ጨለማ ነህ ብለሽ እኔን ስትተቺ
ዘለሽ አትጠግቢ ፥ ስቀሽ አትሰለቺ
ወርሃ-ፅጌ ነው ፤ ዓመት ሙሉ ላንቺ
ደሞ በየቀኑ ፣ ፋሲካ ነው ኑሮሽ
ያ’ለም ሰቀቀኑ ፣ ሩቅ ነው ለጆሮሽ
(የፍጥረት ሰቆቃ)
ለጋ ነው ላ’ምሮሽ፣ገላሽም ነው ጮርቃ
ሌላም አልልሽም ፤ ኖረሽ እዪው በቃ።
በየጎዳናሽ ላይ ፥ አደይ የሚያነጥፍ
በየዛፉ ቅርፊት ፥ ስምሽን የሚጥፍ
በዝቶልሽ ፥ ፈልቶልሽ ፥ አንቺን ሚያሽሞነሙን
ቀምሰሺው አታውቂም ፥ የብቻነት ሸክሙን
አዎ!
መፈቀር ፥ መታጀብ ከኔክታር ይጥማል
ግን ደግሞ ይገጥማል
በተወደሱበት አንደበት መነቀፍ
ውብ ገላ ጠብቆ ፣ ርጥብ ነፋስ ማቀፍ!
አንዳንዴም ይገጥማል
የማይሰምር ምኞት ፥ የማይልቅ ጥበቃ
ሌላም አልልሽም ፤ ኖረሽ እዪው በቃ!
አንቺ ደስታ ወዳጅ
በለምለም አፀድ ውስጥ ፥ ቢራቢሮ አሳዳጅ
ኑሮ ምትታይሽ ፤ እንደ ጣኦስ ቀልማ
እንዳትሸወጂ ባዝማሪዎች ዜማ
በሸንጋዮች ቃላት
ሕይወትም እንደ ጃርት ፥ የሾህ ቀሚስ አላት።
ተድላም ከሃዘን ጋር ያልፋል በፈረቃ
ከሳቅ በስተጀርባ ፥ ይሰለፋል ሲቃ
ሌላ ምን ልበልሽ? ኖረሽ እዪው በቃ።!
- በዕውቀቱ ሥዩም