በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች በኢንቨስተሮች ንብረት ላይ አደጋ ቢከሰት፣ ከመንግሥት ድጋፍ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ተደንግጎ የነበረውን መመርያ የገንዘብ ሚኒስቴር ሻረው፡፡
በተለያዩ ዘርፎች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው እየሠሩ ያሉ ኢንቨስተሮች በንብረቶቻቸው ላይ አደጋ ቢከሰት፣ በርካታ ድጋፎችን መንግሥት እንደሚያደርግ፣ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. መመርያውን ገንዘብ ሚኒስቴር አውጥቶ ነበር፡፡
በሚኒስቴሩ ተዘጋጅቶ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. የወጣው ባለሁለት ገጽ አዲስ መመርያ፣ የቀድሞው መመርያ የተሻረ መሆኑን አስታውቆ፣ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ሽረቱ እንደሚፀና ይደነግጋል፡፡
በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና ወይም በአገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በሰው ሠራሽ ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ቢደርስባቸው፣ መንግሥት በሚሰጣቸው ድጋፎች ሥራቸውን መቀጠል እንዲችሉ ለማስቻል ነበር የተሻረው መመርያ ከሁለት ዓመት በፊት ወጥቶ የነበረው፡፡
የድጋፉ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉትን በሦስት በመክፈልም የወደመባቸውን ንብረት በመተካት ሥራቸውን መቀጠል የሚፈልጉ፣ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ በተፈጠረ ግጭት ንብረታቸው ላይ ጉዳት ደርሶ ድጋፍ ያልተደረገላቸው፣ እንዲሁም ለጉዳቱ ከኢንሹራንስ ተቋማት ካሳ ያላገኙ የሚሉ ናቸው፡፡
የንግድ ትርፍ ግብር ዕፎይታ ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ አደጋው ለሚደርስባቸው አዲስ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ማበረታቻ የግብር ዕፎይታ ጊዜ ዘመንን ማራዘም፣ እንዲሁም በአደጋዎች ንብረታቸው የወደመባቸው ባለሀብቶች ንብረቶቻቸውን ለመተካት ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸውን ዕቃዎች ከቀረጥ ታክስ ነፃ ማድረግ የተሻረው መመርያ ከሚሰጣቸው መብቶች የተወሰኑት ነበሩ፡፡
ውድመት የደረሰባቸው ንብረቶች 25 በመቶና ከዚያ በላይ ከሆነና ሪፖርቱም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል በዚህ መሠረት ከቀረበ ነው ባለሀብቶቹ ድጋፎቹን ማግኘት የሚችሉት፡፡ ንብረታቸውን ለመተካት የባንክ ብድር በሚያገኙበት ሁኔታና ቀድመው የወሰዱትንም ብድር መክፈያ ጊዜያት ማሸጋሸግን በሚመለከት፣ የብሔራዊ ባንክ ቦርድ እንደሚያመቻች መመርያው ያዝ ነበር፡፡
በንብረታቸው ላይ ጉዳት የሚደርስባቸው ባለሀብቶች ለድጋፉ የሚያቀርቡት ጥያቄ በኮሚቴ እየታየ ይመለስ የነበረ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የቀድሞው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ጨምሮ ከአምስት ያላነሱ የመንግሥት ተቋማት የተውጣጡ የኮሚቴ አባሎች ናቸው ጥያቄውን ይመረምሩት የነበረው፡፡
የቀድሞው መመርያ መሻርን አስፈላጊነትና ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ሪፖርተር በተደጋጋሚ የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ለማነጋገር ሙከራ ቢደረግም ሊሳካ አልቻለም፡፡