ተቋማት በቅንጅት ለመሥራት በተስማሙበት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አለመሆናቸውን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ይህንን ያለው ከዘርፉ ተቋማት ጋር በቅንጅት ከመሥራት አንፃር የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈጸጸምን በተመለከተ፣ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋሽንግተን ሆቴል በነበረው የውይይት መድረክ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ ተቋማት በቅንጅት ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ቢፈራረሙም፣ ሁሉም ተቋማት በስምምነቱ መሠረት እየሠሩ ባለመሆናቸው ዜጎችን ከማገልገል አንፃር ክፍተት እያጋጠመ መሆኑን፣ የቢሮው የክርክር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደጀኔ ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ከፍርድ ቤቶችና ከሌሎች ሥልጣን ካላቸው አካላት ዘንድ ከሕዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ላይ የመነጋገር፣ በከተማ አስተዳደሩ የሚወጡ ሕጎችን የማርቀቅ፣ የማፅደቅና መሰል ተግባራትን የሚያከናውኑ ተቋማት የሕዝብን እርካታ ያረጋገጡ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ስምምነት ላይ ቢደረስም በታለመው ልክ እየተሠራ አይደለም ተብሏል፡፡
ለአብነትም ሕጎች ካቢኔ ቀርበው ከፀደቁ በኋላ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቃለ ጉባዔ በወቅቱ አለመስጠቱ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ የሚላኩ የታተሙ ሕጎችን በፍጥነት አለማድረሱ፣ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ተቋም መሬትን በአግባቡ መዝግቦ አለመያዝ፣ ውሎችን በሥርዓት አለመመርመር፣ የቢሮውን ሕግጋቶች ጠብቆ አለመሥራት፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ ሒደቶችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ፍትሕ ቢሮ እንዳይገመግሙ መከላከል፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የቤት ቁጥር ምዝገባ መደበላለቅ፣ በሕገወጥ መንገድ ቤቶች ሲያዙ ዕርምጃ አለመውሰድ፣ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ሠራተኞች በመንገድ ላይ ንግድ ምክንያት ሰዎችን በመደብደብ የሰብዓዊ መብት ጥቃት መፈጸማቸው፣ የትምህርት ቢሮ ለሚፈለጉ ጉዳዮች ማስረጃ አለመላኩ፣ የጤና ቢሮ የሥራ ውሎችን እየገመገመ ወደ ፍትሕ ቢሮ አለመላክና ሌሎች መሰል ክፍቶች በ2015 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ሥራ አፈጻጸም መስተዋላቸውን ቢሮው አስታውቋል፡፡
የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ከማስጠበቅ አኳያ የሰብዓዊ ድርጊት መርሐ ግብር ተቀርፆ የሥራቸው አካል አድርገው እንዲተገበሩ፣ ለተቋማት ማሳሰቢያ መሰጠቱንና ተገቢ ክትትል እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ የዜጎችን መብት ከማስጠበቅ አኳያ ከተቋማት ጋር ባላቸው የቅንጅት ሥራ ፍትሐዊ አሠራር እንዲኖር የሚከታተል ከሆነ፣ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ቤታቸው ፈርሶ፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጸመብን›› ለሚሉ ሰዎች ቢሮው ምን ዓይነት ክትትል እንዳደረገ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ ወይስ የለም ብሎ መጠየቅ እንጂ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል ማለት ትክክል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ከፌዴራል የፍትሕ ተቋማት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ፣ ከዓቃቤ ሕግና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተግባብተን እየሠራን ነው፡፡ ክፍተቶች ግን የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ሕግን የጣሰና የጎላ የቤቶች ማፈረስ አልታየም ሲሉ አክለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በሸገር ከተማ ቤቶች የሚፈርሱባቸው በርካታ ዜጎች በመፈናቀል ለብርድና ለፀሐይ መጋለጣቸው ፍትሐዊ አሠራር ነው ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ‹‹ሕገወጥ ቤት ሕገወጥ ነው ይፈርሳል፡፡ ሕገወጥነትን አናበረታታም፣ ሕግ መከበር አለበት፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ሰብዓዊ መብት ማስከበር ላይ ቁልፍ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ የ90 ቀናት ፕሮጀክት በመንደፍ የደሃውን ቤት አፍርሶ መልሶ በመገንባት ያለበትን ሒደት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሆነ ማሰብ ትክክል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በ2015 በጀት ዓመት 6,317 የፍትሐ ብሔር መዛግብት ላይ ክርክር በማድረግ፣ በ1,734 መዛግብት ላይ በተሰጠው ውሳኔ 93 በመቶ ለመንግሥት በማስወሰን፣ 1,384,368,588 ብር ማዳን መቻሉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በመንግሥት ውሳኔ ካገኙ መዛግብቶች 16 ቢሊዮን ብር ታጣ ተብሎ፣ የታጣውን ገንዘብ ደግሞ በይግባኝና በሰበር አቤቱታዎች ቀርበው ለማሻር ጥረት እየተደረገ በመሆኑ፣ የታጣው ገንዘብ ቁጥሩ ሊቀንስ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
ለተቋማትና ለማኅበረሰቡ የሕግ ግንዛቤ ሥልጠና ከመስጠት አኳያ፣ ቢሮው ለተለያዩ አካላት ሥልጠና ቢሰጥም አሁንም ክፍተት አለበት ተብሏል፡፡
እንዲሁም በ64 የፍትሐ ብሔር መዛግብት ላይ የአፈጻጸም ክስ በማስከፈት ማስፈጸም እንደተቻለ፣ በከተማዋ የሚገኙ ትልልቅ ፕሮጀክቶንና ግባታዎችን በዕግድ እንዲያሳልጥ የሚያደርጉ ጉዳዮችን 94.6 በመቶ መከላከል እንደተቻለም ቢሮው አስታውቋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የክፍለ ከተማ ፍትሕ ቢሮ ተወካዮች ተቋማት በቅንጅት እንዲሠሩ ከዚህ በላይ ድጋፍና ክትትል መደረግ እንዳለበት፣ ሪፖርቱን ሲያቀርብ አፈጻጸሙን ብቻ ሳይሆን ዕቅዱንም አብሮ ማስቀመጥና መግለጽ እንዳለበት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
ቢሮው የከተማ አስተዳደርና የነዋሪዎች መብትና ጥቅም ፍርድ ቤቶችና ሌሎች የዳኝነት ሚና የተሰጣቸው አካላት እንዲያስከብሩ፣ በከተማ አስተዳደሩ የሚወጡ በርካታ ሕጎችን አጀንዳዎችንና መመርያዎችን የማፅደቅና የሕግ ቅርፅ የማስያዝ ኃላፊነት በከተማ አስተዳደሩ የሚሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎለት እየሠራ ቢገኝም፣ የተነሱትን ክፍተቶች ለመሙላት የሁሉም ተቋማት ትጋት ያሻል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ከዘርፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት፣ ተቋማትን በሕግ ጉዳዮች የማማከር፣ ተወካይ ሆኖ የመሥራት ለአመራሩ ለነዋሪዎችና ለአስፈጻሚው አካል ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ለመስጠት፣ ተቋማት የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ሕገ መንግሥቱን ተከትለው የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስለማክበራቸው እንዲያረጋግጥ በአዋጅ ቁጥር 74/2014 መሠረት መቋቋሙ ተነግሯል፡፡