(ክፍል አራት)
በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ)
ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በውስጡ በተለይም በሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች (ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ) መካከል ያሉትን የተዛቡ መዋቅራዊ ግንኙነቶችና ችግሮች ለማመላከት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ከሦስቱ ቅርንጫፎችም በተለይ አንደኛው ‹‹ሕግ አውጭው›› አካል በተደጋጋሚ ሕገ መንግሥቱን እየጣሰ፣ የመንግሥት ሥልጣኑን ቀስ በቀስ በመጠቅለል ራሱን እያጠናከረ መሄዱንና የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መርገጥንም ባህል አድርጎ እንደያዘ፣ ሁለቱን የመንግሥት ቅርንጫፎችም (ሕግ አውጭውንና ተርጓሚውን) በማቀጨጭ አቅም እንዳሳጣቸው ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር ዋናው መንስዔም በሕወሓትና በጊዜው አጋሩ በነበረው ኦነግ የተተከለው፣ በብሔር ፖለቲካ ላይ የቆመው ሕገ መንግሥት እንደሆነና ባለፉት 30 ዓመታት ሥር በመስደድ እያደገ የመጣውን የዘረኝነት (‹‹አፓርታይድ››) አምባገነናዊ ሥርዓትም እንዲያቆጠቁጥ ያደረገው እሱ መሆኑን ለማሳየት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡
ይህ በብሔር ፖለቲካ ላይ የቆመው አስከፊና ኋላቀር የዘረኝነት ሥርዓት አገራችንን ለማያባራ የእርስ በርስ ግጭትና የውጭ ጣልቃ ገብነት ዳርጓት ሰላም በማሳጣት፣ ዛሬ መውጫው የጠፋ አዙሪት ውስጥ ገብታ በመዛቀጥ ላይ ትገኛለች፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ከእዚህ አዙሪት ለማውጣት ያለን ዋና መፍትሔ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ወይም መቀየር እንደሆነም ያለማቋረጥ ለማሳሰብ፣ እኔም እንደ ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ድምፄን ከፍ አድርጌ ለማሰማት ቢያግዝ በሚል ነው በአቅሜ እነዚህን ጽሑፎች በተከታታይ ማቅረብ የጀመርኩት፡፡ ይህን የአገራችን ሰላም፣ አንድነትና ዕድገት የዜጎች ነፃነትና ኅብረት እንዳይዳብር ትልቅ እንቅፋት የሆነውን ኋላቀር ሕገ መንግሥትም፣ በሕዝብ ምክክርና መግባባት ማሻሻል ወይም መቀየር ከተቻለ በተፈጥሮ ሀብትና በጠንካራ ሕዝብ የታደለችዋና የጀግኖች አምባ የሆነችው እናት አገራችን ኢትዮጵያ ዕድል ቀንቷት ትክክለኛ አመራር ካገኘች፣ በጠንካራ ዜጎቿ ከዘለዓለም የድህነትና የቀውስ አዙሪት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወጥታ ለማደግና ከኋላዋ እየመጡ ቀድመዋት የሄዱትንም ለመቅደም ምንም የሚያግዳት ኃይል እንደማይኖር አልጠራጠርም፡፡ እውነተኛዋ ፌደራላዊት፣ ዴሞክራሲያዊትና ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በእርግጥ መገንባት የሚቻለውም ሕዝብ ጠባቂ፣ ሀቀኛ፣ ፍትሐዊና ዘመናዊ ሕገ መንግሥት ስታገኝ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
በዚህ ጽሑፌ ይህንን ኋላቀር፣ ከፋፋይ፣ ዘረኛና ብሔር ተኮር የሆነ ሕገ መንግሥት ለምንና እንዴት አድርጎ ነው ማሻሻል ወይም መቀየር የሚቻለው ለሚለው ጥያቄ አስተያየቴን ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ ይህን ከባድ ጥያቄ ለመመለስ ከመሞከሬ በፊት ግን ለአንባቢያን አንድ መሠረታዊ እውነታ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ይኸውም ዛሬ በአገራችን ፖለቲካ መስክ ላይ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል (እንዲቀየር) የሚፈልጉ፣ ጭራሽ ‹‹መነካት የለበትም›› የሚሉ ጎራ ለይተው የሚፋተጉ ወይም ገመድ የሚጓተቱ (“Tug Of War”) በዋነኝነት ሁለት ኃይሎች ወይም ‹‹የፖለቲካ ልሂቃን ቡድኖች›› መኖራቸውን ነው፡፡ በሐሳብ መለያየቱ ምንም ክፋት የለውም፡፡ ችግሩ ባለፉት የአገራችን የ50 ዓመታት ታሪክ እንደታየው፣ በቅርቡም ሕወሓት በቀሰቀሰው አስከፊ ጦርነት እንደታዘብነው፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልሂቃን ልዩነታቸውን በሰላም መፍታት ሲያቅታቸው ሁልጊዜ ሥራዬ ብለው አገራችንን ወደ ከፋ ቀውስ እንድትገባ ነው የሚመሯት፡፡ ሕዝብን ለማገልገል ሳይሆን፣ በመንግሥት ሥልጣን ላይ በማተኮር ሲሻኮቱና እርስ በርስ ሲጫረሱ፣ ንፁኃኑን ሕዝብም ያለማቋረጥ አስጨርሰውታል፡፡ አገራችንን ሌሎች ከኋላዋ እየተነሱ ሲቀድሟት፣ እሷ ግን ምን ያህል ለዓመታት ካለችበት ጭራሽ ወደ ኋላ እየራቀች እንድትሄድ እንደዳረጓትም ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በመሀሉ በተለይም አገር የሚገነባው ወጣቱ ትውልድ በቅብብሎሽ በየተራ እየጠፋ ነው ያለው፡፡ በፖለቲከኞች ሽኩቻ ሳቢያ የደም መፋሰስ ባህል መቆም አለበት፡፡
ስለዚህ የአገራችን የፖለቲካ ልሂቃንና መሪዎች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ለአገራቸው ሰላም ሲሉ ብቻ ሳይሆን፣ ለራሳቸውም ደኅንነትና ሰላም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያሳትፍ ሁሉን አካታች የሆነ አገራዊ ምክክር እንዲደረግና ሕገ መንግሥቱ በሕዝብ ፍላጎትና መግባባት እንዲሻሻል (እንዲቀየር) አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር መተባበር ይኖርባቸዋል፡፡ ያን ቢያደርጉ ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ ሠርተው ለማለፍም ዕድል ያገኛሉ፡፡ የአንድ አገር ሕገ መንግሥት በሕዝብ ፍላጎትና በሥነ ሥርዓት እንዳስፈላጊነቱ ካልተሻሻለና ካልተጠገነ ፈጣን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ኑሮ ዕድገት ማምጣት አይቻልም፡፡ ሕገ መንግሥትን ያህል አገር የተሸከመ ይቅርና ቤት እንኳን እንዳይፈርስ በየጊዜው ይጠገናል፡፡
‹‹ሕገ መንግሥቱ መነካት የለበትም›› የሚሉት በዋነኝነት አሁን ባለው የብሔር ፖለቲካና ዘረኛ ሥርዓት የሚጠቀሙ፣ በሕይወት እስካሉ ድረስም የደሃይቱን አገር ሀብት ከሕዝቡ እየነጠቁ የሚያካብቱ፣ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› በሚል እነሱ ከበሉ ሌላው ጦም ቢያድርና ሲሞቱም አገሪቱ አብራቸው ብትጠፋ ደንታ የሌላቸው ናቸው፡፡ በዋነኝነት ሕገ መንግሥቱን መሰላል አድርገው ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚያልሙ፣ ሥልጣን ከያዙም የራሳቸውን ጥቅም ማሳደድ እንጂ ለሕዝብ ሰላም፣ ለአገር አንድነትና ዕድገት የማይጨነቁ፣ በተለይም የብሔር ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ ልሂቃን ተብዬዎች ናቸው ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር የማይፈልጉት፡፡ በአንፃሩ በአገራችን ፍትሕ ተረግጦ፣ ሙስናና ዘረኝነት መረን ለቆ፣ የሚዘገንን ግፍና በደል በዜጎች ላይ ሲፈጸም ማየት ያስመረራቸውና ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል፣ በጋራ እንድትገነባና እንድታድግ፣ ከድህነትና ከቀውስ ተላቃም ሌሎች ያደጉ አገሮች የደረሱበትን ደረጃ ፈጥና እንድትደርስ የሚፈልጉና የሚመኙ ናቸው ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል (እንዲቀየር) የሚፈልጉት፡፡
- አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ለምንድነው ለአገር ግንባታና ዕድገት ማነቆ ስለሆነ መሻሻል (መቀየር) አለበት የሚባለው?
ገና ከጅምሩ ሕገ መንግሥቱ በልሂቃኑ ሲረቀቅ ሁሉን አካታችና ሰፊውን ሕዝብ ያሳተፈ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ቢያንስ አንድ ትልቅ ብሔር የአማራ ሕዝብ በሚገባ አልተሳተፈም፡፡ ታዋቂ ኅብረ ብሔር ፓርቲዎችን ኢሕአፓንና መኢሶንንም አላካተተም፡፡ በመሠረቱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ያለ ፈቃዳቸው በጥቂት የብሔር ፖለቲካ ልሂቃን ለኢትዮጵያዊነት ሳይሆን ‹‹ለብሔር ዜግነት›› ታማኝ እንዲሆኑ በዚህ ሕገ መንግሥት ነው የተፈረደባቸው፡፡ በአገራችንም እውነተኛ ፌደራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ኅብረ ብሔራዊ ሳይሆን ዘረኛና ከፋፋይ፣ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነትን የሚያሰፍን ሳይሆን ዜጎችን ለግፍና ለሰቆቃ የሚያጋልጥ፣ አገርን የሚገነባ ሳይሆን የሚያናጋና ከባሰም የሚያፈርስ፣ ኋላቀር ሥርዓት የተተከለው በዚህ ሕገ መንግሥት አማካይነት ነው፡፡ ሕዝቡን ለሰላምና ለፍቅር ሳይሆን ለቂም በቀልና ለግጭት፣ ለሙስና፣ ለመሬትና ለሀብት ዝርፊያ፣ ብሎም ለማያባራ ድህነት፣ ለረሃብና ለድርቅ፣ ለኑሮ ውድነትና ለስደት እንዲጋለጥ ያደረገው በመሠረቱ ይህ ሕገ መንግሥትና እሱ የወለደው ዘረኛ ሥርዓት ነው፡፡ አገራችን በጋራና በሰላም ከማደግና ወደፊት ከመራመድ ይልቅ፣ ሌትና ቀን በድህነትና በፖለቲካ ቀውስ እንድትማስን ያደረጋትም እሱ ነው፡፡
በሕገ መንግሥቱ ያሉትን በርካታ የተዛቡ አንቀጾች በዚች አጭር ጽሑፍ ለመዘርዘር ቦታው አይበቃኝም፣ በቂ እውቀትም አለኝ ብዬ ራሴን አላሞካሽም፡፡ ይሁንና አሁን ላለውና በብሔር ፖለቲካ ላይ ለቆመው ሕገ መንግሥት አንድ ዋና አውታር የሆነውን ጠቅሼ ማለፍ እወዳለሁ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 8 (‹‹የሕዝብ ሉዓላዊነት›› የሚል አርዕስት በተሰጠው) በቁ/1፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው›› ይላል፡፡ ቀጥሎም በዚሁ አንቀጽ በቁ/3 ‹‹ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል›› ይላል፡፡ ይህ እንግዲህ በእኔ አስተያየት በእዚህ አንቀጽ ቢያንስ በተዘዋዋሪ የተቀመጠው ማንኛውም ‹‹ኢትዮጵያዊ ዜጋ››፣ በብሔሩ ወይም ብሔረሰቡ አማካይነት እንጂ፣ በራሱ ወይም በግሉ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ የአገሩ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት አይደለም ማለት ነው፡፡ ለዚያውም እያንዳንዱ ዜጋ ‹‹በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሚመርጣቸው ተወካዮቹ አማካይነት›› ነው ሉዓላዊነት ያለው የሚለው ሕገ መንግሥቱ (በነገራችን ላይ በሕገ መንግሥቱ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዜጋ›› ታዲያ ማነው የሚለው በግልጽ አልተብራራም)፡፡
እዚህ ላይ ዋናውን ፍሬ ነገር እንድትገነዘቡልኝ በትህትና የምጠይቀው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደደም ጠላም ማንነቱ (‹‹ዜግነቱ››) የሚገለጸው ወይም በሕግ የሚታወቀው፣ በዋነኝነት በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን ለየትኛው ብሔር ወይም ብሔረሰብ አባል በመሆኑ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ‹‹ኢትዮጵያ›› ወይም ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የሚባሉት የማንነቱ መገለጫዎች አይደሉም፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቅድሚያ ታማኝነቱ (Loyalty) ለኢትዮጵያ አገሩ ሳይሆን፣ ‹‹ማንነቱ›› ለሚገለጽበት ለብሔሩ ወይም ለብሔረሰቡ ነው ማለት ነው፡፡ የአንድ አገር ዜጎች ለአገራቸው ፍፁም ታማኝ ካልሆኑና ከፍተኛ አገራዊ ፍቅር ከሌላቸውም አገርን በቁጭትና በጋራ ለመገንባት በጣም አዳጋች ነው የሚሆነው፡፡
በዚህ ዓይነት በሕገ መንግሥቱ ሳቢያ ባለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊነት የሚባሉት ዳብዛቸው ቢጠፋ ምንም አያስገርምም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በአንድ ብሔር/ብሔረሰብ ውስጥ በመንግሥት አካል እየተመደበ፣ ‹‹ማንነቱ››] እንዲታወቅ የብሔሩ ወይም የብሔረሰቡ ስም በመታወቂያው ላይ ሲለጠፍበት ነው የኖረው፡፡ እሱ ብቻ አይደለም በሄደበት ሁሉ መስክ፣ በትምህርት ቤት፣ በመሥሪያ ቤት፣ በማኅበራዊ ኑሮው ሁልጊዜ የሚሰማው ፍቅርና ስሜት ስለአገሩ ሳይሆን ስለብሔሩና ብሔረሰቡ፣ ስለቋንቋው ትልቅነትና ከሌላው በምን እንደሚለይ ወይም እንደሚበልጥ በህሊናው እንዲያሰላስል ሆኖ ነው የተቀረፀው፡፡ ብሔሩና ብሔረሰቡ የአገሩ አንድ አካልና አምሳል እንደሆነ እንዳያስብ ነው የተደረገው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ታማኝ በመሆን፣ ስለኢትዮያ የጋራ ልማትና ግንባታ ሌትና ቀን ባይጨነቅና ቁጭት ባይዘው፣ በአንፃሩ ሁልጊዜ ስለዘሩና ብሔሩ ቢያስብና ቢጨነቅ፣ ሌሎችንም በዘርና በብሔር መነጽር እያየ ቢጠራጠርና ቢርቅ ለምን ያስገርማል፡፡
ደግነቱ ኢትዮጵያውያን ምንም ያህል በብሔር፣ ዘር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ቢለያዩም ለዘመናት በማኅበራዊ ኑሮ ተሳስረው፣ ተጋብተውና ተዋልደው በሰላምና በፍቅር ስለኖሩ ባለፉት 30 ዓመታት ጨርስው አልተለያዩም፡፡ የኅብረተሰብ እርስ በርስ መተሳሰር ባህል ደግሞ አገራችን እያደገች ስትሄድና ዜጎች በመሠረተ ልማት በበለጠ ሲገናኙ፣ ሕዝቡም ከገጠር ይልቅ በከተማ መኖርን ሲያዘወትር፣ የብሔርና ብሔረሰብ ወይም የዘር ልዩነቱ እየጠበበና ለመለየትም አስቸጋሪ እየሆነ እንደሚሄድ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ አዲስ አበባንና ባለፉት ዓመታት ሌሎች እንደ አሸን የፈሉትን የኢትዮጵያ ከተሞች መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደ መንግሥት አያያዝ ከሆነ በዘርና በቋንቋ በተላለቁ ነበር፡፡ ወደ አደጉ አገሮች ስንሄድ ደግሞ ለምሳሌ የኒውዮርክ ከተማ ዜጎች ከሁሉም ዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ እየመጡ የሚኖሩባት ስለሆነች፣ በውስጧ እስከ 200 ከሚደርሱ አገሮች (ብሔሮች) የመጡና 800 ያህል የሚሆኑ ቋንቋዎች የሚናገሩ ተደባልቀው በሰላም እንደሚኖሩባት ይነገርላታል፡፡ እንግዲህ የኒውዮርክ ከተማ ኑዋሪዎችን በብሔር፣ በዘርና በቋንቋ እየለዩ መታወቂያ በመስጠት በእዚህ ክልል (ክፍለ ከተማ) ኑሩ ቢባሉ ምን ሊመጣ እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ፣ እብደት ነው የሚሆነው፡፡
አዲስ አበባንም ብሔርተኞች ወደ ኋላ ሊስቧት ቢፍጨረጨሩም የዕድገት አቅጣጫዋ ከኒውዮርክ ብዙም አይለይም፡፡ ይህን ዓይነት የዜጎችና የኅብረተሰብ ትስስር በተለይ በከተሞች ለማስቆም አይቻልምና፡፡ መቆምም የለበትም፡፡ አዲስ አበባን በአንድ ብሔር (ዘር) ሕዝብ እንደ ቀለበት አካቦ ዜጎችን እርስ በርስ እንዳይገናኙና እንዳይዋሀዱ ለማድረግ መሞከር የዋህነት ወይም የኅብረተሰብ ዕድገት ሕግን አለመረዳት ነው፡፡ ዜጎች ሲዋሀዱ ለአገር ዕድገትና ሥልጣኔ ትልቅ አቅም፣ ሀብትና ውበት ይሰጣሉ፡፡ ያ ማለት ደግሞ የመጡበትን ብሔር፣ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ በግድ ይቀማሉ ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምናልባትም ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ ያለ ሥጋት፣ በየትኞቹም የአሜሪካ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ፣ እንደ ሁሉም ዜጎች ከፈለጉ እምነታቸውን፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ቅርሳቸውን በመሰላቸው ዘዴና ማኅበራዊ ኑሮ የማዳበር ሙሉ ነፃነትና መብት አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የብሔር ፖለቲከኞች ግን ይህን አይፈልጉም፡፡ ከተሞችንም ሆነ የገጠር አካባቢዎችን በእነሱ ዘር ብቻ ጠቅልለው ለመያዝ ይፍጨረጨራሉ፡፡ ይህን ጉድ ነው ሕገ መንግሥቱ ለአገራችን ያመጣው፡፡
አሁን በኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪዎች አዲስ አበባን ዙሪያዋን እንደ ቀለበት ከቦ የተቋቋመውን ‹‹የሸገር ከተማ›› የኦሮሞ ተወላጅ ብቻ ይኑርበት ቢባል፣ ምን ያህል ከዘመኑና ከከተሞች ዕድገትና ሥልጣኔ ወደ ኋላ የቀረ አስተሳሰብ እንደሆነ ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ በኢትዮጵያውያን ላይ በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅና ሰብዓዊ ርህራሄ የጎደለው፣ የሚዘገንንና የዘረኝነት ጭካኔ በመፈጸም መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ይህ ነው አንዱ ሕገ መንግሥቱ ለአገራችን ግንባታ ‹‹ዕድገትና ሥልጣኔ›› ካተረፈላት ‹‹ትሩፋቶች››፡፡ በአጠቃላይ አሁን ባለው ሕገ መንግሥት ጥላ ሥር ተወልደው ያደጉት የአዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያውያን፣ ከአገራቸው ይልቅ ብሔራቸውና ብሔረሰባቸው በህሊናቸው ቢቀረፅባቸውና በርካቶቹም ሳይወዱ በጠባቡ በመመልከት የሌላውን ባህል፣ ብሔርና ቋንቋ (ወይም የፈረደበትን የአማራ ሕዝብ) ወይም አገራቸውን ኢትዮጵያን ቢጠሉ ምንም አያስገርምም፡፡ በዘረኝነት መርዝ መበከል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነታቸውንና ኢትዮጵያ አገራቸውን ብዙም አያውቁምና፣ ወይም ለማወቅ ዕድል አልተሰጣቸውምና፡፡ በተለይም ከከተማ ውጪ በገጠር ለሚኖሩና ከራሳቸው ወጣ ብለው የሌላ ብሔርና ብሔረሰብ ተወላጅ ወይም ቋንቋ ለማያውቁ፣ አብረውም ላላደጉ፣ ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊነት የሚለው ብዙም ትርጉም ባይሰጣቸው ምንም ሊያስገርመን አይገባም፡፡ ሥርዓቱ የወለደው ነውና፡፡ ከራሴ ተሞክሮ ለመነሳት በአዲስ አበባ ዙሪያ በሰበታ፣ ቡራዩና አሸዋ ሜዳ አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ዜጎች አማርኛ መናገርና መጻፍ የማይችሉ የኦሮሞ ተወላጆች እንዳሉ ሳይና ስሰማ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ 12ኛ ክፍልና ኮሌጅም ሳይቀር ጨርሰው ሥራ ፍለጋ ወደ አገራቸው ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ክልል ሲመጡ እንግሊዝኛም አማርኛም በሚገባ መናገር፣ ማንበብና መጻፍ ስለማይችሉ የሚቸገሩና ተመልሰው እንደ ማይም የሚሆኑ እንዳሉም ሰምቼ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡
ይህንን ነው እንግዲህ ‹‹የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን›› በተለይ በብሔር ፖለቲካና በሕገ መንግሥቱ ሳቢያ ለደጉ የኦሮሞ ሕዝብ ያመጡለት ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት ነው፡፡ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ከማንም በበለጠ የጎዳው የኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ በተለይም ወጣቶችን ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም፡፡ የኦሮሚኛ ቋንቋ አኅጉር ተሻግረው ከባዕድ አገር ባመጡለት የላቲን ፊደል ቀርቶ፣ በአገራችን በግዕዝ ፊደል ቢጻፍ ኖሮ ምናልባትም እስከ ዛሬ ድረስ ኦሮሚኛን ከአማርኛ ተናጋሪው የሚበልጥ ሕዝብ በተናገረው ነበር የሚል ግምት አለኝ፡፡ የሚገርመው የግዕዝ ቋንቋ በበርካታ የውጭ አገር ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ካሪኩለም ተካቶ ተማሪዎች እንዲማሩት እየተደረገና ለምርምርም እየዋለ በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ ነው፡፡ ይህ ለአገራችን ትልቅ ኩራት ነው፡፡ የእኛ ‹‹ፖለቲካ ልሂቃን›› በአገራቸው ታሪክና በውሸት ትርክት እርስ በርስ ሲባሉ በአንፃሩ ፈረንጆች የአገራችንን ታሪክና ባህል እያሳደጉልን ነው፣ ይገርማል፡፡
በሕገ መንግሥቱና እሱ በተከለው ዘረኛ ሥርዓት ሳቢያ ባለፉት 30 ዓመታት በአገራችንና ሕዝባችን ላይ የደረሰውን ግፍና በደል ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ ሌላ የሚያሳዝነው ደግሞ በከተማ ተዋህደው በሚኖሩ በተለይ በዜጎች ላይ ስንት ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በሰላም ሲታገሉ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በብሔራቸውና ብሔረሰባቸው መታወቂያቸው እየተለዩ በመለቀም ስንቶች በግፍ ታስረዋል፣ ተገድለዋል፣ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ዛሬም በገፍ እየታፈኑና በየእስር ቤቱ እየታጎሩ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሕወሓት አስተዳደር እስር ቤት በብዛት የሚታጎሩትና እየታፈኑ ዳብዛቸው የጠፋው በአብዛኛው የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ነበሩ ይባላል፡፡ በእርግጥ የአማራ ተወላጆች ሕወሓት ገና ሥልጣን በያዘ በበነጋው ነበር ዕልቂት የታወጀባቸው፡፡ ይሁንና ዛሬ ደግሞ ጎልቶ እንደሚታየው በጠራራ ፀሐይ የሚታፈኑትና እስር ቤት የሚታጎሩት በብዛት የአማራ ተወላጆች ናቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ አማሮችም በወለጋና በሌሎችም የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተጨፍጭፈዋል፡፡ ‹‹መጤ ናችሁ ወደ አገራችሁ ሂዱ›› እየተባሉም ተፈናቅለዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንኳን በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ (‹‹የሸገር ከተማ››) ለዓመታት ከኖሩበት ሠፈርና ቤት እየተፈናቀሉ ቤትና ንብረታቸውም እየወደመባቸው ወደ ጎዳናና በረሃ የተወረወሩ፣ ለአውሬም የተዳረጉ ብዙ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹የሸገር ከተማ›› ግፍና መፈናቀል እንደ አማራ ተወላጆች ባይበዛም፣ ለሌሎችም ኢትዮጵያውያን እንደ ጉራጌና ጋሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ለመሳሰሉትም ነው የተረፈው፡፡ በአጭሩ ለእዚህ ሁሉ ግፍ መነሾ የሆነው ሕገ መንግሥቱና በእሱ ላይ የቆመው የብሔር ፖለቲካና የዘረኛ (‹‹አፓርታይድ››) ሥርዓቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች እንግዲህ እንዴት ብላ ነው አገራችን የምትገነባው?
በአጠቃላይ ገና ከጅምሩ ሕገ መንግሥቱ ሲነደፍ በቋንቋና አካባቢ ቢለያዩም፣ በታሪክና በባህል የተሳሰሩትንና ከ80 በላይ የሚገመቱትን የኢትዮጵያ ብሔርና ብሔረሰቦች አስማምቶ፣ በፍቅር አገናኝቶና አዋህዶ በማግባባት አገርን በእኩልነትና በአንድ ላይ በጋራ ለመገንባት ታስቦ ሳይሆን፣ አገርንና ሕዝብን ከፋፍሎ ለመግዛትና የቁርጡ ቀን ከመጣም የኢትዮጵያን አንድነት አናግቶ በማፍረስ፣ የራስን ብሔርና (ክልል) ከተሳካም በዙሪያ ካሉት ሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች መሬት በጉልበት ነጥቆ በመጠቅለል ለመገንጠል ታቅዶ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም፡፡ ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ደግሞ ከወልቃይት ጠገዴ፣ ከጠለምትና ከራያ የተሻለ ያለ አይመስለኝም፡፡ ለእዚህ ሀቅ ሌላ ጥሩ ማስረጃ ደግሞ ሕወሓት በትግራይ በሺሕ የሚቆጠሩ የሰሜን ዕዝ ወታደሮችን በዘራቸው በተለይም አማራዎችን እየለየ በተኙበት እያረደ ጥሎ በቀሰቀሰው ጦርነት፣ በአገራችን የደረሰውን ውድመት ብቻ መመልከት ይበቃል፡፡ የጦርነቱ ዓላማም ካመቸ እንደገና ወደ መንግሥት ሥልጣን ተመልሶ ኢትዮጵያን አንድ ብሔር መሠረት ባደረገ የገዥ መደብ አምባገነንነት ለመግዛት፣ ያ ካልተሳካ ግን አገሪቱን በሕገ መንግሥቱ በተከፋፈለው የብሔርና የክልል ድንበር ሰነጣጥቆና አፈራርሶ ወደ የማያባራ የቀውስ አዙሪት በመክተት፣ በግርግር ትግራይን ‹‹ነፃ አውጥቶ›› አገረ መንግሥት ለማቋቋም አቅዶ እንደነበር ሕወሓት ወደ አስከፊው ጦርነት ዘው ብሎ የገባው ግልጽ ነው፡፡ ይህን እኔ የፈጠርኩት ሳይሆን ራሳቸው የሕወሓት መሪዎችና ካድሬዎቻቸው ቢያንስ በጦርነቱ ወቅት የተናገሩት ስለሆነ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ዕቅዳቸው የከሸፈውና አገራችን ከመፍረስ የዳነችው በልጆቿ መስዋዕትነት ነው፡፡
በእዚህ እኩይ ዓላማ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የትግራይ ወጣቶችን አስጨርሶ በአገራችን ላይ በተለይም በሦስቱ ክልሎች በትግራይ፣ በአማራና በአፋር በሺሕ የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎችን ያስጨረሰበትንና ያወደመበትን ደጋግሞ መጥቀስ የሚገባው፡፡ ለታሪክ ምስክርነት ብቻ ሳይሆን ከተቻለ ለመሪዎችና ለፖለቲካ ልሂቃኑ፣ ካልሆነ ግን በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ቋሚ ትምህርት እንዲሆን ነው፡፡ ለእዚህ ሁሉ ዕልቂትና ቀውስ መነሾ ደግሞ የብሔር ፖለቲካና ዘረኛ ሥርዓት ሥር እንዲሰድ ምክንያት የሆነው ሕገ መንግሥቱ እንደሆነ መርሳት የለብንም፡፡ ያንን ሀቅ ያለማወላወል በተለይም መሪዎች በድፍረትና በቅንነት መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ እንዳለፈው ዘመን የአገራችንን ታሪክ በውሸት ትርክት ቀይሮ፣ ሕዝቡንና አዲሱን ትውልድ ማደናገር አይቻልም፡፡ ሕዝቡ ራሱ በዓይኑ ዓይቶታልና፡፡ ‹‹የብሔር ፖለቲካ ሊቀ ጠበብት›› በተለይም የሕወሓትና የኦነግ መሪዎች ግን ይህን በግልጽ የታየ ሀቅ አምኖ ለመቀበል ያዳግታቸዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንዳይሻሻል ወይም እንዳይቀየር ምንም ሳያፍሩ ሽንጣቸውን ገትረው በግንባር ቀደምትነት የሚከራከሩ እነሱ ናቸው፡፡ ለእነሱ ጥቅም ሲባል ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ቀርታ፣ በድህነት ተቀፍዳ ተይዛ፣ ምስኪኑ ሕዝቧም ሰላም አጥቶ በጦርነትና በቀውስ አዙሪት ሲማቅቅ ቢኖር ደንታ የላቸውም፡፡
ሕገ መንግሥቱን ተንተርሶ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ቀስ በቀስ ከሥር ከሥሩ እየቦረቦሩ የማፍረሱ ፕሮጀክት የጀመረው ሕወሓት ገና የመንግሥት ሥልጣን በያዘ በበነጋው ከ30 ዓመት በፊት ነው፡፡ ዜጎች በምንም ዓይነት መንገድ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የሚል የጋራ ትስስርና አገራዊ ፍቅር እንዳይኖራቸው፣ በብሔራቸውና በክልላቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና እርስ በርሳቸው እንዲጠራጠሩና እንዲጋጩ ሆን ተብሎ ለዓመታት በጠባብ ብሔረተኞቹ ሴራ ሲሸረብባቸው ነው የኖረው፡፡ ለዚህም ሴራ ዋናው መሣሪያ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠናክሩ ባህሎችንና ታሪኮችን ማጥፋት ነበር ትኩረት የተሰጠው፡፡ ለምሳሌ የዓድዋን ድል አያት ቅድመ አያቶቻችን ብሔር፣ ቋንቋና ዘር ሳይለዩ አንግበው አገራቸውን ለማዳን የወደቁለትንና ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ለመላው አፍሪካ ኩራት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማችን የአማርኛን ቋንቋ፣ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ እንደታየው የተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ከውስጥ በመከፋፈል፣ በማጣጣልና ዝቅ በማድረግ የኢትዮጵያዊነትና የዜግነት ስሜቶችን የአገር አንድነትንና ፍቅር መገለጫዎችንና ማዳበሪያዎችን እያደበዘዙ ማጥፋት ትልቁ ዘዴያቸው ሆኖ ነው ለዓመታት የዘለቀው፡፡ በዚያ ሁሉ ሴራ የሕዝቡን አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ጨርሶ ለማጥፋት ሲያቅታቸው ደግሞ በዘርና በብሔር በሃይማኖት እያለያዩ በማጋጨት፣ በመጨፍጨፍ፣ ንፁኃንን ቤታቸውን እያፈረሱ ማፈናቀልንና ማሳደድን ሥራዬ ብለው ያዙት፡፡ ግን ይህ ሁሉ ደርሶባት ኢትዮጵያ አልፈረሰችላቸውም፡፡
በዚያ ብቻ ሳያበቃ የአገራችን ኢትዮጵያ መሬቷ በቋንቋ፣ በብሔርና ብሔረሰብ ተሸንሽኖ ‹‹ክልል›› የሚል ስም በተሰጣቸው ‹‹ትንንሽ አገሮች›› እንድትከፋፈል ተፈርዶባት ዜጎች እንደ ልባቸው በፈለጉት ክልል ያለ ሥጋት የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት፣ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው የመዘዋወር ዕድል ተነፍጓቸው ነው የኖሩት፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ አንድ ክልል ተሻግሮ ከመሄድ ይልቅ ውጭ አገር መሄድ ይቀላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ወደ አገራቸው ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ዘራቸው እየተለየ በተለይም ከአማራ ክልል የሚመጡት ‹‹ፈልሰው የመጡ›› እየተባሉ ወደ መጡበት እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ተገደዋል፡፡ ይህ የሆነበት አንዱም ምክንያት ክልሎቹ ለስሙ ብቻ በተተከለ ‹‹ፌዴሬሽን›› ይሁን ‹‹ኮንፌዴሬሽን›› ለመለየት በሚያደናግር ሐረግ እንዲገናኙ ተደርገው፣ ጠንካራ አገር ወይም ‹‹አገረ መንግሥት›› እንዳይገነቡ ሆነ ተብሎ ነው በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው፡፡ እርግጥ ሕገ መንግሥቱ በሰጣቸው መብት ተጠቅመው ብሔሮች (ክልሎች) በራሳቸው ቋንቋ፣ አስተዳደርና ሰንደቅ ዓላማ መተዳደራቸው ምንም ጉዳት የለውም፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውም ነውና፡፡ ይሁን እንጂ ቋንቋን፣ ብሔርንና ክልልን ምክንያት በማድረግ ዜጎችን በዘር እየለዩ ከፋፍሎ ለመግዛትና ለመጨቆኛ፣ እርስ በርስም ለማጋጫ መሣሪያ ማድረግና ለዚያ የሚያመች የክልል ሕገ መንግሥት በመቅረፅ ጭራሽ የማዕከላዊ መንግሥቱንና የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ሥርዓት መገንባት ተገቢ አልነበረም፡፡ በእዚህ ዓይነት አገራችን ውጥንቅጡ የወጣ የኅብረተሰብና ፖለቲካ ቀውስ እንድትገባ ያመቻቸው በመሠረቱ ይኸው በብሔር ፖለቲከኞች የተረቀቀውና የሚወደሰው ሕገ መንግሥት ነው፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ የሕገ መንግሥቱና የዘረኛ ሥርዓቱ ትሩፋቶች፡፡ በእዚህ ሁኔታ እንዴት አድርጎ ነው ታዲያ አገር የሚገነባው፣ የሕዝቡ ድህነት እየጠፋ ልማትና ዕድገት የሚመጣው፡፡
በእዚህ አያበቃም፣ በውስጣቸው የሚኖሩ ከተለያዩ ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች የሚወለዱትን በዘር እየለዩ፣ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ዕድል እንዳይኖራቸው የሚያደርግ፣ ሥራዬ ተብሎ በሕገ መንግሥታቸው የተደነገገ የዘረኛ (‹‹አፓርታይድ››) አንቀጽ ያላቸው በርካታ ክልሎች ናቸው፡፡ የፌደራል መንግሥቱም የክልል መንግሥታት ዘረኝነቱን እንዲያቆሙ ለማድረግ በሕገ መንግሥቱ ሥልጣን አልተሰጠውም ወይም እንዲሰጠው የሚፈልግ አይመስልም፡፡ የራሱ ተቋማት ከብሔሮችና ክልሎች በተውጣጡ አባላት የተዋቀሩ ስለሆኑ እሱን ራሱን ለመቀየር በጣም አዳጋች ነው፡፡ ለምሳሌ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥቱ ስለማይፈቅድ ከተለየ ብሔር (ከአማራ ወይም ከኦሮሞ) የሚወለዱት ‹‹እንደ ሁለተኛ ዜጋ›› ስለሚቆጠሩ የክልሉ ባለቤትነት የላቸውም፡፡ እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተወላጆችም ሙሉ የፖለቲካና ኢኮኖሚ መብት ወይም ዕድል አይሰጣቸውም፡፡ በተመሳሳይ በቁጥር በጣም አናሳ የሆኑት የሐረሪ ተወላጆች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማትን ሕገ መንግሥቱን ተገን አድርገው በበላይነት በመቆጣጠር፣ በቁጥር የሚበዙትን (በተለይም የአማራና የኦሮሞ ተወላጆችን) በሥራቸው ረግጠው በመያዝ እኩል ዕድሉ እንዲኖራቸውና እንዲሳተፉ አይፈቅዱላቸውም፡፡ በድሬዳዋ ከተማም ዘረኝነቱ ብዙ ልዩነት የለውም፡፡ ለምሳሌ አማሮች የፖለቲካና የአስተዳደር ሥልጣን እንዲይዙ አይፈቀድላቸውም፡፡ በሰፊው የአገሪቱ ክልል በኦሮሚያ ጭራሽ የባሰ ነው፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ለዓመታት በክልሉ የኖሩና ኦሮሚኛ ቋንቋም አቀላጥፈው የሚናገሩ አማሮች፣ እንደ ኦሮሞዎች እኩል የፖለቲካና የኢኮኖሚ መብት ወይም ዕድል የላቸውም፡፡ በወለጋና በሌሎችም አካባቢዎች ‹‹ነፍጠኛ›› ‹‹መጤዎች ናችሁ ወደ አገራችሁ ሂዱ›› እየተባሉ ይጨፈጨፋሉ፣ ለዓመታት ከኖሩበት ቤትና ቀዬአቸውም በሺዎች የሚቆጠሩ እየተፈናቀሉ በዱር በገደል ተሰደዋል፡፡ ይህ ነው የሕገ መንግሥቱ ውጤት፡፡
እንግዲህ ኢትዮጵያዊነት ዜግነቱስ ይቅርና አሁን ባለው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የተፈቀደውን ‹‹የብሔር ወይም የክልል ዜግነት›› መብት እንኳን የሌላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ከላይ የጠቀስኳቸው ምስክር የሚሆኑ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ሁሉ ዜጎች በገዛ አገራቸው ‹‹አገርና ብሔር አልባ›› የሆኑ ናቸው፡፡ አገራችን ይህን ሁሉ ጉድ በውስጧ ተሸክማ ታዲያ እንዴት ብላ ነው ከድህነት ልትላቀቅ፣ ልትለማና ልታድግ የምትችለው? እንዴት ብላስ ነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደ አገር ልትገነባና በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በቴክኖሎጂና በዕውቀት ልታድግና ልትበለፅግ የምትችለው? በአፍሪካ ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛችና በነፃነቷ ኮርታ ለዘመናት የኖረች አገር ዛሬ ከአካባቢ አልፎ አኅጉሩን በነፃ ንግድና ኢኮኖሚ ለማስተሳሰርና በጋራ ለማሳደግ ግንባር ቀደም ሆና መምራት የሚገባት ኢትዮጵያ፣ በገዛ ልጆቿ ከቅኝ ግዛት በባሰና ጥቁር ዜጎችን ከሰው በታች አድርጎ ለዓመታት በባርነት ከገዛው አስከፊው የደቡብ አፍሪካ ዘረኝነት (አፓርታይድ) በማይተናነስ ሥርዓት አዙሪት ውስጥ ገብታ ትማቅቃለች፡፡ ይህን ሁሉ ጉድ በውስጧ ተሸክማ ማደጉስ ቀርቶ ዛሬ እንዴት ብላ ነው ኢትዮጵያ አገራችን ከፖለቲካ ቀውስ ወጥታ ሰላምና መረጋጋት ልታገኝ የምትችለው? ለእዚህ ነው በቅድሚያ ለእዚህ ሁሉ ምስቅልቅል፣ ቀውስና ኋላቀርነት መነሾ የሆነውን ሕገ መንግሥት በአገራዊ ምክክር፣ በውይይትና በብሔራዊ መግባባት ማሻሻል ወይም መቀየር ያስፈልጋል የሚባለው፡፡ ይህንን ለማመቻቸትና በግንባር ቀደምትነት ለመምራት ደግሞ፣ በተለይም የፌዴራል መንግሥቱ መሪዎች ቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርባቸዋል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
- የብልፅግና ፓርቲ በድንገት ዘው ብሎ የገባበትና መውጫው የጠፋበት ‹‹አጣብቂኝ››!
አገራችን ኢትዮጵያ ምናልባትም ባለፉት 50 ዓመታት ከገጠሟት ውስጥ በአጭር ጊዜ ማለትም ባለፉት አምስት ዓመታት (ሕወሓት ከወደቀ በኋላ) ያየችውን ዓይነት ፈተና ያየች አይመስለኝም፡፡ እነዚህን የተወሳሰቡ ችግሮች የወለዳቸውም ከላይ ደጋግሜ እንደጠቀስኩት በሕገ መንግሥቱ ተወልዶ፣ ባለፉት 30 ዓመታት ሥር የሰደደውና የተገነባው፣ በብሔር ፖለቲካ የቆመው ሥርዓት እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለይ የፖለቲካው ችግር ከኢኮኖሚውና ከማኅበራዊ ቀውሱ ጋር ተወሳስቦ አንዱ ከሌላው ጋር እየተጠመጠመ በመተብተብ ውሉን ለይቶ ለመፍታት፣ ለአገር መሪዎችና ለፖለቲከኞችም በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ የሆነበት ወቅት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሕዝቡም በኑሮ ውድነት፣ ሰላም በማጣት፣ በጦርነት፣ በእርስ በርስ ግጭት፣ በመፈናቀል፣ በረሃብ፣ በግፍና በሙስና በመሰቃየት ያልገጠመው ዓይነት መከራ አይገኝም፡፡ ችግሮችን ጭራሽ እንዲወሳሰቡና እንዲቆላለፉ ያደረጋቸው ደግሞ ዋናው የሕወሐት ጦርነት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ጦርነቱ በተለይም ለማደግ ገና በመንገዳገድ ላይ የነበረውን የደሃይቱን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ፋይናንስና መሠረተ ልማት በማውደምና ሕዝቡን ለዕልቂት፣ ለረሀብና ለኑሮ ውድነት በማጋለጥ አገራችንን ቢያንስ ሰላሳ ዓመት ያህል ወደ ኋላ እንደመለሳት ለመገመት አያዳግትም፡፡
እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመፍታትና አገራችን ከገባችበት የሥቃይ አዙሪት ወጥታ፣ ከሕመሟም አገግማ እንድትጠነክር ለማድረግ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሁሉም አገሩን የሚያፈቅር ኢትዮጵያዊ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ መረባረብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ እርግጥ በመሪዎች ላይ ያለው ኃላፊነት ከሁሉም ይበልጣል፡፡ በተለይም በከባድ ፈተና ወቅት ሕዝብን አስተባብሮ አገርን ለማዳን ትክክለኛ አመራር ወሳኝ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ሕዝቡና በተለይም የፖለቲካ ልሂቃኑ የአገራችን ችግሮች ውስብስብ መሆናቸውን፣ መሪዎቹም አቅም ሊያጡና ሊሳሳቱ የሚችሉባቸው ዕድሎች ሰፊ መሆናቸውን ተረድተው የጋራ አገራችንን ለማዳን በጋራ መፍትሔ ማፈላለግ እንጂ ማባባሱ መፍትሔ አያመጣም፡፡ ተያይዘን ከአገራችን ጋር ገደል መግባት ሊያስከትል ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም የአንድ አገር ጥሩ መሪ ትልቁ ችሎታ ደግሞ ከስህተቱ እየተማረ፣ አቅጣጫውን ማስተካከልና በተለይም ትህትናን በመላበስ ዝቅ ብሎ ሕዝቡን እያዳመጠ መምራት መቻሉ ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ሕዝብን ከጎኑ ያላሠለፈ መሪ አገሪቱን ምንም ቢሆን ከተወሳሰቡ ችግሮቿ ሊያወጣት አይችልም፡፡ ‹‹ወደ ፈተና አታግባኝ›› የሚባለው ፀሎት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለመሪዎች ደግሞ ካወቁበትና ዕድሉን ከተጠቀሙበት ፈተና ውስጥ መግባቱ ያን ያህል መጥፎ አይደለም፡፡ በዓለማችን ታዋቂና ታላላቅ የአገር መሪዎች እንደ ኔልሰን ማንዴላ፣ አብርሃም ሊንከን፣ ፍራንክሊን ሩዝቨልት፣ ዊንስተን ቸርችል፣ ማህታማ ጋንዲና ማርቲን ሉተር ኪንግ ያሉት ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ እየሠሩ መሄድ የቻሉት አገሮቻቸው ከባድ ፈተና ውስጥ በገቡበት ጊዜ ብልኃትን፣ ቆራጥነትንና የሕዝብ ተቀባይነትን በሚገባ እያቀናጁ በመምራት ከፍተኛ ስኬትና መሥረታዊ ለውጥ ለማስገኘት በመቻላቸው ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ የተከሰቱት የተወሳሰቡ ችግሮችም ለመሪዎች ያን የመሰለ ታሪካዊ ዕድል መስጠት አቅም እንዳላቸው ምንም አያጠራጥርም፡፡ አገራችን ደግሞ በተለይ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በመሪዎች አላድላት አለ እንጂ፣ በታሪክና በሕዝብ ጥንካሬ ከእነዚህ ሁሉ አገሮች ብትበልጥ እንጂ አታንስም ነበር፡፡
በእኔ አስተያየት የዛሬው የብልፅግና ፓርቲ መሪዎች ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሥልጣን እንደያዙ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንደገቡት፣ አገራችንን ከኢሕአዴግ (ሕወሓት) ኋላ ቀር የብሔር ፖለቲካና ዘረኝነት ሥርዓት አላቀው ወደ ኢትዮጵያዊነት ለማሻገር ሕልም እንደነበራቸው የሚያመላክቱ በርካታ ምልክቶች የነበሩ ይመስለኛል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ኢሕአዴግን ‹‹ብልፅግና›› ብለው ስሙን ቀይረው ያቀፋቸውን ድርጅቶች በማዋሀድና አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ በመፍጠር፣ አገራችንን አንድ አድርጎ ለመምራት ያደረጉት ሙከራ እንደ አንድ ጥሩ የተስፋ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ያለ በቂ ዝግጅት ከብሔር ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያዊነት ለመሻገር በሚል ወደ ወንዙ ዘው ብለው እንደገቡ ይመስለኛል ያልጠበቁት ችግር ያጋጠማቸው፡፡ ቀጥለውም እየተንገዳገዱ የሞላውን ወንዝ መሻገር ሲያቅታቸው ያገኙትን አለት ሥር የበቀለ ቋጥኝ (ዛፍ) ሙጥኝ ብለው ይዘው ወደ ኋላ ለመመለስም ሆነ ወደፊት ለመሄድ ግራ ገብቷቸው እየተወዛወዙ ያሉ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ መሻገር ስላቃታቸው ጭራሽ ፊታቸውን ወደ ኋላ አዙረው ወደ መጡበት ለመመለስም እየሞከሩ ያሉ ይመስላል፡፡
ወደ ኋላ መመለስ ግን እሳቸውን ብቻ ሳይሆን አገራችንን ከሕወሓቱም ጊዜ የባሰ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባት ይችላል፡፡ ይልቁንም የሕዝቡን ጩኸት ቢያዳምጡና ቢደፍሩ ጠንካራ ገመድ ሰጥቶ ወንዙን የሚያሻግራቸው እሱ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ዋናው ነገር ወንዙን ለመሻገርም እኮ ጉልበት ሳይሆን ብልኃት ነው የሚያስፈልገው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደ ኋላ ለመመለስም እኮ በጉልበት መሞከሩ ጥሩ አይደለም፣ አያዛልቅም፡፡ ከሕወሃት ስህተት ቢማሩ ጥሩ ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የብሔር ፖለቲከኞችም ይህንን ሀቅ አምነው መቀበል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ሕዝቡ ቀድሞ ሄዷል፣ የሚመራው አጣ እንጂ የብሔር ፖለቲካ አንገሽግሾታል፡፡ በተለይም የሕወሓት ጦርነት የፖለቲካ ልሂቃኑንና መሪዎችን እንጃ እንጂ ሕዝቡን በሚገባ አስተምሮታል፡፡ ስለዚህ ለአገራችን ከቀውሱ አዙሪት መውጫ መንገዱን በጋራና በብልሀት ማፈላለጉ ለልሂቃኑም ለሕዝቡም የሚበጅ ይመስለኛል፡፡
ሕወሓት (ትሕነግ) ሕገ መንግሥቱን ሲያረቅ ሆነ ብሎ ‹‹ብሔር ተኮር ፖለቲካው›› እንዳይጠፋና ኢትዮጵያ የምትባል አገርም አንድ ሆና በጠንካራ ኅብረ ብሔር ፓርቲ እየተመራች ለረዥም ዓመታት እንዳትዘልቅ ነበር የወጠነው፡፡ ከኅብረ ብሔር ፓርቲ ይልቅ ራሱ በበላይነት የሚቆጣጠራቸውን ‹‹አሻንጉሊት›› የብሔር ድርጅቶች ‹‹በግንባር ስም አገናኝቶ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር – ኢሕአዴግ›› የሚል ስም ሰጥቶ ራሱን ‹‹የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር›› ብሎ በእኩልነት ሽፋን የበላይነቱን ተቆጣጥሮ መቀጠልን ነበር የመረጠው፡፡ በበላይነት መቀጠሉ ካልተሳካለትና ግንባሩ የሚፈርስ ከመሰለው ትግራይን ‹‹ነፃ አውጥቶ›› ለመገንጠል በማቀድ ነበር ሕገ መንግሥቱንም ሆነ በብሔር ላይ የቆሙትን ድርጅቶችና የክልል (‹‹የፌዴራል ሥርዓቱን››) አወቃቀር በሥልት ያነፀው፡፡ ይህ ሴራው ደግሞ ከሞላ ጎደል ለሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን ከፋፍሎ፣ ሕዝቡንም በሚገባ በበላይነት ቀጥቅጦ እንዲገዛ አስችሎታል፡፡ ችግሩ ‹‹ሁሉም ያልፋል እስኪያልፍ ያለፋል›› እንደሚባለው፣ ‹‹መቶ ዓመት እቆያለሁ›› እያለ በከንቱ ሲመካ የኖረውን የሕወሓት ዘረኛ መንግሥት ግፍ ያንገፈገፈው ሕዝብ በአመጽ ከ27 ዓመታት በኋላ ከመንግሥት ሥልጣኑ ነቀለው፡፡ ያኔ ሕወሓት ወደ ሁለተኛው (‹‹Plan B››) ፊቱን አዞረ፡፡ ኢትዮጵያን እስከ ማፈራረስ በመድረስ በግርግር ትግራይን የመገንጠል ሕልሙን ገፋበት፡፡ ይህን ዕቅዱን ቶሎ በተግባር ለማዋል ያጣደፈው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ኢሕአዴግን አፍርሰው በድንገት ብልፅግናን ማወጃቸው ነው፡፡ ሕወሓት የበላይነትን እንጂ እኩልነትን አያውቅም ለዚያም ነው ሌላ ቀርቶ ‹‹አጋር ድርጅቶች›› በሚል ስም ምናልባት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑትን ኢትዮጵያውያን ብሔር ብሔረሰቦች ወደ ሥልጣን እንዳይጠጉ አድርጓቸው የኖረው፡፡ ለነገሩ ሕወሓት ተደናብሮ ቶሎ ‹‹ወደ ሽፍትነት›› አመራ እንጂ ብልፅግና ስለታወጀ የብሔር ፖለቲካው ጨርሶ አልጠፋም፣ የሚፈራው ኢትዮጵያዊነትም ገና አልመጣም ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልፅግናን ሲያውጁ ሕወሓትን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሕወሓት ደጋፊዎችና የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ በተለይም ሕገ መንግሥቱን ከሕወሓት ጋር አብረው የቀየሱትን የኦሮሞ ብሔርተኞችንም ጭምር ነበር ያደናበሩት፡፡ ለምሳሌ ያህል የሕዝባዊ ለውጡ ዋና አጋርና መሪ የነበሩትን ኦቦ ለማ መገርሳን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው›› እንዳላሉ፣ ‹‹የኦሮሞ ጥያቄ ገና ሳይመለስ›› ወደ ውህደት ፓርቲ (ብልፅግና የሚባል) እንሄዳለን በሚል ሽንጣቸውን ገትረው ነበር የተሟገቱትና በኋላም ባልታወቀ ምክንያት ከድርጅታቸው ጠቅልለው ገሸሽ ያሉት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የብልፅግና ጉዞ›› ከሁሉም በበለጠ ያስደሰተው ግን ‹‹የብሔር ፖለቲካን›› የሚቃወሙና በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊት፣ ፌዴራላዊትና ኅብረ ብሔር አንድነት ላይ የቆመች ኢትዮጵያን ለማየት የሚጓጉትን በሙሉ ነበር፡፡ እውነትም እኚህ ታሪካዊ መሪ አገራችንን ከኋላቀሩና ከፋፋዩ የብሔር ፖለቲካና የዘረኝነት ሥርዓት ለማውጣት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ያሉና ተስፋ ያሳደሩባቸው በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን ነበሩ (እኔንም ጨምሮ)፡፡
ችግሩ ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል (ወይም ሳይቀየር) ጠንካራና ሁሉንም ዜጋ በእኩል የሚያሳትፍ፣ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊና ኅብረ ብሔራዊ ግንባር ቀደም ፓርቲ ለመመሥረት እንዴት አድርጎ ይቻላል የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ቢያንስ በጣም ያዳግታል አለዚያም አይቻልም ባይ ነኝ፡፡ ለዚያም ይመስለኛል የብልፅግና ፓርቲ ወንዙን ሳይሻገርና ገና ሩቅ ሳይሄድ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው፡፡ ለእዚህ ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የብልፅግና ፓርቲን በጉዞው የገጠሙትን ከባድ ፈተናዎች ማየቱ ራሱ በቂ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ሲታይ ኢሕአዴግና ብልፅግና በመሠረቱ ብዙም ልዩነት ያላቸው አይመስሉም፡፡ እርግጥ ብልፅግናንም ያዋቀሩት በውስጣቸው በብሔር፣ በክልልና በዘር ሳይቀር ሕወሓት ያጣመራቸው ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህም ድርጅቶች በተለይም የሦስቱ (ኦሮሞ፣ አማራና ትግራይ) እርስ በርሳቸው የሚጠራጠሩና በሥልጣን የሚሻኮቱ፣ አልፎ አልፎም አገራችንን አደጋ ላይ እስኪጥሉ ድረስ የሚጋጩና አሠላለፋቸውን እየቀያየሩ በሴራ የሚራኮቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ እንኳን በኦሮሞና በአማራ ብልፅግና መሀል የተፈጠረውን ውጊያ ቀረሽ ግጭት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሚገርመው እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ‹‹ኦሮማራ›› በሚል ስያሜ ተገናኝተው የሕዝቡን ብሶትና አመጽ ተገን አድርገው ሕወሓትን ገንድሰው ለመጣል እንዳልቻሉ፣ ዛሬ አልፎ አልፎ ለይስሙላ በአደባባይ ቢተቃቀፉም ውስጥ ለውስጥ ግን ‹‹ዓይንህ ለአፈር›› እንደሚባባሉ ምንም አያጠራጥርም፡፡ እንዲያውም ሕወሓት በተዓምር ከሞተበት ነፍስ ዘርቶ ሲያርግ፣ የኦሮሞ ብልፅግና መሪዎች በጣም ደስ ያላቸው ይመስላል፡፡ ሁለቱ ተባብረው በአማራ ብልፅግና ላይ እያሴሩ እንደሆነ የሚጠቁሙ በርካታ ምልክቶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የልሂቃኑ ፖለቲካ በሴራ የተካነ እንደሆነ ለመረዳት ኮሌጅ መግባትን አይጠይቅም፡፡
የሚገርመው ግን ብልፅግና ፓርቲ ይህ ሁሉ ፈተና ከፊቱ ተደቅኖበት እያለ ከሌሎች በተለይም ከብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎች ለይቶ ሕዝቡ እንዴት ግልብጥ ብሎ ሊመርጠውና የመንግሥት ሥልጣን ላይ ሊያስቀምጠው እንደቻለ ነው፡፡ በእኔ እምነት በመሠረቱ ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በዘርና በሃይማኖት ሳይከፋፍል የሚመራው ጠንካራ ኅብረ ብሔር ድርጅት ለማግኘት ምን ያህል እንደሚጓጓ ነው፡፡ ብልፅግናንም ያንን የረዥም ጊዜ ሕልሙን ያሳካለት መስሎት ነበር ሕዝቡ እንዲያ ግልብጥ ብሎ የመረጠው የሚል ግምት አለኝ፡፡ በዚህ ላይ በቂ ጥናት መደረጉን አላውቅም፣ ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ለእዚህ በርካታ ምስክሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያፈቅረው አገር ወዳድ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የኢትዮጵያን ስም ሲያነሱ፣ በተለይ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ድጋፉን ያሳየባቸው ወቅቶች በቂ ምስክር የሚሆኑ ይመስለኛል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን እንደያዙ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያውያን ስንሞት ኢትዮጵያ ነን›› ሲሉ ስሰማ እኔ ራሴ ሳላስበው እንባዬ በጉንጮቼ ፈሷል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ››፣ ‹‹ኢትዮጵያ›› እያሉ ሕይወታቸውን ለመስዋዕትነት አሳልፈው የሰጡት ከበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች (ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከትግራይ፣ ከጉራጌ፣ ከወላይታና ከሌሎችም) የተወለዱት የወጣትነት ጓደኞቼ ናቸው ይታዩኝ የነበሩት፡፡ እውነትም በሕወሓትና በጠባብ ብሔርተኞች አገራችን ኢትዮጵያ አልሞተችም ነበር ያልኩት፡፡ እውነቱን ለመናገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከመጡበት ከኦሮሞ ብሔር ሕዝብ በበለጠ የአማራ ክልል ሕዝብ ነበር ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ያንን የመሰለ ከፍተኛ ድጋፍ የሰጣቸው፡፡ ያን ታሪክ ምንጊዜ ቢሆን አይረሳውም፡፡
ሕወሓት በጣም ገፍቶ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ከተተው እንጂ የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት የጀርባ አጥነት ነበር፡፡ እርግጥ ዛሬም ቢሆን ያው ነው፡፡ ሆኖም ለ30 ዓመታት ያህል ያለማቋረጥ በዘር ተለይቶ የወረደበት ግፍ ገና ሳያባራና ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኝ የአማራ ሕዝብ ከብሔር ፖለቲካ የሚወጣ አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ ሕወሓት በለስ ቀንቶት ደብረሲና ሲደርስም ‹‹አገራችን ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ወረራ በጋራ እናድናት ተነሱ›› ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ ጥሪ ሲያደርጉና ወደ ጦር ሜዳ ሲዘምቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ብሔር፣ ዘር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይገድበው እንዴት እንደ ማዕበል ግልብጥ ብሎ እንደተነሳ፣ በልጆቹና በሕይወቱ መስዋዕትነት እየከፈለ ኢትዮጵያን እንዳዳናት ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት በውጭ አገሮች በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንም ጭምር (ዳያስፖራው) አገርን ለማዳን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለመንግሥታቸው ከፍተኛ ድጋፉን ነበር የሰጣቸውና በጋራ የተረባረበው፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል ዛሬ ብዙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን (በተለይም ከዳያስፖራው) በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተከድተናል የሚል ስሜት ቢያድርባቸው አያስደንቅም፡፡ ሁሉም ወንዙን መሻገር አቅቷቸዋል ወይም አይፈልጉም ብለው ያምናሉና፡፡
በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ከሕወሓት በተጨማሪ ሌሎችም ጠባብ ብሔርተኞችና አሸባሪዎች በብሔር ፖለቲካና በዘረኝነት ላይ የቆመውን ሕገ መንግሥት ተንተርሰው፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ንፁኃንን በተደጋጋሚ ሲጨፈጭፉና ሲያፈናቅሉ የፌደራልና የክልል መንግሥታት መሪዎችና የፀጥታ አካላት በጊዜ ለማስቆም አለመቻላቸው በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያንን በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጡና ተስፋ እንዲቆርጡ ነው ያደረጋቸው፡፡ የሚደንቀው ይህ ሁሉ ግፍ በሕዝብ ላይ እየተፈጸመና የመንግሥት ፀጥታ አካላትም ኃላፊነታቸውን ባልተወጡበት ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በብሔር፣ በሃይማኖትና በክልል ሳይለያይ አያት ቅድመ አያቶቹ ያቆዩዋትን አገሩን አልከዳትም፡፡ ሕወሓት በውጭ ጌቶቹ እየታገዘ ሊያፈርሳት ሲዘምትባትም ከመከላከያ ጎን በአንድነት በመቆም ጠላቶቹን በቆራጥነት እየተከላከለ ከባድ መስዋዕትነት በመክፈል ያዳናት ሕዝቡ ነው፡፡ በተለይም የአማራና አፋር ሕዝብ፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻያና ፋኖ የሕወሓትን ወረራ በመቋቋም ከመከላከያ ጎን ሆነው ያሳዩትን ጀግንነትና የከፈሉትን መስዋዕትነት ታሪክ ምንጊዜም አይረሳውም፡፡ ይህን የመሰለ ጠንካራ የአገር ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት ስሜት ደግሞ በሁለቱ ክልሎች ብቻ ሳይሆን በኦሮሞ፣ በሶማሌ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላና በሌሎችም እንደታየ ምንም አያጠራጥርም፡፡ የገዥ መደቦችና የብሔር ፖለቲከኞች ለጥቅማቸው ሲሉ በዘርና በቋንቋ እየከፋፈሉ ለዓመታት እያጋጩ ሊበታትኑት ቢጥሩም፣ ሕዝቡ እንደ አያት ቅድመ አያቶቹ የአገሩን አንድነትና ክብር በሕይወቱ መስዋዕትነት በጀግንነት ተከላክሎ ነው የጋራ አገሩን ያዳናት፡፡
ችግሩ አሁን ያለው ኋላቀርና ከፋፋይ ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በብሔር ፖለቲካ የሚመሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አሸን ሲፈሉ፣ በተለይም በፈተና ወቅት ግንባር ቀደም መሪ ሊሆኑ የሚችሉ ጠንካራ ኅብረ ብሔር ፓርቲዎችን ግን እስከ ዛሬ ድረስ አገራችን ማፍራት አልቻለችም፡፡ ብልፅግናም ምንም እንኳን ገና ታዳጊ ቢሆንም አሁን በያዘው አካሄድ ከቀጠለና ራሱን ከዘረኝነት ነፃ ካላወጣ፣ ጠንካራ ‹‹የኅብረ ብሔር ፓርቲ›› ይወጣዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ጠጋ ብሎ ላየው ከኢሕአዴግ ምንም ያህል የሚሻል አይመስልም፣ ምናልባት ቢብስ እንጂ፡፡ ለእዚህም ችግሩ አንድም የኢሕአዴግን ቢሮክራሲና የካድሬ መዋቅር መውረሱና የአንድ ብሔር የበላይነትን ለማንገሥ ከእሱ መጥፎ ትምህርት በመቅሰሙ ቢሆንም፣ ይህ ሕገ መንግሥት እስካለ ድረስ ጠንካራ ኅብረ ብሔር ፓርቲ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ከኅብረ ብሔር ይልቅ ‹‹ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎች›› ገና መፈልፈላቸውንም አያቆሙም፡፡ ሌላው ቀርቶ አዳዲስ የብሔርና ብሔረሰብ ክልሎች እስከተወለዱ ድረስ የእነሱ ልጆች ብሔር ተኮር ፓርቲዎችም ጊዜያቸውን እየጠበቁ እንደሚወለዱ መገመት አያዳግትም፡፡ ይህን ለማስቀረት ያለው አማራጭ ሕገ መንግሥቱን አሻሽሎ የአገራችን ፖለቲካ ከብሔርተኝነት ነፃ እንዲሆን ማድረግ ብቻ ነው፡፡
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ከዘር፣ ከብሔርና ከሃይማኖት ነፃ እንዲሆን በሕገ መንግሥቱ መደንገግ ይኖርበታል፡፡ ዜጎች የብሔር፣ የቋንቋና የሃይማኖት እኩልነት መብታቸው እንዲከበር አገራችን የግድ በብሔር፣ በዘር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ላይ በቆመ ሕገ መንግሥት ላይ መተከልና እነሱም በብሔር የፖለቲካ ፓርቲ ሥር መሠለፍ የለባቸውም፡፡ በእዚህ ረገድ በዴሞክራሲ ካደጉትና ከሠለጠኑት አገሮች ተሞክሮና ታሪክ ብዙ መማር ይቻላል፡፡ ከሁሉም መርሳት የሌለብን በብሔር ፖለቲካ ሰበብ ነው በሕወሓት ጦርነት አገራችን ልትጠፋ ተቃርባ የነበረው፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥትና ‹‹የፌዴራል›› መዋቅር ለውስጥ ግጭት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ጠላትም አገራችንን ከፋፍሎ ለማስጠቃት አመቺ ስለሆነ፣ ምንጊዜም ለህልውናዋ አያሠጋትም ብሎ በድፍረት መናገርም አይቻልም፡፡
ለማጠቃለል እናት አገራችን ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት 50 ዓመታት ብዙ ደምታለች፣ ሕዝቡ በቃላት ለመግለጽ በሚያስቸግር አስከፊ ሥቃይ ውስጥ አልፏል፣ እያለፈም ይገኛል፡፡ እስከ ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቿን በጦርነት እየገበረች፣ ንፁኃን ዜጎቿን በእስር፣ በጭፍጨፋና በመፈናቀል እያጣች በዕድገት ከሁሉም በታች ሆና እየቀጠለች ነው፡፡ ሰላም አጥታ፣ ጥቂቶች መሬትና ሀብቷን እየዘረፉ ሲንደላቀቁ፣ ምስኪኑ ሕዝብ ግን ሕይወቱ ረክሶ ዜጎች በየመንገዱ ወድቀው ሲለምኑ፣ መጠለያ ውስጥ ታጭቀው ለበሽታ፣ ለረሃብ፣ ለእርዛትና ለአውሬ ሳይቀር እየተዳረጉ ነው፡፡ ይህ ግፍ መቆም አለበት፡፡ መንግሥት ቢያንስ አሁን ባለው ሕገ መንግሥት የተጻፉትን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበርና ማስከብር አለበት፡፡ እሱንም ተስኖት እየጣሰ ዜጎችን በዘፈቀደ እያፈነ፣ እያሰረና እያሰቃየ ባለበትና በአገራችን አንፃራዊ ፍትሕና ሰላም እንኳን ሳይሰፍን ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል አዳጋች ነው፡፡ በእዚህ ሁኔታ ሁሉን አሳታፊና አካታች አገራዊ ምክክር ማድረግም አይቻልም፡፡
ስለዚህ በቅድሚያ አገራዊ ምክክሩ ሁሉንም ባካተተ መንገድ በነፃ መንፈስ እንዲካሄድ፣ መንግሥት ራሱን በቅንነት መርምሮ ሁኔታዎችን ለማስተካከልና ለማመቻቸት ቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርበታል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትንና መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የኅብረተሰብ አንቂዎችንና ምሁራንን፣ ባለሀብቶችን በዘርና በብሔር እየለየ እያፈነና እያሰረ፣ ድሆችን ቤታቸውን በማፍረስ ጎዳና ላይ እየወረወረ፣ ፍትሕን እየረገጠ ምን ዓይነት ሰላምና ዕርቅ በአገራችን ሊመጣ ይችላል? ሰላምና ዕርቅ ደግሞ እውነተኛ አገራዊ ምክክር ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ያለ አገራዊ ምክክር ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል አይችልም፡፡ በእውነት ሕዝብ ለማዳመጥ፣ አገራችንን ከቀውስ አዙሪት ለማውጣትና ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል (በመቀየር) ወንዙን ለማሻገርና ታሪክ ለመሥራት ቁርጠኛ ከሆነ፣ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት በቅድሚያ የሕዝቡን ጩኸት አዳምጦ በአገራችን አንፃራዊ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን በቅንነትና በቁርጠኝነት መጣር ይኖርበታል፡፡ ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለአገራችንና ለሕዝባችን ስል ወንዙን ከፓርቲያቸው ጋር እንዲሻገሩም ከልብ እመኛለሁ፡፡ ይህን ብዬ በሚቀጥለው ጽሑፌ (ክፍል አምስት) ለመሆኑ ሕገ መንግሥቱ ቢሻሻል ወይም ቢቀየር አሁን ካለው ብሔር ተኮር አስከፊና ዘረኛ ሥርዓት ምን የተለየ ሁኔታ በአገራችን ሊያመጣ ይችላል የሚለውን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያ ቸር ወሬ ያሰማን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይጠብቅ!
ለሕዝባችንም ሰላምና አንድነትን ያውርድልን!
ከአዘጋጁ፡፡ ጸሐፊው ‹‹በሀገር ፍቅር ጉዞ መጽሐፍ›› ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡