ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ አነጋጋሪ ከነበሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንዱ የግል ትምህርት ቤቶች እጅግ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ እያደረጉ ያሉትን ዝግጅትና የፈጠረው ውዥንብር ተጠቃሽ ነው፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ አብዛኛዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች በደቦ ሊባል በሚችል ደረጃ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን ይፋ እያደረጉ መሆኑን ተከትሎ የተቃውሞ ድምፆች መሰማታቸው ቀጥለዋል፡፡
መፍትሔ በታጣለት የዋጋ ንረት እየተመታ ያለውና ከወቅታዊ የዋጋ ንረት ጋር እየተፋለመ ያለው ወላጅ ልጆቹን የሚያስተምርባቸው ትምህርት ቤቶች ይዘው የቀረቡት የዋጋ ጭማሪ አስደንጋጭ ነው፡፡
መቶ በመቶና ከዚያ በላይ የዋጋ ጭማሪ አድርገናል ብለው በድፍረት የቀረቡ የግል ትምህርት ቤቶች እንዲህ ያለውን የጭማሪ ምጣኔ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱበት ምክንያት ለሚሰሚ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
ከተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶችና እየተሰሙ ካሉ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው በአብዛኛው እናደርገዋለን ያሉት የዋጋ ጭማሪ ከ50 በመቶ በላይ ነው በአንድ ጊዜ ይህንን ያህል ጭማሪ ሲያደርጉ ምንን መሠረት አድርገው እንደሆነ ግራ ከማጋባቱም በላይ በአገሪቱ ሕግ የለም ወይ? የሚያስብል ነው፡፡ በዋጋ ንረት የደቀቀው ኅብረተሰብ ገቢው ባልጨመረበትና ይሄ ነው የሚባል አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ ከየት አምጥቶ ይህንን ክፈል ሊባል እንደቻለም ግልጽ አይደለም፡፡
በእርግጥ አሁን ካለው የዋጋ ንረት አንፃር የምናስከፍለው ክፍያ ተመጣጣኝ አይደለም የሚለው ምክንያታቸው ከሞላ ጎደል ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ቀድሞም ቢሆን በአዲስ አበባ ያሉ የግል ትምህርት ቤቶች እያስከፈሉ የቆዩት ዋጋ እጅግ የተጋነነ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አብዛኛው የግል ትምህርት ቤቶች ሲከፈሉ በቆዩት ልክ አገልግሎቱን ሰጥተዋል ተብሎ ስለማይታመንም አሁን እየጠየቁ ያሉት የዋጋ ጭማሪ ይደረግ ከተባለም በልካቸው ሊሆን ይገባ ነበር፡፡
ነገሩን በደንብ አድምተን እንየው ከተባለ ደግሞ ለየትኛውም አገልግሎታቸውና ውጤታቸው ነው የምንጨምረው? ብለን ልንከራከርበት የምንችለው በቂ ምክንያት እንዳለንም መገንዘብ ይገባል፡፡ በቅርቡ የ12ኛ ክፍል ፈተና ያስፈተኗቸው ተማሪዎች ያገኙትን ውጤት ብቻ መመልከት በቂ ነው፡፡ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቁ ያልሆኑ ተማሪዎች ማብቃት ያቃታቸው ፈተና በመስረቅ ተማሪዎችን ሲያሳልፉ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ዛሬ 50 እና መቶ በመቶ የዋጋ ጭማሪ አድርገናል የሚሉበት በምን ሞላራቸው ነው?
ዛሬ የዋጋ ጭማሪ አድርገናል ብለው ከወላጅ ኮሚቴ ጋር እያደረጉ ያሉትን ምክክር ያህል በአገር ደረጃ ውርደት በሚባል ደረጃ ማትሪክን ያለፉ ተማሪዎች 20 እና 30 በመቶ አለመሙላታቸው እየተገለጸ ‹‹ጎበዝ ይህ ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል›› ብለው እንኳን ድምፃቸውን አላሰሙ እኮ ናቸው፡፡
ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ በቂ ተማሪዎች ላለመገኘቱ አንዱ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ጭምር መሆኑ በግልጽ እየታወቀ ለዚህ ችግር የመፍትሔ አካል መሆን ሲገባቸው ዘለው ገንዘብ ላይ ሙጥኝ ማለታቸው ማንነታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
ነገሩን ጠንከር አድርገን ካልሞገትንበትና አሁን እንደሚታየው ከወላጅ ኮሚቴም ይሁን ይመለከታቸዋል ከተባሉ የመንግሥት አካላት ጋር እየተደረገ ያለው ድርድርና ውይይት ጭማሪውን ለማስቀነስ ብቻ መሆን የለበትም፡፡
ዜጎች ከሚበሉት ቀንሰው የተጋነነ ዋጋ እየከፈሉ የሚያስተምሩት በተሰረቀ ፈተና ወደ ኮሌጅ የሚገባ ዜጋ ለማፍራት አይደለም፡፡ ወላጆች ኑሮዋቸውን እየጎዱ ልጆቻቸውን በውድ ዋጋ የሚያስተምሩት ለአገር በማሰብ ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን በሚከፍሉት ልክ ልጆቻቸው እየታነፁ ካልሆነ አንቆ ገንዘብ ጨምሩ የሚሉትን ትምህርት ቤቶች እስኪ ያስገኘኸው ውጤት መባል አለበት፡፡
አሁን ላይ የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ወደ መቀመቅ ገባ የሚባለው እኮ የግል ትምህርት ቤቶች ስለሚያስከፍሉት ገንዘብ የሚጨነቁትን ያህል ለትምህርት ሥርዓቱ መጠንከርና መሻሻል ያገባናል ብለው ባለመሥራታቸው ነው፡፡
ስለዚህ አሁንም የግል ትምህርት ቤቶች ወቅታዊ የዋጋ ጭማሪ ከመጋነንም በላይ ቅጥ ያጣና ተቆጣጣሪ አልባ እየመሰለ ነውና የሚመለከተው አካል ሁሉ በያገባኛል ስሜት ሊመክርበትና አካሄዳቸው መስመር እንዲይዝ መደረግ አለበት፡፡
የአገሪቱ ትምህርት ጉዳይ ዘቅጧል እያልን ትምህርት ቤቶች ብቁ ዜጋ እያፈሩ አይደለም እየተባለ ለዚህ ለአገር አደጋ ለሆነ ጉዳይ መፍትሔ ይዞ እንደመቅረብ ገንዘብ የሚያሳድዱ የግል ትምህርት ቤቶችን አደብ ማስገዛት ካልተቻለ አሁንም በውድ ዋጋ የተማሩ ግን ማትሪክ የማያልፉ ብዙዎችን እየቀፈቀፉ ከመሄድ ውጭ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡
የዋጋ ጭማሪው የተጋነነ ነው የምንለው የሚከፈለውን ያህል ልጆችን እያበቁ ባለመሆናቸው ብቻ አይደለም፡፡ በገፍ የሚከፈላቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚያስተምሩ አስተማሪዎች የተሻለ ደመወዝ ይከፍላሉ ተብሎ ስለማይታመን ነው፡፡
ቅጥራቸውና አስተዳደራቸው ከገንዘብ ማግኘት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በሚቀበሉት የክፍያ ልክ አስተማሪዎችን ሊከፍሉ ስለማይችሉ ብሎ መምህራንም ይዘዋል ተብሎ ስለማይታመን ነው፡፡
አጠቃላይ ገቢና ወጪያቸው በትክክል ከተፈተሸ እነዚህ ተቋማት የቢዝነስ እንጂ የዕውቀት ማዕከላት ናቸው ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር የሚከብድ ከሆነ ችግሩን አውቆ መፍትሔ መፈለግ ግድ ይላል፡፡
ስለዚህ የወላጅ ኮሚቴዎችና ትምህርት ቤቶች እያደረጉት ያሉት ሙግት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ ጉዳዩ የመንግሥት አካላት የሚገቡበት ምሁራንም ሐሳባቸውን የሚሰጡበት መሆን አለበት፡፡
ይህንን ያህል እየተከፈለ ምን ተገኘ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥም በየትኛውም መስክ ለሚሰጥ አገልግሎት ትክክለኛ ዋጋ መከፈል እንዳለበት ቢታመንም ከልክ በላይ የሚጠየቅ ክፍያ ግን ልጓም ሊበጅለት ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርት በተለየ ታይቶ ለዚህ የሚከፈለው ክፍያ ሥርዓት ያለው ቁጥጥር የሚደረግበት ሊሆን ካልተገባ በቀር የትምህርት ተቋማት ክፍያና የትርፍ ምጣኔ በሕግ ሊገደብ ይገባል፡፡
ልቅ ቢዝነስ ሊሆንም አይገባምና ራሳችንን የመሰለ አሠራርና ዋጋ ተመን ሊኖረው ይገባል፡፡ በስመ ነፃ ገበያና ቢዝነስ ዕውቀት ሸቀጥ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ዘርፉንም አናሳድግ የተበላሸውን የትምህርት ሥርዓት ማስተካከልም ዘበት ይሆናል፡፡