Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኮስሞ ትሬዲንግ አክሲዮኖች የተሸጡት በማስፈራራትና በማስገደድ መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ

የኮስሞ ትሬዲንግ አክሲዮኖች የተሸጡት በማስፈራራትና በማስገደድ መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ

ቀን:

  • የአክሲዮኖቹ ሽያጭ ውል እንዲፈርስ ውሳኔ ተሰጥቷል

ከሦስት ዓመታት በፊት ታኅሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ጄጄ ፕሮፐርቲ ማኔጀመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበርና ወ/ሪት አዜብ ምሕረተ አብ የተባሉ ከሳሾች፣ ኮስሞ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበርን 19,900 የአክሲዮን ድርሻን በ19.9 ሚሊዮን ብር እንደገዙት በመግለጽና ከሻጭ ላይ ለመረከብ ክስ የመሠረቱ ቢሆንም፣ ግዥው የተፈጸመው በማስፈራራትና በማስገደድ መሆኑን በማረጋጡ የሽያጭ ውሳኔ እንዲፈርስ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ፡፡

ጄጄ ፕሮፐርቲና ወ/ሪት አዜብ በኮስሞ ትሬዲንግ ከፍተኛ ባለድርሻና የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በነበሩት አቶ ኃይለኢየሱስ መንግሥቱና ሁለት ልጆቻቸው (ባለድርሻ ናቸው) ላይ የመሠረቱትን የፍትሐ ብሔር ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አምስተኛ ችሎት፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ እንዳብራራው፣ የአቶ ኃይለኢየሱስ እያንዳንዳቸው 1,000 ብር ዋጋ ያላቸው 19,900 አክሲዮኖችን በ19,900,000 ብር ገዝተው ቅድመ ክፍያ 12,400,000 ብር ከፍለዋቸዋል፡፡

ለቀሪው ክፍያ 7,500,000 ብር ከኅብረት ባንክ የሚመነዘር ቼክ አዘጋጅተው የድርጅቱ ስመ ሀብት እስከሚዛወር ድረስ አቶ ብርሃኑ ጌታነህ በተባሉ ግለሰብ እጅ እንዲቀመጥ መደረጉን ፍርዱ ያስረዳል፡፡ በአቶ ኃይለ ኢየሱስ ልጆች የተመዘገበና እያንዳንዱ 1,000 ብር ዋጋ ያላቸው 50 አክሲዮኖች 50,000 ብር ለወ/ሪት አዜብ መዘዋወሩንም ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ድርጅቱ ከአዋሽ ባንክና ከኅብረት ባንክ፣ እንዲሁም ከሌሎች ሦስተኛ ወገኖች የሚከፈልን ዕዳ ተከሳሾቹ ሊከፍሉ ግዴታ መግባታቸውንም በፍርዱ ተገልጿል፡፡ ከሳሾች የፈጸሟቸው የአክሲዮን ግዥዎች ሕጋዊ መሆናቸውን በማብራራት፣ አክሲዮናቹ እንዲተላለፍላቸው ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ክስ መመሥረታቸውን ፍርዱ ያብራራል፡፡

ተከሳሾቹ አቶ ኃይለ ኢየሱስ መንግሥቱና ሁለት ልጆቻቸው የክስ መጥሪያ ደርሷቸው የካቲት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ምላሽ ሰጠተዋል፡፡ ከሳሾቹ ጄጄ ፕሮፐርቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ወ/ሪት አዜብ ምሕረተ አብ በሕግ አግባብ የገዙት የአክሲዮን ሽያጭም ሆነ ውል እንደሌለ ገልጸው፣ የኮስሞ ትሬዲንግ ንብረት የሆነውን ሕንፃ መግዛታቸውን በመግለጽ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 191421 ክስ መሥርተው የነበረና ገንዘቡ እንዲመለስላቸው ጠይቀው የነበሩ ቢሆንም፣ ግልጽ የሆነ ውል ስላልነበራቸው ክሱ ሊቀጥል አለመቻሉን ፍርዱ ያብራራል፡፡ ጉዳዩን የመረመረው፣ ፍርዱን የሰጠውም ፍርድ ቤት ጉዳዩን ማለፉን ጠቁሟል፡፡

የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭን በሚመለከት እነ አቶ ኃይለኢየሱስ በሰጡት የክስ መቃወሚያ ክርክር እንደገለጹት፣ አክሲዮን የሚተላለፈው በአክሲዮኖች መዝገብ ላይ ሠፍሮ፣ በንግድ መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ቢሆንም፣ እንደ ተራ ነገር አክሲዮን ‹‹ገዝተናል›› በሚል የቀረበው ክስ በንግድ ሕግ ቁጥር 522 እና 523 (3) ድንጋጌ መሠረት ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡

ከሳሾች ፣ አቶ ኃይለ ኢየሱስ ሐምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ፈርመውታል ያሉት ሰነድን በሚመለከት ፣ አቶ ኃይለ ኢየሱስ በሰጡት ምላሽ  ፈቃደኛ ሳይሆኑ ታስረው፣ ተደብድበውና ፍፁም ሰብዓዊ መብታቸው፣ ከወ/ሪት አዜብ (ሁለተኛ ከሳሽ) ጋር ግንኙነት ካላቸውና በወቅቱ በነበሩ የፍትሕና የደኅንነት አካላት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ጭምር እየተነገራቸው በማስፈራራትና በማስገደድ እንዳስፈረሟቸው መግለጻቸውን ፍርዱ ያብራራል፡፡ አቶ ኃይለ ኢየሱስ ከአገር እንዲወጡ በማድረግና ኮስሞ ትሬዲንግን እንደሸጡላቸው በማስመሰል ውሳኔ ማስጠታቸውንም በምላሻቸው ገልጸዋል፡፡

በከሳሾቻቸውና በእሳቸው መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖር ሕገወጥ የአራጣ ብድር እንዳለ በማስመሰል 50,000,000 ብር እንደተበደሩ ማድረግን ጨምሮ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት እንደተፈጸመባቸው በማብራራት ምላሽ መስጠታቸውን ፍርዱ ያብራራል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሽ ዘርዘር ያለ ምላሽ መስጠታቸውን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ባለ 20 ገጽ የፍርድ ትንታኔ አስፍሯል፡፡ ከውል ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ፈቃድ መስጠት መሆኑን የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ አቶ ኃይለ ኢየሱስ ውሉን የፈረሙት ተገደው መሆኑን፣ በቤተሰባቸውና በራሳቸው ላይ ይደርስ የነበረው ዛቻና ማስፈራራት ከባድ ስለነበር፣ ፍርድ ቤቱ የአክሲዮን ሽያጩ ውል የተደረገው በኃይል ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዞ ግራ ቀኙ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ ማድረጉንም በፍርዱ ገልጿል፡፡

ምስክሮቹን ከሰማ በኋላ ፍርድ ቤቱ አግባብነት ካላቸው የፍትሐ ብሔር ሕጎችና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች ውሳኔዎች ጋር በማገናዘብ መዝገቡን መመርመሩንም ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም አቶ ኃይለ ኢየሱስ ውሉን የፈጸሙት በግዳጅና በጫና ውስጥ ሆነው እንደሆነ ምስክሮቻቸው ማስረዳት መቻላቸውን ፍርድ ቤት መገንዘቡን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም በአቶ ኃይለ ኢየሱስ ባለቤትነት ይታወቅ የነበረው ከኮስሞ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የአክሲዮን ባለቤነት ድርሻን በሚመለከት የተደረገው ስምምነት በሕይወታቸው ወይም በንብረት ላይ የማይቀር አደጋ፣ እንዲሁም በልጆቻቸውና በራሳቸው ሕይወት ላይ አደጋ ይደርሳል በሚል ፈርተው በማስገደድና በማስፈራራት መሆኑ በመረጋገጡ፣ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 218፣ 306 እና በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1678 (ሀ)፣ 1706 እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰ/መ.ቁ 46490፣ 54827 እና 103151 መሠረት ውሉ እንዲፈርሰ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...