Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር (ክፍል ዘጠኝ)

ሆድና የሆድ ነገር (ክፍል ዘጠኝ)

ቀን:

በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

እንደ በፊቱም አትብላ

እንደ ኋለኛውም አትብላ…

ሰውዬው በእግር ጉዞ ላይ እያለ ስንቁ አለቀበት፡፡ የጉዞ መንገዱ ግን ገና አላለቀም ማለት ከአሰበበት ቦታ ገና አልደረሰም፡፡ በባዶ ሆዱ ብዙ ተጓዘ፡፡ “ይቅርታ” የማያውቀው ረሃብ በበኩለ ገስግሶ ወደ እሱ መጣኸ ያሰቃየውም ጀመረ፣ እናም ጉልበቱ እየከዳው ሄደ፣ ድካሙም እያየለ መጣ፣ እነዚ መንገዱን አፈፍ-አፈፍ እያደረጉ ይራመዱ የነበሩ እግሮቹ፣ የኤሊ ጉዞን ተለማመዱት…

በመካከሉ ከአንድ የደረሰ የባቄላ አዝመራ ካለበት የእርሻ ቦታ ደረሰ፡፡ ፈጠን ብሎ፣ ከአዝመራው ውስጥ ቁጭ አለ፡፡ ፈጠን ብሎ የባቄላውን የእሸት ዛላ በመቁረጥ፣ ከእነገለፈቱ (ከእነ ሽፋኑ) መብላት ያዘ… ረሃቡ በመጠኑ ተግ ሲልለት ደግሞ፣ ባቄላውን ፈለፈለ (ገለፈቱን እያስወገደ) መብላት ያዘ… ረሃቡ ሲያቆምለት ደግሞ ባቄላውን እየጠረጠረ (የባቄላውን ሽፋን እያስወገደ) መብላት ጀመረ…

ፈንጠር ብሎ እንደ ተቀመጠ፣ የዚህን የተራበ መንገደኛ የአበላል ሁኔታ ከመጀመርያ ጀምሮ ሲከታተል የነበረ ሰውዬ፣ ወደ ረሃብተኛው መንገደኛ በመምጣት እንዲህ አለው፣ “እንደ መጀመርያውም አትብላ፣ እንደ ኋለኛውም አትብላ፣ እንደ መካከለኛው ብላ” በማለት መከረው፡፡

ይህን ሰውዬ የባቄላውን እሸት ከእነ ገለፈቱ ያስበላው አጅሬው ረሃብ ነው፡፡ “ረሃብ ቀን አይሰጥም” የሚል አባባል አለ፡፡ ከዚህ ሰውዬ አንፃር ካየነው ግን፣ ረሃብ ቀን ብቻ ሳይሆን፣ ደቂቃዎችም መስጠት ቀርቶ ለማበደር ምን ያህል ንፉግ እንደ ሆነ ይገባናል፡፡ የባቄላ እሸት ዛላን ቀንዝፎ እየፈለፈሉ በመብላትና እየቀነዘፉ ከነዘለፈቱ በመበላት መካከል ያለው የጊዜ ርቀት የሴኮንዶች ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ረሃብ ጊዜ አይሰጥምና ግለሰቡ ለሴኮንዶች በመታገስ እየፈለፈለ መብላት አልሆነለትም፡፡ ትዕግሥቱን ነሳው…

ረሃብ ትዕግሥትን ከመፈታተን አልፎ ተርፎ፣ የማገናዘብ ችሎታችንንም ክፉኛ የሚፈታተን “ከይሲ” ነው፡፡ አንድ አብነት እንመልከት፡-

ከፍተኛ ድርቅ በአንድ አካባቢ ይከሰትና ረሃብን ይወልዳል፡፡ ገበሬዎቹ፣ የቤት እንስሳታቸውን ከተማ ወደሚገኙ የገበያ ቦታዎች ጭምር በመውሰድ እጅግ በጣም ርካሽ በሆነ ዋጋ መሸጥ ጀመሩ፡፡ በርካሽ ዋጋ የሸጡት፣ የቤት እንስሳቱ ስለከሱ አይደለም፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም የሚፈጥረው ተቃርኖ ነው፣ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ብዙ ሻጭ ገበሬዎችና በጣም ውስን የሆኑ የከተሜ ገዥዎች ስለተፈጠሩ፡፡

ገበሬዎቹ ያላቸውን ጥሪት አሟጠው በመሸጥ የረሃቡን ቀን ለማለፍ ብዙ ተፍገመገሙ፣ ተፍገመገሙ፣ ግን አልሆነም… በመካከሉ አንድ ገበሬ የቤት እንስሳቱን፣ ሌላ ሌላውንም ንብረት ሸጦ፣ የአሏህ ፈቃዱ ሆኖ ዝናብ ቢጥል፣ ከሌላ ሰው በሬ ጋር አቀናጅቶ የሚያርስበት አንድ በሬ ብቻ ቀረው… ይህ ገበሬ እንደ ሌሎቹ ብጤዎቹ ሁሉ፣ በየቀኑ ወደ ሰማይ ማንጋጠጡን ባያቋርጥም፣ ደመና ቀርቶ፣ ሰማዩ መገርጣት የሚባል መልኩን ረስቶት፣ የተወለወለ መስታወት በመሰለ ደማቅ ሰማያዊ መልኩ ከመጀንጀን ወይ ፍንክች! እና እሱም ሆነ ቤተሰቡ ምን ይብላ? አንድ በሬውን ማረድ ግድ ሆነ፡፡

በአንድ በኩል ከጓዳው የቀረ አንድ በሬውን ጨክኖ ሊያርደው በመሆኑ ጥልቅ የሆነ ሐዘን ሆድ ሆዱን እየበላው፣ በሌላ በኩል ምግብ የሚባል ነገር ካየ ውሎ ያደረ ሆዱ በረሃብ ዶማው ሆዱን እየቆፈረው፣ ሌባ እንደ በረበረው ቤት በተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ ሆኖ በሬውን አረደው… ውስጡን እያቃጠለው ያለውን ጥልቅ ሐዘን፣ የዕንባውን እንክብሎች በፊቱ ላይ በማውረድ እንዳይገላገለው የተዘበራረቀ ስሜቱ አገደው…

ሥጋው ተጠባበሰና ከቤተሰቡ ጋር ከቦ በላ፡፡ ቤተሰቡ ጠገበ፣ እሱም ጠገበ፡፡ ከዚያም በታላቅ ሐዘንና ቁጭት ውስጥ እንደ ተዋጠ እንዲህ አለ፡-

“እንዲህ ልጠግብ፣ በሬዬን አረድኩት፡፡”…

(በሬውን ባያርድ ኖሮ መች ይጠግብ ነበር? ብቻም ሳይሆን እሱም ሆነ ቤተሰቡ ረሃብ ለሚወልደው በሽታም ሆነ ሞት ከመጋለጥ መች ይተርፉ ነበር?)…

በሌላ በኩል ረሃብ ስስትንም ያስተምራል፣ ወይም ስስታም ያደርጋል፡፡

ሰውዬው በግ አረደ፡፡ ከደጁ ካለ ዛፍ ባላ ላይ አንጠልጥሎ ቆዳውን እየገፈፈ ነው፡፡ ቂጥኝ የያዘው ዘመዱ ቆሞ እየተመለከተ ነው፡፡ ቆዳውን ገፎ እንደ ጨረሰ፣ የሚቆራረጠውን ሥጋ የሚያስቀምጥበት ዕቃ ለማምጣት፣ ወደ ቤት ገባ፣ ትልቅ ቆሬ (በሳፋ መልክ ከእንጨት የተሠራ) ይዞ ተመለሰ፡፡

እንደ ተመሰለም፣ ቂጥኝ የያዘውን ዘመዱን፣ “ሥጋውን ነካኸው’ንዴ?” በማለት ጠየቀው፡፡ (በዚያን ጊዜ “ቂጥኝ በማንኛውም ንክኪ ይተላለፋል” ተብሎ ስለሚታመን፣ የበሽታው ተጠቂዎች ይገለሉ ነበር፡፡)

ሰውዬው ምንም የነካው ነገር የለም፡፡ ሆኖም “ከጠየቀኝማ” በማለት (ባለመታመኑም ሊናደድ መቻሉ እንደ ተጠበቀ ሆኖ)፣ “አዎ” አለው፡፡

“የት ላይ?” አለው፡፡

ወደ ተሰቀለው ሥጋ ተጠጋና ከላቱ አካባቢ እየነካ “እዚህ ላይ!” አለው፡፡

“አራጁ” ጥያቄውን ቀጠለ፡፡

 “ሌላስ?”

የታፋውን አካባቢ እየነካ “እዚህ ላይ!”

  “ሌላስ?”

የወገቡን አካባቢ እየነካ “እዚህ ላይ!”

“ሌላስ?”

የሆዱን አካባቢ እየነካ “እዚህ ላይ!”

“ሌላስ?”

የፍርምባውን አካባቢ እየነካ “እዚህ ላይ!”

“ሌላስ?”

የደንደሱን አካባቢ እየነካ “እዚህ ላይ!”…

በመጨረሻም የታረደው በግ ሙሉ በሙሉ በቂጥኝ በሽታ ለተያዘው ሰው ተሰጠ… ብቻውን የአንድ በግ ሥጋ መብላቱ ነው፡፡ መቼስ ተንኮል ሲደመር ስግብግብነት የማይሠራው ነገር የለ?

ረሃብ ስስትን ከማስተማርና ስግብግብ ከማድረግም አልፎ ተርፎ፣ አለቅጥ ራስ ወዳድ ያደርጋል፣ ወዳጆች እንዲጣሉ፣ ፍቅር በጥላቻ እንዲቀየር፣ መተማመን በመከዳዳት እንዲተካ ያደርጋል፡፡

በአንድ ወቅት ሁለት ሰዎች የጭብጦ (ከበሶ የተዘጋጀ) ስንቅ ይዘው መንገድ ይገባሉ፡፡ በመንገድ ላይ እያሉ፣ ስንቃቸው ተገባደደ፡፡ አንድ ቀን ቁርስ ለመብላት ከአንድ ዛፍ ጥላ ሥር አረፍ አሉ፡፡ ጭብጦ የያዘውን አገልግል ከፈቱ – የቀሯቸው ሁለት ጭብጦዎች ብቻ!

ውኃ ስላለቀባቸው ተረኛ የነበረው ሰውዬ ውኃ ለማምጣት፣ የውኃ መቅጃቸውን ቅል ይዞ ወደ ወንዝ ሄደ፡፡ በመካከሉ ይኼንኛው ሰውዬ አንዱን ጭብጦ በላው… ወንዝ የወረደው ውኃውን ይዞ ሲመጣ፣ ከአገልግሉ ውስጥ ያለው ጭብጦ አንድ ብቻ መሆኑን አየ፡፡ በድንጋጤ ተሞልቶ፣ በሚቁለጨለጩ ዓይኖቹ  ከጭብጦው ላይ አፈጠጠበት፡፡ ጭብጦውም በተራው እየተቁለጨለጨ አየው፡፡ በድንጋጤ ተሞልቶ የሚቁለጨለጩ ዓይኖቹን ወደ ጓደኛው አዞረ፡፡ ከዚያም እንዲህ አለው፡-

“አንዱስ?”   

ከፊታቸው ወዳለው ጭብጦ በጣቱ እያመለከተ፣”አንዱማ ይኼው!”

“ወንዝ ስሄድ ሁለት ነበር፡፡”

“አዎ ነበር፡፡”

“አንዱስ?” 

አሁንም ከፊታቸው ወዳለው ጭብጦ በጣቱ እያመለከተ፣ “አንዱማ ይኼው!”

ውኃ ቀጂው እንደገና ጠየቀ፣ “ወንዝ ስሄድ ሁለት ነበር፡፡”

“አዎ ነበር፡፡”

“አንዱስ?” 

ጓደኛው አሁንም ከፊታቸው ወዳለው ጭብጦ በጣቱ እያመለከተ፣ “አንዱማ ይኸው!”

ውኃ ቀጂው አሁንም እንደ ገና ጠየቀ፣ “ወንዝ ስሄድ ሁለት ነበር፡፡”

“አዎ ነበር፡፡”

“አንዱስ?” 

አሁንም ከፊታቸው ወዳለው ጭብጦ በጣቱ እያመለከተው፣ “አንዱማ ይኸው!”…

አጅሬው ሆድ እንዲህ ስስታምና ራስ ወዳድም ያደርጋል…

ስለሆድ በተነገሩ የሐበሻ የወግ ባህል ውስጥ ያሉት አንዳንዶቹ ትርክቶቻችን፣ የነገ ተተኪ የሆኑ ሕፃናትን በስስታምነትና ራስ ወዳድነት ባህሪ እንዲቀረፁ የማድረግ ሚና ያላቸው ጭምር ናቸው…

“ሚስቴ ወልዳብኝ አራስ

አንጣልኝ ብላኝ ደንደስ

ከቤቴ በላይ ስደርስ

እኔው ብሶብኝ ጉርስ”…

በሐበሻ ወግ ውስጥ ያለውና ከሆድ ጋር የተያያዘው አንዳንዱ ትርክት፣ ከራስ ወዳድነት ባሻገር ያለፈን ተግባር ሊያበረታታ የሚችልበትም ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ የሚያበረታታበት መንገድ ግን እጅግ ሥልታዊና ደበቅ ባለ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ ለአብነት እናቅርብ፡-

በአንድ ሠፈር ለረጅም ጊዜ የኖረች አንዲት ውሻ ነበረች፡፡ በአንድ ወቅት ወደ ስድስት ወይም ሰባት ቡችሎችን ትውልዳለች፡፡ ቡችሎቿ እያደጉ ሲሄዱ፣ የሚበላ ነገር ለመፈለግ ሲሉ ሠፈሩን ማሰስ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው አደረጉት፡፡ ቀስ በቀስም ወደ ሰው ቤት ዘው እያሉ በመግባት መሰራረቅ ያዙ፡፡ እናም ከሠፈሩ ሰው የምሬት ቃላት መሰማት ይጀምራሉ፡፡ ጊዜ ባቡሩ እየነጎደ በሄደ ቁጥር የቡችሎቹ የስርቆት ተግባር አድማሱን እያሰፋ በመምጣቱ፣ የሠፈሩ ሰው ስሞታና ምሬት ይበልጥ እየጨመረ ሄደ፡፡

ጆሮ ለራሱ ባዳ እንደሆነ አይቀርምና የሠፈሩ ሰው በልጆቿ መማረሩንና ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ መግባቱን የቡችሎቹ እናት ሰማች፣ በዚህም በጣም አዘነች፡፡ ልጆቿን ለመምከር ወሰነች፡፡ አንድ ቀንም ሰብስባ እንዲህ አለቻቸው፡-

“ልጆቼ ሆይ! ይኼ ሠፈር ታፍሬና ተከብሬ የኖርኩበት አገር መሆኑን ሁላችሁም ታውቃላችሁ፡፡ ማንም ሰው ስሜን እንዲች ብሎ በክፉ አንስቶት አያውቅም፡፡ አሁን ግን በእናንተ ምክንያት ስሜ እየጎደፈ ነው፡፡ በወጣትነቴ ያልሆነውን በዚህ የእርጅና ዕድሜዬ ለምን ስሜ እንዲጠፋ ታደርጋላችሁ? የሰው ሊጥ ከፍታችሁ እየላሳችሁ አስወቀሳችሁኝ፣ አስወገዛችሁኝ፡፡”

አንዷ ቡችላ ጥያቄ አቀረበች፡- “እማዬ ሙሀቻውን (የሊጥ ዕቃውን) ተከፍቶ ካገኘሁትስ?”

እናትም እንዲህ ስትል መለሰችላት፡- “ተከፍቶ ካገኘሽውማ፣ እስከሚያጎርሱሽ ነው’ንዴ የምጠብቂው?” ብላት እርፍ!..

ይህ የውሻዋ ትርክት ስርቆትን ወይም ሌብነትን የሚያበረታታ ነው፣ እጅግ ሥልታዊ በሆነ መንገድ መቅረቡ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፡፡ እናት ስርቆትን አትደግፍም፣ የማትደግፈው ግን ለስርቆት የተመቻቸ ነገር እስከሌለ ድረስ ብቻ ነው… ሕፃናት ልጆቻችን ስርቆትን እንዲፀየፉትና እንዲርቁት ሊያደርግ በሚገባ መንገድ መታነፅ ሲገባቸው፣ የዚህን ዓይነት ተረቶች እየተነገሯቸው ካደጉ፣ ስርቆትን ቀለል ያለ ጥፋት አድርገው በአዕምሯቸው እንዲሥሉት የማድረግ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ከፍ ሲል ከቀረበው ተረት በተጨማሪ ስርቆትን ፊት ለፊት የሚያበረታቱ ሥነ ቃላዊ አባባሎችም አሉን፣ “ሲሾም ያልበላ፣ ሲሻር ይቆጨዋል”ን የመሳሰሉ፡፡ በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ ስርቆት፣ ከመብላት እኩል ደረጃ ተሰጥቶት ነው የቀረበው፡፡ መብላት ደግሞ በሐበሾች ባህል፣ እስካሁን ድረስ በትንታኔ እንዳየነው፣ ልዩ ቦታና ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገሩ የተሾመ ሰው የመንግሥትና የሕዝብን ሀብት መዝረፍ እንደሚገባው አስምሮ የተናገረው፣ ሐበሾች በወግ ባህላቸው ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጡት ምግብ ጋር በማነፃፀር ሳይሆን፣ ከዚያም በላይ ከፍ በማድረግና እኩል ደረጃ በመስጠት ነው፡፡

ስርቆትን ከመብላት ጋር እኩል ደረጃ በመስጠት ስርቆት ፊት ለፊት ከሚያበረታቱት አባባሎች፣ ሌብነታቸውን እንደ ጀብዱ ወደሚተርኩት እናምራ፡፡ ለዚህም አንድ አብነት እንጥቀስ፣ ለዚያውም የቅርብ ዘመን ከሆኑት አባባሎች፡-

“የካናዳን ስንዴ፣ በላነው በዘዴ፡፡”

በ1977ቱ ድርቅ የወሎ ገበሬ በረሃብ ሲረግፍ፣ ዘግይቶም ቢሆን የዕርዳታ ስንዴ ወደ አካባቢው ጎረፈ፡፡ የተራበው ሰው ቀቅሎም ይሁን ፈጭቶ እንዲበላው የመጣውን የካናዳ አገር ስንዴ፣ በማከፋፈሉ ሒደት ውስጥ ያሉት የመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እያወጡ (እየሰረቁ) ቸበቸቡት፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ግን “የካናዳን ስንዴ፣ በላነው በዘዴ” ብለው የመግጠማቸው ነገር ነው፣ ሰው እንዴት “ሰረቅሁ፣ ዘረፍሁ” ብሎ ይፎክራል? ሰው እንዴት በነውሩ ይኮፈስ፣ ይመፃደቃል?

(እዚህ ላይ አባባሉን የገጠሙት የመንግሥት ሠራተኞቹንና የኃላፊዎቹን ስርቆት የታዘቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሆኑ፣ የግጥሙን ኃይልና ጉልበት ልብ በሉልኝ፡፡ ገጣሚዎቹ፣ በፅናት የሚቃወሙትን የዘራፊነት ባህሪ ለራሳቸው ሰጥተው ነው የአንጀታቸውን መቃጠል በግጥም የገለጹት፡፡)

ለተራበ ሕዝብ የመጣውን ስንዴ ዘርፈው የሸጡት ግለሰቦች ከፍተኛ ትርፍ ዛቁ፡፡ (ወረቱን በስርቆት ላይ የመሠረተ ሰው፣ እንዴት የስንጥቅ ስንጥቅ አያተርፍም?) እናም አንድ አካባቢ ቤት ሠሩ፣ ለተራበ ሕዝብ የመጣውን ስንዴ ሰርቀው፣ ቤት ሠሩ፡፡ በድርጊታቸው የበገኑት ደሴዎች፣ ከስንዴ ስርቆት ለተገነባው የመንግሥት ሠራተኞች ሠፈር ስም አወጡለት፣ “ካናዳ ሠፈር” በማለት፡፡ (ከጥቂት ዓመታት በፊት ለሥራ ጉዳይ መቀሌ በሄድኩበት ወቅት፣ መቀሌዎች በዝርፊያ ለተገነባ አንድ መንደር “ሙስና ሠፈር” የሚል ስያሜ መስጠታቸውን ተረድቻለሁ፡፡)… 

በዚህ ሁሉ መሀል፣ ሐበሾች ከምግብ እጥረትና ከረሃብ ጋር ያላቸውን “እሰጥ አገባ” በተረታቸው፣ በምሳሌያዊ ንግግራቸው፣ በግጥማቸው፣ ወዘተ. እንዴት እየተፈላሰፉበት፣ “እየተቀኙበት”ና እየተቹት ጭምር ዘመናትን እንደ ዘለቁ ልብ በሉልኝ… (በክፍል አሥር እንገናኝ)፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...