር› የሚለው ጥሩና ተወዳጅ የሠራዊት አዛዥ ለበታቾቹ እንደ አባት የሚቆጠር በመሆኑና እሳቸውም ይህንን የሚያሟሉ ሲሆን፣ ‹ሆቴል› የሚለው ደግሞ በራዲዮ ግንኙነት አጠቃቀም የፊደሎች አሰያየም መሠረት የእሳቸው ስም መጀመሪያ የሆነው የH ፊደል Hotel በሚል ስለሚጠራ ነው፡፡›› የሚሉት ሻለቃ ማሞ፣ ስለ ጄኔራል መኰንኑ የሚከተለውን ምስክርነት ዜና ዕረፍታቸው መሰማቱን ተከትሎ አስተጋብተዋል፡፡
‹‹ጄኔራል ሁሴንን መጀመሪያ የማውቃቸው ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ በኤርትራ ምድር በአልጌና ጦር ግንባር በዚያን ወቅት እኔ ገና የብርጌድ ዘመቻ መኰንን እያለሁ ሲሆን፣ ከዚያ በመቀጠል ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ የመክት ዕዝ ዋና አዛዥ ሆነው፣ የዕዙ ረዳት ዘመቻ መኰንን ሆኜ ከእሳቸው ጋር ተቀራርቦ የመሥራት ዕድሉ ገጥሞኛል፡፡ ጄኔራል ሁሴን ከሚታወቁበትና ከሚደነቁበት የአዛዥነት ዘይቤአቸው ውስጥ የወጣት መኰንኖችን ብቃትና ችሎታ፤ እንዲሁም ዝንባሌአቸውን ጭምር ፈጥነው በመረዳት በተገቢው ቦታ በመመደብ የተግባር ዕውቀትና ልምድን ቀስመው የላቀ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የማድረግ ችሎታቸው ነበር፡፡ እኔም አንዱ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ስለነበርኩ እስከ ሕይወቴ ፍጻሜ ድረስ ሳደንቃቸው፤ ሳስታውሳቸውና ሳመሰግናቸው እኖራለሁ፡፡››