ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመርያ በነበረው የክቡር ዘበኛ ሚሊታሪ አካዴሚ ሦስተኛ ኮርስ ተመራቂና የአየር ወለድን ጦር ከመሠረቱት ከፍተኛ መኮንኖች አንዱ ናቸው፡፡ አሜሪካ በሚገኘው ፎርት ቤኒክ ጆርጂያ የመኮንኖች ሥልጠና ማዕከል ከፍተኛ የውትድርና ሙያ ተከታትለው ተመርቀዋል፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች በምሥራቅና በሰሜን ጦር ግንባሮች በተካሄዱት ዓውደ ውጊያዎች ላይ የወገንን ጦር በመምራት ግዳጃቸውን በሚገባ የተወጡ ሲሆን፣ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የሁለተኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በኮሪያ ልሳነ ምድር ተካሂዶ በነበረው ጦርነት ከቀሩት የኢትዮጵያ ዘማቾች ጋር ሆነው ዓለም አቀፍ ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡ ስለማኅበሩ እንቅስቃሴ፣ ስለኮሪያ ዘማቾች ሁኔታና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ኮሎኔል እስጢፋኖስን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በኮሪያ ልሳነ ምድር ተካሂዶ ስለነበረው ጦርነት መንስዔና የኢትዮጵያ ወታደሮች የከፈሉትን መስዋዕትነት ባጭሩ ቢገልጹልን?
ኮሎኔል እስጢፋኖስ፡- ኮሪያ ሰሜንና ደቡብ በሚል ለሁለት ተከፍላ ነበር፡፡ ሰሜን ኮሪያ በቻይና የታገዘ ወረራ ደቡብ ኮሪያ ላይ ማካሄዷን ተያያዘችው፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቀረበላት ጥሪ መሠረት 3520 የክቡር ዘበኛ ወታደሮች በማሰማራት ዓለም አቀፍ ግዳጇን ተወጥታለች፡፡ ይህ ዓይነቱም ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከአፍሪካ ብቸኛዋ አገር እንድትሆን አድርጓታለ፡፡ በኮሪያ ልሳነ ምድር በተለያዩ ዓውደ ውጊያዎች ተሰማርተው ዓለም አቀፍ ግዳጃቸውን በከፍተኛ የጀግንነት ወኔ በመፋለም ላይ ከነበሩትም የወገን ኃይሎች መካከል 121 መስዋዕት ሲሆኑ፣ 526 ያህሉ ደግሞ ቆስለዋል፡፡ በሁለቱም ኮሪያዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከፀና በኋላ ቁስለኞቹና የቀሩትም ወታደሮች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የተሰውትም አስክሬናቸው በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መካነ መቃብር በክብር ያረፈ ሲሆን በጠላት የተማረከ ወይም የጠፋ ወታደር የለም፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ምን ያህል የኮሪያ ዘማቾች በሕይወት ይገኛሉ? ከማኅበሩ ወይም ከኢትዮጵያና ከኮሪያ መንግሥታት ምን ዓይነት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው?
ኮሎኔል እስጢፋኖስ፡- በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች 78 ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የአልጋ ቁራኛ ሲሆኑ፣ ጥቂቶቹ ግን በደህና ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ዘማቾቹ ከኢትዮጵያና ከኮሪያ መንግሥታት ምንም ዓይነት ድጋፍ አያገኙም፡፡ ነገር ግን የኮሪያ ሕዝብና የግል ድርጅቶች የገንዘብና የሕክምና ድጋፍ ያደርጉላቸዋል፡፡ ለልጆቻቸው፣ ለልጅ ልጆቻቸውና በአጠቃላይ ቤተሰቦቻቸውን እየደገፉ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የድጋፍ ዓይነቱን ዘርዘር አድርገው ቢያስረዱን?
ኮሎኔል እስጢፋኖስ፡- የድጋፉ ዓይነት በዝርዝር ሲታይ፣ በሕይወት የሚገኝ አንድ የኮሪያ ዘማች በወር 2,100 ብር ሒሳብ፣ በየሁለት ወሩ 4,200 ብር ይደርሰዋል፡፡ ገንዘቡም የሚደርሳቸው በቡና ባንክ ነው፡፡ የተጠቀሰው ባንክ በሌለበት ቦታ ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስማቸው በተከፈተ ሒሳብ ቁጥር ገቢ ይደረግላቸዋል፡፡ ገንዘቡን ከኮሪያ ሕዝብና ድርጅቶች አሰባስቦ በባንክ በኩል የሚልክላቸው ቢሮውን በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የከፈተውና ‹‹ወርልድ ቱጌዘር›› የተባለው የኮሪያ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ በማኅበሩ እጅ ምንም ገንዘብ አይገባም፡፡ ከዚህም ሌላ የጤንነት መታወክ ለሚገጥማቸው ዘማቾች ማንኛውንም ዓይነት የሕክምና አገልግሎት አዲስ አበባ በሚገኘው ኮሪያ ሆስፒታል ውስጥ በነፃ ያገኛሉ፡፡ እንዲሁም ብርድን ወይም ቅዝቃዜን መከላከልና በኤሌክትሪክ ኃይል እየታገዘ ሙቀት ማመንጨት የሚችል ብርድ ልብስ በቅርቡ በነፍስ ወከፍ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በጦርነቱ ለተሰው፣ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ለሞቱና በሕይወትም ላሉት የኮሪያ ዘማቾች ቤተሰቦች (ሚስት፣ ልጅና የልጅ ልጅ) የሚደረግላቸው ድጋፍ ይኖር ይሆን?
ኮሎኔል እስጢፋኖስ፡- አዎ! ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡ በመጀመርያ ለኮሪያ ዘማቾች ልጆትና የልጅ ልጆች ኮሪያ ሄደው የቴክኒክና የሙያ ሥልጠና ትምህርት እንዲያገኙ ተደርጎ ነበር፡፡ ሥልጠናቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ አገር ቤት ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ ኮሪያ ያሉት ልዩ ልዩ ድርጅቶችና ኩባንያዎች በርካሽ ደመወዝ ይቀጥሯቸዋል፡፡ ኩባንያዎቹና ድርጅቶቹም ርካሽ ዋጋ የሚጠይቅ ጉልበት በማግኘታቸው ተደስተው ቅጥሩን በስፋት ተያያዙት፡፡ እንደወጡ መቅረትን ለማስወገድ የሚቻለው በአገር ውስጥ የማሠልጠኛ ተቋም በማቋቋም ብቻ መሆኑን በመረዳት ወደ ኮሪያ መላኩ ቀርቶ በእንጦጦ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ (ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት) ውስጥ የኮሪያ ዘማቾች ልጆችና የልጅ ልጆች ብቻ የሚሠለጥኑበት አንድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋቋመ፡፡ ተቋሙም የመማርና የማሠልጠኑን ሥራ ተያያዘው፡፡ ነገር ግን ለትምህርትና ለሥልጠና የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ መሣሪያዎች በየጊዜው እየተሰረቁ ተቋሙ ባዶውን እስከ መቅረት ደረሰ፡፡ በዚህም የተነሳ ያለው አማራጭ ተቋሙን መዝጋት ብቻ ሆነ፡፡ ስለሆነም ተቋሙ ወደ ኮሌጁ እንዲዛወር ተደረገ፡፡ ይሰጥ የነበረውንም የሥልጠና አገልግሎት አቆመ፡፡
ሪፖርተር፡- እንደቆመ ቀረ? ወይስ ሌላ ቦታ ላይ በአዲስ መልክ ተቋቋመ?
ኮሎኔል እስጢፋኖስ፡- ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ኮሌጅ ቅጥር ጊቢ ተቋቁሞ የነበረው ተቋም ከተዘጋ በኋላ ‹‹ኮይካና ኤልጂ›› የተባሉት የኮሪያ ኩባንያዎች ከወርልድ ቱጌዘር ጋር በመተባበር አዲስ አበባ ውስጥ ሰሚት አካባቢ አዲስ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋም አቋቋሙ፡፡ በተቋሙ ውስጥ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት መሠልጠን ይችላል፡፡ ነገር ግን ለሚሰጠው ሥልጠና መጠነኛ የሆነ ክፍያ ያስከፍላል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለኮሪያ ዘማች ልጆችና የልጅ ልጆች ሥልጠናውን የሚሰጠው ወይም ሥልጠናውን የሚከታተሉት በነፃ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ባልታወቀ ምክንያት በተቋሙ የሚሠለጥኑት ልጆትና የልጅ ልጆች ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ለሥልጠና በምን መልክ ነው የሚመዘገቡት?
ኮሎኔል እስጢፋኖስ፡- ማኅበሩ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ጽሕፈት ቤት እየቀረቡ እንዲመዘገቡ የሚገልጽ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ ማስታወቂያ የሚወጣው በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በመለጠፍ ነው፡፡ የማስታወቂያውን ጥሪ ተቀብለው የሚመዘገቡትም በሁለት ዓይነት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው መንገድ ባሉበት ትምህርት ቤት በትምህርት አቀባበላቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሆነው ከተገኙ ባሉባቸው ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉና በዚህም በየወሩ 2,000 ብር እንዲከፍላቸው ይደረጋል፡፡ በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት ያስመገቡት ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋም እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ማስታወቂያውን የሚያነቡና የሚመዘገቡት ልጆችና የልጅ ልጆች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ አባቶቻቸው ወይም አያቶቻቸው የኮሪያ ልጆች መሆናቸውን አጣርቶ የሚያቀርበው ማኅበሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የማኅበሩ የገቢ ምንጭ ምንድነው? ማኅበሩ እንደ ማኅበር ለዘማች ቤተሰቦች የሚያበረክተው ድጋፍ አለ?
ኮሎኔል እስጢፋኖስ፡- ማኅበሩ በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባለሦስት ወለል ሕንፃ አሠርቶ እያከራየ ነው፡፡ ከኪራይ የሚገኘው ገቢ ለማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ሥራ ማከናወኛና ለዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ ይውላል፡፡ የዘማች ቤተሰቦች ቁጥር ከ1000 በላይ ሲሆን፣ ከኪራይ የሚገኘውና ለእነርሱ ድጋፍ የሚውለው ገንዘብ በየወሩ ይሰጣቸው ቢባል፣ በወር አሥር ብር ያህል እንኳን ላይደርሳቸው ይችላል፡፡ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ሲባል ገንዘቡን እያጠራቀምን በነፍስ ወከፍ 100 ብር እንሰጣቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ለእያንዳንዱ ቤተሰብ የምንሰጠው ገንዘብ ወደ 500 ብር ከፍ ብሏል፡፡ ገንዘቡም የሚሰጣቸው ገና፣ ፋሲካ (ትንሳዔ በዓል) እና የዘመን መለወጫ በዓል ሲደርስ ነው፡፡ ቢያንስ የእንቁላል ወጪያቸውን ሊሸፍንላቸው ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ ማኅበሩ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ በኪራይ ላይ ያለውን ሕንፃ ያሠሩልንና ሕንፃውን ያረፈበትን ቦታ በማኅበሩ ስም የገዙልን የኮሪያ ኩባንያዎችና ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የማኅበሩ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ተብሎ ይታሰባል?
ኮሎኔል እስጢፋኖስ፡- ማኅበሩ ለጊዜው በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥለጣን ሥር ነው የተመደበው፡፡ ባለሥልጣኑ ማኅበሩን ወደፊት የሚወስደው ወይም የሚረከበው ባለድርሻ አካል ነው የሚል መመርያ አለው፡፡ በዚህም ጉዳይ ዙሪያ ከባለሥልጣኑ ጋር ተነጋግረናል፡፡ በእኛ አስተሳሰብ ግን የኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች ማኅበርን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሊወርሰው ወይም ሊረከበው ይገባል፡፡ ለተግባራዊነቱም አንዳንድ ጥረቶችን እያደረግን ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ያስፈለገበትም ዋናው ምክንያት የማኅበሩ ታሪክ በወታደር ዙሪያ ያጠነጠነ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ታሪክ ስለሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያለነው ሁላችንም አርጅተናል፡፡ እኔ ለምሳሌ አሁን 91 ዓመቴ ነው፡፡ ስለዚህ ድንገት ጥሪ ሊደርሰኝ ይችላል፡፡ ይህም በመሆኑ ሊረዱንና ድጋፍ ሊሰጡን የሚችሉ የዘማች ልጆች አሉ፡፡ እነዚህ ልጆች ቢረከቡ ለጊዜው ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ግን ቀጣይነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ወደ ልጆችና የልጅ ልጆች ሲሄድ ታሪኩ እየጠፋ ይሄዳል፡፡ ነገር ግን ተረካቢው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ከሆነ በሥሩ ከተቋቋመው ሰላም ማስከበር አካል ጋር ማኅበሩ ተዋቅሮ ቀጣይነት እንዲኖረውና ታሪኩም ተረስቶ እንዳይቀር ያደርጋል፡፡