Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ› ዝግጅት በጥናታዊ ሥራ ላይ የተደረገ ውይይትን በተከፋፈለ ቀልብ ሆኜ ሰምቼ ነበር፡፡ ውይይቱ የገዥዎች/መሪዎች እረኛዊ ዓይነት ሚና በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ያለው ስለመሆኑ የሚያወሳ የነበረም ይመስለኛል፡፡ አጣርቼ ባልሰማሁት ውይይት ላይ ከዚህ ያለፈ ነገር መናገር አልችልም፡፡ ወደ ታወከ ‹‹ዩቲዩብ›› ውስጥ ገብቼ ዝግጅቱን ማዳመጥም፣ ማጣራትም ዋና ፍላጎቴ አልነበረምና አላደረግኩትም፡፡ የእኔ ልብ የተጠመደው ውይይቱ አዕምሮዬ ውስጥ በፈጠረው ጥያቄ ላይ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራል አገረ መንግሥት በአግባቡ ቢገነባ እንኳ ሙገሳውን የሚያሳርፍበት ግለሰባዊ አለኝታ አይሻ ይሆን? ጥያቄው ይህ ነው፡፡

ሀ) የኢትዮጵያ ሰዎች አነሰም በዛ ከእምነት ሥርዓታቸውና ከማኅበራዊ ወጎቻቸው ጋር ኑሯቸው በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡ በሞት ጊዜ፣ በቀብርና በማፅናናት ጊዜ፣ በልደት፣ በክርስትና፣ በሠርግ፣ በሥጋዊና በመንፈስ ሕክምና ሁሉ ከእምነት ሥርዓታቸውና ወጎቻቸው ጋር ይራከባሉ፡፡ ከፈጣሪያቸው ጋር በፆምና ፀሎት ይነጋገራሉ፡፡ ከዚያ ባለፈ ጥሩ ህልም አሳይቶኛል ብለው መልካም ነገር እንደሚጠብቁ ሁሉ፣ መጥፎ ህልም አሳይቶኛል ብለው የሚሠጉበትና ከመንገድም የሚቀሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ሰዎች በእክላቸው ጊዜ ወደ ፈጣሪ አቤት ከማለት ባሻገር፣ የቅዱሳንና የመላዕክትን ዕገዛ የሚሹበትም ሁኔታ አለ፡፡ የዕገዛ ፍላጎቱ ሰዎች ድረስ ሊሄድም ይችላል፡፡ ለቡራኬ፣ ለምርቃት፣ በፀሎት እክልን ለማለፍም ሆነ ፍላጎትን ለማቃናት፣ ወይም እርኩስ መንፈስን ለማባረር/ከክፉ መንፈስ ለመጠበቅ የሃይማኖት ሰዎችን መጥራት ወይም ወደ ‹‹አዋቂ›› መሄድ እንግዳ አይደለም፡፡ የሃይማኖት መሪዎች (አስተማሪዎች) በዕድሜ ቢያንሱ እንኳ አንቱ የተባለ ተከባሪነት በአማኒያኑ ዘንድ ይሰጣቸዋል፡፡ የእነሱ ሥፍራ በፈጣሪና በምዕመናኑ መሀል ያለ ዓይነት ነው፡፡ የፈጣሪን ‹‹በጎች› የማያንፁ፣ የሚያበርቱ፣ የሚያበራክቱና የሚመሩ ‹‹መልካም እረኞች›› ናቸው፡፡ ምእመናን ከተኩላ (ከሰይጣናዊ ጥፋት) የሚጠበቁ ናቸው፡፡ ከሞላ ጎደል ይህንን የመሰለ ዕሳቤ በኅብረተሰቡ ውስጥ አለ፡፡ ‹‹ወደድንም ጠላንም ፈጣሪ ከጻፈልን ውጪ እንሆንም…፣ ፈጣሪ ያላለው አይሆን!…፣ ፈጣሪ ያመጣውን መቀበል ነው…፣ ፈጣሪ ላያስችል አይሰጥም…፣ ፈጣሪን ካልረሳን እሱ ይጠብቀናል፣ ፈጣሪን ስንረሳ እሱም ይረሳናል/ይቀጣናል….›› እንዲህ ያሉ አባባሎች የብዙ ኢትዮጵያውንን አጠቃላይ አመለካከት ያንፀባርቃሉ፡፡

- Advertisement -

በአባባሎቹ የተንፀባረቀው አመለካከት፣ ከግላዊ የሕይወት ውጣ ውረድ አንስቶ እስከ መንግሥታዊ ሥልጣን ውጣ ውረድና የሰላም ፈተና ድረስ በማብራሪያነት ይሠራበታል፡፡ በዚህ አመለካከት ውስጥ ሆነን ኑሯችን ያለበትን ደረጃና ሁኔታ እንደምንቀበልና ለመቀየር እንደምንሰንፍ ሁሉ ለመቀየርም እንፍጨረጨራለን፡፡ የመጣውን መንግሥት እንደምንቀበል ሁሉ እንቃወማለንም፡፡ ተቃውሟችን ለመጣል መንገድ እስከ መፈለግ እንደሚሄድ ሁሉ፣ ‹‹እግዜር ተጣልቶን ነው እሱ ይማረን! ደጉን ያምጣልን!›› ብሎ እስከ መለማመን የሰፋ ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የመጡና የሄዱ ገዥዎችም ከሞላ ጎደል የሥልጣን አወጣጥና ቆይታቸውን ከፈጣሪ መፍቀድ ጋር ያገናኙታል፡፡ ‹‹ንግርት ተነግሮልኛል/በህልም ተነግሮኛል›› የሚል መነሻ መጠቀም እንደነበር ሁሉ፣ ‹‹በፈጣሪ የተመረጥኩ/የተሰየምኩ ነኝ›› ማለትም ነበር፡፡ በፈጣሪ ተሰየምኩ ሳይባልም ሥዩመ-ፈጣሪ መሆን ይቻላል፡፡ እስከ ዛሬ ከምናውቃቸው ‹‹መሪዎች›› ራሱን ከፈጣሪ ጋር ያላገናኘ ሰው ማነው ቢባል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ልንል እንችል ይሆናል፡፡ ለእሱም ቢሆን በሕዝብና በፓርቲ ‹‹መመረጥ›› ከወግ ጌጥ ያለፈ ትርጉም የሌለው፣ ከሕዝብም ከፓርቲም በላይ በሆነ ደረጃ ወደ አፍአዊ መመለክ የተሻገረ ‹‹አይከስስ አይገሰስ ንጉሥ›› ነበር፡፡ ‹‹ቆራጡ መሪ!፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ!፣ ለኢትዮጵያ የተሰጠ…፣ ዳግማዊ ቴዎድሮስ!›› የሚል ውዳሴ በየውዳሴ ንግግር የሚዘንብለት፣ ከእሱ አፍ የወጣ ቃል እንደ ፈጣሪ ቃል የሚጠቀስ፣ የ‹‹ትክክለኛ›› አስተሳሰብና አኗኗር ‹‹መለኪያ›› የሚደረግም ነበር፣ ቢያንስ ቢያንስ ለተሸነጋገለ ኑሮ፡፡

‹‹መሪዎች›› የሕዝብ ሙገሳን ለማግኝት ባህታውያንን/የሃይማኖት ሰዎችን፣ እረኞችንና አዝማሪዎችን እንደሚጠቀሙ ሁሉ፣ ውዳሴ ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎችን እንደ ዘመናቸው ዓውድ ይሠራሉ፡፡ ቤተ እምነቶች ማስገንባት፣ በጦርነቶች ገድል መሥራትና ገድል ማጻፍ፣ ወዘተ ወዘተ፡፡ ኅብረተሰቡም ባይጥመውም ኑሮ በዘዴ ብሎት፣ ፈጣሪ የወደደውንና የሃይማኖት መሪዎች የተቀበሉትን መሪ ይቀበላል፡፡ ተቀብሎም የጀግና ተግባርን፣ ድል አድራጊነትን፣ የቸርነት ሥራን ሰምቶም ሆነ አስተውሎ ለማወደስ ቅርብ ነው፡፡

በሥልጣን ዘመናቸው ውዳሴ ደርቶላቸው ከሥልጣን ሲለዩ/ሲያልፉ ውዳሴም ጥሏቸው የሄደ፣ በሥልጣን ዘመናቸው ውስጥ በአንድ ጊዜ ውዳሴና ቅዋሜ የገጠማቸውም ገዥዎች ነበሩ፡፡ ከአሞጋሻቸው ይልቅ አውጋዣቸው፣ በተለይ ወደ መጨረሻ፣ በርክቶ ከሚሄዱ ገዥዎች ውስጥም እነሱን በተካው ገዥ ዓይን ተመዝነው ወይም በእነሱ ጊዜ የነበረ የኑሮ ሁኔታ ከእነሱ መሄድ በኋላ ከመጣው ኑሮ ጋር ተነፃፅሮ ምሥጋናና ሙገሳ ተመልሶ የጎበኛቸውም ታይተዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱ የኋላ ምሥጋና በተራ ሕዝብ ግምገማ እንደሚመጣ ሁሉ የመሪዎቹ በጎ አስተዋፅኦ በጥፋታቸው ከመሸፈን ተፈልቅቆ ወጥቶ እንዲታይ ከመደረግ ጋር የሚገናኝበትም ሁኔታ አለ፡፡ ዘመነ ሥልጣናቸው ራቅ ያለና በሥነ ጽሑፍ በዘፈን፣ በተውኔትና በመነባንብ ውዳሴ የደራላቸውና በታሪካቸው ውስጥ የነበሩ እንከኖችን አታሰሙን አታሳዩን የተባለላቸውም የታሪክ ሰዎች አሉ፡፡

ወጣም ወረደ የውዳሴና የዝና አስተሳሰባችን ብዙ ማጣራትን ይሻል፡፡ ዝና ማግኘት ሲገባቸው ተሸፋፍነው የቀሩ ጀግኖች በታሪካችን ውስጥ ጥቂት አይደሉም፡፡ በጣም በታሪክ ሳንርቅ ዓድዋ ጦርነትን ከፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጋር የተካሄደ የአምስት ዓመት ትግልን በርብረን ጀግኖቻችንን ምን ያህል በአግባቡ አውቀናል? አፄ ኃይለ ሥላሴ በመንግሥታቱ ሊግ ፊት ቆመው ሊጉ የነግ በእኔ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ባደረጉት ዝነኛ ንግግርና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም ባደረጉት አስተዋፅኦ ስማቸው እየተሞገሠ ነው፡፡ ከእሳቸው አስተዋጽኦና ከዝነኛ ንግግራቸው ጀርባ የነበሩትን ጀግኖች ግን ኅብረተሰቡ እንዲያውቃቸው ተደርጓል? የ1969 ዓ.ም. የሶማሊያ ወረራና ጦርነት ጊዜ ፈጣን የሕዝብ ጦር በማደራጀትና ጦርነቱን መክቶ ወደ ድል በመቀየር ቅንብር ውስጥ ዋናዎቹ ማርሽ ቀያሪዎች (በቅስቀሳና በአደራጅነት በወታደራዊ ተጋድሎ) እነማን ናቸው? ጥያቄው መቀጠል ይችላል፡፡

ለ) ጥያቄዎችን በአግባቡ የመመለስ ሥራ ተሠራም አልተሠራም፣ ኅብረተሰባችን እንደ ትናንቱና እንደ ዛሬው ነገም የሚያወድሳቸውና የሚኮንናቸው የታሪክ ሰዎች ይኖሩታል፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት በአግባቡ ቢደራጁም፣ ተቋማት ላይ ከመተማመን ባሻገር የግለሰብ አሰባሳቢነት ላይ መተማመን አብሮ መቀጠሉ በቅርብ ነጋችን ውስጥ የሚቋረጥ አይመስልም፡፡ ማንም ተመረጠ ማን በርካታ ሕዝብ ግለሰቦች ላይ የማይወራከብበት፣ ከሚመጡና ከሚሄዱ ግለሰቦችና ፓርቲዎች በበለጠ አገረ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የነፃነትና የመብቱ አለኝታ አድርጎ የሚተማመንበት ማኅበራዊ ልቦና ለኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ገና ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡

ዓለማችን ወዴትና እንዴት እንደምታመራ ባልታወቀበት ድንግዝግዝ ውስጥ ነው የምትገኘው፡፡ ይህንን ለማለት የሚያበቃውም፣ ጎራዊ የኃይል አሠላለፉና የውጥረት/የውጊያ አካባቢዎች ጭምር በግልጽ የሚታወቁ፣ ዘመኑም የጅምላ ጨራሽና የከፍተኛ ቴክኖሎጂ የጦር ትጥቅ የተሰነቀበት ሆኖ ሳለ፣ ጦርነቶች ሳይሰፉ ለማስቆም የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ የሌለበት (የዝምዝም) ሁኔታ ውስጥ መሆናችን ነው፡፡ ይህ ዓለማዊ ድግዝግዝ በራሱ፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ፓርቲያዊና ግለሰባዊ አሰባሳቢ መሪ ማግኘትን ተገቢና ተፈላጊ የሚያደርግ ነው፡፡

በመጋቢት 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትርነት ብቅ ያለውና የመንግሥት መሪ ከመሆን እማዊ ምልከታ ጋር አደግሁ ያለን ዓብይ አህመድ፣ በፍጥነት አከታትሎ በወሰዳቸው አፈና አርጋቢ/ኩርፊያ አቅላይና ሰላማዊ ትግል አበረታች ዕርምጃዎች የሕዝብ መወደድና አድናቆት ከሁሉም ወገን የጎረፈለት መሪ ነው፡፡ የሕዝብ ፍቅር የሰውየውን ፎቶ እያበዛ በየመንገድ ግድግዳ ላይ፣ በየመኪና፣ በየአልባሳት ላይ ሲለጥፍና ሲያትም ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ውዳሴው ‹‹የኢትዮጵያ ሙሴ/ለኢትዮጵያ እግዜር የሰጣት መሪ›› እስከ መባልም ተራምዷል፣ በአጨብጫቢነት ሳይሆን ከምር በሆነ ስሜት፡፡ ሄዶ ሄዶ ዝናና ውዳሴው በተወሰነ ደረጃ ቢኮማተርም እየሰፋ… እየጠበበ፣ እየሞቀ… እየበረደ ዛሬ ድረስ አለ፡፡ ምንም ተባለ ምን፣ ሰውየው በቀላል የማይልፈስፈስ መንፈስ ብርቱ ነው፡፡ ከሥልጣን በፊት ቢያንስ በልቡ የገቡ ሰዎችን በመተዋወቅ እንዳሰናዳ ሁሉ፣ ሥልጣን ላይ ከወጣም ወዲህ ዓይንህ ለአፈር በተባለበት ጊዜ እንኳ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ወደር የሌለው ምሥጉን ለመሆን፣ በተለይ ትጉህ ወጣት ልሂቃንን ከየሙያ ዘርፉ ከጀርባው አድርጎ ከመሥራት አልቦዘነም፡፡ ሰውየው ቸኮል ማለትና በስሜት መነጠቅ ባያጣውም ብልህ ነው፡፡ ኢትዮጵያን አትራፊ ወደሚያደርግ ሥራ ሊቀየር የሚችል ዕምቅ ፀጋን ጠልቆ ማስተዋል የሚችልና ያንን ፈጥኖ ለማልማት የሀብት ዕገዛ ለማስተባበርና ሠርቶ ለማሠራት ምናቡም ብልኃቱም ትጋቱም ያለው ሰው ነው፡፡ ከእንጦጦ የምኒልክ ግቢ አንስቶ በአዲስ አበባ የተሠሩ ቱሪዝም ነክና ዕውቀት ነክ ልማቶች (የሳይንስ ሙዚየምና አብረሆት ቤተ መጻሕፍትን ጨምሮ) የዚህ ውጤት ናቸው፡፡ የቱሪዝም ገብ ልማቱ ከአዲስ አበባ ውጪም ‹‹በገበታ ለአገር›› እና ‹‹በገበታ ለትውልድ›› በየአቅጣጫው ተሰማርቷል፡፡ የዓረብ ኤምሬትስ ባለሀብቶችና የሚድሮክ ኩባንያ በተለያየ ሥፍራ የተያያዙት የቀበጠ ዘመናይ ቀዬ ግንባታ እዚህ የሚወሳ አይደለም፡፡

ዓብይ ያሠራቸው በተለይ የመዝናኛና የወንዝ ዳር ልማቶች አሽሟጣጭ ባያጡም፣ በኢትዮጵያ በመላ ዓይን ገልጠው በማራኪነታቸውና በጥራታቸው የተዋጣላቸው ሥራዎችን የመገንባት ፍላጎትን ኮርኩረዋል፡፡ የዓብይ አመራር ፈያጅነት ከዚህም ያለፈ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የደኅንነት አውታር ኢትዮጵያዊ ቅስሙ ውስጡን ለቄስ በነበረበት ሰዓት፣ የእሱን ብልህነት የተመረኮዘ የውጭ ቁልፍ ዕገዛ ባይገኝ ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ህልውና ምናልባት ታሪክ በሆነ ነበር፡፡ ይህ አስተዋጽኦው ብቻውን ሁሌም በታሪክ የሚታወስ ያደርገዋል፡፡ ከሕፃናት እስከ አዋቂ ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች (ያለ ብሔረሰብና ያለ ሃይማኖት ልዩነት) የሚወደድ (የእኛ የተባለ) የመከላከያ ዘርፈ ብዙ ኃይል በመገንባት ረገድም የሰውየው አመራር የዋዛ አልነበረም፡፡ በቀፎው የቀረውን የአገሪቱን የመረጃ የደኅንነት አውታር በፍጥነት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲዋደድ አድርጎ በመገንባት ረገድም የዓብይ አህመድ ሚና ልዩ ቦታ አለው፡፡ የራሱን የመጽሓፍት ሽያጭ ገቢን ከሌሎች በጎ አጋዦች ከተገኘ ሀብት ጋር በማቀናጀት በገራገሯ ባለቤቱ ዝናሽ ታየ በኩል በተከታታይ በተለያዩ ሥፍራዎች የተገነቡ ልዩ ልዩ ማኅበራዊ አገልግሎት ነክ ሥራዎች ማዕድ በማጋራትና የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ዓብይ ያካሄደው ፈር ቀዳጅ እንቅስቃሴ፣ በአገሪቱ በየአቅጣጫው የሰብዓዊ ርኅራኄና የበጎ ሥራ እንዲነቃቃ የውዴታ ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል፡፡ እየተስፋፋ በመጣው ተማሪዎችን በምገባና በትምህርት ቤት ትጥቅ በመደጎምና በድሆች ምገባ እንቅስቃሴ ውስጥም የእሱ አሻራ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ ያለ ፆታና ዕድሜ ልዩነት በአገራቸው ሁለገብ ሕይወትና ሙያ ውስጥ በንቃትና በትጋት ሲንቀሳቀሱ የታዩትም የዓብይ አህመድ አመራር ባመጣው ትርጉም ያለው አሳታፊነት ነው፡፡

በግብርና የበጋ ስንዴና የፍራፍሬ ልማት፣ አሮጌ እርሻንና መኸር አሰባሰብን በዘመናዊ ጥበብ በመተካት ጥረትና ‹‹በአረንጓዴ አሻራ›› እንቅስቃሴ፣ ወጣቶች የዲጂታል ኢኮኖሚ ሞተር እንዲሆኑ የፈጣሪነት ጉጉትን ባነሳሳውና ልምምድን ባደፋፈረው ጥንስስ ውስጥም የዓብይ አህመድ ሚና ከጠቅላይ ሚኒስትርነትም ያለፈ ጉዳዬ ባይነት ነበረበት፡፡ በዚህ ጽሑፍ ያልተጠቀሱትን ግንባታዎችንና ልማቶችን ጨምሮ በአምስት የፈተና ዓመታት ውስጥ ይህን ያህል ለመሥራት መቻሉ፣ በዓብይ የቅርብ አመራርና ሠርቶ የማሠራት ትጋት ውስጥ ስርቆትና ቡጥቦጣን ተቀናቅኖ ሥራዎችን በጥራትና በታቀደላቸው ጊዜ የማቀላጠፍ ዕምቅ አስኳል እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡ ይህ አስኳላዊ ጥንካሬ ነገ ልሽቀትና ሙስናን ለማመንመን ተስፋ የሚሰጥና የሚያበረታታ ነው፡፡

የሱዳን ቀውስ በቀጣናችን ውስጥ ምን ይዞብን እንደሚመጣ ባይታወቅም፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በአገር ውስጥ ያሉ የጦርነትና የሽብር እንቅስቃሴዎችን በተለያዩ ተመጋጋቢ ዘዴዎች እያቃለለች ሙሉ የውስጥ ሰላም ወደ መጎናፀፍ እያመራች ትገኛለች፡፡ የተሻለ ሰላም በሚገኝባቸው መጪ ጊዜያት የተጀማመሩ የልማት ውጥኖች ዕውን መሆን ይችላሉ፡፡ ከእስካሁኑ የፈተና ጊዜ በበለጠ መጪው የኢትዮጵያ ልማት አስገራሚ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ በሰይፍና በደም አገርን በማነፅ፣ በለውጥና በልማት አገርን በማስወንጨፍ፣ እየታደሰ ዘመን የሚሻገር ሕገ መንግሥታዊ መሠረት በመጣል፣ ወዘተ ‹‹አባቶች/ታልልቅ መሪዎች›› እየተባሉ የሚዘከሩ የታሪክ ሰዎችን ልዩ ልዩ አገሮች ውስጥ እናገኛለን፡፡ በሩሲያ፣ በጀርመን፣ በጣሊያን፣ በቱርክ፣ በህንድ፣ በቻይናና በደቡብ ኮሪያ፣ ወዘተ ወዘተ፡፡

ኢትዮጵያም ፈጠነም ዘገየም ሁለገብ እመርታ በመምራት ረገድ ታላቁ መሪ ለመባል ዕድልና አቅም ያለው ውሎ ሲያድር እንደ ጉሽ ጠላ የሚጠራ ወጣት መሪ ኢትዮጵያ በእጇ ላይ ዛሬ አለ – ዓብይ አህመድ፡፡ ሰውየው በዝነኛነት በኢትዮጵያ ውስጥ ስሙን መትከል ይፈልጋል፡፡ ስሙን መትከል የሚሻው ግን በአንፋሽ አከንፋሾች ኃይል ሳይሆን፣ የሚታይና ለማንኳሰስ/ለማደብዘዝ የማይመች ሥራ በመሥራት ነው፡፡ እስካሁን በአምስት ዓመት ውስጥ በሠራው/ባሠራው ሥራ እንኳ ከኢትዮጵያ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መሪዎች ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ፣ የለውጥ ምሁራንና ወጣቶች ተባብረው ኢትዮጵያን በማስመንደግ ተልዕኮ ውስጥ ይህንን ሰው በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

ይህንን ስል ይህ ሰውየው ለይቶለት አጨብጫቢ ሆኖ አረፈ የሚሉ፣ ከዚያም አልፎ የሚደነግጡ ይኖራሉ፡፡ ከሚደነግጡትና በአወዳደቄ ከሚያዝኑት ውስጥ ዋነኞቹ በጨለምተኝነት ጉድጓድ ውስጥ የገቡ ሰዎች ይመስሉኛል፡፡ ጨለምተኞች እኔ እንደተረዳኋቸው፣ ኢትዮጵያ ላይ የሚላወሰውን የለውጥ እውነታ ከማንበብ ፈንታ የ‹ዩቲዩብ› መሪሳ እየተጋቱ የደነበዙ ይመስለኛል፡፡ ዓብይ ታላቅ መሪ ይሆናል ማለት ይቅርና ኢትዮጵያ ትመነደጋለች ብሎ ተስፋ ማድረግም ለእነሱ ደስ የማይል ቅዠት ሆኖ እንደሚሰማቸው አስተውያለሁ፡፡ ለእነሱ ‹‹ዓብይ አህመድ በኢትዮጵያ ላይ የመጣ ደህና መሳይ ዘረኛና እየሳቀ የሚያስጨፍጭፍ ሰው ነው››፡፡ ዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ከመጣ በኋላ ሥልጣን የቋመጠ ቆበራቸውን እያዝረበረቡ ቢያንዣብቡና በላይ በታች ቢሉ የሚያቀምሳቸው ሲያጡ ቅዋሜና ስድብ የጀመሩና እስከ ዛሬ ከዚህ ፈቀቅ ያላሉ አሉ፡፡ ሥልጣን ባይቋምጡም በውስጥና በውጭ የዳር ተመልካች ሆነው በይፋና ውስጥ ለውስጥ ዓብይን ሲቆነጥሩ ውለው የሚያድሩም አሉ፡፡

ምንም ቢባል፣ የለውጥ ዕድል በግብታዊ ቅዋሜ ከመትረክረክ ማለፍ በተቸገረበት (ኢትዮጵያ ለውጥ በመምራት ረገድ የወላድ መሃን በሆነችበት) ጊዜ፣ ከአፋኝ ገዥዎች ጎሬ ሕይወታቸውን ለአደጋ ሰጥተው ከወጡ ጥቂት ጎበዞች አንዱ ነው፡፡ ዓብይ ብቅ ብሎ ሰፊ ድጋፍ ከጎረፈለት ጊዜ አንስቶ ብልጭ ብልጭ ይሉ የነበሩ ወደኋላ ላይም ፈጠው የወጡ እንከኖች ነበሩት፣ አሁንም አሉት፡፡ እንተች ከተባለ ከመንግሥት አመራሩ አንስቶ እስከ ጻፋቸው መጻሕፍት ድረስ እንከኖች መምዘዝ ይቻላል፡፡ ቁምነገሩ ግን እንከን የመምዘዝና የመሰተር ጉዳይ ሳይሆን፣ የጥቅል ተግባሩን ለአገር የሚበጅ መሆኑን የማስተዋል ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያን አስተባብሮ ግስጋሴ ውስጥ በማስገባት በኩል ያለውን የሚታይና ዕምቅ አቅም የማገዝ ነው፡፡ ኢትዮጵያን አስተባብሮ ወደ ለውጥ ከመውሰድ አኳያ ምን አገዛችሁ? ብርሃን የሚሆን ምን ጻፋችሁ? ምን ያህል ጥርጣሬንና መከፋፈልን ታገላችሁ? በሚል ወሳኝ ጥያቄ ውስጥ፣ ዓብይ ላይ የሽርደዳና የስድብ ናዳን የሚለቁት ብዙዎቹ ይህ ነው የሚባል መልካም ታሪክ የላቸውም፡፡ ከዚያ ይልቅ ብዙዎቹ ዳር በቆመ ነቀፋና ነገር አመንዣኪነት መሃንነትን የሚወክሉ ናቸው፡፡

ዓብይ ከዚህ ውስጥ የለበትም፡፡ በመሬት ሥሪት ለውጥ ደርግ ያገኘውን ታላቅ ድጋፍ በቀይ ሽብርና በ1977 ዓ.ም. ድርቅ ሙልጭ አድርጎ እንደበላው ደርግ ያለ ገዥ አይደለም ዶ/ር ዓብይ፡፡ በኃይለኛ የስለላና የጥርነፋ መዋቅር ሰቅዞና የኢንተርኔት ማኅበራዊ መድረኮችን አፍኖ እየተጠላ በ‹ተከበረው› ሕወሓት/ኢሕአዴግ ዓይን የሚታይ ገዥም አይደለም ዓብይ፡፡ ዓብይ አህመድ ሀብት ለማግበስበስ ቀሰሙን በኢትዮጵያ ላይ ያልሰካ፣ ከዚያ ይልቅ ኢትዮጵያን ለማንሳት ባለ በሌለ አቅሙ የሚጥር፣ ከልሂቅ ነኝ ባይ አንስቶ እስከ ወጠጤ መሃይም ድረስ በሚወረውሩት ስድብ ቅስሙንና ትኩረቱን ሳያስነካ በዕቅድ መሥራትና ማሠራት መቻሉን በተግባር ያስመሰከረ ጀግና ነው፡፡ የዓብይ ጀግንነት የሚታወቀውን ከ2010 ዓ.ም. እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ እየገባች ባለፈችባቸው የቀውስ ሁኔታዎች ውስጥ የአገር መሪነቱ ከሸርዳጆቹ ባንዳቸው ተይዞ ቢሆን ኖሮስ ተብሎ ሲታሰብ ነው፡፡ የዓብይና የመሰሎቹ ጀግንነት አሁን ኢትዮጵያ ሰላም እያመጣች ባለችበት ሁኔታ ውስጥ ገና ይፈካል፡፡ ከብዙ የልማት ውጤታማነት ጋር የዝናውን መፍካትም ማንም ሊያስቆመው አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እመርታዎች መገማሸራቸው አይቀርም፡፡ ይህ ሁሉ ወሬዬ በተጨባጭ እየሆነ ያለንና የሚሆንን የማስተዋል ነገር እንጂ፣ የማሸርገድ ነገር አይደለም፡፡ አሸርጋጆች የዓውደ ርዕይ ዝግጅትን ሳይቀር ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጪነት›› የሚሉ ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡

ሐ) ግስጋሴና እመርታ በምን በምን? የሚል ጥያቄ ውስጥ ሆነን እመርታ የምንናፍቅባቸውን ትልሞች ለማውጣት እንሞክር፡፡

  • የውስጥና የቀጣና ሰላምን በማዛለቅ፣ ረሃብን፣ የመሬት/የአካባቢ መራቆትን፣ ድህነትን አዝቅት ከቶን የነበረን ከፋፋይ ሠፈርተኝነትን የሚረታ ባለ ሰፊ አድማስ አረንጓዴ ሕይወትና ኢኮኖሚ በመገንባት፣
  • የአገራችንን ብሔራዊ ገቢ ከብዙ ዘርፍ በሚመነጭ ትርፋማነት እያሳደጉ ኢትዮጵያን ብርቱ የንዋይ ባለስንቅ በማድረግ፣
  • የኢትዮጵያን ትምህርትና ሥልጠና በሰው ልጅ አክባሪነት፣ በኢትዮጵያዊና በአፍሪካዊ መተሳሰብ፣ ተፈጥሮን በማክበርና በመንከባከብ እሴቶች ከሥር ጀምሮ ልጆችን የማነፅ ደም ግባት እንዲኖረው አድርጎ በማበልፀግ፣ የአዲስ ሐሳብ፣ የምርምር፣ የፍልሰፋና የመለኝነት መፍለቂያ እንዲሆን በማድረግ፣
  • የዴሞክራሲ ግንባታን ከኢትዮጵያዊ የታላላቆች፣ የወላጆችና የአዛውንት፣ የሴት ልጅ አክብሮት ጋር በማላላስ፣
  • የኢትዮጵያዊነትን ልማት በብዝኃነት ገጽታዎች የተዋበ፣ ትጉህ የሥራ ባህል ያለው፣ አገር በቀል ባህሉን ያራመደ፣ የታቀደ የቤተሰብ ኑሮና የመኗኗር ክህሎት አጠቃላይ ዕውቀቱ የሆነ ዜግነት ላይ በመድረስ ጎዳና በመምራት፣
  • ዜጎች የሚያልሙት ሕይወት ከእነ እርካታና ኩራቱ፣ በተቆለለና በተቀናጣ ኑሮ መንፈላሰስንና ሀብት በሀብት ላይ መከመርን በማባረር ራስ ወዳድነት የተጠመደ ከመሆን ይልቅ፣ በየደረጃው በሚገኝ የዕውቀት የፈጠራና የሀብት አቅም አገርን እየጠቀሙና ማኅበራዊ ኃላፊነትን እየተወጡ መተለቅን፣ እንዲሁም የሰዎች ክብረኛ ኑሮ የተንሠራፋባት አገርን ማየት ንቃቱ እንዲሆን አድርጎ በማነፅ፡፡

እነዚህ የእመርታ ትልሞች ናቸው፡፡ በውስጣቸው ብዙ ፈርጆችና ዘለላዎች አሏቸው፡፡ አንዱ ፈርጅ ውስጥ ባለች ዘለላ ላይ የሚገኝ ስኬት አዎንታዊ ተፅዕኖው ሁሉም ትልሞች ውስጥ ሊጋባ እንደሚችል ሁሉ፣ የአንዷ ዘለላ ስኬታማነት ከተለያዩ ትልሞች ውስጥ ብዙ ሰበዞችን የሚፈልግ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ለማጤን እንድንችል ሰላምን መልሶ ከማጎልበት ጋር የኑሮ ንረትን (በተለይ በመሠረታዊ ቀለብ ረገድ) ያለብንን ችግር የማቅለል ሥራ ምሳሌ እናድርግ፡፡

በቀለብ አቅርቦት ያለውን አጠቃላይ እጥረት ለመወጣት ከምርት ሥራ የተፈናቀለውን መልሶ በማቋቋም፣ አምራች በማበራከት፣ ምርታማነትን በመመንደግ፣ ከውጪ የሚገቡ ነገሮችን ብዛት በአገር ውስጥ መረታ በማጣጣትና የግድ ከውጭ ለሚገቡም ተገቢ የውጭ ምንዛሪ በመሰነቅ የውስጥ ገበያውን በተከታታይ ለማጥገብ መቻልን ይጠይቃል፡፡ ይህ የውስጥ ገበያን ጥያቆት የማጥገብ ጉዳይ ብዙ ነገሮችን የዕቅድ ሒሳብ ውስጥ መያዝን ይፈልጋል፡፡ የአገራችን የሕዝብ ቁጥር ብዛት፣ ከፀጥታ ጋር የተያያዘ ወታደራዊ እንቅስቃሴ፣ ወታደራዊ ነክ ሥልጠናና ግንባታ፣ የትምህርት ቤቶች ምገባ፣ የደሃ ደሃዎችን በልዩ ልዩ መልክ መደጎም፣ እነዚህ ሁሉ እንደ አሰፋፋቸው የሚፈጥሩትን የፍጆታ ጥያቆት ዕድገት ማሰብ ይፈልጋል፡፡ ገና መፍትሔ ያላገኘ የውስጥ ስደት የአምራች ቅነሳና የፍጆታ ጥያቆት ድርብ ችግር ይፈጥራል፡፡ የውጭ ቱሪዝም ፍሰት የሚፈጥረው ፍላጎት፣ ከጎረቤት አገሮች የሚመጣ ፍላጎት፣ በተለይ የኢትዮጵያ አመጋገብ በአፍሪካና በምዕራብ እየተወደደ በመምጣቱ ምክንያት የተፈጠረ ፍላጎት፣ እነዚህ ሁሉ ከኢትዮጵያ ወጣ ሲባል ከገበያ ዘግኖ ከመሄድ አንስቶ በሕጋዊ ወጪ ንግድና በኮንትሮባንድ የመሹለክ ፈርጅ አላቸው፡፡ እነዚህም በሒሳብ ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ በጠንቃቃ አኗኗር/አያያዝ ጉድለት የሚደርሱ ብልሽቶች፣ በጎርፍና በቃጠሎ የሚደርሱ ጥፋቶች የመሠረታዊ የልማት አውታሮች ላይ የሚደርሱ የማሰናከል/የማጉደል ወንጀሎች፣ በምግብ ነክ ነገሮች ላይ ባዕድ ነገር ከልሶ የማትረፍ ወንጀሎች የሚፈጥሩት ብክነት (የተመረዘው አቅርቦት እስከተያዘ ድረስ)፣ እነዚህን የመሳሰሉት ሁሉ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የአቅርቦትንና የጥያቆትን መግባባት ይረብሻሉ፡፡ የኑሮ ንረትን የማቅለል ጉዳይ የምርት አቅርቦትን ከማትረፍረፍ ባሻገር ስንጥቅ አትራፊ በመሆን ጥማት የታወረ ስድ ነጋዴነትን (የሽቅባ ንግድን፣ ደብቆ ማከማቸትን፣ ተወዳድሮ ከመሸጥ ይልቅ ከላይ እስከ ታች እየተነጋገሩ የሽያጭ ዋጋ መቆጣጠርን፣ የሕዝብ የፍጆታ ንግድን ለፖለቲካ ፍላጎት መሣሪያ ማድረግን ሁሉ) የገራ ሥልጡን የንግድ ሥርዓት መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ የቤተሰብ ዕቅድን፣ ሥራ አጥነትን ታፍ ታፉ የሚያቀል የሥራና የሥራ ፈጠራ ዕድል በየዘርፉ መፍካትን ይሻል፡፡ የበጎ አድራጎት መዋጮዎችንና የግብር ዕድገትን በዋጋ ቅጠላ ላካክስ የሚል የንግድ አስተሳሰብን ከትርፌና ከትርፍ ፍላጎቴ ቀንሼ አገር ላግዝ ወደሚል አስተሳሰብ መሳብንም ይጠይቃል፡፡ መንግሥትም ነገሮች እስኪረጋጉ (የምርት መትረፍረፍ እስኪፈጠርና ኢኮኖሚው የውጭ ምንዛሪ ነክ አተነፋፈሱ እስኪስተካከል ድረስ፣ ከግብር መሸሽንና ግብር ሽቀባን ከማዳከም በቀር አዲስ ግብር የመጣልና የግብር ምጣኔ ከማሳድግ መቆጠብ እንደምንም ይኖርበታል፡፡ የምርት መትረፍረፍ ሲመጣም በገዥ ማጣትና በአክሳሪ ዋጋ መውደቅ መመታት እንዳይከተል የመትረፍረፍን ተከታታይነት አስተውሎ መጠባበቂያ ክምችት ከመፍጠር አንስቶ ኢንዱስትሪያዊም ሆነ ሌሎች መሰማሪያዎች እንዲያገኝ ለማድረግ አስቀድሞ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ጃፓኖችና ቻይኖቹ በኤክስፖርት ኢኮኖሚ መመዘዝ የአገር ውስጥ ምንዛሪያቸውን ዋጋ ከማቅለል ጋር የተግባባላቸው ጥርስ ነክሶ መሥራት፣ በቁጠባ መኖርና በአገራቸው ምርት ላይ የተመሠረተ ኑሮ መኖር ቅርሳቸው ስለነበር ነው፡፡ ለእኛ ደግሞ የውጭ ምንዛሪን ዝቅ ማድረግ መዝረክረኪያ ሊሆንብን የቻለው ኑሯችን የገቢ ሸቀጦች ምርኮኛ፣ የውጭ ብድር እስረኛ ስለነበርና ራሳችንን የኮንትሮባንድ መጫወቻ እስከ ማድረግ ድረስ ኢኮኖሚ ነክ አገር ወዳድ ንቃታችን ዝቅተኛ ስለነበር ነው፡፡ እነዚን ድክመቶች መቀየር ከቻልንና የደቡብ እስያኑንና የነዱባይን ብልኃት በደንብ አጥንቶ ከዘመናችንና ከእኛ እውነታ ጋር በሚዋደድ መላ የኤክስፖርት ኢኮኖሚን ማቃናት አይሳነንም፡፡

በቀጣናችን ውስጥ ከጎረቤቶቻችን ጋር ፀጥታችንንና የጋራ ልማታችንን ማግባባትና ማዛለቅ ራሱን የቻለ ብዙ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ ጋር የውስጥ ሰላማችንን፣ ኢኮኖሚያችንን፣ ፍትሕን የማስተዳደር ውስብስብ ትግሎች ይሳሳባሉ፡፡ ከሙስና፣ ከሸፍጥና ከሻጥር ጋር የምናደርገው ትግል እንኳ አድማሱ በአገር ግቢ ውስጥ የታጠረ አይሆንም፡፡ የሕዝብ ቀለብ እጥረትን የማሸነፍ ጉዳይ እንኳ ከአገር ውስጥ አልፎ ጎረቤት አገሮችን ተሻግሮ ባህር ማዶ የሚሄድ ክር እንዳለው ከላይ የተቀመጡት ነጥቦች ያስገነዝባሉ፡፡ በሁሉም ዘርፍ እመርታ ለማምጣት የምንጥረው ከዚህ ሁሉ ጋር ነው፡፡

ከውስብስብ መደበኛ ሥራ ጋር የልማት ግስጋሴን ለማፍጠን የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ላይ ካለው የሥራ ጭነት የተወሰነውን ወደ ርዕሰ ብሔር (ፕሬዚዳንት) አመራር ማሳለፍ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ችግር እየለዩ የበጎ አድራጎት ዕገዛን (በሙያ በገንዘብ) እያስተባበሩ የመገንባት ሥራዎች፣ የተማሪዎች ምገባና የዝቅተኛ ኅብረተሰብ መልከ ብዙ ድጎማዎች በፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በኩል ሥራቸው እንዲመራ ማድረግ ይቻላል፡፡ እከሌ እከሊት ፀደቁብኝ በሚል የስሜት ንካት እየነፈረቁ እጅ ልሳም የሚሉ ክስተቶች እንዲቀንሱና ኅብረተሰባችን ‹‹የእኛ ለእኛ መረዳዳት ጠቀመኝ/ደረሰልኝ›› ብሎ እንዲያስብም ለማኅበራዊ እንክብካቤያችን ሥርዓት የመጣል ነገር ቢጀማመር ጥሩ ነው፡፡ በበጎ ሥራዎች መስፋፋት መላ ኅብረተሰባችን እንደመደሰቱ እጅግ ትንሽ አቅም ካለው አንስቶ እስከ ዲታው ድረስ ለዚህ ዓይነት ዓላማ የዜግነት መዋጮ (ዝቅተኛ) በቋሚነት የሚከፈል ይኑር ቢባል ሁሉም ደስተኛ ይሆናል ብዬ ተሰፋ አደርጋለሁ (ይህ እንደታሰበበት በሰሞኑ ዜና ሰምተናል)፡፡ ከዚህ ባሻገር ለበጎ ሥራና ለማኅበራዊ እንክብካቤ ትርፋቸውን የሚያውሉ የተወሰኑ የአገልግሎት ንግዶችን መድቦና ሌሎች ብልኃቶችን እየፈጠሩ ገቢን ማበራከት የሥርዓት ግንባታው ማኮብኮቢያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

እንዲህ ነገሮችን እያሳላን በለውጥ መገስገስ ከቻልን ከዘርፍ ወደ ዘርፍ እርስ በርሱ የተመጋገበ የኢኮኖሚ መሠረት ያለውና ነውጥ ጠሪ የኑሮ ደረጃዎች ሸለቆ የማይፈጥር የኅብረተሰብ ሥርዓት መገንባት እንችላለን፡፡ ይህ ግን የሚሳካው ሥራችን ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቀጣናዊና አኅህጉራዊ ማዕቀፍ እስካለው ድረስ ነው፡፡ ቁልጭ ባለ ቃል ልናገረው፡፡ በቀጣናችን ውስጥ የብልፅግና ደሴት ሆነን ቀውስና ረሃብ በታየበት ተራድዖ ጫኝ በመሆን ትልም ውስጥ ብንጓዝ እዚያ ማማ ላይ ከመድረሳችን በፊት ከዙሪያችን የሚመጣ የስደት ጎርፍና ውንብድና ቁልቁል ይወስደናል፡፡ ከእኛ ጋር አካባቢያችንን የምናነሳ ፈርጥ በመሆን ጎዳና ብንጓዝ ግን አካባቢያችን ራሱ የለማ አጥር ይሆነናል፡፡

በዚህ አቅጣጫ ዓብይና ብልፅግና ፓርቲ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ አዲስ ትንሳዔ መሠረት ጣዮች እንደሚሆን፣ በደቡብና ምሥራቅ ኢትዮጵያ በተለይም በቦረናና በሶማሌ የሚካሄድ ረሃብን የሚረታ ልማት ለዙሪያ አካባቢው አብሪ ኮከብ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ስኬት ለቀጣናችን! ስኬት ለአኅጉራችን!!  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...