በአበበ ፍቅር
ከተሽከርካሪዎች የሚወጡ በካይ ጋዞችን መቆጣጠር የሚያስችል ሕግ ሊወጣ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ሕግ ካልወጣላቸው ከአሮጌ ተሽከርካሪዎች የሚወጣ ጭስ እስካሁን ድረስ በትክክል የሚታወቅ ሕግ የሌላቸው በመሆኑ፣ ባለሥልጣኑ ሕግ ለማውጣት ሙከራ እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን ሕጉ መውጣት የነበረበት በፌዴራል ደረጃ ቢሆንም፣ እዚያ ስላልወጣ እኛ ዝም ብለን መቀመጥ ሳይሆን፣ ‹‹ከሚመለከታቸው ከትራንስፖርት ኤጀንሲ፣ ከአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመሆን በመመርያ የሚሆን ድራፍት በማውጣት እናቀርባለን፤›› ብለዋል፡፡
‹‹እኛ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የለንም፣ ነገር ግን ለሕግ የሚሆኑ ሐሳቦችን የማመንጨትና ሠርቶ የማቅረብ ኃላፊነት አለብን፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለዋል፡፡
በዚህ መልክ ‹‹ሕግ ያልወጣላቸውን እናወጣለን፤›› ያሉት አቶ ዲዳ፣ ሕግ የወጣላቸውን በተሰጣቸው ደረጃ በታች ስለመሆናቸው ወይም ሕጉን በትክክል እየተተገበሩ መሆናቸውን በክትትልና በቁጥጥር እያዩና አቅጣጫ እያስቀመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሕግ የወጣላቸው ከፋብሪካ የሚወጡ ቆሻሻዎችና በካይ ነገሮች ከተፈቀደለት በላይ የሚያመነጭ ከሆነ ፋብሪካው ይታሸጋል፣ ሲታሸግም ለሠራተኞች ደመወዝ የመከፈል ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ሌሊት ላይ ሰዎች በሰላም እንዳይተኙ ከፍተኛ ድምፅን በማውጣት አካባቢን የሚረብሹ በርካታ ቤቶችን በዳሰሰ ወቅት እንዳገኘ ገልጸዋል፡፡ በሁለት ወራት ውስጥ በሁሉም ክፍለ ከተማ በ423 ቤቶች ላይ በተደረገ ዳሰሳም 208ቱ ከሚፈቀደው በላይ ከሌሊቱ 5፡00 ሰዓት ከፍተኛ የድምፅ ብክለትን ሲያስከትሉ መገኘታቸውን ዋና ሥራ አስያኪጁ ተናግረዋል፡፡
በዚህም የታሸጉ ቤቶች መኖራቸውን አክለዋል፡፡ የአየር ብክለትን የሚያባብሱ በርካታ ነገሮች አሉ ያሉት አቶ ዲዳ፣ ‹‹በዓለም ላይ ግን በጣም እያስቸገረ ያለው የፕላስቲክ ብክለት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በመሆኑም የዓለም ሁሉ ችግር የሆነውን የፕላስቲክ ብክለት እንግታ፣ መፍትሔንም አናምጣ በማለት እያከበሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፕላስቲከ ብክለትን ለመቆጣጠር እንደ አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በፕላስቲከ ጠርሙሶች የተሞላ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ላይ ግን በተደረገ እንቅስቃሴ ፕላስቲኮችን ሰብስቦ ወደ ሌላ ቁሳቁስ በመቀየርና ወደ ውጭ በመላክ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በዓለም ለ50ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም አካባቢ ጥበቃ ከግንቦት 25 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በተለያዩ ዝግቶች እየተከበረ ነው፡፡