Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን ዳግም መመረጥ ለዓለም ፖለቲካ ምንድነው?

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን ዳግም መመረጥ ለዓለም ፖለቲካ ምንድነው?

ቀን:

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሴፕ ታይፕ ኤርዶሃን ዳግም በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመሪነት ሥልጣኑን ተቆናጠዋል፡፡ የኤርዶሃን የሥልጣን ዘመንም ቀጥሏል፡፡ እሑድ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በተደረገው ዳግም ምርጫ 52.2 በመቶ ድምፅ በማግኘት ተገዳዳሪያቸውን ከማል ኪሊ ዳሮግሉን አሸንፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን 47.8 በመቶ ድምፅ ያገኙትን ተፎካካሪያቸውን ኪሊ ዳሮግሉን በማሸነፍ እ.ኤ.አ. እስከ 2028 ቱርክን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ድጋፍ ቢያገኙም፣ ዛሬም በደቡብ ምሥራቅ ቱርክ ከሁለት ወራት በፊት ለተከሰተውና 50 ሺሕ ያህል ለሞቱበት የመሬት መንቀጥቀጥ አፋጣኝ ምላሽ አልሰጡም በሚል ይተቻሉ፡፡

በሳቸው የቀደመ ሁለት የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ዘመን ቱርክ ከምዕራባውያን ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሻክሯል፣ ኑሮ ተወዷል የሚሉ ጥያቄዎች የሚነሱባቸው ፕሬዚዳንቱ፣ ከአገር ውጭ ደግሞ በምዕራባውያን ይወቀሳሉ፡፡

ባለፉት ሁለት አሥር ዓመታት ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን ዓለምን ለሁለት በከፈለው ፖለቲካ ከሁለቱም ጎራ ሆነው አገራቸውን መምራት ችለዋል፡፡ ቱርክ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ብትሆንም፣ እሳቸው ኔቶን ከምትቃወመው ሩሲያ ጋርም የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡

ከሰባት አሥርት በላይ ያስቆጠረው ኔቶ ጥምረት ውስጥ ቱርክ በተለያዩ የጦር ቀጣናዎች በሰላም አስከባሪነት ተሳትፋለች፡፡ ምዕራባውያን ፀብ አጫሪ በማለት ቃላት ከሚወራወሩባት ሩሲያ ደግሞ የጦር መሣሪያ ገዝታለች፡፡ ከኔቶ ጋር ያላት ግንኙነት የተጠናከረ ቢሆንም፣ ሞስኮን ያስከፋል የምትለው አገር በኔቶ ውስጥ በአዲስ አባልነት እንዲገባ አትፈቅድም፡፡

ቱርክ፣ ከኔቶ አባል አገሮች ውስጥ ያልተለመደና የሚቃረን ድርጊት በማድረግ እንደምትታወቅ ያሰፈረው ሎስአንጀለስ ታይምስ፣ ይህ የቱርክ ባህሪ በተለይ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ጎልቶ መውጣቱን ይገልጻል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከጦርነቱ በኋላም ቢሆን ከአሜሪካና ከአውሮፓ ጋር ወዳጅ ቢሆኑም፣ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አላቋረጡም፡፡ ይልቁንም ከምዕራባውያን አጋሮቻቸው ይልቅ ከሩሲያ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ጠንካራ ሆኗል፡፡ በሩሲያና ዩክሬን መካከል የሰላም ድርድር እንዲደረግ የሞከሩ መሪም ናቸው፡፡

ኤርዶሃን ለሦስተኛ ጊዜ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን በመያዛቸው አቋማቸውን እንደጠበቁ ይቆዩ ይሆን?

የኢሮኤዥያ ግሩፕ የአውሮፓ ዳይሬክተር ኢሚር ፔካር እንደሚሉት፣ ኤርዶሃን በምዕራባውያኑና በሩሲያ መሃል ሆነው ወሳኝ ሚና ይዘው የሚቀጥሉ ቢሆንም፣ ይህ ለምዕራባውያን አቀንቃኞች የሚመች አይሆንም፡፡

የሁለተኛው ዓለም ጦርነት እ.ኤ.አ. በ1945 ማክተሙን ተከትሎ የተመሠረተውን ኔቶ፣ ምሥረታው ሦስት ዓመታት ሳያስቆጥር የተቀላቀለችው ቱርክ በጥምረቱ ውስጥ በወታደር ተዋጽኦ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷም ለኔቶ የጀርባ አጥንት ያስብላታል፡፡

ሆኖም 85 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን ቱርክ የሚመሩት ኤርዶሃን፣ በምዕራባውያኑ ዘንድ ወደ ሩሲያ በማዘንበላቸው ይተቻሉ፡፡ ሕዝባቸውን ከዓለማዊ ወደ መንፈሳዊ አስተዳደር እየቀየሩት ነው በሚልም ምዕራባውያኑ ያነሷቸዋል፡፡

በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎም ምዕራባውያን አገሮች በሩሲያ ላይ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ሲጥሉ፣ ቱርክ ለሞስኮ የሕይወት መሥመር የሆነች አገር ነች፡፡ ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ጠብቀው መቆየታቸው ለምዕራባውያኑ አልተመቸም፡፡

ኤርዶሃን ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታም፣ ቱርክ እንደምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ማዕቀብ እንደማትጥል፣ ቱርክ ጠንካራ አገር ብቻ ሳትሆን ከሩሲያ ጋር አዎንታዊ ግንኙነት እንዳላትና ሩሲያና ቱርክ በእያንዳንዱ ዘርፍ እንደሚፈላለጉ ተናግረዋል፡፡

ቱርክ ከፍተኛውን የኃይል አቅርቦት የምታገኘው ከሩሲያ ነው፡፡ አንድ ሦስተኛ ያህል ነዳጅ ዘይትና ጋዝ የምታስገባው ከሩሲያ ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች በቱርክ የመጀመሪያ የሆነውንና በቀጣዩ ዓመት አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚጠበቀውን የኑክሌር ጣቢያ አብረው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

የሁለቱ አገሮች የዓምና የንግድ ልውውጥ ከ62 ቢሊዮን ዶላር የዘለለ ሲሆን፣ ቱርክም ለሩሲያ ጎብኚዎች ተማራጭ አገር ሆናለች፡፡ አውሮፓ ለሩሲያ ዜጎች በሯን ብትዘጋም፣ ቱርክ ሩሲያውያን የሚኖሩባትና የሚሠሩበት አገር ሆናለች፡፡

የአሜሪካ የረዥም ጊዜ ወዳጅና የኔቶ አባሏ ቱርክ፣ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ የመጣው በኤርዶሃን ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አቀነባብሯል ብላ ቱርክ የምትወነጅለውና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ፋቱላህ ጉለን ሙቭመንትን አሜሪካ ባለመቃወሟ ነው፡፡ በኋላም የቱርክ ከሩሲያ የጦር መሣሪያ መግዛት ያስቀየማት አሜሪካ፣ የቱርክና የሩሲያ ግንኙነት እያደገ መምጣቱንም እንደማትደሰትበት በዋሽንግተን የብሩኪንግሥ ተቋም አማካሪ አማንዳ ስሎት ይገልጻሉ፡፡

ቱርክ ከምዕራባውያንም ከሩሲያም ሆና እንደምትቀጠል ደግሞ ገልፍ ኒውስ ያለውን ምልከታ አስፍሯል፡፡

ኤርዶሃን፣ በሩሲያ የተሠሩ ወታደራዊ ትጥቆችን መግዛትና ሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ባለመቀበል የሚቀጥሉ ሲሆን፣ ምናልባትም የስዊድንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ሊቀበሉ ይችላሉ ሲል ዘገባው አስፍሯል፡፡

ከሩሲያ፣ ቻይና፣ እንዲሁም ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክረው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው፣ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን የምግብ አቅርቦት እጥረት ለመታደግ የተጫወቱት ሚና በሁለት ወገን ክርክር እንዲነሳባቸውም አድርጓል፡፡

አንድም ከሩሲያ በሌላም ከምዕራባውያን የተጣመሩት ኤርዶሃን፣ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ‹‹ዓለም የቱርክን ዘመን›› ያያል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...