Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ ደላሎችን መቆጣጠር ፈተና እንደሆነበት የአማራ ክልል አስታወቀ

በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ ደላሎችን መቆጣጠር ፈተና እንደሆነበት የአማራ ክልል አስታወቀ

ቀን:

በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተሰማሩ ዋና ዋና ደላሎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ለሚፈጽሙት ወንጀል ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ፈተና እንደሆነበት፣ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር የሚልኩና ድንበር የሚያሻግሩ በሰዎች ንግድ ላይ የተሰማሩ ደላሎች በክልሉ ቢኖሩም፣ ዋና ዋና ደላሎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ባለመቻሉ፣ ወንጀሉ እየተባባሰ መሆኑን የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገረመው ገብረ ፃዲቅ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚፈጽሙ በርካታ ደላሎች መኖራቸውንና በተለይ በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋና በጎንደር (በመተማ) ሰዎች በሕገወጥ ደላሎች አማካይነት እንደሚዘዋወሩ፣ በዚህም ሳቢያ ከባድ ችግሮች እንደሚደርሱባቸው፣ አብዛኛውን ጊዜ ተዘዋዋሪዎችንና የጉዳቱን ሰለባዎች እንጂ ደላሎችን ማግኘት ከባድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ዋና ዋና ደላሎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚቻልበት አጋጣሚ ቢኖርም፣ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንቅፋት መሆናቸውን አቶ ገረመው አክለው ገልጸዋል፡፡

በሕገወጥ ደላሎች አማካይነት የተለያዩ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳቶች ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ማቆያ ባለመኖሩና ወደ አካባቢያቸው ስለሚበታተኑ፣ በተፈጸመባቸው ወንጀል ፍትሕ ለማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ሲሞከር፣ ለምስክርነት መገኘት አለመቻላቸው አንዱና ዋነኛው ተግዳሮት መሆኑን ኃላፊው ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ምስክር ባለመኖሩ ምክንያት በርካታ የወንጀል ጉዳዮች ዕልባት ሳያገኙና ውጤታማ ሳይሆኑ ይቀራሉ፤›› ያሉት አቶ ገረመው፣ ችግሩን ለመፍታት ከፌዴራል የፀጥታና ከሌሎች የክልል ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ በወንጀል ረገድ ከፍተኛ እየተባሉ በሕግ ቅጣት የማይጣልባቸው ደላላዎችና ወንጀል ፈጻሚዎች በርካታ መሆናቸውን እንደሚያምኑ ገልጸው፣ ‹‹እንዲያውም ሥራው አልተሠራም ለማለት ይቻላል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት በሕወሓት ታጣቂዎች ተገደው ተወስደዋል የተባሉ ወጣቶች፣ ከአላማጣ ከተማና ከዋግኸምራ ዞን፣ በማንነታቸው ምክንያት በኮረም ማረሚያ ቤት ለፍርድ መታሰራቸውን ቤተሰቦቻቸው የሚገልጹላቸው ባለሥልጣናትና ወጣቶችን በተመለከተ ቢሮው ምን ዓይነት ጥረት እንዳደረገ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ጉዳዩን እንደማያውቁና ለወደፊት አጣርተው እንደሚያሳውቁ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚያስችል የልምድ ልውውጥ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ፍትሕ ቢሮ ጋር፣ ማክሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል አካሂዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ከዚህ በፊት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሞ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች ጉዳዮችን በየክፍለ ከተማው ከሚገኙ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ በመቆየቱ ልምዱን ለአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በውይይቱ ወቅት ያጋራ ሲሆን፣ ክልሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የተሻለ ግንዛቤ እንዳገኘ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሠራቱ ለውጥ ማምጣት ቢቻልም፣ አሁንም ቢሆን በአዲስ አበባ ከተማ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እየተንሰራፋ መምጣቱን፣ ለዚህም ከዚህ በላይ በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ የክርክር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደጀኔ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ‹‹የፍሪደም ፈንድ›› ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መለሰ፣ ‹‹ፍሪደም ፈንድ›› በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለፉት ስምንት ዓመታት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ ክትትል ሲያደርግ እንደቆየ ገልጸው፣ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት በዓለም ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ አሥር ሚሊዮን ሰዎች በባርነት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን፣ በተለይ በሰዎች የመነገድ ወንጀል እየተስፋፋ መሆኑን፣ ለመስፋፋቱም በኢትዮጵያ ሰዎች በየቀኑ በሕገወጥ መንገድ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ከአገር መውጣታቸውን እንዳላቆሙ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲስፋፋ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከስምንት ዓመታት ክትትላቸው በመነሳት እንዲያስረዱ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዳንኤል፣ ሕጉ ጠንካራ ቢሆንም አፈጻጸም ላይ ክፍተት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳይን በሰፊው ተንትነው መረዳት እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...