Monday, June 24, 2024

የመንግሥት ተደራራቢ የገቢ ምንጭ የማስፋት ዕርምጃና የዜጎች ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከሁለት ዓመታት በላይ በጦርነት ውስጥ ባሳለፈችው፣ ውስጣዊ የግጭት መካረሮችና የእርስ በርስ ትንኮሳዎች እስካሁን ተዳፍነው ባሉባት ኢትዮጵያ፣ በተለይ ኢኮኖሚዋን ከጦርነት የዞረ ድምር ለማውጣትና የተለጠጠውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን እያማተረ መሆኑ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

      ወቅታዊው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ገጽታ ሲቃኝ ዜጎች በኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ ነው፡፡ የሸቀጦች ዋጋ በየቀኑ መናርና የገቢያቸው አለማደግ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አዳዲስ የመንግሥት ውሳኔዎች ቅፅበታዊ በሆነ መንገድ ይፋ ተደርገው ተግባራዊ እንዲሆኑ ‹‹አቅጣጫ›› ሲቀመጥ ይስተዋላል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከዕለት ወደ ዕለት ኑሮን እያከበዱ ካሉ ዋነኛ ጉዳዮች የምግብ ዋጋ ንረት ይጠቀሳል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት በርካታ ዜጎች ሊቋቋሙት የማይችሉት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ናቸው ተብሎ እየተነገረ ነው፡፡

        ከምግብ በተጨማሪ የቤት ኪራይና የሕክምና ወጪዎች ከዜጎች የመክፈል አቅም በላይ ከሆኑ ውሎ አድሯል የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ የነዳጅና ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ እንዲሁ ከሁለትና ከሦስት እጥፍ በላይ ውድ ሆኗል፡፡

      የአገሪቱን ኢኮኖሚ በቅርበት የሚከታተሉት የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ በፌስቡክ ገጻቸው ከሰሞኑ እንዳሰፈሩት፣ በዚህ የውጥረት ወቅት በተጨማሪነት ከሚጠበቁት ‹‹የኑሮ ፈተናና ንዝረቶች›› መካከል የንብረት (ፕሮፐርቲ) ታክስ፣ የአከራይ ተከራይ ግብር፣ የገቢ ግብር፣ የአፈርና የጣራ ግብርና የትምህርት ቤት ክፍያዎች ጭማሪ ከሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ጋር ተዳምረው የዜጎችን ፈተና እያከበዱ ነው ብለዋል፡፡

እግር በእግር እየተከታተሉ ይፋ የሚደረጉት አዳዲስ የመንግሥት ገቢ ማስፋፊያ ዕርምጃዎች ከጦርነት፣ ከሥራ መዳከም፣ ከነዳጅ፣ ከውኃ፣ ከመብራት ታሪፍ ጭማሪና ከኑሮ ውድነት፣ ከሥጋትና ከማኅበራዊ ቀውስ ያላገገመውን ኅብረተሰብ ክፉኛ እየፈተኑት መሆኑን አቶ ሙሼ አስረድተዋል፡፡

የዜጎች ገቢ ባላደገበት ሁኔታ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈንና ለማጥበብ እያደረጋቸው የሚገኙ ተደራራቢ ዕርምጃዎችና ውሳኔዎች አንደምታን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞችና ዜጎች በተለያዩ መንገዶች ይገልጹታል፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ ለሪፖርተር በሰጡት አስታያየት፣ የ2015 ዓ.ም. በጀት በሚፀድቅበት ወቅት የበጀት ክፍተቱን በመመልከት፣ መንግሥት የገቢ አድማሱን ለማስፋት የተለያዩ ውሳኔዎች ይወስናል የሚል ሐሳብ ሰጥተው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

አዳዲስ የግብር ዓይነቶችን ጨምሮ በነባሮቹ የገቢ መሰብሰቢያዎች፣ እንዲሁም በአገልግሎቶች ላይ ተደራራቢ በሆነ መንገድ የሚወርዱት የመንግሥት ውሳኔዎች ተደራራቢ ስህተቶችን ለማረም፣ ሌላ የተደረበ ስህተት እንደ መሥራት ይቆጠራል ይላሉ፡፡ 

ኢኮኖሚው በጣም ጠንካራ እንዲሆን መሠራት ያለባቸው በብዛት ሳይሠሩ ሲቀሩ የበጀት ሥርጭት፣ በቂ የሥራ ዕድሎች፣ በቂ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን መፍጠር ሳይቻል ይቀራል በማለት ያስረዳሉ፡፡ በጀት በሙሉ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ነገሮች ላይ ሳይውል ሲቀር፣ ሌሎች (ዘርፎች) ላይ ማለትም ግጭትን ማብረድና ጦርነት ላይ ሲውል፣ እንዲሁም የውጭ ዕዳ በጣም ከፍተኛ ሲሆን መንግሥት ተደራራቢና ተከታታይ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ይናገራሉ፡፡

አንድ ኢኮኖሚ በቂ የሥራ ዕድል አልፈጠረም ማለት ፖሊሲውን የሚያስተዳድሩ (የሚመሩ) ሰዎች ጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው በሚል አስረጂ የሚያቀርቡት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ይህም ጥሩ የሆነ ፖሊሲ ካለማውጣት ወይም ጥሩ የሆነውን ፖሊሲ ካለመተግበር ከመሆኑም በተጨማሪ፣ አገሪቱ የምታገኘውን ብድርና ዕርዳታ በአግባቡ ካለመጠቀም፣ የበጀት መሠረትን ለማስፋት የተቋማትን አቅም ካለማሳደግ የሚመነጭ የስህተት ውጤት ነው ባይ ናቸው፡፡

አቶ ዋሲሁን እንደሚያስረዱት፣ በኢኮኖሚክስ አስተምህሮ ሁሉም ፖሊሲ ጥሩ ውጤት ላያመጣ ይችላል የሚል ዕሳቤ አለ፡፡ ነገር ግን በጣም የተደራረቡ ስህተቶች በሚኖሩበት ጊዜ ስህተቶቹን ለማረም በሚል የሚወሰደው መፍትሔ ሌላ ተጨማሪ ስህተት ሊያመጣ እንደሚችል በመጠቆም ያስጠነቅቃሉ፡፡

አቶ ዋሲሁን ጉዳዩን “The Cobra Effect” ከሚባለው ዕሳቤ ጋር ያገናኙታል፡፡ በጣሊያናዊው ኢኮኖሚስት ሆረስት ሲበርት የቀረበውን ሐሳብ ሲያትቱም፣ አስቸጋሪ ነገሮችን ለማለፍ በሚል የሚመጣ መፍትሔ ሌላ አስቸጋሪ መዘዝ ያመጣል በማለት ነው፡፡

እንግሊዞች ህንዶችን ቅኝ በገዙበት ወቅት ዕባቦች ከተሞችን ያስጨንቁ እንደነበር፣ በዚህ ጉዳይ የተጨነቁት ቅኝ ገዥዎች ችግሩን ለማርገብ ለዕባብ አዳኞች ክፍያ መክፈል መጀመራቸውን ሲያስረዱ፣ ‹‹እያንዳንዱ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ዕባቦችን እየገደላችሁ አምጡ ሩፒ እንከፍላለን፤›› በማለት እንግሊዞች በወቅቱ ወሰኑ፡፡ ወዲያው ሰዎች ይኼን ታክቲክ በመከተል ዕባብ ገድሎ ማምጣት ገንዘብ ያስገኛል በማለት ዕባብ የሚራባበት እርሻ በማዘጋጀት እያረቡና እየገደሉ ማምጣት ጀመሩ፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ዕባብ አስቸግሮናል በሚል የመጣው የክፍያ መፍትሔ ህንዶች ዕባብ እንዲያረቡ አደረገ፡፡ ነገር ግን የእንግሊዝ መንግሥት ጉዳዩን ሲያጤን የበጀት ወጪው እያደገ መጣ፡፡ ስለሆነም የበጀት ለውጥ (Allocation) መኖር አለበት በማለት ከዚህ በኋላ የተገደለ ዕባብ አንቀበልም የሚል ውሳኔ ላይ ደረሰ፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ዘዴው መጀመሪያ ላይ ዕባቦችን ቀንሶ የነበረ ቢሆንም፣ ወዲያው ግን አንከፍልም ሲባል እየረቡ የነበሩትን ዕባቦች አርቢዎቹ እንዲለቁና ከተማዋን እንዲያጥለቀልቁ አደረጓቸው ይላሉ፡፡

‹‹በአንድ አገርም መጀመርያ የተሠሩት ሥራዎች አስቸጋሪ ሲሆኑ፣ አስቸጋሪ የሆኑትን ጉዳዮች ለመቀልበስ የሚኬድበት መንገድ ሌሎች አስቸጋሪ ቀውሶችን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ለዚህም ይመስላል አሁን በኢትዮጵያ የችግር መደራረቦች እንዲስተዋል ያደረገው፤›› ይላሉ አቶ ዋሲሁን፡፡

የበጀት ጉድለት የሚፈጥረው ኢኮኖሚው በተመራበት ድክመት ልክ መሆኑን፣ ጉድለቱ እየተለጠጠ የሚመጣውም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ከኢኮኖሚ ባለሙያዎች አንደበት የሚሰማ ሙያዊ አስተያየት ነው፡፡

ምርቶችን ወደ ኢኮኖሚው የሚያመጡ በጣም አንገብጋቢ ፕሮጀክቶች ላይ የሚወጣው ገንዘብ፣ ብድርና ዕርዳታዎችን ለመጠቀም የነበሩ ድክመቶች፣ የአገር ውስጥ የገቢ መጠንን ለማስፋት የተሠሩ ሥራዎች በሙሉ ደካማ ሲሆኑ በአንድ አገር የበጀት ጉድለቱ ይለጠጣል ይላሉ፡፡

የኢኮኖሚ ተንታኙ እንደሚሉት፣ የበጀት ጉድለትን ለማስፋት የሚደረጉ ሙከራዎች ማይክሮና ማክሮ ኢኮኖሚውን ይጎዱታል፡፡ በትምህርት ቤቶችና በመሳሰሉት ላይ የሚደረጉት ጭማሪዎች ማይክሮ ተብለው ሲገለጹ፣ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲታተም የሚያስገድዱት ማክሮ ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህን ለመቀልበስ በተደራራቢነት የሚወሰዱት ዕርምጃዎች አሁን በኢትዮጵያም እየተወሰነ ነው ማለት ይቻላል በማለት ያክላሉ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ የቆየ በመሆኑ ተደራራቢ ታክሶችን ለመቀበል አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለአብነትም ኤክሳይዝ ታክስ የሚጨመረው አስመጪና አምራች ላይ ቢሆንም፣ ተፅዕኖው በቀጥታ ሸማቹ ላይ ይተላለፋል፡፡ የንብረት (ፕሮፐርቲ) ታክስ ግብር ባለንብረቱ ላይ ቢጨመርም ባለንብረቱ በቀጥታ ወደ የሚሰጠው አገልግሎት ያስተላልፈዋል፡፡ 70 በመቶ የሚደርስ ቀጥተኛ ያልሆነ የኢኮኖሚ ተሳትፎ ያለው የማኅበረሰብ ክፍልን ይዞ ጥቂት አምራቾች ላይ የሚጣለው የታክስ ሥርዓት ተፅዕኖው ታች ይሆንና ብዙዎችን የሚነካ ይሆናል፤›› በማለትም ያብራራሉ፡፡

የአብዛኛው ዜጋ የኢኮኖሚ አቅም ስላልተገነባ በአንዳንድ ዘርፎች መንግሥት እጁን እያስገባ ያደረገውን ጥረት ያስታወሱት አቶ ዋሲሁን፣ ለአብነትም ትምህርት ቤቶች ረዘም ላለ ጊዜ የደመወዝ ክፍያ ጭማሪ እንዳያደርጉ መከልከሉን ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹የአገልግሎት ወጪ ከፍተኛ ሆነብን›› በሚል ምክንያት ዳግም ለቀቅ በተደረገው የአከፋፈል ሁኔታ፣ ትምህርት ቤቶች በግማሽና በእጥፍ ጭማሪ ለማድረግ እንዲንደረደሩ እያደረጋቸው መሆኑን፣ ‹‹ገበያውን አረጋጋለሁ›› በሚል በመንግሥት የሚወሰዱት አንዳንድ ዕርምጃዎች የቤት ኪራይን ጨምሮ ሰፊ ተፅዕኖ ሊያመጡ እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡

የአገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ መሞከሩ አሉታዊ እንዳልሆነ፣ ገቢን ማሳደግ መሠረተ ልማትና የድጎማ ሥርዓቶች እንዲቀጥሉ የሚያደርግና ታች ያለውን ማኅበረሰብ ታሳቢነት ከግንዛቤ የሚከት እንደሆነ አቶ ዋሲሁን ያስረዳሉ፡፡

ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ የአገር ውስጥ የገቢ መጠንን ማሳደግ ነው? ወይስ የመንግሥት ወጪ አጠቃቀም ሥርዓት ማበጀት ነው በጣም አስፈላጊው?›› የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን የኢኮኖሚ ተንታኙ ያክላሉ፡፡

‹‹ገቢን አሳድጋለሁ›› በሚል የሚወሰደው የመንግሥት ውሳኔና ዕርምጃ ፈጣንና ዘርፈ ብዙ በተለይም ተደራራቢ ሆኖ ሲመጣ፣ ተፅዕኖው በአምራቹም ሆነ በሸማቹ ላይ ጫና እንደሚፈጥር በመግለጽ፣ ይህ እንዴት ነው መስተካከል ያለበት የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

‹‹የግብር ጫና ተደርጎ የግብርና ምርትና ምርታማነት የሚያድግ ከሆነ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በረዥም ጊዜ ውስጥም ቢሆን ይከፍላል፡፡ ነገር ግን ገቢ ተሰብስቦ የሚሠራው አንገብጋቢ ያልሆኑና ገበያ የማያመጡ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል የማይፈጥሩ ፕሮጀክቶች ወይም አስተዳደራዊ ወጪዎች ላይ ከሆነ የሚውለው በጣም አስቸጋሪ ነው፤›› ሲሉ አቶ ዋሲሁን ይሞግታሉ፡፡

አንዳንድ ክልሎች ደመወዝ መክፈል አለመቻላቸውና ይህም የሆነው አስተዳደሮቻቸውን በመለጠጥ ወደ ክልልና ዞን፣ እንዲሁም ሌሎች መዋቅሮችን ሲዘረጉ የሚከፍሉት ደመወዝ በማደጉ እንጂ በልማት ላይ ስላዋሉት አይደለም የሚለው ሐሳብ ከላይ ለተገለጸው ጉዳይ ለማሳያ የቀረበ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች እየተከሰተ ያለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት በሌሎች አገሮች እንደታየው፣ ቀጣዩ የቀውስና የግጭት መነሻ እንዳይሆን ያሠጋል የሚለው ሐሳብ በተደጋጋሚ ይንሸራሸራል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ኢኮኖሚ በሁለት ኃይሎች ይመራል፡፡ አንደኛው ራሱ ኢኮኖሚው ሲሆን፣ ሁለተኛው ፖለቲካ ነው፡፡ እዚህ ላይ መሠረታዊው ጉዳይ የፖለቲካ ፍላጎትንና የኢኮኖሚ ፍላጎትን አስታርቆ የተሄደበት መንገድ ነው ይላሉ፡፡ ቅድሚያ የፖለቲካ ቅኝትን ከግምት በመክተት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ኢኮኖሚውን በጣም ዋጋ ሊያስከፍሉት እንደሚችሉም ያስረዳሉ፡፡

የአንድ አገር ኢኮኖሚ በጣም ጠንካራ እንዲሆን ጠንካራ ፖለቲካ አስፈላጊ መሆኑንና ጠንካራ የፖለቲካ ተቋምና አስተሳሰብ ያስፈልጋል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ አገሪቱ ጥሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንድታወጣና ተጨማ ድጋፍና ብድር እንዲመጣ የሚያስችሉት ፖለቲከኞችና ዕሳቤያቸው መሆኑን በአስረጅነት በማቅረብ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የተደበቁትንም ሆነ ፊት ለፊት ያሉትን የፖለቲካ ፍላጎቶች ለማስፈጸም በሚኬድበት ርቀት ግን፣ ኢኮኖሚው እንዲጎዳ ማድረግ አስቸጋሪነቱን ያስረዳሉ፡፡

ከጦርነት በኋላ የአገር ውስጥ የገቢ መጠንን ማሳደግ፣ የግብር መረብ ውስጥ ያልነበሩ ሰዎችን እንዲመጡ ማድረግና ቀላል የቢዝነስ ምኅዳሮችን ማሳደግ እንደሚገባ እንደሚመከረው ሁሉ፣ ከግጭት በኋላ ያለ ኢኮኖሚ ድጎማ እንደሚፈልግና ድጎማ ለማድረግና የበጀት ጉድለቱን ለማስታረቅ የሚሠራ ሥራ መኖሩን ያክላሉ፡፡ በሁለት ጉዳዮች መካከል ያለው መስመር ጠባብ ስለሆነ ኢትዮጵያም በንፅፅር ተጠቃሚነት (Comparative Advantage) በምትለው ዘርፍ ላይ ርብርብ ብታደርግ ይመከራል ይላሉ ኢኮኖሚስቶች፡፡ ለአብነትም ግብርና አሁንም ርብርብ የሚፈልግ ዘርፍ እንደሆነ በአስረጅነት ያክላሉ፡፡

“Important Daily Satisfaction Model” የሚባለው ሞዴል እንደሚያትተው፣ መንግሥት መሠረታዊ ነው የሚለው ነገር ለሕዝቡ የኢኮኖሚ ዕርካታ ምላሽ የሚሰጥ ነው ወይ? የሚለውን ማረጋገጥ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አስፈላጊ ነገሮች ላይ ነው ርብርብ እያደረገ ያለው? የሚለውን መመርመር ተገቢ መሆኑን በመጥቀስ፡፡

የተለያዩ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት መንግሥት በጥናት ላይ የተመሠረቱ አዋጭ የገቢ ምንጮችን ማስፋት ይጠበቅበታል፡፡ በከባድ የኑሮ ውድነት እየተደቆሰ ያለውን ሕዝብ ከሚያገኘው ውስን ገቢ ላይ በተለያዩ መንገዶች የግብር ዓይነቶችን መቆለል ተገቢ አይደለም ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -