ከዓመታዊ ውድድሮች መካከል በቀዳሚነት ዋጋ የሚሰጠው በሁለት ዓመት አንዴ የሚከናወነው ሻምፒዮና የዓለም ፈርጦችን ያገናኛል፡፡ በርካታ አትሌቶች በሻምፒዮናው ለመካፈል የምንጊዜም ህልማቸው ነው፡፡
በተለያዩ አገሮች የሚሰናዳው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከኦሊምፒክ ቀጥሎ በአትሌቶች እንዲሁም በተመልካች ተጠባቂ ነው፡፡ አትሌቶች በዚህ ውድድር ለመካፈል ዓመቱን ሙሉ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ በቤት ውስጥ በአጭርና በመካከለኛ፣ እንዲሁም በውጭ በተመሳሳይና በረዥም ርቀቶች፣ በማራቶን፣ በዕርምጃ፣ እንዲሁም በሜዳ ተግባር አገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶች በአኅጉራዊ ውድድሮች እየተካፈሉ ለዓለም ሻምፒዮናው ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡
የዓለም አትሌቲክስም በሻምፒዮናው መቃረቢያ ይፋ በሚደረጉ የማለፊያ መሥፈርት መሠረት፣ አትሌቶች በአባል አገሮች እንዲመረጡ ያሳውቃል፡፡ በዚህም መሠረት ፌዴሬሽኖች በግል፣ በአገር ውስጥና በአኅጉር ውድድሮች ተሳትፎ ያደርጉና ጥሩ ሰዓት ያስመዘገቡ አትሌቶችን መርጠው ለሻምፒዮናው የማሰናዳት ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ምንም እንኳን ብሔራዊ ፌዴሬሽን የአገር ውስጥ ውድድሮች አድርጎ አትሌቶች የመምረጥ ሥልጣን ቢኖረውም፣ የዓለም አትሌቲክስ ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት መመራት ግዴታ አለበት፡፡
የዓለም አትሌቲክስ አትሌቶች በግልም ሆነ አገራቸውን ወክለው በተሳተፉበት ሻምፒዮና የሚያስመዘግቡትን ሰዓት የመመዝገብ ሥልጣን አለው፡፡
በዚህም መሠረት በዓለም ሻምፒዮና መካፈል የሚችሉ አትሌቶችን ለመለየት የምርጫ መሥፈርት (Qualification Standard) ያስቀምጣል፡፡ የመግቢያ ሰዓት ደረጃው በሁሉም ርቀቶች የሚለያይ ነው፡፡
ከነሐሴ 13 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በሃንጋሪ ቡዳፔስት ለሚሰናዳው የዓለም ሻምፒዮና የማለፊያ መሥፈርቱን ከአንድ ዓመት አስቀድሞ የዓለም አትሌቲክስ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የዘንድሮውን ሻምፒዮና ተከትሎ የዓለም አትሌቲክስ ይፋ ያደረገው የማለፊያ ደረጃ ከቀድሞው ጠንከር ያለ መሆኑን ባለሙያዎች አንስተዋል፡፡
ቀድሞ 50 በመቶ የዓለም አትሌቲክስ ይፋ በሚያደርገው መሥፈርት እንዲሁም ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ አትሌቶች በዓለም በተቀመጠላቸው ደረጃ (World Ranking) መሠረት ተመራጭ እንደሚሆኑ ያስቀምጣል፡፡
የዘንድሮውን ሻምፒዮና አስመልክቶ ይፋ በሆነው ሚኒማ መሠረት፣ በተለይ በ5,000 እና 10,000 ሜትር ርቀቶች የተቀመጠው የማጣሪያ ሰዓት ከምንጊዜውም በላይ ከባድ መሆኑ ተነስቷል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ከዓመት በፊት ይፋ ባደረገው ሚኒማ መሠረት፣ አትሌቶች ለ5000 ሜትር 13፡07፡00፣ ለ10000 ሜትር 27፡10፡00 ወንዶች ማሟላት እንደሚገባቸው አስቀምጧል፡፡ ለሴቶች ደግሞ እንደቅደም ተከተሉ 14፡57፡00 እንዲሁም 30፡40፡00 ማሟላት እንደሚገባቸው አስቀምጧል፡፡
ይህም ላለፈው የዓለም ሻምፒዮና ከወጣው የማጣሪያ ሚኒማ ሰዓት ማሻሻያ አድርጓል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ በሌሎቹም ርቀቶች ላይ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታውቋል፡፡፡
የኢትዮጵያ 10 ሺሕ ሜትር የቅድመ ማጣሪያ ውድድሮች
ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና ከምትጠበቅበት ርቀቶች መካከል የ10 ሺሕ ሜትር ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሜዳሊያ ከሚሰበስቡባቸው ርቀቶች መካከል 10 ሺሕ ሜትር ቀዳሚው ነው፡፡
በርቀቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ተጠባቂ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ መሠረት ሰዓት ያላቸው አትሌቶችን ለመምረጥ የማጣሪያ ውድድር ያሰናዳል፡፡ በኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ደረጃን መሥፈርት ማሟላት የሚችል የውድድር ስታዲየም ባለመኖሩ በውጭ አገር ሲደረግ ከርሟል፡፡
ለዚህም የኔዘርላንዷ ሄንግሎ ከተማ ተመራጭ በመሆኗ የረዥም ርቀት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማሟያ ውድድሮች ያደርጉባታል፡፡
በዓለም ሻምፒዮናው ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ የሚከናወነው የማጣሪያ ውድድሩ ከአንድ እስከ ሦስት የወጡ አትሌቶች በቀጥታ ይመረጣሉ፡፡ አራተኛ የሚወጣው በተጠባባቂነት ይያዛል፡፡
የማጣሪያ ውድድሩ በሄንግሎ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታ ላይ መገኘቷና አትሌቶቹም የማሟያ ሰዓቱን በኢትዮጵያ ማምጣት አይቻልም ከሚል ድምዳሜ መደረሱ እንደሆነ ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡
በኢትዮጵያ የማሟያ ሰዓት ሙከራ ተደርጎ አያውቅም፡፡ በአንፃሩ የዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና የሚካፈሉ የ10 ሺሕ ሜትር አትሌቶች ለመምረጥ የአገር ውስጥ ማጣሪያ ለማድረግ ማቀዱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
የማጣሪያ ውድድሩን በሐዋሳ ስታዲየም በሰኔ ወር እንደሚያደርግ ያስታወቀው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ ትችት እየቀረበበት ነው፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የማጣሪያ ውድድር ለማድረግ ሐዋሳ መምረጡን ተከትሎ የተለያዩ አሠልጣኞች የሚፈለገውን ሰዓት ማምጣት አይቻልም ሲሉ መከራከሪያ እያቀረቡ ነው፡፡
ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ አስተያየት መሠረት፣ የዓለም አትሌቲክስ ያስቀመጠውን የ10 ሺሕ ሜትር ሰዓት ማለትም በወንዶች 27፡10፡00 እንዲሁም በሴቶች 30፡40፡00 ማምጣት ቀላል እንዳልሆነ ያነሳሉ፡፡
እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ከሆነ የማጣሪያ ውድድሩ በደፈናው በሐዋሳ አዘጋጅቶ አትሌቶች ከመምረጥ ይልቅ፣ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ውድድሩን ማከናወን እንደሚገባ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የዓለም አትሌቲክስ የ10 አትሌቶች ስም ዝርዝር ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንዲልክ በሚያሳውቅበት ወቅት፣ የተመረጡትን አትሌቶች አዘጋጅቶና በማጣሪያው አሳትፎ መምረጥ እንደሚቻል ያነሳሉ፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የማጣሪያ ውድድር ተደርጎ አያውቅም፡፡ በዘንድሮ ሻምፒዮና ማሟያ ሐዋሳ ላይ ሰዓቱ ይመጣል? አይመጣም? የሚለውን ለማረጋገጥ ቀድሞ መሥራትና መሞከር ይገባል፤›› በማለት አሠልጣኙ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
በሌላ በኩል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሐዋሳ ሊያደርገው ያቀደው የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ከዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና ያላገኘ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ከሆነ ዕውቅና ባልተሰጠበት ከተማ ቅድመ ማጣሪያ ውድድር ማድረግ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችልና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑንም አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ያሳስባሉ፡፡
በሌላ በኩል ለፌዴሬሽኑ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች አስተያየት ከሆነ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በውጭ አገር ማጣሪያውን በማድረግ ለከፍተኛ ወጪ ከመጋለጥ ለመዳን በአገር ውስጥ ማወዳደሩን መርጧል፡፡ አጋጣሚውም ለአዳዲስ አትሌቶች ዕድል የሚከፍት በመሆኑ በአገር ውስጥ ማድረጉ ተመራጭ አድርጎታል፡፡
የሚፈለገውን ሰዓት ለማምጣትም አትሌቶች በአሯሯጭ እንዲሮጡ እንደሚደረግ እየተነገረ ይገኛል፡፡
የማጣሪያ ውድድሩ በሐዋሳ ይከናወን አይከናወን በሚለው ጉዳይ የተለያዩ ትችቶች መቅረባቸውን ተከትሎ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለሪፖርተር አስተያየት ከመስጠት የተቆጠበ ሲሆን፣ በቅርቡ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ገልጿል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ በጉዳዩ መወያየቱ ተሰምቷል፡፡ አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪውን ተከትሎም ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. አሠልጣኞች ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ይመካከራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደ ሪፖርተር ምንጭ ከሆነ በሐዋሳ ይደረጋል ተብሎ የተገለጸው ሐሳብ በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና የሌለው በመሆኑ ሊቀለበስ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡