Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዳይመንድ ሊግ ድምቀቷ ጉዳፍ ፀጋይ በሞሮኮ ደምቃለች

የዳይመንድ ሊግ ድምቀቷ ጉዳፍ ፀጋይ በሞሮኮ ደምቃለች

ቀን:

የዓለም ሻምፒዮኖችን የሚያሰባስበው የዳይመንድ ሊግ የሁለተኛ ዙር ውድድር በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ራባት ከተማ እሑድ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በኳታር የተጀመረው የዳይመንድ ሊግ የዓለም ከዋክብቱ በተለያዩ ርቀቶችና የሜዳ ተግባራት ፉክክር አድርገዋል፡፡ በውድድሩ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖች ተሳትፈውበታል፡፡ በወንዶች 3,000 ሜትር ጌትነት ዋለ፣ በሴቶች 1,500 ሜትር ጉዳፍ ፀጋይ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ብርቄ ኃየሎምና ወርቅነሽ መሰለ ከተወዳደሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ይገኙበታል፡፡

በወንዶች 3,000 ሜትር ጌትነት ዋለ 8፡05፡15 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በርቀቱ ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ኃይለ ማርያም አማረ ቢካፈልም ሳያጠናቅቅ ቀርቷል፡፡ ውድድሩን ሞሮኳዊ የዓለምና የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ሱፋይን ኤልባካሊ የግሉን ምርጥ ጊዜ 7፡56፡68 በማስመዝገብ አሸንፋል፡፡

ሁለተኛ የወጣው ኢትዮጵያዊ ጌትነትም የራሱን ምርጥ ጊዜ 8፡05፡15 ሲያስመዘግብ፣ኬንያዊው አብርሃም ኪስዎታ በ8፡05፡51 ሦስተኛ ወጥቷል።

ሌላው በራባት ድምቀት የነበረው የሴቶች 1,500 ሜትር ውድድር ሲሆን፣ኢትዮጵያውያት አትሌቶች አራቱንም ደረጃዎች በበላይነት አሸንፈዋል። በዚህም መሠረት ጉዳፍ ፀጋይ በ3፡54፡03 አንደኛ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ በ3፡57፡65 ሁለተኛ፣ ብርቄ ኃየሎም በ3፡57፡65 ሦስተኛ፣ እንዲሁም ወርቅነሽ መሰለ በ4፡01፡81 አራተኛ በመሆን ውድድሩን ተቆጣጥረውታል፡፡ 

የዳይመንድ ሊግ ድምቀቷ ጉዳፍ በራባት ደምቃ ነበር ያመሸችው፡፡ የዓለም የ5,000 ሜትር ሻምፒዮናዋ ጉዳፍ በአስደናቂ ብቃት የመጀመርያውን ዙር 1፡01፡3 ስትሮጥ 800 ሜትሩን ለማጋመስ 2፡03፡6 ፈጅቶባታል፡፡

የመጀመርያዋን ከቤት ወጪ ውድድር ያደረገችው ጉዳፍ ያጠናቀቅችበት ጊዜ እንዳስደሰታት ገልጻለች፡፡ ‹‹ይህ የመጀመርዬ የቤት ውስጥ ውድድር ነው፡፡ በማሸነፌና በገባሁበት ሰዓት ደስተኛነኝ፡፡ አሁን ጥሩ አቋም ላይ እገኛለሁ፡፡ ከጉዳትም ነፃ ነኝ፤›› ስትል ከውድድሩ በኋላ አስተያየቷን ለሚዲያ ሰጥታለች፡፡ 

በመካከለኛ ርቀቱ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈች የምትገኘው ጉዳፍ፣ በምትካፈልባቸው የ800፣ 1,500፣ 3,000፣ 5,000፣ 10 ሺሕ ሜትር ርቀቶች እንዲሁም የአንድ ማይል ውድድሮች የራሷን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ቀጥላለች።

ከእነዚህም መካከል እ.ኤ.አ. 2021 በፈረንሣይ የቤት ውስጥ 800 ሜትር ውድድር 1፡57፡52 በመግባት፣ ብሔራዊ ክብረ ወሰን በእጇ ከመጨበጥ ባለፈ በዓለም 10ኛው የምንጊዜም ሴት አትሌት መሆን ችላለች፡፡ 

በተመሳሳይ ዓመት በፖላንድ በተደረገ 1,500 ሜትር ውድድር 3፡54፡01 የገባችበት ሰዓት 12ኛ ምርጥ ሰዓት ተደርጎ ተመዝግቦላታል፡፡

ጉዳፍ በግል ካደረገቻቸው ውድድሮች በዘለለ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና 1,500 ሜትር ብሔራዊ ክብረ ወሰን የያዘችበት፣ እ.ኤ.አ. በ2022 የዓለም ሻምፒዮና በ5,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያን ማሳካት የቻለችበት ውድድር ይታወሳል፡፡  

የመካከለኛ ርቀት የምታዘወትረው ጉዳፍ ርቀቷን ወደ 10 ሺሕ ሜትር እያሳደገች ትገኛለች፡፡ አትሌቷ በ2021 ፖርቱጋል በተካሄደው የ10 ሺሕ ሜትር ውድድር 29፡29፡42 በመግባት ስድስተኛው ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ በዚህም መሠረት ዘንድሮ በሚከናወነው የዓለም ሻምፒዮና ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዷ ነች፡፡

አትሌቷ የኦሪጎን የዓለም ሻምፒዮና በ5,000 ሜትር አሸናፊ በመሆኗ፣ በዘንድሮ ሻምፒዮና በርቀቱ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ትጠቀሳለች፡፡ በአንፃሩ ጉዳፍ ከ5,000 ሜትር ጎን ለጎን በ10 ሺሕ ሜትር ርቀት ትሳተፋለች? አትሳተፍም? የሚለው በቅርቡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚያሰናዳው የመለያ ውድድር ላይ መካፏሏ ከተረጋገጠ ነው፡፡ 

በየዓመቱ የሚከናወነው የዳይመንድ ሊግ፣ በተለያዩ ከተሞች በተከታታይ በሚደረግ የመም እና የሜዳ ተግባር ውድድሮች 40 አትሌቶች የተጋበዙበት ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ በዳይመንድ ሊግ መጠሪያ መከናወን ከመጀመሩ በፊት “ጎልደን ሊግ” የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ በየዓመቱ አዳዲስ ሕጎችን ይዞ የሚከናወነው ውድድሩ በተለያዩ ከተሞች ይቀጥላል። ሚያዝያ 27 ቀን በኳታር የጀመረው የዳይመንድ ሊግ በ12 ከተሞች ተከናውኖ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በአሜሪካ ኢውጂን ይጠናቀቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...