ፈንጂዎችንና ሌሎች የጦር መሣሪያ ቅሪቶችን የማስወገድ ተልዕኮ የተሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ፈንጂ ማስወገድ አገልግሎት (UNMAS) በዋናነት በትግራይ ክልል እንዲሁም ጦርነት በተካሄደባቸው አዋሳኝ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲሰማራ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቀደ።
ፈንጂዎችና ሌሎች ያልፈነዱ የጦር መሣሪያ ቅሪቶች ጦርነት በተካሄደባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ በመሆኑ አካባቢዎችን ከፈንጂዎች ለማጽዳት እንዲቻል፣ የተመድ ፈንጂ ማስወገድ አገልግሎት እንዲሰማራ መፈቀዱን የአፍሪካ ኅብረት መረጃ ያመለክታል።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ትግበራ የሚከታተለው የፌዴራል መንግሥት፣ የሕወሓትና አፍሪካ ኅብረት የጋራ ኮሚቴ ሁለተኛ ስብሰባ ረቡዕ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን፣ የስብሰባው ማጠቃለያ የሆነው መግለጫም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተመድ ፈንጂ ማስወገድ አገልግሎት በትግራይና በሌሎች ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች እንዲሰማራ መፍቀዱንና ይህንንም በአዎንታ እንደሚቀበለው አስታውቋል።
ፈንጂዎችና ሌሎች ያልፈነዱ የጦር መሣሪያ ቅሪቶች በትግራይና በሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በነዋሪዎች በተለይም በሕፃናት ላይ የሞትና የአካል ጉዳት አደጋ እያደረሱ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ለአብነት ያህል በዚህ ወር በአፋር ክልል በፈነዳ የወደቀ የሞርታር ጥይት የአራት ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ በትግራይ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል 300 በሚሆኑት ውስጥ በርካታ የጦር መሳሪያ ቅሪቶች መገኘቱም ታውቋል።
‹‹የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፈንጂ ማስወገድ አገልግሎት እንዲሰማራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ማግኘቱን የጋራ ኮሚቴው በደስታ ተቀብሏል›› የሚለው የጋራ ኮሚቴው መግለጫ፣ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ፈንጂዎችን ለማስወገድና የተጎዱትን ሕዝቦች ኑሮና ሰብዓዊ ክብራቸውን ለመጠበቅ እንዲሁም ወደ መደበኛ ኑሮአቸው ለመመለስ የጋራ ኮሚቴው ከተመድ ፈንጂ ማስወገድ አገልግሎት ጋር በቅርበት ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል።
ሪፖርተር ያገኘው መረጃ፣ የተመድ ፈንጂ ማስወገድ አገልግሎት በቅርቡ በመቀሌ ከተማ ቢሮውን እንደሚከፍትና ዋና መቀመጫውን በመቀሌ አድርጎ በሁሉም ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሚሰማራ ያመለክታል።
የሰላም ስምምነቱን ትግበራ እንዲከታተልና እንዲያረጋግጥ በአፍሪካ ኅብረት የተቋቋመው ኮሚቴ፣ እስካሁን ያካሄዳቸውን ተግባራት የተመለከተ ሪፖርት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የውጭ ኤምባሲዎች ወታደራዊ አታሼዎች በተገኙበት፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በመቀሌ ከተማ አቅርቧል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት ኮሚቴውን የሚመሩት ናይጄሪያዊው ጄኔራል ስቴፈን ረዳኒ፣ የተመድ ፈንጂ ማስወገድ አገልግሎት ጦርነት በተካሄደባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲንቀሳቀስ ፈቃድ ማግኘቱን ጠቁመው፣ በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
‹‹እንደ ውትድርና ባለሙያ የትግራይ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት ሲመለሱና ገበሬዎች እርሻቸውን ሲቀጥሉ፣ በወደቁ ፈንጂዎችና ተቀጣጣይ ጦር መሳሪያዎች አደጋ እንዳያጋጥሟቸው ፈጣን ክትትል የሚያስፈልገው ቦታ እንደሆነ ይሰማኛል፤›› ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በትግራይ ሙሉ በሙሉ ትምህርት የማስጀመር ውጥን እንዲሳካ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ በማድረግ፣ በተፈናቃዮች የተሞሉ ትምህርት ቤቶችን ነፃ ማድረግ እንዲሁም ትምህርት ቤቶቹንና ከባቢያቸውን ከፈንጂዎች ማጽዳት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ነገር ግን ይህንን ለማድረግ የትግራይ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ለቀው አለመውጣት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። በስምምነቱ መሠረት የፌዴራል መንግሥት የተደራጁ የኤርትራ ጦሮች ከትግራይ እንዲወጡ ማደረጉን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ በኤርትራ ጦር የተያዙ አካቢቢዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
የኤርትራ ጦር በተቆጣጠራቸው የትግራይ አካባቢዎች ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን ከማወኩ አልፎ ተርፎ በቅርቡ የሰላም ስምምነቱን ትግበራ እንዲከታተልና እንዲያረጋግጥ በአፍሪካ ኅብረት የተቋቋመው ኮሚቴ እነዚህን አካባቢዎች እንዳይጎበኝ በኤርትራ ጦር ተከልክሎ መመለሱን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።