Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ቀን:

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በርካቶችም በድካም የዛለ ሰውነታቸውን ለማደስ ይጠቀሙበታል፡፡ ለዓይን ማራኪ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ይዝናኑበታል፣ አረፍ ብለው ያወጉበታል፡፡

መስቀል አደባባይ በየዓመቱ የመስቀል በዓል የሚከበርበት፣ የመንግሥት ትልልቅ ዝግጅቶች የሚከናወንበት፣ በተለይ በሰንበት በርካቶች የሰውነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበትና የተለያዩ የሙዚቃ ትዕይንቶች በየወቅቱ የሚቀርቡበት የከተማዋ ስመ ጥር አደባባይ ነው፡፡

ዘመናዊነትን በተላበሰ መልኩ ተሠርቶ ከተመረቀ ከሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላም፣ የተለያዩ አገልግሎቶች እየሰጠ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሥፍራው ለመቀመጥም ሆነ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ጎራ ያሉ ሰዎች ክፍያ መጠየቅ ጀምረዋል፡፡

- Advertisement -

ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ሕዝባዊ አደባባይ (ኦፕን ስፔስ) ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ይህ ቦታ፣ እንደ አዲስ ወደ ውስጥ ለመግባት ክፍያ መጠየቁ አግባብነት የለውም የሚሉ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ አግባብነት የለውም ከሚሉት መካከል ለዓመታት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ቦታው ላይ አረፍ ብለው ያሳልፋ እንደነበር የነገሩን አቶ እሸቱ ተስፋዬ ይገኙበታል፡፡

ከሥራ ሲወጡ ሦስት ልጅ ካፈራችላቸው ባለቤታቸው ጋር ወደ መስቀል አደባባይ ሄደው መንፈሳቸውን እንደሚያድሱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ቦታው በተለይ ከቀትር በኋላ ነፋሻማ በመሆኑ ወጣቶች፣ ሕፃናት እንዲሁም አረጋውያን ሳይቀሩ ወደ ሥፍራው እንደሚመጡም አስረድተዋል፡፡

በተለይም እሑድ፣ እሑድ በአደባባዩ በርካታ ሰዎች እንደየፊናቸው ቁጭ ብለው፣ አሊያም ደግሞ እንቅስቃሴ እያደረጉ ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ እሳቸውም ይህ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ፡፡

ጥንዶች ጊዜያቸውን ያሳልፉበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ እሸቱ፣ መንግሥት ዘመናዊነት በተላበሰ መልኩ በከፍተኛ ወጪ ቦታውን አድሶ ለአገልግሎት ክፍት ሲያደርግ ተደስተው የነበረ ቢሆንም፣ ቆይቶ ለመግቢያ 20 ብር መጠየቁ አግባብነት የለውም ይላሉ፡፡

መንግሥት ለፕሮጀክቱ በርካታ ወጪዎችን ፈሰስ ቢያደርግም፣ ከመጀመርያው ጀምሮ አደባባዩ ለማኅበረሰቡ ክፍት ሆኖ እንዲያገለግል ነው የተሠራው የሚሉት እኚህ አባት፣ ቦታው ላይ ለበርካታ ዓመታት ማኅበረሰቡ ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይከፍል ይጠቀምበትና መንፈሱን ያድስበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

እንደነዚህ ዓይነት ቦታዎች ለማኅበረሰቡ ያለ ምንም ክፍያ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው የሚናገሩት እኚህ አባት፣ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ በርካታ መዝናኛ ቦታዎች ከፍተኛ ክፍያ ስለሚጠይቁ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ መዝናኛ ቦታ ለመውሰድ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

መስቀል አደባባይ በርካታ ወገኖች እንደልባቸው የሚዝናኑበት ቦታ መሆን ሲገባው፣ ለአንድ ሰው መግቢያ 20 ብር ክፍያ መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን፣ ቦታው የተለያዩ ኩነቶች ሲዘጋጁበት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገባ አክለው ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ እንኳን ሦስት ልጃቸውን ይዘው የበፊት ትዝታቸውን ከባለቤታቸው ጋር ለማጣጣም ወደ ቦታው ማቅናታቸውን ያስታወሱት አቶ እሸቱ፣ በቦታው የተለያዩ አገልግሎቶችን ተጠቅመው ከፍተኛ ወጪ ማውጣታቸውን ያስረዳሉ፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነት በናረበት ለእንደነዚህ ዓይነት ቦታዎች ክፍያ መጠየቁ አግባብ አለመሆኑንና ይህ ታሳቢ ቢደረግ መልካም እንደሆነ ያምናሉ፡፡

አደባባዩ ሃይማኖታዊ፣ ሕዝባዊና ሌሎች ማኅበራዊ ዝግጅቶች በተለይ በከተማዋ ብዙኃኑን ታሳቢ ያደረጉ ኩነቶችን በተሻለና ምቹ በሆነ መንገድ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል መልኩ ቢገነባም፣ የማኅረበሰቡን ፍላጎት በተባለው ልክ ማስኬድ ካልተቻለ ዋጋ የለውም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰነዘሩት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አባት እንደገለጹት፣ መስቀል አደባባይ ከምሥረታው ጀምሮ ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይደረግበት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

መስቀል አደባባይ ሰዎች የሚተዋወቁበት፣ ትዳር የመሠረቱበት፣ እርስ በእርስ በመነጋገር ሐሳባቸውን በነፃነት የገለጹበት እንዲሁም የተለያዩ ኩነቶች የተከበሩበት እንደመሆኑ መጠን፣ ቦታውን በአግባቡ በመያዝ ለማኅበረሰቡ በነፃ አገልግሎቶች መስጠት ሲኖርበት ለመግቢያ ክፍያ መጠየቁ አግባብነት የለውም ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ቦታው ላይ በርካታ ሰዎች እንደመዝናኛነት ቢጠቀሙበትም፣ አንዳንድ ግለሰቦች የሱስ አማጭ ነገሮች መጠቀሚያና መናኸሪያ አድርገውት እንደነበር፣ ነገር ግን መንግሥት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ገንብቶ ለማኅበረሰቡ ክፍት ካደረገ በኋላ፣ እንዲህ ዓይነት አጓጉል ድርጊቶች መቅረታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ሆነ ጥሩ ገቢ ያላቸው ሰዎች ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ቦታው በመሄድ ጥሩ ጊዜ ያሳልፉ እንደነበር፣ ይሁን እንጂ በቅርቡ ክፍያ መጠየቅ ከጀመረ በኋላ ተጠቃሚዎች መቀነሳቸውን መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ የሚገኙ ፓርኮችና የመዝናኛ ቦታዎች ለመግቢያ የሚያስከፍሉት ክፍያ ከፍተኛ እንደሆነ፣ መንግሥትም በእንዲህ ዓይነት አሠራር እጁ ስላለበት ለዚህ ገደብ እንዳላበጀ፣ ዜጎችም በተለይ ቤተሰባቸውን ይዘው በተለያዩ ቦታዎች ገብተው ለመዝናናት ቢፈልጉም፣ ክፍያው ኪሳቸውን የሚጎዳ በመሆኑ ሳይገቡ ይቀራሉ ብለዋል፡፡

በአገሪቱ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ከፍሎ ለመዝናናት አይደለም የዕለት ጉርስን እንኳን ከባድ እንዳደረገው፣ መንግሥትም ይህንን ታሳቢ አድርጎ ማንኛውም ሰው የመስቀል አደባባይ አገልግሎትን በነፃ እንዲያገኝ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በመስቀል አደባባይ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ብዙ ትዝታዎችን እንዳሳለፉ የሚናገሩት እኒህ አባት፣ ከዚህ በኋላም መንግሥት እንደነዚህ ዓይነት ቦታዎችን በማስፋት ለብዙዎች የመዝናኛ ቦታ ችግር መፍትሔ ማፈላለግ አለበት ብለዋል፡፡

የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ታደሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የክፍያ ሥርዓቱ የተጀመረው የተቋሙ ቦርድ አፅድቆ ለከተማ አስተዳደሩ ደብዳቤ በመላክ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ነው፡፡

በመሆኑም ከታኅሣሥ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም ሰው 20 ብር መግቢያ በመክፈል ወደ ቦታው ገብቶ እየተጠቀመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ቦታው በዘመናዊነት ተገንብቶ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን፣ ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ገብተው የተለያዩ ቁሳቁሶች እየሰረቁ በማስቸገራቸው ክፍያ እንዲኖረው ተደርጓል ሲሉ አቶ ጥላሁን አስረድተዋል፡፡

የክፍያ ሥርዓቱን አስመልክቶ እስካሁን ድረስ ተገልጋይ ከሆኑ አካላት ምንም ዓይነት ቅሬታ አለመቅረቡን፣ በሶሻል ሚዲያ ግን በጽሑፍ ቅሬታ ያሰሙ አካላትን ማየታቸውን አብራርተዋል፡፡

አብዛኛው ሰው ሲገባ ደስተኛ ሆኖና የተመቸውን ነገር ተጠቅሞ እንደሚወጣ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ኪስን በማይጎዳ መልኩ ለአንድ ሰው መግቢያ 20 ብር መጠየቁ ችግሩ አይታየኝም ብለዋል፡፡

ከሰኞ እስከ እሑድ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር የተለያዩ መሆኑን፣ እስካሁን ግን በቀን እስከ 15 ሺሕ ብር ገቢ እንደሚያገኙ፣ ይሁን እንጂ የሚገኘው ገቢና ተቋሙ ለተለያዩ ነገሮች የሚያወጣው ወጪ እንደማይመጣጠን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በቀን የሚገኘው ገቢ ለውኃ ክፍያ እንኳን እንደማይበቃና ማኅበረሰቡም ቅሬታ ሲያነሳ ነገሮችን አገናዝቦ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትን ሲገነባ ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱን የተናገሩት አቶ ጥላሁን፣ ወጪውን ግምት ውስጥ በማስገባት የቦታ ይዞታውን መንከባከብ የግድ ይላል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ከሰኞ እስከ እሑድ ድረስ የተለያዩ ዝግጅቶች በማዘጋጀት ማኅበረሰቡ የሚጠቀምበትን ለማመቻቸት ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ 87 ቋሚ ሠራተኞችንና ከ300 በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞችን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ተቋሙ፣ እንዲህ ዓይነት ቅሬታ ሊቀርብበት አይገባም ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ይዞታው ጫት የሚቃምበትና የተለያዩ ድርጊቶች የሚፈጸሙበት እንደነበር፣ መንግሥት ቦታውን በተሻለ ሁኔታ ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት በማድረጉም ትክክለኛ የከተማዋ መዲና ሊሆን ችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡  

በሌላ በኩል በአደባባዩ መንግሥታዊ የሆኑ ዝግጅቶች ሲኖሩ ተቋሙ ለቦታው ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማያስከፍል፣ እስካሁንም ከ7 ዓመት ዕድሜ ክልል በታች የሆኑ ሕፃናት ልጆች እየከፈሉ አለመሆኑን አቶ ጥላሁን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ