Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ባለፈው ዓመት ለማዳበሪያ የደጎመው 15 ቢሊዮን ብር ለአርሶ አደሮች አለመድረሱ ጥያቄ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ለ2014/15 በጀት ዓመት እርሻ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ያለውን የዋጋ ንረት ታሳቢ በማድረግ ያደረገው የ15 ቢሊዮን ብር ድጎማ ለአርሶ አደሮች አለመድረሱ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ አስነሳ፡፡

ምክር ቤቱ ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ የግብርና ሚኒስቴርን የ2015 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

የፓርላማ አባላቱ በ2014/2015 ዓ.ም. የምርት ዘመን መንግሥት ለአርሶ አደሮች 15 ቢሊዮን ብር ወይም በኩንታል 1,100 ብር ድጎማ ቢያደርግም፣ ገንዘቡ እስካሁን አርሶ አደሮቹ አለመድረሱን ጠቅሰው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የመንግሥት የአፈር ማዳበሪያ ድጎማ ለአርሶ አደሮች የቀረበው፣ አርሶ አደሮቹ የማዳበሪያ ግዥውን ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ከየካቲት እስከ ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. በነበሩት ወራት ውስጥ ግዥ ከአፈጻጸሙ በኋላ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

የግብርና ሥራ ከተጀመረ በኋላ ገንዘቡ መመለስ የነበረበት ቢሆንም፣ ለአንድ ዓመት ያህል በዝግ የባንክ ሒሳብ ተቀምጦ መቆየቱን የጠቀሱት የፓርላማ አባላቱ፣ አንድ አርሶ አደር ከድጎማው ማግኘት የነበረበትን ከ2,000 እስከ 15,000 ብር ድረስ አለመተላለፉን የፓርላማ አባላት ገልጸዋል፡፡

አቶ በጋሻው ተክሉ የተባሉ የምክር ቤት አባል፣ የግብርና ሚኒስቴር የድጎማ ገንዘቡን መመለስ እንዳለበት አቅጣጫ መቀመጡን ቢያስታውቅም፣ ለአንድ ዓመት ያህል ሳይከፈል መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ አቶ መስፍን ዳኜ የተባሉ የምክር ቤት አባል ለ2014/2015 ዓ.ም. የምርት ዘመን መንግሥት ያቀረበው 15 ቢሊዮን ብር ለአርሶ አደሮች አለመተላለፉን ተናግረዋል፡፡ አክለውም በተያዘው ዓመት እየቀረበ ያለው የማዳበሪያ አቅርቦት በጣም ውስን መሆኑን፣ ከጥቂት ወራት በፊት በጀመረው ዝናብ ሳቢያ አሁን ማዳበሪያውን ለገበሬ ማቅረብ እንዳልተቻለም ጠቁመዋል፡፡

በርካታ የምክር ቤት አባላት አርሶ አደሮች ለቀጣይ የምርት ዘመን ማዳበሪያ ቀድሞ መግባት የነበረበት ቢሆንም፣ አርሶ አደሮች እየደረሳቸው አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም ታለፍ ይታወቅ የተባሉት የምክር ቤት አባል በቆላማ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ማሽላ ያለ ማዳበርያ እየዘሩ መሆኑን፣ በደጋ አካባቢ ያሉ የቢራ ገብስ አምራቾችም ያለ ምንም የአፈር ማደበሪያ አቅርቦት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባሏ እንደሚሉት መንግሥት በጥቅምት ወር የማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል ቢልም፣ አሁን ያለውን ዝናብ የሚጠቀሙና በመጪው ሰኔ ወር በመደበኛነት የግብርና ሥራ የሚጀምሩ አርሶ አደሮች ግን ማዳበሪያ አልደረሳቸውም፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ተወካይ አንድ የምክር ቤት አባል እንደገለጹት፣ አርሶ አደሩ ጊዜውን የጠበቀ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት እየቀረበለት አይደለም፡፡ እሳቸው ተመርጠው ከመጡበት አካባቢ እስከ ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ዞኑ ከሚጠበቀው አጠቃላይ የአፈር ማዳበሪያ አሥር በመቶ የሚሆነውን ብቻ እንዳገኘ ተናግረዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ደኤታዋ ሶፊያ ካሳ (ዶ.ር) ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ የአፈር ማዳበሪያ ድጎማው አርሶ አደሩ ግዥ ከፈጸመ በኋላ የተለቀቀ በመሆኑ የድጎማ ገንዘቡን ለመመለስ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደተፈጠረ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር ሒሳብ አናበው ለጨረሱ ክልሎች ገንዘቡ መተላለፉን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ በቀጣይ ለክልሎች የተላለፈው ገንዘብ ለአርሶ አደሮች መተላለፉን ሚኒስቴሩ ይከታተላል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአማራና የደቡብ ክልሎች የሸጡበትንና ድጎማውን አናበው ባለመጨረሳቸው፣ የድጎማ ገንዘቡ እስካሁን አለመለቀቁን አስረድተዋል፡፡

የድጎማ ገንዘቡ በንግድ ባንክ ዝግ አካውንት የተቀመጠ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ክልሎች ከግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አናበው በጨረሱ 24 ሰዓት ውስጥ ይተላለፋል ብለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ለ2015/2016 አጠቃላይ የምርት ዘመን 15 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት ካለፈው ዓመት የተረፈ 2.2 ሚሊዮን ኩንታል የአገር ውስጥ ከውጭ የገባ 5.6 ሚሊዮን ኩንታል ለአርሶ አደሮች መቅረቡን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ከዚህ ውስጥ ለገበሬው የተሠራጨው 3.7 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ትልቁ ነገር ማዳበሪያ አገር ውስጥ ማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ የገባውን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እስካልተሰጠ ድረስ ማዳበሪያ አቅርቧል ብሎ በሙሉ ልብ መቀመጥ አይቻልም ሲሉ አክለዋል፡፡

ለአሮሚያ ክልል 2.4 ሚሊዮን ኩንታል፣ ለአማራ ክልል 1.3 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ አለመተላለፉን የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ማዳበሪያን በመጋዘን ውስጥ ይዞ አርሶ አደሩን ማስጮህ ተገቢ ባለመሆኑ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ማዳበሪያ ወስደው ወደ አርሶ አደሩ ማድረስ አለባቸው ብለዋል፡፡ ‹‹የምክር ቤት አባላት በየምርጫ ጣቢያቸው በየደረጃው ያለውን አመራር በመጠየቅ ተባበሩን፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የማዳበሪያ ፍላጎት ከ20 ሚሊዮን በላይ ቢሆንም፣ በየዓመቱ እየተሠራጨ ያለው ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በታች መሆኑን አስረድረተዋል፡፡ አክለውም ወደ አገር ውስጥ የገባ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የማድረስ ጉዳይ አንገብጋቢና የምክር ቤቱን ዕገዛ የሚፈልግ እንደሆነ ግርማ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡

ወደ አገር ውስጥ ከገባው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች የተላለፈው ከ50 በመቶ እንደማይበልጥ፣ ይህ እየሆነ ያለውም ክልሎች በተገቢው ወቅት ሊደርስላቸው ለሚገቡ አካባቢዎች በትክክለኛው መንገድ እያሠራጩ ባለመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች