Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ከዓመታት በፊት አሶሼትድ ፕሬስ ከወደ አሜሪካ ያሰማን ዘግናኝ ዜና ለዛሬው ገጠመኜ መነሻ ሆኖኛል፡፡ የኒውዮርክ ፖሊስ ባልደረባ የሆነ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት የሰው ሥጋ ለመብላት በማቀዱ ሰሞኑን ፍርድ ቤት ጥፋተኛ እንዳለው መዘገቡን አስታውሳለሁ፡፡ ግለሰቡ ጥፋተኛ ሊባል የቻለው በኢንተርኔት አማካይነት ከሌላ ግለሰብ ጋር ባደረገው ተደጋጋሚ ውይይት፣ ወጣት ሴቶችን ካገተ በኋላ ገድሏቸው ሥጋቸውን ጠብሶ ለመብላት በማሴሩ ነው፡፡ ይህ ሴራ ሊጋለጥ የቻለው ደግሞ በሚስቱ አማካይነት ነው፡፡ ሚስቱ በኢንተርኔት ከሌላ ሰው ጋር የሚያደርገውን ውይይት ኮምፒዩተር ላይ ካየች በኋላ ልጇን አንጠልጥላ ከቤቷ ትሸሻለች፡፡ ከዚያም የባሏን አደገኛ አዝማሚያ ለኤፍቢአይ በማሳወቋ በቁጥጥር ሥር ይውላል፡፡

የ28 ዓመት ወጣት የሆነው የኒውዮርክ ፖሊስ ባልደረባ ጂልቤርቶ ቫል ጠበቃ ግለሰቦች በማሰባቸው ምክንያት መከሰስ የለባቸውም ብለው ቢከራከሩም፣ ዓቃቤ ሕግ ግን ዳኞች ተከሳሹ ሊፈጽማቸው የነበሩ አደገኛ ድርጊቶች በማስረጃ ስለቀረቡላቸው ጥፋተኛ ነው ማለታቸውም በዘገባው ተካቶ ነበር፡፡ የሕግ ባለሙያዎችም አንድ ሰው አንድን ነገር በማሰቡ ወይም በማቀዱ ሊከሰስ አይገባውም የሚለውን አስተያየት ተቃውመዋል፡፡ በማሰብ ብቻ የተወሰነ ወንጀል ሳይሆን ወደ ተግባር ሊለወጥ የሚችል ወንጀል ነው ማለታቸውም እንዲሁ፡፡

የተከሳሹ ጠበቃ በሐሳብ ደረጃ ላይ የነበረ ጉዳይ በመሆኑ ግለሰቡ ሊከሰስ አይገባም ቢሉም፣ ከራሱ ኮምፒዩተር የኢንተርኔት ውይይት የተገኙበት ማስረጃዎች ግን አስደንጋጭ ነበሩ፡፡ የማይታወቅ ከተባለው ሰው ጋር ባደረገው የኢንተርኔት ውይይት፣ የልጁን እናት ጨምሮ ስድስት ሴቶችን በማገት፣ አሰቃይቶ በመግደልና ከዚያም በኋላ በመጥበሻ ሥጋቸውን በመጥበስ ለመብላት ማቀዱን የተገኘው መረጃ ላይ ሠፍሮ ነበር፡፡ ይህንን አደገኛ ዕቅዱን የደረሰችበት ሚስት ማስረጃዎቹን በሙሉ ለኤፍቢአይ በመስጠቷ ሴራው እንደከሸፈበት ዜናው በስፋት ማተቱ አይረሳኝም፡፡

ይኼው ግለሰብ ከሌላኛው ሰው ጋር ባደረገው ሌላ የኢንተርኔት ውይይት ወጣት ሴቶችን ካገተ በኋላ ከእነ ሕይወታቸው እንደ ዶሮ አሮስቶ ማድረግ እንደሚፈልግ ገልጾ፣ በተለይ አንዲት የሚያውቃት ለብቻዋ የምትኖር ሴት ለእሱ ቀላል ዒላማ እንደሆነችና እሷን ከእነ ሕይወቷ መጥበስና ስትሰቃይ ማየት እንደሚያስደስተው መናገሩ በማስረጃነት ቀርቦበት ነበር፡፡ ሴቶቹን ለመጥበስ የወይራ ዘይትና ዝርግ መጥበሻ ተመራጭ መሆኑን በመግለጽ ጭምር፡፡ በተለይ ደግሞ የልጃገረድ ሥጋ መብላት እንዴት እንደሚያስጎመጀው መናገሩም ተዘርዝሯል፡፡ ሚስቱ ይህንን ሁሉ ነገር ነው ለፍርድ ቤቱ እያለቀሰች የተናገረችው፡፡ በእርግጥ ኤፍቢአይም የሰውየውን ዕቅድ ከኢንተርኔት ዘርግፎ አውጥቶ ለዓቃቤ ሕግ እንደ ማስረጃ አቅርቦ ነበር፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ዘግናኝ የሆነ ዜና በምዕራቡ ዓለም አልፎ አልፎ ስለሚሰማ እነሱን እንዴት እንደሚያደርጋቸው ለእነሱ ትተን፣ ለእኛ ግን እጅግ ዘግናኝና አስደንጋጭ ነው፡፡ የተለያዩ የእምነት ሥርዓቶችን ብንከተልም እኛ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዓይነት የአውሬነት ባህሪያትን ፈጽሞ ለማስተናገድ ዝግጁ አይደለንም፡፡ ነገር ግን ዓለም በዚህ ዘመን ወደ አንድ መንደርነት እየተለወጠች በመሆኑ፣ በተለይ ከምዕራቡ ዓለም እንደወረዱ የምንቀበላቸው ነገሮች ደግሞ እየበዙ ናቸው፡፡ እነዚህ የባህል ወረራ አካል የሆኑ ችግሮች በተለይ በዘመን አመጣሹ ቲክቶክ አማካይነት ወጣቶቻችንን እየከበቡ ናቸው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከወዳጆቼ ጋር ስነጋገር አንዳንድ አሳሳቢ ችግሮቻችን የምዕራቡ ዓለም ተፅዕኖ ውጤት መሆናቸው አግባብቶናል፡፡ ከእነዚህ መካከል ልቅ ወሲብ፣ ግብረ ሰዶም፣ አደንዛዥ ዕፅ፣ ከመጠን ያለፈ አልኮል፣ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹በምዕራቡ ዓለም ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሙሉ ከበስተጀርባቸው እነዚህ የረከሱ ድርጊቶችን ያነገቡ ናቸው…›› ያለን አሜሪካ የተማረ ጓደኛችን፣ ‹‹ሰውን እያሰቃዩ መግደል፣ የሰው ፊት ላይ አሲድ መድፋት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሰው አግቶ ገንዘብ መጠየቅ፣ ወዘተ የሥነ ልቡና ቀውስ ያለባቸው ሰዎች ድርጊት ነው…›› አለን፡፡ ‹‹ብዙዎቹን የምዕራባውያን ፊልሞች ብትመለከቱ እነዚህን ሁሉ ቀውሶች ታያላችሁ፡፡ አሁን ደግሞ በቲክቶክ አማካይነት የተለያዩ ወንጀሎች ከምዕራብ አገሮች ወደ አገራችን እየተሸጋገሩ በመሆናቸው ካልተቆጣጠርናቸው ውጤቱ አደገኛ ነው…›› በማለት አስረዳን፡፡

በቅርቡ ጎረቤት ለቅሶ ለመድረስ ሄጄ ከማውቀው የሠፈሬ ሰው ጋር ጎን ለጎን ተቀምጠን በለሆሳስ ወሬ እንጀምራለን፡፡ ይህ የሦስት ልጆች አባት የሆነ ሰው ስለአገር ወቅታዊ ጉዳይ አንስቶ ትንተና ሲጀምር፣ እኔ ደግሞ የሚያወራው ሁሉ ከራሱ አዕምሮ የፈለቀ ሳይሆን ከማኅበራዊ የትስስር ገጾች የለቃቀመው እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ ፌስቡክና ቲክቶክ ላይ የሚነገሩ ቀልዶችን ሳይቀር እየደባለቀ ቁምነገሩን ለማዋዛት ሲሞክር፣ የሚነግረኝ ነገር ምንጩ ምን እንደሆነ ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ እሱ ግን እንደ ዘመኑ የፖለቲካ ተንታኞች ድርቅ ብሎ የራሱ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ በመሀል ግን የቲክቶክን ነገር ሳነሳለት እጁን ጭንቅላቱ ላይ ጭኖ፣ ‹‹እኔም ልጆቼም ቲክቶክ ላይ ተጥደን ሱሰኞች ሆነን ተቸግሬያለሁ…›› እያለ በመንገፍገፍ ነግሮኝ፣ ‹‹እኔስ ዕድሜዬ እየገፋ ነው፣ ነገር ግን የልጆቼ ነገር እያሳሰበኝ ነው…›› ብሎ በጭንቀት ሲተክዝ ስንቱ ይሆን በቲክቶክ ሱስ እየናወዘ ያለው ብዬ እኔም ሐሳብ ገባኝ፡፡

በእርግጥም በየቢሮው፣ በየካፌው፣ በየቤቱ፣ በየትምህርት ቤቱ፣ ወዘተ የቲክቶክ ሱሰኞች ከመጠን በላይ በዝተዋል፡፡ ቲክቶክን ለደህና ጉዳይ ብንጠቀምበት ትልቅ ጥቅም የሚገኝበትን ያህል፣ ለአጓጉል ዓላማ ካዋልነው ግን አደጋው ከምናስበው በላይ ይሆናል፡፡ የሰው ሥጋ ለመብላት ሲያቅድ ስለነበረው ሰው እያሰብኩ ሳለሁ፣ በሌላው የዓለም ጥግ የሚፈበረከው አስፋሪ ድርጊት ነገ ምን ይዞብን ይመጣ ይሆን እያልኩ ለአገራችንም ለሕዝባችንም ሠጋሁ፡፡ በበኩሌ በመልካም ሥነ ምግባር ተኮትኩተው ያደጉ ልበ ብርሃን ኢትዮጵያዊ ታዳጊዎቻችን፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ከጥፋት ይታደጋሉ በማለት ልቤ በተስፋ ይሞላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትውልዱን በአልባሌ ነገሮች እያከሰሩ አገር ለማጥፋት የሚያሰሩ ተንኮለኞች ጉዳይም ያሳስበኛል፡፡ በዚህ መሀል ግን ትውልዱ የማይወጣበት አዘቅት ውስጥ እንዳይገባ መላ እንፈልግ እላለሁ፡፡

(ናትናኤል አራርሳ፣ ከላፍቶ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...