- ስልክ እያወራሽ ነበር እንዴ?
- ኧረ በጭራሽ… ምነው?
- ታዲያ ምንድነው ብቻሽን የሚያስቅሽ?
- አይ… በቴሌቪዥኑ የሚቀርበው ነገር ነዋ።
- ምንድነው?
- ድሮ ድሮ ዜና ለመስማት ነበር ቴሌቪዥን የምንከፍተው፡፡
- አሁንስ?
- አሁንማ ቀልዱን ተያይዘውታል… አንተ ግን በደህናህ ነው ዛሬ ያለ ወትሮህ ያመሸኸው?
- ከተቋማችን ሠራተኞች ጋር ቀኑን ሙሉ ኮንፈረንስ ላይ ነበርኩ፣ እሱን እንደ ጨረስኩ ደግሞ ቢሮ መግባት ነበረብኝ።
- አንተም እዚያው ላይ ነዋ የዋልከው?
- እዚያው ላይ ማለት?
- ኮንፈረንሶች ተካሄዱ የሚል ዜና ነበር ለብቻዬ ሲያስቀኝ የነበረው፣ አንተም እዚያ ኮንፈረንስ ላይ ነበርክ ማለቴ ነው።
- ምንድነው ታዲያ ያሳቀሽ… ኮንፈረንስ ተካሄደ መባሉ ነው ያሳቀሽ?
- የኮንፈረንሱ መሪ ቃሉ ነው ያሳቀኝ።
- መሪ ቃሉ ምን ይላል?
- ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን የሚል ነው።
- ታዲያ ምንድነው ያሳቀሽ?
- ሁለቱም።
- ሁለቱም ማለት?
- ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር የሚለውም፣ ሕዝባችንን እናሻግራለን የሚለውም፣ ኧረ ሦስተኛም አለ…
- እ… ሦስተኛው ምንድነው?
- መሪ ቃሉ ራሱ ተሻጋሪ መሆኑ።
- ተሻጋሪ ማለት?
- ጊዜ አይገድበውም ማለቴ ነው።
- እንዴት?
- ይህንኑ መሪ ቃል ባለፈው ዓመትም ሰምቼው ነበር።
- ታዲያ ብትሰሚውስ? ችግር አለው?
- እኔ መስማቴ ችግር የለውም፣ ግን ደግሞ…
- እ… ግን ድግሞ… ምን?
- ፈተናውም፣ መሪ ቃሉም መሳ ለመሳ መቀጠላቸው ትንሽ አያስገርምም? እንዲያው አያስተዛዝብም?
- ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ መፍትሔ ሊያገኝ እንደማይችል መዘንጋት የለበትም።
- በፈተና ላይ ፈተና መደራረቡስ መዘንጋት አለበት?
- ፈተናዎች የሚያፀኑን መሆኑም መዘንጋት የለበትም።
- እሱ ደግሞ ቤታችሁ ስትሆኑ የምትጠቀሙት መሪ ቃል ነው?
- ምኑ?
- መዘንጋት የለበትም የምትለው? ይልቅ እስኪ ልጠይቅህ?
- እሺ… ጠይቂኝ?
- ባለፈው ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በግጭት ምክንያት ተዘጋ ተብሎ ጤፍ ሰባት ሺሕ ብር መግባቱን ታስታውሳለህ?
- አዎ።
- አሁን ግን መንገዱ ተከፍቷል።
- አዎ፣ መከላከያ ከገባ በኋላ መንገዱ ተከፍቷል።
- የጤፍ ዋጋ ግን ሰባት ሺሕ ሆኖ ቀረ… አይደለም?
- አዎ፣ ዋጋው ከወጣ በኋላ አልወረደም።
- መንግሥት ፈተናውን ወደ ዕድል እቀይራለሁ እያለ ይምላል፣ መሪ ቃል ያወጣል እንጂ ፈተናውን ወደ ዕድል የሚቀይረው ሌላ ነው ማለት ነው?
- ሌላው ማለት… ማነው?
- ነጋዴው፡፡
- ነጋዴውም ኦኮ የማኅበረሰቡ አካል ነው፣ ይኼ መዘንጋት የለበትም።
- የከተማው ነዋሪ በኑሮ ውድነት ፈተና እየተሰቃየ ትምህርት ቤቶች መቶ ፐርሰንት ዋጋ መጨመራቸውስ… በዚህ ላይ ምንም አትሉም?
- ምን እንላለን?
- ወይ ፈተና ነው በሉ፣ ወይም ዕድል ነው በሉ፣ ካልሆነ ደግሞ እነሱም የማኅበረሰቡ አካል ናቸው በሉ።
- በእርግጥ እነሱም የማኅበረሰቡ አካል ናቸው፣ ግን…
- እ… ግን ምን?
- የምንከተለው የነፃ ገበያ መር ኢኮኖሚ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
- መዘንጋት የለበትም?
- አዎ፣ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ መርህ እየተከተልን ዋጋ አትጨምሩ ማለት አንችልም፣ ይህ መዘንጋት የለበትም።
- እንደዚያ ከሆነ እናንተም ተውታ?
- ምኑን?
- መዘንጋት የለበትም እያላችሁ ሕዝቡን አታስታውሱት… ተውት፡፡
- ምኑን ነው የምንተወው?
- መሪ ቃሉን!