Saturday, June 15, 2024

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ ነው፡፡ በመኸር እርሻ ሰብሎችን የሚያበቅሉ መሬቶች ዝግጅት ሲደረግም ሆነ በዘር ወቅት፣ እንዲሁም ከዓረም እስከ ተባይ መከላከልና የኩትኳቶ ሥራዎች አርሶ አደሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ በሥራ ይወጠራሉ፡፡ ይህ ወቅት ለአርሶ አደሮች ብቻ ሳይሆን ለመላው የአገሬው ሕዝብ ህልውና ወሳኝ በመሆኑ፣ ከምንም ነገር በላይ ለሰላምና ለመረጋጋት መስፈን ትልቅ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ አብዛኛውን የሥራ ጊዜያቸውን በእርሻ ላይ የሚያሳልፉ አርሶ አደሮችም ሆኑ ሌሎች ወገኖች፣ ከማንኛውም ዓይነት ግጭትና ሁከት ርቀው ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሊታረስ ከሚገባው 60 ሚሊዮን ሔክታር ውስጥ 15 ሚሊዮን ሔክታር ብቻ እየታረሰ፣ ለመግለጽ የሚያዳግት ድህነት ውስጥ ተሁኖ ሰላም አደፍራሽ ድርጊቶች ላይ መሰማራት ያሳፍራል፡፡ አለመግባባቶችን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ፈር ማስያዝ ሲገባ፣ ዋናውን የምግብ አቅርቦት ምንጭ እርሻን ማስተጓጎል ወንጀል ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ለሁለት ዓመታት ያህል እጅግ አስከፊው ጦርነት የተካሄደባቸው ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ብቻ ሳይሆኑ ኦሮሚያን ጨምሮ ሌሎችም ክልሎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች የክረምቱን እርሻ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ዕገዛ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የመኸር እርሻው በበቂ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ፀረ ተባይና ሌሎች ግብዓቶች ታግዞ ያልታረሱ መሬቶች ጭምር ምርት እንዲሰጡ ማስቻል ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በቸልተኝነትና በብቃት አልባነት ምክንያት አገር ከመጠን በላይ እየተጎዳች ስለሆነ፣ የእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ የግዴለሾች ሰለባ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለከንቱ የፖለቲካ ዓላማ ሲባል ከሚደረግ የሴራና የሸፍጥ ድርጊት በተጨማሪ፣ ለግላዊና ለቡድናዊ ጥቅም ብቻ ሲሉ ትርምስ ከሚፈጥሩ ነውጠኞችም መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለሚነሱ ሰላማዊ ጥያቄዎች ሰላማዊ ምላሾች እየተሰጡ፣ ነፍጥ አንስተው ከሚፋለሙት ጋር ደግሞ ሰላማዊ ንግግርና ድርድር እየተደረገ መረጋጋት ማስፈን የግድ መሆን አለበት፡፡

በዚህ ወቅት የመኸር እርሻ በአግባቡ ተከናውኖ በቂ ምርት ማግኘት ካልተቻለ በርካታ ሚሊዮኖች ለረሃብ አደጋ ይጋለጣሉ፡፡ መንግሥትም ሆነ የሚገዳደሩት ወገኖች ከምንም ነገር በላይ ለሰላማዊ መፍትሔዎች ትኩረት ይስጡ፡፡ ከራሷ አልፎ ለዓለም ገበያ የመትረፍ ትልቅ ዕምቅ አቅም ያላት ኢትዮጵያ፣ ዝንተዓለም የረሃብና የተመፅዋችነት ተምሳሌት መደረጓ ሊያስቆጭ ይገባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ነዳጅ፣ ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ምርቶች ዋጋ አልቀመስ ማለቱ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ በጣም ከፍተኛ ፅኑ የምግብ ችግር አለ፡፡ የአገር ውስጥ ገበያውን በተለያዩ የምግብ ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ከመሙላት ባሻገር የኤክስፖርት ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የግድ መሆን አለበት፡፡ የኤክስፖርት ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለና የገቢ ምርቶች ዋጋ በጣም ውድ እየሆነ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ተሁኖ ከሰላም ይልቅ ግጭት ላይ ጊዜን ማጥፋት ጤነኝነት አይደለም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች በጦርነትና በድርቅ መፈናቀላቸው፣ ከአቅም በላይ የሆነው የኑሮ ውድነት በርካታ ሚሊዮኖችን እያስጨነቀ መሆኑ አይዘንጋ፡፡

የሰላም ዕጦት የእርሻ ሥራዎችን ከማስተጓል በተጨማሪ፣ የተመረቱ ሰብሎች ወደ ገበያ እንዳይቀርቡ ከፍተኛ ተግዳሮት መፍጠሩ ይታወቃል፡፡ ከብልሹው የግብይት ሥርዓት ባልተናነሰ የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱ በሰላም ዕጦት ሲቆራረጥ፣ በአርሶ አደሮችም ሆነ በሸማቾች ላይ ከባድ ጫና ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት መንገዶች ሲዘጋጉ እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች ወደ ገበያ ባለመቅረባቸው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪዎች ታይተዋል፡፡ አጋጣሚውን ለመጠቀም የፈለጉበት ስግብግቦች የሰቀሉትን ዋጋ ማውረድ ቀርቶ በየዕለቱ ሲጨምሩ ከልካይ የለባቸውም፡፡ በዚህ መሀል አምራቾቹ አርሶ አደሮችም ሆኑ ተከላካይ የሌላቸው ሸማቾች የጉዳቱ ሰለባ ለመሆን ተገደዋል፡፡ የሰላም መታወክ ያልታሰበ ሲሳይ የሚያስገኝላቸው ደግሞ እየተናበቡ ግጭቶች እንዲቀሰቀሱና እንዲስፋፉ የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ከአብዛኞቹ ግጭት በስተጀርባ ያሉት ሴረኞች አገር ብትታመስና ሕዝብ በከባዱ ቢጎዳ ደንታቸው አይደለም፡፡ መንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የጥቅም ተካፋዮቻቸውም እንዲሁ፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል ብሔራዊ መንግሥታት አንድ መገንዘብ ያለባቸው ቁምነገር፣ ከግጭቶች በተጨማሪ ድርቅና ረሃብ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ በስፋት እያንዣበቡ መሆናቸውን ነው፡፡ ሰሞኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በድርቅ ለተጎዱ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ዕርዳታ ካልቀረበ፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ የከፋ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡ በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ ለሚገኙ 32 ሚሊዮን ሰዎች ሰባት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ ከለጋሾች 2.4 ቢሊዮን ዶላር መሰባሰቡን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ በማጣታቸው ምክንያት ለፅኑ የምግብ ችግር የተጋለጡ የድርቅ ተጎጂዎችን መደገፍ ካልተቻለ፣ ቀውሱ ተባብሶ ወደ አስከፊ ሁኔታ በመለወጥ በርካቶች ሊሞቱ እንደሚችሉም ተመድ አክሏል፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ከድርቅ ተጎጂዎች በተጨማሪ በርካታ ሚሊዮኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶችና ግጭቶች ተፈናቅለው የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ያለህ እያሉ ነው፡፡

አፍሪካ ውስጥ በአየር ንብረት መዛባትና በግጭቶች ሳቢያ የተራቡ ሰዎች የሞት ቁጥር እየጨመረ መሆኑንና ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ውስጥ በ40 ዓመታት ታይቶ የማያውቅ አደገኛ ድርቅ መከሰቱን ከተመድ መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ በድርቁ ምክንያት አዝመራዎች መበላሸታቸውና 13 ሚሊዮን ያህል እንስሳት መሞታቸውም ተመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያም በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ፅኑ የምግብ ችግር መፍጠራቸው በተመድ መግለጫ ውስጥ ተካቷል፡፡ እንደሚታወቀው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወገኖች፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ማግኘት አለመቻላቸውን በስፋት እየተናገሩ ነው፡፡ ሸምቶ አዳሪው ብዙኃኑ ሕዝብም በምግብ ዋጋ ንረት ምክንያት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ መምራት ተስኖታል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ አስተማማኝ ባልሆነበት በዚህ የከፋ ጊዜ፣ ወገብን ጠበቅ አድርጎ ራስን ለመቻል ከመንቀሳቀስ ውጪ ያሉ ከንቱ ድርጊቶች ለማንም አይጠቅሙም፡፡ የምግብ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ አማራጮች ላይ መረባረብ የግድ ነው፡፡ የመኸር እርሻው ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!       

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...