Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አርሶ አደሮች የቲማቲም ማሳቸውን ወደ በጋ ስንዴ እንዲቀይሩ መገደዳቸውን ተናገሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ‹‹የአመለካከት ችግር ተፈጥሮ ካልሆነ በስተቀር ስንዴ በሌሎች ምርቶች ላይ ተፅዕኖ አላሳደረም››

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ አርሶ አደሮች፣ የቲማቲምና የአትክልት ማሳቸውን ወደ በጋ መስኖ ስንዴ እንዲቀይሩ መገደዳቸውን ተናገሩ፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ አርሶ አደር ለሪፖርተር እንደተናገሩት በወረዳው ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ፍራፍሬ ማምረት ተከልክሏል፡፡

በዚህም ሳቢያ የአትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት ችግር በመኖሩ የዋጋ መናር መከሰቱን ገልጸው፣ በቅርቡ የቲማቲም ዋጋ ጣሪያ የነካው ያልተጠበቀ ዝናብ እንዳለ ሆኖ የበጋ ስንዴ መዝራት ግዴታ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

በዱግዳ ወረዳ መቂ ዙሪያ አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ተከልክሎ እንደነበር የገለጹት አርሶ አደሩ፣ ተክለው የተገኙትም እንደተነቀለባቸውና የታሰሩም ጭምር መኖራቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በወረዳውና በአካባቢው ስንዴ መዝራት ግዴታ መሆኑን፣ ከተቆጣጣሪዎች ተደብቀው ቲማቲም የተከሉም ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት እንደወደመባቸው ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ወረዳ ከተቆጣጣሪዎች ተደብቆ ተዘርቶ የነበረው ማሳ ከ40 እስከ 60 ሔክታር የሚገመት እንደነበር፣ የቲማቲም ምርቱ በረዶ በቀላቀለ ዝናብና በጎርፍ ሳቢያ ከጥቅም ውጪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የወረዳው አርሶ አደሮች የበጋ መስኖ ስንዴ መዝራት ግዴታ በመሆኑ የቃሪያ፣ የቲማቲም፣ የሽንኩርትና የሌሎች አትክልቶች ዋጋ መወደዱ ከዚህ ጋር ያያይዙታል፡፡

እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጻ፣ በወረዳው ለስንዴና ለሌሎች ምርቶች እኩል ትኩረት ቢሰጣቸው የዋጋ መናሩ አይከሰትም ነበር፡፡

አሥራ ስምንት ሔክታር የበጋ መስኖ ስንዴ መዝራታቸውን የጠቆሙት ሌላኛው አርሶ አደር፣ ከፍላጎታቸው ውጪ ወደ ስንዴ ምርት መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው የቲማቲም ዋጋ መናር ምክንያት ብለው ያስረዱት፣ ከዚህ ቀደም 0.50 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረው የቲማቲም ችግኝ ወደ ስምንት ብር ከፍ በማለቱ ነው ይላሉ፡፡

የቃሪያ ችግኝም አንድ ብር ሲሸጥ የነበረው አሥር ብርና ከዚያ በላይ በመጨመሩ ለዋጋ መወደድ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

እንደ ችግር ያነሱት ከዓመት በፊት ከአንድ እስከ ሁለት ሺሕ ብር ሲሸጥ የነበረው ኬሚካል አሁን ግን 4,000 እና 5,000 ብር በመሆኑ፣ ገበያ ለሚወጡ ምርቶች መወደድ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንድ ሔክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ከዚህ ቀደም እስከ 200 ሺሕ ብር እንደሚያስፈልግ፣ አሁን ግን እስከ 600 ሺሕ ብር ለግብዓት ብቻ እንደሚያወጡ ተናግረዋል፡፡

የዱግዳ ወረዳ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ገመቹ ኮራጂ፣ በወረዳው በ2015 ዓ.ም. 25,771 ሔክታር መሬት በዘር መሸፈኑን፣ ከዚያ ውስጥ 25,721 ሔክታር የበጋ መስኖ ስንዴ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በወረዳው ቲማቲምና ሽንኩርት፣ ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከሚያመርቱ አርሶ አደሮች ጋር ውይይት ተደርጎ የበጋ ስንዴ መዘራቱን አስረድተዋል፡፡  

ስንዴው ከተሰበሰበ በኋላ ወዲያው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ወደ ማምረት እንደሚገቡ ገልጸው፣ ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥማቸው እየሠሩ መሆኑን አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡

ምናልባት ሊገጥም የሚችለው የምርት እጥረት መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን ግን የስንዴ ምርት ተሰብስቦ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት መዞሩን አክለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፋይሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በ2015 ዓ.ም. የበጋ መስኖ ስንዴ በአንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ለማልማት ታቅዶ ነበር፡፡

በዚህም 38 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት አቶ በሪሶ፣ 1.1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ እስካሁን 34 ሚሊዮን ኩንታል ያህል መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ምርት የሚሰበስብበት ጊዜ ገና መሆኑን፣ ምርቱ በአጠቃላይ ሲሰበሰብ ካለፈው ወቅት በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ሰብሎች የሚሸፈን 7.4 ሚሊዮን ሔክታር መሬት መኖሩን፣ ከዚህ ውስጥ 1.1 ሚሊዮን ሔክታሩን በበጋ መስኖ ስንዴ መሸፈኑንና በበልግ ወቅትም 1.12 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በተለያዩ አዝርዕት መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም የተለያዩ የአስተራረስ ዘዴዎችን በመጠቀምና ምርትን አፈራርቆ በመዝራት፣ 11 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በተለያዩ አዝዕርት ለመሸፈን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ የግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ የበጋ መስኖ ስንዴ አዋጭነቱ በጥናት ተረጋግጦ፣ ለአገር የውጭ ምንዛሪ ማግኘትን ታሳቢ ተደርጎና መሠረታዊ ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮችንና ባለሙያዎች አምነውበት የገቡበት መሆኑን፣ ወቅቱን ጠብቆ ምርቶችን በማፈራረቅ በመዝራት እንደሚቻል ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል፡፡

ገበያን ለማረጋጋትና ያለውን ፍጆታ ለማሟላት እየተሠራ መሆኑን፣ በዚህም ከ500,000 ሔክታር መሬት በላይ ሌሎች ምርቶች መመረታቸውን ገልጸዋል፡፡

የበጋ መስኖ ስንዴ በሌሎች ምርቶች ላይ ተፅዕኖ አላሳደረም የሚሉት ምክትል ኃላፊው፣ ትኩረት ተደርጎ ስንዴ ላይ በመሠራቱ የአመለካከት ችግር ተፈጥሮ ሊሆን እንደሚችሉ አክለዋል፡፡

ከስንዴ ምርት ጋር ተጓዳኝ የሆኑ ምርቶችን ማምረት ያስፈልጋል ያሉት አቶ በሪሶ፣ የሚነሱ ጥያቄዎች በጥናት እየተለዩ ይፈታሉ ብለዋል፡፡ ለ2016 ዓ.ም. የበጋ ስንዴ ለመዝራት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን፣ በጥናቱ መሠረት ችግሮች እየተለዩ መፍትሔ ይሰጠዋል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

በማስገደድ ስንዴ ለምን ትዘራላችሁ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኃላፊው፣ ‹‹በማስገደድ ሥራ ተሠርቶ ውጤታማ አይኮንም፤›› ብለዋል፡፡ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ለመናሩ የበጋ መስኖ ስንዴ ተፅዕኖ የለውም? ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፣ ተፅዕኖ አለው፡፡ የለውም ለማለት በጥናት ማስደገፍ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

በ2016 ምርት ዘመን በክልሉ የታቀደው 2.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈንና 50 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች