Friday, September 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ጊዜያዊ ስጦታ

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በእንግሊዝኛ ‹A – Temporary – Gift› የተሰኘው የአስማ ሁሴን መጽሐፍ፣ ‹‹ጊዜያዊ ስጦታ›› በሚል ርዕስ በቀለማውያን ተተርጉሞ በ2014 ታትሟል፡፡ የትርጉሙ አርታዒ አሕመድ ሑሴን (አቡ ቢላል) ናቸው፡፡

የመጽሐፉ ጭብጥ

‹‹ጊዜያዊ ስጦታ››፣ የአንዲት ባሏ የግብፅ ኢስላማዊ ወንድማማችነት በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ከአድማ በታኞች በድንገተኛ አደጋ የተገደለባት አሳዛኝ፣ ነገር ግን እጅግ ጠንካራ ሴት ታሪክ ያወሳል፡፡ ድርጊቱ የተከናወነው እ.ኤ.አ. ኦገስት 16 ቀን 2013 (ማለትም ነሐሴ 8 ቀን 2005) ነው፡፡

የመጽሐፉ ፋይዳ

መጽሐፉ ከሁሉ አስቀድሞ ፍቅር ከጋብቻ በኋላም ቢሆን፣ ሊያድግና ሊያፈራ የሚችል መሆኑን በማሳየት ሙስሊም ወጣቶች ሐላል ጋብቻ እንዲፈጽሙ የሚያደፋፍር ሲሆን፣ የሌሎች እምነት ተከታዮችም ዘላቂ ፍቅር ለመመሥረት ከጋብቻ በፊት ዝሙት መፈጸም እንደማያስፈልግ ያስተምራል። በሁለት የትዳር ጓደኞች ሊኖር ስለሚገባው መተሳሰብና መከባበር እስከ ቤተሰብ ድረስ ሥር ሊሰድ እንደሚችል ውብ በሆነ አገላለጽ ያስተምራል። ለመፈቀር፣ ሴቶች ለባሎቻቸው፣ ባሎች ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በረቀቀ መንገድም ቢሆን ወጣት ተጋቢዎች እንዲገነዘቡ ያደርጋል።

እጅግ አስደንጋጭ፣ አሳዛኝ፣ የመጨረሻ አለኝ የሚሉትን ነገር፣ ባል፣ ሚስት፣ ሌላም አላህ ቢወስድ ሁሉም በእርሱ ፈቃድ የሚከወን ስለሆነ መንፈሰ ጠንካራና ታጋሽ መሆንንም ያስረዳል።

የመጽሐፉ ትርጉም

ተርጓሚዎቹ ለደራሲው ታማኝ ሆነው የተረጎሙት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ለዚህ ታዳሚ ሲባል ስለትርጉም አንዳንድ ነጥቦችን ለማውሳት እወዳለሁ፡፡ በዚህም መሠረት ስለትርጉም ጥናት ካደረጉ ባለሙያዎች አንዱ ማይልደር ኤል ላርሶን (Larson, Mildred L). ናቸው፡፡ እሳቸው የሚጠይቁት ከመገኛው ቋንቋ ወደ ተቀባዩ ቋንቋ ሲመለስ ሐሳቡን በሚገባ አስተላልፏል?፣ እቅጫዊነቱ (አኪዩረሲ) ምን ያህል ነው?፣ በሚያውቀው ቋንቋ ተተርጉሞ የቀረበለት አንባቢ የደራሲውን መልዕክት ለመረዳት አስችሎታል?፣ ደራሲው ከቀረጻቸው ገጸ ባህሪያት ጋር ለመተዋወቅ፣ ለመግባባት፣ ሲቸገር ለመቸገር፣ ሲደሰት ለመደሰት፣ ሲያዝን ለማዘን፣ ወዘተ ችሏል?፣ መገኛ ቋንቋው ከተቀባዩ ቋንቋ በእጅጉ የራቀ እንኳን ቢሆን ምን ያህል ተመሳሳይ መልዕክት ለማስተላለፍ በቅቷል?፣ ተርጓሚው ሲተረጉመው የመገኛ ቋንቋውንና የተቀባይ ቋንቋውን የቃላት አፈጣጠር፣ አስተዳደግ፣ የሰዋስው አወቃቀር፣ የእርስ በርስ ግንኙነት፣ የሁለቱ ባህል የዕውቀት ደረጃ፣ ምን ያህል ነው? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

መግቢያ

የኔ ዐምር

ከብዙ ጥቅም አልባና የብቸኝነት ጊዜያት በኋላ ነበር ልቤ በልቡ ውስጥ ቤቱን ያገኘው፡፡ የእሱ ልብ ነበር ‹‹ከእኔ ጋር እስካለሽ ፍርኃትና ሐዘን አያገኝሽም›› ያለኝ፡፡ የእሱ ልብ እውነትን አሳየ እንጂ አልተናገረም፡፡ ምክንያቱም አብረን ያሳለፍናቸው እነዚያ ውብ ጊዜያት ሙሉ በሆነ ደስታና ደኅንነት የተሞሉ ነበሩ፡፡ እርስ በራሳችን በሚገባ የተጣመርን ጥንዶች ነበርን፣ መጀመሪያ ላይ ለማመን ከብዶን የነበረ ቢሆንም፣ ግን እንደዚያ ነበርን፡፡ እኔ ስናደድ በዝምታ ይታገሰኛል፣ እሱ ሲናደድ በዝምታ አልፈዋለሁ፡፡ ሐዘኔን ያስወግድልኛል፣ ሐዘኑን አስወግድለታለሁ፡፡ ትርጉም ያለው አንድ የእሱ እቅፍ ጭንቀቴን በሙሉ ልክ እንደ በረዶ ያቀልጠዋል፡፡ የእሱ አንድ ዕይታ፣ እጄን በእጆቹ ሲነካቸው ሁሉ ነገሬን ያረጋጋኛል፡፡ ሁሉም ነገር ደህና እንደ ሆነና ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለ እንዳምን ያደርገኛል፡፡

የኔ ዐምር

በትርጉም መሥፈርት መሠረት የጊዚያዊ ስጦታ ትርጉም ጥሩ ደረጃ የሚሰጠው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሌላው ኒያንግን ሁዋንግ የተባሉ የትርጉም ባለሙያ ሲሆኑ እርሳቸውም አንድ የትርጉም ሥራ ትርጉም ሊባል የሚችለው በመገኛው ቋንቋ የተላለፈውን መልዕክት የሚወክል ሆኖ የቀረበ እንደሆነ ነው ካሉ በኋላ፣ ‹‹ትርጉም ሳይንስ፣ ኪነጥበብ፣ ክህሎት ነው» ካሉ በኋላ «ከፍችና ከአመለካከት አኳያ ለመገኛ ቋንቋው፣ ለቅርጹና ለስታይሉ ታማኝ ሆኖ መተርጎም፣ የተተረጎመለት ሰው በሌላ ቋንቋ የጻፈለትን ሰው ሐሳብ በትክክልልና በቀላሉ እንዲረዳው ማስቻል ያስፈልጋል» ሲሉ ለትርጉም ሥራ ምን ያህል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚስፈልግ ያስረዳሉ፡፡ በእኚህ ሰው ትንታኔ መሠረት አንድ ሰው ለመተርጎም ከመነሳቱ በፊት የመገኛ ቋንቋን የቃላት፣ የሐረጎች፣ የምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ አባባሎች ወዘተ ማወቅ እንደሚጠበቅበት ያስገነዝባሉ፡፡ የሳይንስ ትርጉሞች በማያወላዳ መንገድ የቀረቡ፣ የቅኔ ግጥሞች ስሜቱን ሳይቀር የያዙ፣ ልቦለድ ታሪኮች መቼቱና ገጸ ባህሪያቱን በትክክል የሚገልጹ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ ባለሙያው ከዚህም በተጨማሪ ‹‹አንድ ትርጉም ሲሠራ በመጀመሪያ መገኛ ቋንቋውን ደጋግሞ ማንበብና መገንዘብ ሲሆን ሥራው ሲጀመር መታየት ያለበት ጉዳይ የቃላት አመራረጡና ዘይቤው (Diction)፣ የአገላለጽ ጥንካሬው (arugmentation)፣ ስፋቱና ጥልቀቱ፣ የሐሳብ ግድፈቱ (Omission) እና ድግግሞሽነቱ (Repetition)፣ ከመሠረታዊው ሐሳብ ያለው ተቃርኖ (Conversion)፣ የሐሳብ አደራደር ወይም አቀማመጥ የመለወጡ (Rearrangement)፣ ከዕውነታው፣ ከመሠረታዊ ሐሳቡ ያለው አፈንጋጭነት (Negation)፣ በረዥምና ድርብ ድብልቅ ዓረፍተ ነገር የቀረበውን ሐሳብ ከፋፍሎ ያቀረበት መንገድ (Division) ነው» በማለት ያብራራሉ፡፡

ከዚህ ትንታኔ አኳያ ትርጉሙን ከእንግሊዝኛና ዓረብኛ ቋንቋ ችሎታ፣ ከኢስላማዊ ትምህርት ችሎታ በማለት ከፍለን ልንመለከተው እንችላለን፡፡

በዚህም መሠረት ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው ተርጓሚዎቹ ለጸሐፊዋ ታማኝ ሆነው መተርጎማቸው ለመተርጎም የሚያስችል የእንግሊዝኛ ዕውቀት እንዳላቸው ለመረዳት ይቻላል፡፡ መጽሐፉ በዓረብኛ ባይጻፍም የጻፈችው ዓረብኛ በተለይም የግብፅ ዓረብኛ ተናጋሪ እንደመሆኗ መጠን በውስጡ ከዓረብ በተለይም ከግብፅ ዓረብ ባህል፣ አመለካከት፣ አስተሳሰብና እምነት ጋር ተያይዞ የሚነገር ወይም እነዚህ ነገሮች የሚገለጹባቸው ባህሪያት ስለሚኖሩት ጸሐፊው በዚህ ረገድ ያላቸው ዕውቀት ምን ያህል ነው? ብሎ መጠየቅን ከዚህ አንጻር ማየት ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ተርጓሚዎቹም ሆኑ አርታኢው ሙስሊሞች ስለሆኑ ቢያንስ ቢያንስ ከእስላማዊ አመለካከታቸው አኳያ ሊታይ የሚችል ቅርበት አላቸው፡፡ ከእንግሊዝኛው ወደ አማርኛ ትርጉም ሥራው ሲታይም ጥሩ ግንዛቤ አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ይህን መጽሐፍ የሌላ እምነት ተከታይ የሆነ ሰው ቢተረጉመው ኖሮ ችግሩ ፈጦ ሊታይ ይችል ነበር፡፡ 

አቻ ትርጉም

«ዊኪፒዲያ» የተባለው የድረ ገጽ ዓውደ ጥበብ ደግሞ በአንድ ቋንቋ የቀረበውን የሐሳብ ፍች ተረድቶ እኩል የሆነ ትርጉም ያለው ዓውድ፣ በሌላ ቋንቋ በማቅረብ ተመሳሳይ የሆነ መልዕክት የሚያስተላልፍ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህም ሲሆን ተተረጎመ ማለት ይቻላል፤» ይላል፡፡ ይህ ዓውደ ጥበብ ስለመገኛና ተቀባይ ቋንቋ የሚያቀርበው መሠረታዊ ሐሳብ ተመሳሳይ ስለሆነ እዚህ ላይ መድገም አላስፈለገም፡፡

የተለያዩ ባለሙያዎች እንደሚያስገነዝቡት የትርጉም ሥራ ሲሠራ የቃላት አጠቃቀም፣ አመራረጥ፣ ዕድገት እንደሁኔታው ሊለያይ ይችል ይሆናል፡፡ በአንዱ ቋንቋ ያለው ቃልም በሌላው ቋንቋ ላይኖር ይችላል፡፡ ወይም የመጀመሪያው ጸሐፊ ቀበልኛ ቃላት መጠቀሙ ትርጉሙ በመደበኛ መዝገበ ቃላት ላይገኝ ይችላል፡፡ እንደዚህ ያለው አጋጣሚ ሲኖር ቃሉን እንዳለ መጠቀም አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ኮምፒዩተርን በጥሬው እንደመጠቀም ማለት ነው፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የቃላቱ አመጣጥ ሥረ መሠረት ትርጉምም ሆነ የዓረፍተ ነገሩ አቀማመጥ እንደ ሁኔታው ሊለዋወጥ ስለሚችል ተርጓሚው አንድን ሥራ ሲተረጉም ይህንንም እግምት ማስገባት እንዳለበት ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡

ከዚህ ትርጓሜ አኳያ ‹‹ኤ ቴምፖራሪ ጊፍት›› በሚል ርዕስ አስማ ሁሴን የጻፈችውን ቀለማውያን ‹‹ጊዜያዊ ስጦታ›› በማለት የተረጎሙት ከሥራ ለማዋል ጥረት ተደርጓል ለማለት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ምናልባት ተርጓሚዎቹ እንደ ጸሐፊዋ ሴቶች ስለሆኑ ቁስሏን፣ ጉዳቷን፣ ብሶቷን ጥንካሬዋን ለመግለጽ ችለዋል ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ በትርጉሙ ገጽ 49 በእንግሊዝኛው ገጽ 31 ላይ ያለውን ለአብነት እንመልከት፡፡

Above all, the earth is never just one thing. I am also never just one thing.I write and share because that is how I survive. To write is to purge myself of this strange darkness within me, examine its shape and colour and taste so that I can attempt to transform it into hope.

And now, more than ever, I need to hope. ሲል በአማርኛው ደግሞ፣

ይህ ሁሉ ታዲያ ምድር በፍጹም ባለአንድ ገጽታ ብቻ አለመሆኗን ያሳያል፡፡ እኔም እንደዚያው፡፡ ካለሁበት ሕመምና ሐዘን ለማውጣት ስል ታሪካችንን ጽፌ አጋራኋችሁ፡፡ መጻፍ በውስጤ ያለውን ፅልመት እንዳስወግድ ያደርገኛል፣ ውስጤ ያለውን ድንግዝግዝ እንድፈትሽ፣ መልኩን፣ ቀለሙን እንድመረምርና ወደ ተስፋ እንድለውጠው ያደርገኛል፡፡ ስለዚህ ጻፍኩት። እናም አሁን፣ ከጠበቅኩት በላይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

በዚህ ትርጉም የእንግሊዘኛው አንቀጽ 3 የአማርኛው ትርጉም አንቀጽም 3 በመሆኑ የአንቀጽ አቀማመጥ ልዩነት አናይም፡፡ በትርጉም ረገድ ግን የተጻፈው ሐሳቡን በመውሰድ በራስ አገላለጽ ነው፡፡ ይህ ትርጉም ‹‹ከሁሉም በላይ ምድር አንድ ነገር ሆና አታውቅም፡፡ እኔም እንደዚሁ አንድ ነገር አይደለሁም፡፡ በሕይወት ለመቆየት የቻልኩት ስለጻፍኩትና ስላጋራሁ ነው፡፡ መጻፍ ከውስጤ ከነበረው ጨለማ (ጽልመት) መውጣት ማለት ሲሆን ቅርጹን፣ ቀለሙንና ጣዕሙን መሞከር ደግሞ ወደ ተስፋ ለማሸጋገር ያደረግሁት ሙከራ ነው፡፡ እና አሁን፣ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተስፋ ያስፈልገኛል›› በሚል ቢተረጎም መሬት አንድ ነገር ሆና አታውቅም ማለት ምን ማለት ነው? ምድር ለራሷ ነገር (thing) አይደለችም እንዴ? መጻፍ ማለት ለባለታሪኳ ሐዘን ሰቆቃዋን አውጥታ ለወረቀቱ መስጠት ማለት ሲሆን በመጻፍ ሒደት የሐዘን ሰቆቃዋን ጥልቀት፣ ገጽታ፣ ቅርጽ ፍንትው አድርጋ በማሳየት ከሐዘን ሰቆቃው ባሻገር ወዳለው ተስፋ ማሸጋገር ነው፡፡ ይህ አገላለጽ በመጽሐፉ የተለያዩ ገጾች በተለያዩ ሰበቦች ተገልጾ የምናገኘው ሲሆን በተለይ በገጽ 119 እንደሚከተለው ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡

ልባችን /ነፍሳችን/ በተመሳሳይ ሁኔታ በአንድ መንገድ ላይ አትሄድልንም፤ በጣም ለስላሳ፣ በአካባቢዋ ባሉ ነገሮች የምትጎዳ፣ ልትቀያየር የምትችል፣ የራሷ የሆነ ከፍታና ዝቅታ ያላት ናት። በብርሃንና ጨለማም ትገለጻለች፤ ያለ ምንም እምነትና አምልኮ ተርባ ስትቆይ ቀስ በቀስ በመዛግ የማትታይ ትሆናለች። ስለዚህ አማኞች ፈፅሞ አይረጋጉም፤ ሁልጊዜ ሚዛናዊና ለልባቸው ሕይወት የሚሰጥ ነገር ይፈልጋሉ።

በመቀጠል አንተን ማጣት ፀሐይ በሌለችበት ዓለም ላይ እንደመንቃት ነው። አንተን ማጣት በበረሃ ላይ ውኃ አጥቶ እንደመኖር ሆኖ እያለ፣ ዓለም የእኔን ካለአንተ መቀጠል እንዴት ሊጠብቅ ይችላል? ምናልባትም በአንዴ ተስፋ ቆርጦ ማለፍ ያለውን የፍቅር ቅዝቃዜ፣ በልብ ላይ ያለው ውጋትና ድርቀት አልተሰማቸው ይሆናል። ምናልባትም ያጡት አንተን ብቻ ስላልሆነ አንተን ማጣት ምን ማለት እንደሆነ አይረዱት ይሆናል፣ ከቀን ወደ ቀን የአንተን ዕይታ ማጣቴና አንተን ቀዝቃዛ ሆነህ መመልከቴ፣ ሌላ ሴት ብትሆን የማትቋቋመውን ሁኔታህን ማየቴ አሁን ላይ ይገርመኛል።

አሁንም መኖር የቻልኩት ልጃችን እንድታድግና እንድትጫወት ፀሐይን በመፈለጓ ነው። የኔ ቆንጆና አንጸባራቂ ጓደኛ! እኔ አጥቼሃለሁ፣ ስለዚህ ያንተን ቦታ ወስጄ አንጸባርቃለሁ። ምናልባትም አንድ ቀን እሷም እኔ ፍቅርን ብርሃናማ ሆኖ እንደተረዳሁት ትረዳ ይሆናል።መቀጠልን የመረጥኩት እንደዚህ ነው፡፡

ሁልጊዜም ሩቂያን እጇን ይዤ በሕይወት መንገድ ወደፊት ስጓዝ፣ ምንም ማድረግ አልችልም፣ ግን ምናልባት በዚያ ግድያ ሕይወቱ ባያልፍ ኖሮ ይሞላ የነበረውን የአባቷን ቦታ እመለከታለሁ። ምንም ማድረግ አልችልም፣ ግን ምንም ነገር ባደርግ አንድ እጇ ባዶ መሆኑን አስተውላለሁ። የእኛን ፍቅር ዐምርን የገደሉትን እነዚያን ራስ ወዳዶች የአላህ ቅጣት እንዲያገኛቸው ዱዐ አደርጋለሁ። የሆነ ጊዜ ላይ የእውነት የሠሩት ሥራ ምን እንደሆነ ይገባቸው ይሆናል፣ ያኔ ከልጄ እጅ ላይ የማንን እጅ እንደነጠቁ ይረዳሉ (ገጽ 90)።

የእኔ ምኞት ምድርን ስትመጪ ከነበረችበት የተሻለች አድርገሻት እንድትሄጂ ነው። ይህ ነው የአንቺ ዓላማ፣ ይህ ነው አንቺ ልትሆኚ የሚገባሽ፣ ሁላችንም ልንሆንና ልናደርገው የሚገባን ይህ ነው ማማ የእኔ ፍቅር። (ገጽ 94)

‹‹ከሁሉም በላይ ምድር አንድ ነገር ሆና አታውቅም፡፡ እኔም እንደዚሁ አንድ ነገር አይደለሁም፡፡ በሕይወት ለመቆየት የቻልኩት ስለጻፍኩትና ስላጋራሁ ነው፡፡ መጻፍ ከውስጤ ከነበረው ጨለማ (ጽልመት) መውጣት ማለት ሲሆን ቅርጹን፣ ቀለሙንና ጣዕሙን መሞከር ደግሞ ወደ ተስፋ ለማሸጋገር ያደረግሁት ሙከራ ነው፡፡ እና አሁን፣ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተስፋ ያስፈልገኛል›› ስትል በገጽ 90፣ 94፣ 119፣ እና በ189 የገለጸችውን ያንጸባርቃሉ፡፡ ይም ይተነብያሉ፡፡ በእንግሊዘኛው ፎርሻዶ በሚለው የአጻጻፍ ቴክኒክ መመርመር ይቻላል፡፡

ዳንኤል ዌይስቦርት የተባለው ባለሙያ ደግሞ፣ ተርጓሚዎች የመገኛውን ቋንቋ መልዕክት በትክክል የማስተላለፍ ግዴታ አለባቸው በማለት ያስገነዝባል፡፡ ማክጉየሪ የተባለው ሰው ደግሞ በመገኛ ቋንቋ የተላለፈው መልዕክት በተቀባዩ ቋንቋ የሚገኘው መልዕክት ተመሳሳይ መሆን ብቻ ሳይሆን አወቃቀሩም ቢሆን ተቀራራቢ መሆን አለበት በማለት ያስገነዝባል፡፡ በዚህ ረገድ ጊዜያዊ ስጦታ በመልካም ሁኔታ የተተረጎመ ሲሆን አንባቢው በመገኛ ቋንቋው የተጻፈው ምን ይሁን ሳይል የሚያነበው ሆኖ ይገኛል፡፡

ኒውማርክ የተባለው ሰውም እንደገለጸው ‹‹ትርጉም ማለት በአንድ ቋንቋ የተላለፈውን መልዕክት በሌላ ቋንቋ መተካት ጥበብ ነው»፡፡ ሲተረጎም ቋንቋውንና ባህሉን አሳምሮ ማወቅ እንደሚገባም የሚያስተምሩ ምሁራን አሉ፡፡ ‹‹ትርጉም ቃል በቃል፣ ውርስ፣ ሊሆን ሲችል ሲተረጎምም ሐሳቡ ተስፋፍቶ ወይም ተጨምቆ ቢቀር የተሻለ መሆኑ ታምኖ የሚቀርብበት ሁኔታ ይኖራል፤›› በማለት ያስረዳል፡፡

ከዚህ አኳያ ተርጓሚዎቹ የግብፅ ወይም የካናዳ ወይም የሁለቱን ቋንቋና ባህል በሚገባ ያውቃሉ ማለት ነው? በኔ ግምት እንደዚህ ያለው ችሎታ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ስንቱ የዓለም ተርጓሚ ነው ሲተረጎም ቋንቋውንና ባህሉን አሳምሮ የሚያውቀው? ብለን ስንጠይቅ በቂ መልስ አናገኝም፡፡ ተርጓሚዎቹ ግን እንደ ጸሐፊዋ የእስልምና እምነት የሚከተሉና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ስለ ግብፅ ስለሚያውቁ ከባህሉና ከቋንቋው ብዙ የራቁ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ በገጽ 94፣ 123፣ 131፣ 155 እና 189 የሚከተለው ሰፍሮ እናገኛለን፡፡

ዲሴምበር 25 ቀን 2013

አራት ወር ከአሥር ቀናት አለፉ። የዒዳዬ ጊዜ አበቃ። ራሴንና ልቤን ቀና ማድረግና ወደተለመደው፣ የድሮው የኑሮ ሁኔታ መመለስ አለብኝ። እውነታው ግን አሁንም የሚሰማኝ ትናንት ያጣውህ ያህል ነው፡፡

ከጠመንጃው ጀርባ በነበረው ደካማ ነፍስ ላይ ግን አዝንበታለሁ። ያንተን ነፍስ ከአካልህ ለማውጣት ምክኒያት የሆነውን ሰው ግን ፍትኃዊ የሆነው አላህ (ሱ.ወይመልስለታል፣ ሁሉም ነገር በሚታወቅበት ቀን እሱ ላይ የሚመሰክሩት ብዙ ናቸው። ያለምንም ወቅትና ቁሳዊ ገደብ፣ በጊዜያት ሒደት በማይደበዝዝና በማይከስም ሁኔታ መሬቱ በደምህ እንደተበላሸ ነው።

እኛ ራሱ የራሳችን አይደለንም። አላህ (ሱ.ወ) ዐምርን ለሆኑ ጊዜያት እንደ ስጦታ ሰጠኝ፣ አላህ ይህንን ስጦታ በመውሰዱም ዐምር እስካሁን ከእኔ ጋር ቢኖር የማልማረውን ብዙ ነገር አስተምሮኛል፣ ስለ ሕመም፣ ጀግንነት፣ መሰዋዕትነት አስተምሮኛል። ወደ ዘለዓለማዊና እውነተኛ ወደሆነው ቤት እንድጓጓ አስተምሮኛል። ምንም ያህል ወደዚህ ዓለም ተረከዜን ቆፍሬ ባስገባ፣ እርሱ በፈለገው ጊዜና ቦታ ወደእርሱ የምመለስ መሆኔን አስተምሮኛል። አንዳንድ ጊዜ የሚሰጡን ስጦታዎች የሚያስፈልጉንን ያህል፣ የተሰጡንም ስጦታዎች ሊወሰዱብንም ያስፈልገናል። ምናልባትም እንደዚያ ሲሆን ለስጦታው ሰጪ ያለንን ፍላጎትና ፍቅርን እንረዳለን።

የሚቆጠረው እንባ

ሩቂያ ዓመት ከስድስት ወር ሲሞላት በራሷ በመተማመን፣ የቤተሰቦቿን ፎቶ ይዛ ወደ እኔ እያመላከተች ማማ፣ ወደራሷ እያመላከተች ረቃ (እስካሁን ስሟን በሥርዓት መጥራት አልቻለችም) ወደ ዐምር እያመላከተች ደሞ ባባ ትላለች።

“ባባ!”

እኔ እንባዬን መቁጠር አልቻልኩም፣ የሚጠረጉት ወዲያውኑ ነበር። ከአካባቢውም ተነው የተረሱ ሆነዋል። የዐምር ቤተሰቦችም እንባቸውን አልቆጠሩም። የሩቂያ እስካሁን አልታወቀም ነገር ግን የትንሳኤ ቀን ሲመጣ፣ አላህ ሁሉንም ፍጥረታት ወደ እርሱ ሲሰበስብ፣ እንደገና ነፍሳችንን ሲያጣምራት እርሱ ፊት ለፍርድ እንቀርባለን። በዚያም ቀን ተመልሶ የማይታይ የሕይወታችን ቅፅበት የለም። እያንዳንዱ የፈፀምነው ድርጊት ድንገተኛ በሆነ ትውስታ መልሰን እናያለን፣ ሁሉም በድብቅም ሆነ በግልፅ ጨለማን ተገን አድርገን ይሁን በቀን ያነባናቸው እንባዎች ይቆጠራሉ።

የሕይወት ሸክም ከባድ በሚሆንበት ወቅት ጉልበትህ ሲብረከረክ፣ እጆችህ ላይ ያሉት ጡንቻዎች የያዝከውን ሸከም መሸከም ሲያቅታቸው ወደ መሬት እየተመለከትክ ‹‹ከዚህ መሞት አይቀልም!›› እያልክ ትገረማለህ፡፡ ሰዎች የሕመማቸውን መጨረሻ ይመኛሉ፡፡ ነገር ግን በፍፁም ሞትን አይመኙም፡፡ በሕመማቸው መጨረሻ ምን እንደሚመጣ ቢያውቁ ቢያንስ አይመኙም፡፡ ፍፁም ጥልቅ የሆነ ብቸኝነት እንደሚገጥማቸው፣ ከአፈር በታች ሲሆኑ ያላቸው እምነትና በጎ ሥራቸው ብቻ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ካላወቁ፣ የሚወዷቸው ሰዎች የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት ትተዋቸው ሲሄዱ የኮቴያቸው ድምፅ እንደሚሰማቸው ቢያውቁ አያደርጉትም፡፡

መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ‹‹ከእናንተ መካከል ማናችሁም ሞትን አትመኙ መልካም ሥራ ያለው ቢጨምር ኃጢአት የሠራ ቢመለስ እንጂ›› (ቡኻሪ)፡፡

በአምስቱ ገጾች የሰፈረውንና በሌሎችም ገጾች በተለይም ፈውስ የሚለው ምዕራፍ ስለ ሃይማኖቱ የማያውቅ ሰው ቢተረጉመው ኖሮ ያለ ችግር ያከናውነዋል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ከአምስቱ ገጾች እንደምንረዳው ተርጓሚዎቹ ሙስሊሞች በመሆናቸው ጸሐፊዋ ምን ዓይነት መልዕክት ማስተለለፍ እንደፈለገች ለመረዳት እንዳስቻላቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡

ጋብሪየላ ባስኮ የተባለው ባለሙያም ስለ ትርጉም ቴክኒክ ሲያስረዳ ተርጓሚው ሲተረጉም የተዋሳቸውን ቃላት በአይታሊክስ ቢያስቀምጥ ይመረጣል፡፡ የዓረፍተ ነገሮች አቀማመጥ ለውጥ ማድረግ ሊኖር ይችላል፡፡ በመገኛው ቋንቋ ያለው ምሳሌያዊ አነጋገር ወይም ሐረግ በተቀባዩ ቋንቋ ባይኖር ከዚያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ማስቀመጥ፣ ‘Modulation’ ምሳሌ ላንተ ትቼልሃለሁ የሚል ቢኖር «ውሰደው» በሚል መተካት፣ አቻ በሆነ መንገድ መተካት ‘Reformulation or Equivalence’፣ የቄሶች ዳንስ ከማለት የቄሶች ሽብሸባ፣ ረገዳ ቢሆን ይመረጣል፡፡ በተቀባዩ ቋንቋ ወይም ባህል የሌለ አቀራረብን በራስ መተካት ለምሳሌ በአንድ ሆቴል በእንግሊዝኛ «ሜኑ ዲሽ» የሚል ቢኖር «የዕለቱ ድስት» በማለት ከመተርጎም «የዕለት የምግብ ዝርዝር ማሳያ» በማለት መተካት፣ አንዱ ቃል በሌላው ቃል በፍጹም መተርጎም የማይቻል ቢሆን ከዚያ ጋር ተቀራራቢ በሆነ ወይም አካኪያሽ ቃል መተካት Compensation ለምሳሌ በእንግሊዝኛው (you) ዩ የሚለው ቃል አንተንም አንቱንም የሚያጠቃልል በመሆኑ በአማርኛ ሲተረጎም እንደሁኔታዎ አንቱ ወይም አንተ ብሎ መለየት ያስፈልጋል፡፡

ሙሐመድ አልበክሪ የተባለ የሰሜን አሪዞና ምሁር የሥነ ጽሐፍን ትርጉም በሚመለከት ከአንድ ሥራ በመነሳትና የተለያዩ መረጃዎችን በመጥቀስ እንዳመለከተው ሲተረጎም የትረካ ዘይቤው፣ በዓረፍተ ነገር ውስጥ ባለው አገባብ መሠረት ማድረግ (Semantic Prosody)፣ ከሰዋስዋዊ አቀማመጡና ሥርዓተ ነጥቡ (Syntax and Punctuation)፣ በሰዋስው ውስጥ ያለው የጾታ አገላለጽ (Grammatical Gender) ለምሳሌ በሴትነት የሚጠሩና በወንድነት የሚጠሩትን ለይቶ ማወቅ ድመቷ፣ አይጧ፣ ነፋሱ፣ ዝናቡ፣ ወዘተ የሚሉትን ለይቶ ማወቅ ይስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ዘይቤያዊ አነጋገሮች (Metaphors)፣ የሾርኒ አነጋገሮች (Allusions)፣ ይኖሩ እንደሆነ  ማስተዋል ይገባል፡፡

ከግብፅ ወደ ቶሮንቶ ስመለስ ቤተሰቦቼ አየር ማረፊያ መጥተው ሲቀበሉኝ እኩለ ሌሊት ሆኗል፡፡ ሩቂያን በመኪና መቀመጫዋ ላይ አስቀምጬ አጠገቧ በዝምታ ተቀመጥኩ። የልቤ ሁለተኛ አካል ሳይኖር እንዴት ወደ ቤት እንደምገባ ግራ ገብቶኛል። በዚሁ ቅጽበት ወደ መስኮት ተመለከትኩ፡፡ ከባድ ከሆነ ጥበቃ በኋላ ጨረቃን ከዚህ በፊት አይቻት በማላውቀው መልኩ ጥልቅና ወርቃማ ሆና ተመለከትኳት። በእርግጥ ሙሉ ጨረቃ አልነበረችም፣ ግማሽ ነበረች። ቢሆንም ግን በህልሟ ላይ ያለችውን ትመስላለች። ያኔ የሚገርም የሆነ ሰላም በውስጤ ተሰማኝ፣ እንደዚህም ስላረጋጋኝ አላህን ከልቤ አመሰገንኩት (ገጽ 96) ።

ተምሳሌታዊ አገላለጽ

በመጽሐፉ ውስጥ በርካታ ተምሳሌታዊ አገላለጾች መኖራቸውን የሚረዱት አንባቢው ስለሚያነበው ውስብስብ ታሪክ በቀላሉ መረዳት እንዲችል ለማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጸሐፊው አንድን ትልቅ ሐሳብ በአንድ ወይም በተወሰኑ ተምሳሌታዊ አገላለጾች ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ የደራሲው በጥልቅ ስሜት የተሞላ ሐሳብ ለመግለጽም በተምሳሌታዊ ቴክኒክ መጠቀም በታላላቅ ጸሐፊያን ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ተምሳሌታዊ ቴክኒክ በንጽጽር፣ በአሽሙር፣ በሙሻዙር ሐሳባቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ በመጽሐፉ ገጽ 111 የሚከተለው ሰፍሮ እናገኛለን፡፡

እኔ የሆነ ጌዜ ቤት ነበረኝ። ዐምር እጄን ይዞ ‹‹አንቺ ለኔ ቤቴ ነሽ›› ሲለኝ አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ ምድር ላይ ያለሁት ቤቱ! እሱም ለእኔ ቤቴ ነበር። አሁን ግን እሱ ከዚህ ዓለም ተሰናብቶ ሄድዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሥር መሠረት የሌለው ከርታታነት ይሰማኛል። የጓዝ ጥቅሙ አይታየኝም። የትኛውም ቦታ ለእኔ ደስ የሚልና የሞቀ አይደለም። ከዚህ በኋላ ቤቴ የትም አይደለም። ቤት ለሌለው ልብ ደግሞ ከእውነተኛው ቤት ሌላ መፍትሔው ምንድነው? ለዚህ ቀዝቃዛና ጨለማ ለሆነው ጊዜ ጥገኝነትን፣ ዘልዓለማዊ የሆነውን መጠለያና ዘልዓለማዊ መሸሸጊያ ከሆነው አላህ አሰ-ሶመድ (የሁሉ መጠጊያ) መለመን ነው። ከእርሱ ውጪ ያለው ሁሉ ይቀያየራል። ከእርሱ ውጪ ያለ ሁሉ ወዳቂ ነው። ቤት የሰው ዘር በሙሉ፣ የእኛ የመጀመሪያ እናትና አባቶቻችን የኖሩበት ቦታ ነው። ያ ቦታ ደስተኛ የነበሩበት ነው። ቤት ማለት በጊዜና ቦታ ሰንሰለት የማይገደብ ውበት ነው። ተራችን ሲደርስ አንዴ የምንሄድበት ቦታ አይደለም። ምግባችንን የምንበላበት፣ ልብሳችንን የምንቀይርበት ቦታ አይደለም። ያ ቤት ማለት ትንሽ ጊዜ የምንቆይበት ጊዜያዊ የሆነ ቦታ ነው። አዎ! ቤት ማለት ልባችን ያለበት ነው። ስለዚህ ጥያቄዬ ‹‹ያ ቤት የት ነው?›› መሆን አልነበረበትም አውቃለሁ ቤቴ ጀነት ነው። ጥያቄው መሆን የነበረበት፣ ልቤ ግን የት ነው? የሚለው ነው። ለየትኛው ነው የሚጓጓው? ለእውነተኛው ወይስ አላፊ ለሆነው ቦታ

ሌላው ተምሳሌታዊ አገላለጽ በጺም ተመስሎ የሚመጣው ነው፡፡ በገጽ 263 እንደሚከተለው ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡

ዐምር ካለፈ ከዓመት በኋላ ቤት ለመቀየር እየተዘጋጀሁ በነበረበት ወቅት በድሮ ልብሶቻችን መካከል ልዩ የሆነውን የዐምርን የፂም ዘለላዎች አገኘሁ፡፡

በመዳፎቼ መካከል እንደያዝኳቸው ረዥምና የተጠቀለሉ የፂም ዘለላዎቹን ስመለከት በነበርኩበት ቆሜ ቀረሁ፣ ተንቀጠቀጥኩ ያኔ እንደነበሩት አሁንም ጥቁር ናቸው።

ከእሱ ጋር ከተለያየሁ አንድ ዓመት ሆኗል፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን እንኳን የሆነን አልመስል አለኝ፣ ምንም ያለፈ አይመስልም። በጠዋት ወደ ሥራ ለመሄድ ሲዘጋጅ የነበረበትን ቀን አስታወሰኝ፣ መስታወት ፊት ለፊት ቆሞ ፀጉሩንና ፂሙን ሲያበጥር እነዚህ የፂሙ ረዣዥም ዘለላዎች ሳይታወቁት ወደመሬት ወድቀው ከአቧራው ጋር ይደባለቃሉ፡፡

እሱ እዚህ ክፍል ውስጥ እኔ ከመግባቴ በፊት ለዕለት ጉዞው እየተዘጋጀ እንደነበር ተሰማኝ። በዚያን ጊዜ የፂሙ ዘለላዎች ምንም ላይመዝኑና ቅንጣት ያህል ዋጋ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ሆኖም አሁን ግን እጅግ ውድ ዋጋ ከምሰጣቸው ንብረቶቼ መካከል ሆነዋል፡፡

ፂሙን እንዳገኘሁ በመጀመርያ ያደረግኩት ነገር፣ ወደ ማዕድ ቤት ሄጄ ጠንካራ ላስቲክ ሆኖ መዝጊያ ያለው መያዣ (ዚፕ ሎክ) ውስጥ መክተት ነበር። ከመያዣው ውስጥ ያለውን አየር ሙሉ በሙሉ ለማስወጣት ሞከርኩ፡፡ ቀጥሎም በተደጋጋሚ እያሳነስኩ አጣጠፍኩት፡፡ ከዚያም በትንሿ ቦርሳዬ (ዋሌት) ውስጥ ከሠርጋችን አነስተኛ ፎቶ ጋር አብሬ አስቀምጬ ቆለፍኩበት።

ይህንን የጠፋ፣ ባለቤቱ ከተቀበረ ዓመት ያለፈውን የፂም ዘለላ ባገኘሁበት ቅፅበት የዐምርን የቀብር ቀን አስታወስኩ። ዓመት እንዳለፈው ትውስ አለኝ። በሐኪም ቤቱ የአስክሬን ማስቀመጫ ክፍል ውስጥ ከጎኑ ከቆምኩ፣ ፊቱን አተኩሬ ከተመለከትኩና እነዚያን ቀጫጭን ፂሞቹን ካሻሸሁ በአብሮነት ያቺ የመጨረሻ ጊዜያችን ነበረች። በገጽ 267 ደግሞ ዐምር ከሞተ ከዓመት በኋላ በድሮ ልብሶች መካከል ተሸጉጠው ያገኘኋቸው ትንሽ የፂም ዘለላዎች ለእኔ ትልቅ ግኝት ነበሩ። አላህ (ሱ·ወ) ከሰጠኝ ምቾቶች በተጨማሪ አሁንም ድረስ በምሄድበት ማንኛውም ቦታ ይዤው ነው የምሄደው። ስለምናፍቀውና ስለምወደው ብቻ ሳይሆን በአንድ ወቅት እዚህ የነበረ እውነተኛ ሰው በፍጥነት ከምድር ላይ እንደተወሰደ ስለሚያስታውሰኝ፣ ፂሞቹ የእኔና የዐምርን የአብሮነት መጨረሻና ወደ አፈር ውስጥ ከመወርወሩ በፊት የነበረውን ቅፅበት ያስታውሱኛል። የቀብሩ ቀን አላህ (ሱ.ወ) እንዴት ከዚያ ከባድ ጭንቅ ውስጥ መውጫ እንዳበጀልኝ፣ አላህ (ሱ·ወ) ደስታን እንደሰጠኝና እየሰጠኝም እንዳለ ያስታውሰኛል። ሁልጊዜ ጠዋት ስነሳ ነብሴ በሰውነቴ ውስጥ እንዳለች የአካሌ ሁሉም ክፍሎች የአላህን ፍቅር ለማግኘት በሚያስችለኝ ነገር የመሥራት ሌላ ዕድል እንደተሰጣቸው ያስታውሰኛል። እያንዳንዷ ቀንና እያንዳንዱ ፀጋ ወይም ቡራኬ ስጦታዎችን ሁሉ ሰጪ ከሆነ የተሰጠኝ እንደሆነና ሁሉም ሕመም ራሱ ዘውታሪ እንዳልሆነ ያስታውሰኛል።

ከሐዘን ወደ ብሩህ ተስፋ ያለው ሕይወት መመለስ፡፡

የምፈልገው ዕረፍት የለሽ መሆንን ነው፡፡ የደከሙ ዓይኖችና እጆችን እፈልጋለሁ፡፡ የምችለውን ነገር ሁሉ እስከምሰጥ፣ በሁሉም የሰውነት አካሎች ጌታዬን እስከምገዛ፣ ሌሎች ሰዎችን በችግሮቻቸው ጊዜ እስከምደግፍ መቃብሬ ውስጥ እስከምገባ በፍጹም ማረፍን አልፈልግም። የማረፊያው ጊዜ በጣም ቅርብ ነው፡፡ የምፈልገው ነገር በዚህ ሕይወት ዕረፍት የለሽ መሆንን ነው፡፡

መጠገን

ዐምር ባለቤቴ፣ አዛኜ፣ መተማማኛዬ፣ አፍቃሪዬና አጋሬ ነበር፡፡ በድንገት እሱን ካጣሁ በኋላ ብቸኝነት ተሰማኝ፡፡ ከሁሉም የተለየ አየር እተነፍስ ነበር፡፡ ከወላጆቼና ከጓደኞቼ የተለየ ቋንቋ እናገር ነበር፡፡ ወዳልተለመደ ሁኔታ ተቀየርኩ፡፡ እየደበዘዝኩና እየጠፋሁ ነበር፡፡ ማንም ሊረዳኝ አልቻለም፣ እኔም ማንንም መረዳት አልቻልኩም። እዚህ ምድር ላይ የቀረሁት እኔ ብቻ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር፡፡ ሕመም ባይተዋር ያደርጋል፡፡ የሕይወትን አሳዛኝ ክስተት ለመረዳት ሰዎች አንዳንድ ምልክቶችን፣ ምቾቶችንና የተለየ ክስተት ፍለጋ ወደ ሰማያት ይሄዳሉ፡፡ እባካችሁ ተረዱኝ፣ ከዚህ ሕመም እንድድን እርዱኝ እያሉ ይናገራሉ፡፡ በፍጥነት ጥያቄያቸው መልስ ካላገኘ ራሳቸውን ዝም ብለው ይመለከታሉ፣ ይዞራሉ ወይም ይናደዳሉ እናም ይሰበራሉ፡፡ ለዚህ ነገር መልስ ሰዎች በተደጋጋሚ ‹‹በፈተና ውስጥ ስታልፍ አላህ የት እንዳለ ካሰብክ አስተማሪ በፈተና ወቅት ዝም እንደሚል አስታውስ›› ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ይህ ንግግር ምንም ጥቅም የሌለው ነው ምክንያቱም እውነታው አላህ (ሱ.ወ) በፍጹም ዝም አለማለቱ ነው፡፡ እርሱ ተማሪዎች አሰጨናቂ ፈተና ላይ በሚሆኑበት ወቅት መናገርን የሚከለክል አይደለም፡፡ የመመሪያ እና የመፈወስ ቃሉ በፈለግነው እና በማንኛውም ሰዓት ለማንበብ በምንችለው መጽሐፍ ውሰጥ ተመዝግቧል፡፡ እርሱ ዝም አላለንም፣ እኛ ነን ለማዳመጥ አሻፈረን ያልነው፡፡ ካደመጥን አላህ (ሱ.ወ) ራሱን አል-ጀባር ብሎ ገልጿል፡፡ ተከላካይ፣ አጽናኝ፣ የሁሉም ቁስሎች ፈዋሽ ማለት ነው፡፡ ጀብር የሚለው ቃል ስርወ ቃሉ ጃቢራህ ነው፡፡ የተሰበረን አጥንት ለመጠገን የሚያገለግል ማለት ነው፡፡ በዚህ ህልውና ወደፊት ስንሄድ በትክክል ህልውናችን ወደ ስበርባሪነት ሲቀየር መሰበሩ በሚፈጥረው ድምፅ ስንደናገጥ አላህ አንዳንዴ እንዲህ እንዲሰማን ይረዳናል፡፡ የተሰበረውን መጠገን የሚችለው እርሱ ብቻ ነው፡፡ የሚቀይረን እንደገና ልባችንን ሙሉና ጠንካራ የሚያደርገውም እርሱ ብቻ ነው፡፡

 {እናንተ ሰዎች ሆይ! የጌታችሁ ግሳጼ በደረቶች ውስጥም ላለው (የመጠራጠር በሽታ) መድኃኒት ለምዕምናንም ብርሃንና እዝነት በእርግጥ መጣችላችሁ፡፡} (ዩኑስ10፡57)፡፡

አላህ (ሱ·ወ) ለእኔ መንገድን ያበጀልኝ በምክንያት ነው፡፡ ጥቅልና ሙሉ ምክንያቱንም እርሱ ብቻ ነው የሚያውቀው፣ አሁን ላይ እኔ ትናንሽ የምክንያቶቹን ክፍሎች በጉዞዬ ውስጥ እያወቅኩኝ ነው። ዐምርን ማጣት ማለት ሁሉንም ዕቅዶቼን ወደኋላ ትቼ ዳግም በዚህ ምድር ላይ ያለኝን ዓላማ መገምገም ማለት ነው። የእሱ መሄድ ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ወዳልታወቀ አቅጣጫ ነው ያቀጣጨው። ባለፉት ዓመታት ብዙ ሰዎች በጽሑፌ ዳግም ቀና ብለዋል፣ በዐምር ፍቅር ምርኮኛ ሆነዋል፣ እኔም አካፍዬዋለሁ፣ እነዚህ አንባቢዎች በአዲሱ መንገዴ ላይ አብረውኝ ተጉዘዋል፣ በውልብታም ቢሆን የፍቅርን፣ የውበትንና የማጣትን ክብደት አይተዋል፣ የፅልመትን መካከል ምስክር ሆነዋል፡፡ እኔም አዳዲስ ህልሞችን እንዴት እንደማገኝና ከመሬት ቆፍሬ በምን መልኩ ማውጣት እንዳለብኝ ተምሬያለሁ።

አላህ (ሱ·ወ) በችግር ውስጥ ላሉ አማኞች ሁሉ ቃል ገብቷል፣ እኔም ከቃሉ የሆነ ብዙ ምቾት አይቻለሁ፣ ልጄ በየቀኑ ደስታን ታመጣልኛለች፣ ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ አብረውኝ ቆመዋል፣ በዚህ ወጀብ ውስጥም በሁለት እግሮቼ መራመድ እንድችል ረድተውኛል፣ አዕምሮዬ አስደሳችና አስገራሚ በሆኑ የፈጠራ ሐሳቦችና የሥራ ዕቅዶች ተሞልቷል። ፀሐይ አሁንም በየቀኑ ትወጣለች፣ በእኔና በልጄ ላይ ብርሃኗን እያንፀባረቀችና እያሞቀችን፣ ሙሉ ጨረቃም ሰማይን ግርማ ሞገስ እያላበሰች እዩኝ እዩኝ በማይለው ብርሃኗ እነዚያን የጨለማ ምሽቶችን እየሞላች ተስፋን ታንሾካሹካለች። አላህ (ሱ.ወ) እጅግ አዛኝ ነው (ገጽ 267)።

መጽሐፉ ለምን ጊዜያዊ ስጦታ ተባለ?

በመሠረቱ ርዕሱ ለምን እንደተባለ ከአጠቃላዩ የመጽሐፉ መልዕክት መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ፍቅር እስከ መቃብር በሚል ርዕስ የተጻፈው መጽሐፍ ከመጽሐፉ መልዕክት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም፣ ኦሮማይ፣ ወንጀልና ቅጣት፣ እንደዚሁ፡፡ አንዳንዱ ርዕስ የዋናውን ገጸ ባህርይ ርዕስ ሊይዝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኦቴሎ ወይም ሮሚዮና ዡሌት፣ አና ካሪኒና መጠቀስ ይቻላል፡፡

ጊዜያዊ ስጦታ ግን፡-

እኛ ራሱ የራሳችን አይደለንም። አላህ (ሱ.ወ) ዐምርን ለሆኑ ጊዜያት እንደስጦታ ሰጠኝ፣ አላህ ይህንን ስጦታ በመውሰዱም ዐምር እስካሁን ከእኔ ጋር ቢኖር የማልማረውን ብዙ ነገር አስተምሮኛል፣ ስለሕመም፣ ጀግንነት፣ መስዋዕትነት አስተምሮኛል። ወደ ዘልዓለማዊና እውነተኛ ወደሆነው ቤት እንድጓጓ አስተምሮኛል። ምንም ያህል ወደዚህ ዓለም ተረከዜን ቆፍሬ ባስገባ፣ እርሱ በፈለገው ጊዜና ቦታ ወደእርሱ የምመለስ መሆኔን አስተምሮኛል። አንዳንድ ጊዜ የሚሰጡን ስጦታዎች የሚያስፈልጉንን ያህል፣ የተሰጡንም ስጦታዎች እንዲወስዱብን እንሻለን፡፡ ምናልባትም እንደዚያ ሲሆን ለስጦታው ሰጪ ያለንን ፍላጎትና ፍቅርን እንረዳለን።

የመጽሐፉ ዋና መልዕክትም ይኸው ነው፡፡

አመሰግናለሁ!

  ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles