Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልስድስት አሠርታትን የተጎናፀፈው ኅብረተ አፍሪካ

ስድስት አሠርታትን የተጎናፀፈው ኅብረተ አፍሪካ

ቀን:

ከአፍሪካ የተውጣጡ ልዑካን በአዲስ አበባ ከተማ በመሰባሰብ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት የተመሠረተበት 60ኛውን የምሥረታ በዓል ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. አክብረዋል።የሠላሳ ሁለት ነፃ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች አአድን የመሠረቱት በ1955 ዓ.ም. ግንቦት 17 ቀን (ሜይ 25 ቀን 1963) የመመሥረቻ ቻርተሩን በመፈረም ነው፡፡የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዓበይት ዓላማዎች ሆነው በቻርተሩ ተጠቅሰው ከነበሩት ውስጥ አኅጉሪቱን ከቅኝ ግዛትና ከአፓርታይድ ማላቀቅ በአፍሪካ አገሮች መካከል መተጋገዝን ማሳደግ፣ ለልማት ማስተባበር ይገኙበታል፡፡በዓሉ በአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት በሚገኘው ኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን ጨምሮ የአባል አገሮች እንደራሴዎች ተገኝተዋል።በዕለቱ ንግግር ያደረጉት፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፡ “ለአፍሪካ ህዳሴና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት” መሠረት የጣሉትን የድርጅቱ መሥራቾችን የሚያከብር በመሆኑ ዕለቱ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ጠቃሚ ቀን ብለውታል።አፍሪካ ከጥገኝነትና ከተለያዩ ችግሮቿ ሳትላቀቅ ነፃ ነች ማለት እንደሚያዳግት የገለጹት በሥነ በዓሉ ተገኝተው ንግግር  ያደረጉት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ  ናቸው፡፡ ለቀጣይ  የኅብረቱ ርዕዮች ስኬት፣  የአፍሪካ አገሮች መሪዎች፣ ለአኅጉሪቱ ውስብስብ ችግሮች፣ በጋራ አቋም ትኩረት  መስጠት  እንዳለባቸውም  አሳስበዋል፡፡በዋዛ ያልተፈረመው ቻርተር

‹‹የተነሳሳንበትን ከፍተኛ ተግባር በመልካም አከናውነን ብንገኝ ስማችንና ግብራችን በታሪክ መልካም ስም ይኖረዋል። ተግባራችንን ሳንፈጽም ብንቀር ግን ይታዘንብናል።
ስለእዚህ እምነታቸውን የጣሉብን ሕዝቦቻችን በሚመጡት ጊዜያቶች ውስጥ ከእኛ የሚጠብቁትን ሁሉ ለመፈጸም እንዲያበቃን ሁሉን የሚችለው ፈጣሪያችን ጥበብና አስተዋይነት እንዲሰጠን እናምነዋለን፣ እንለምነዋለን።››

 ይህ ዲስኩር ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከስድሳ ዓመታት በፊት ዕለቱ ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም.  የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (አአድ) ህልው ለማድረግ አዲስ አበባ ከተማ  ለከተሙት  32 የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት  መሪዎች የተናገሩት ነበር፡፡

የአፍሪካ አንድነት እንዲሁ አልጋ ባልጋ ሆኖ አልመጣም፡፡  ከአንድ ኢዮቤልዩ በፊት አአድን ለመመሥረት በተደረገው እንቅስቃሴ የተሰባሰቡት ከቅኝ አገዛዝ የወጡት የአፍሪካ መሪዎች ከቀጣናቸው ውጭ ለተባበረች አፍሪካ እምብዛም ቁብ ባልሰጡበት፣ ‹‹የሞኖሮቪያና የካዛብላንካ›› በሚባል ሁለት ጽንፍ የነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡

ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ይህን ቀጣናዊ መንገድን በማቋረጥ የአፍሪካን አንድነት ለማብሰር የተንቀሳቀሱት፤ ኢትዮጵያ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን የአአድን ቻርተር አዘጋጅታ አስፈላጊውን የዲፕሎማቲክ ዝግጅት በእነ አቶ ከተማ ይፍሩ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር)፣ ዶክተር ተስፋዬ ገብረ እዝጊእ (ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ) ካደረገች በኋላ፣ የአፍሪካ ሕዝብና የመንግሥታት መሪዎች ሁሉ ከዚህ ቀደም የነበረችውን አቋም ባለመከተል በአዲስ አበባ የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንዲገኙ በማድረግ ነው አአድን ህልው ያደረጉት፡፡

ቻርተሩ የተፈረመውም እንዲህ በዋዛ አልነበረም፡፡ ሸርተት ሸርተት ያሉ መሪዎችን በጽናት የታገሉት ንጉሠ ነገሥቱ የመሪዎቹን ጉባኤ ሲከፍቱ ባደረጉት ታላቅ ንግግር፣ ‹‹ስብሰባችን የአፍሪካ አንድነት የሚመሠረትበትን ቻርተር ለማጽደቅ ሳይስማማበት ሊበተን አይገባውም፤. . .የተባበረ ጥረቱን ከዚህ በበለጠና በተቀደሰ ዓላማ ላይ የሚያውለውን የአፍሪካን መንግሥታት ጎዳና አሁን ዕርምጃ እንውሰድ፡፡ ይህንንም ስናደርግ ነፃ ለሆነች ብቻ ሳይሆን ለተባበረች አፍሪካ ዓላማ ነው፤›› በማለት አስረግጠው በመናገራቸው እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በቆየው ጉባኤ የአፍሪካ አንድነት ቻርተር ተፈረመ፡፡ አአድም ህልው ሆነ፡፡ ኖሮም ለአፍሪካ ኅብረት መጠርያነት ደረሰ፡፡

ለአንድነቱ መነሻ ከሆኑት  ሁለቱ ጎራዎች  የአንደኛው የካዛብላንካ መሪና  በፓን አፍሪካኒዝም  አቀንቃኝነት የሚታወቁት የጋናው ፕሬዚዳንት ኩዋሜ ንኩሩማህ እንደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁሉ ታሪካዊ ንግግር ነበር ያደረጉት፡፡ እንዲህም አሉ፡-

 ‹‹ግርማዊነትዎ፣ ክቡር ፕሬዚዳንት፣ ክቡራን ተሳታፊዎች፣ ወንድሞችና ወዳጆች፤ ዛሬ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ከ32 አገሮች ያላነሱ ተወካዮች ተገናኝተናል። የቁጥራችን መጨመር ሕዝባችን ለነፃነቱ ያሳየው ጽናትና ጥብቅ ትስስር ማረጋገጫ ነው። አህጉራችንን ለማዋሐድ መላው የአህጉሪቱ ነዋሪ በእዚህ ጉባኤ ላይ የኅብረታችንን መሠረት እንድናኖር ኃላፊነቱን ጥሎብናል።››

ታሪካዊው የአፍሪካ አዳራሽ

      መጨረሻ ላይ የሁሉም ወገን ፍላጎት አንድና ተመሳሳይ ሆኖ የታየበትና የፀናበት አፍሪካም አንድነቷን ያንፀባረቀችበት  ይህ ታሪካዊው የአፍሪካ አዳራሽ፣ አፍሪካውያን በአፍሪካ ምድር ለመወያየት ይችሉ ዘንድ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያቀረበችውን ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ በያኔ አጠራሩ ‹‹የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና የሶሽያል ምክር ቤት›› ኢትዮጵያችን ለእኅትማማች አገሮች ዓላማ ስትል ያደረገችውን ትግል በማሰብና በማስታወስ፣ በሚያዝያ ወር 1950 ዓ.ም. አዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) መቀመጫ እንድትሆን በመረጣት ጊዜ የስብሰባ አዳራሽ አልነበረም፡፡ አፍሪካውያን አፍሪካን ስለሚመለከት ጉዳዮች ንግግር የሚያደርጉበት ጉባዔ የሚቀመጡበት፣ የሚዘክሩበት በአኅጉራቸው ሳይሆን ከአኅጉራቸው ውጪ ነበር፡፡ ይህ ክስተት ማብቃት አለበት ብለው ታጥቀውና ጠቅለው የተነሡት ‹‹አባ ጠቅል›› ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አሁን ኢሲኤ የሰፈረበትንና የአፍሪካና ለዓለም አቀፍ ጉባኤዎች መሰብሰቢያ ሆኖ የሚያገለግለውን የአፍሪካ አዳራሽ በኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት በአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ባሠሩበት ጊዜ   ስለ አዳራሹ ፋይዳ ያኔ የተናገሩት ለጥቅስ የሚበቃ ነው፡፡ ‹‹ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ስለ አፍሪካ ጉዳዮች ለመወያየት የሚደረጉት ስብስባዎች ከአፍሪካ ውጭ ነበር፡፡ የሕዝቦቿም የወደፊት ዕድል አፍሪካውያን ባልሆኑ ወገኖች ይወሰን ነበር፣ ዛሬ የበርሊን [ጀርመን] እና የአልጂስራስ [ስፔን] ወገኖች ቀርተው፣ በአክራና በአዲስ አበባ ጉባኤዎች አማካይነት የአፍሪካ ሕዝብ እነሆ ከብዙ ጊዜ በኋላ ስለራሱ ፕሮብሌም የወደፊት ዕድል ለመወያየት በቅቷል፡፡››

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከ60 ዓመት በፊት በአአድ መሥራች ጉባኤ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፡- ‹‹የዛሬ አንድ መቶ ዓመት የሚኖሩት ትውልዶች የአፍሪካን ታሪክ በሚመረምሩበት ጊዜ ስለዚህ ስለ ዛሬው ጉባዔ ምን አስተያየት ይኖራቸው ይሆን?››

ምድረ ዓለም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ‹‹የአፍሪካ አንድነት መሥራች›› ብሎ እንዲህ አግዝፏቸዋል፡፡ ‹‹ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካን አንድነትና የናሽናሊዝም ስሜት ሊፈጥሩ ከቻሉት እጅግ ኃያላንና ብርቱም ከሆኑት ሰዎች አንዱ ናቸው ከፈጸሙዋቸው ዓቢይ ተግባሮች ሁሉ ጎልቶ የሚታየው የሞንሮቪያና የካዛብላንካ ቡድኖች በሚል ስም ይጠሩ የነበሩትን ተፎካካሪ የፖለቲካ አስተያየት አስማምተው የአፍሪካን አንድነት ድርጅት መመሠረታቸው ነው፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...