Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉለኢኮኖሚያችን ጤና ማጣት የሦስቱ ካቢኔዎች አንፃራዊ አስተዋጽኦና የባንዳዎች ሚና

ለኢኮኖሚያችን ጤና ማጣት የሦስቱ ካቢኔዎች አንፃራዊ አስተዋጽኦና የባንዳዎች ሚና

ቀን:

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)

መንደርደሪያ

ከሰሞኑ በኢኮኖሚያችን ይዘት ዙሪያ የተለያዩ መግለጫዎች፣ በተለይም ኢኮኖሚው ስለመታመሙ አመላካች መልዕክቶች በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ቀርበዋል፡፡ የመንግሥት ሚዲያዎች የዘጠኝ ወሩን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይዘት፣ በተለይም የፌዴራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ አፈጻጸም የሚገመግመው የመደበኛውን ካቢኔ አባላት ስብሰባ ድምዳሜን ሊያሳውቁን ሞክረዋል፡፡ ኢመደበኛ ካቢኔዎች (ወደኋላ መለስ ብዬ የምገልጻቸው የግርዶሽና የውጭ ኃይሉ ሥውር ካቢኔ ማለት ነው) እና ከእነሱ ውጪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ገምጋሚዎችና ተንታኞች ደግሞ፣ የኢኮኖሚውን ወቅታዊ ይዘት ከራሳቸው መረጃና ምልከታ አንፃር ትንተና በማድረግ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስና የኅትመት ሚዲያዎች ላይ አስተያየትና ምክረ ሐሳብ ሲያቀርቡም ይስተዋላል፡፡

በግሉ ዘርፍ የሚዲያ አካላትም በወቅቱ የኢኮኖሚያችን ይዘት ላይ፣ ከመደበኛው ካቤኔ ስብሰባዎች ትርክት አንፃር፣ በኤሌክትሮኒክስም ሆነ በኅትመት ውጤቶች በርካታ  ዘገባዎችና መጣጥፎች ቀርበዋል፡፡ በወዲያኛው ሳምንት መጨረሻ በሪፖርተርና በፎርቹን ጋዜጦች ላይ የወጡ የኢኮኖሚውን ጤንነት መጓደል አመላካች የሆኑ ጽሑፎች ነበሩ፡፡

ይህ ጽሑፍ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ሚዲያዎች ላይ የተነሱ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ዳሶ፣ በተለያዩ መድረኮችም ስለኢኮኖሚው የሚባለውን በመቃኘት አጭር የማስገንዘቢያ መልዕክት ይዞ ቀርቧል፡፡ በተለይ የውጭ ኃይሎች እኛን በፖለቲካ ጉዳዮች እርስ በርስ እያጋጩ ለዘመናት በወረራ ያላገኙትን ኢኮኖሚያዊ ይዞታና ጠቀሜታ እንዴት እያሳኩ እንዳሉ፣ ለዚህም የኢኮኖሚ አጥፊዎችን (ባንዳዎችን) እንዴት እንደሚጠቀሙባቸው ከግዙፍ ተከፋይነታቸው ጋር አጎዳኝቶ ጽሑፉ መረጃዎችን ለአንባብያን አቅርቧል፡፡

የኢኮኖሚ ጤንነት መገለጫዎች

በማክሮ ኢኮኖሚክስ አስተምህሮ መሠረት የኢኮኖሚ ጤንነት ከዋጋ ግሽበት፣ ከሥራ አጥነት፣ ከንግድና ከመንግሥት በጀት ሚዛን መዛባት፣ ከኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ ከዕድገት ጉድለት፣ ከሀብትና ገቢ ድልድልና ሥርጭት መዛባት መለኪያዎችና መመዘኛዎች አንፃር ሊጠናና ሊመረመር ይችላል፡፡

በእነዚህና በሌሎች ተጓዳኝ ሆነው በሚጠቀሱ መለኪያዎችና መመዘኛዎች፣ የፌዴራል መንግሥቱ መደበኛ ካቢኔ የሰሞነኛው ስብሰባ ከሞላ ጎደል ኢኮኖሚያችን ጤናማ ይመስላል የሚል ዝንባሌ ያለው ድምዳሜ ላይ የደረሰ እንደሚመስል የመንግሥት ሚዲያ ዘገባዎች ያመላክታሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ጤናማ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚያችን ችግር ውስጥ ነው ያለው የሚል እንድምታ ያላቸውን መረጃዎችና ትንታኔዎችን ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ተቺዎችም ጠበቅ አድርገው ኢኮኖሚው ‹‹ቀውስ›› ውስጥ ነው ያለው ብለው ሲሞግቱ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ማጣቀሻ አድርገው ከሚያቀርቧቸው መለኪያዎችና መረጃዎች መሀል ለምሳሌ በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው የዋጋ ግሽበት ይዘትና መጠን ነው፡፡

የመደበኛው ካቢኔ አባላት ግሽበቱን አለሳልሰው ሊያቀርቡት ቢሞክሩም፣ ኢመደበኛ የካቢኔ አባላትና ሌሎች ገለልተኛ ሙያተኞች ደግሞ የሚያለሳልሱት ሳይሆን፣ በጣም ከፍተኛ የሆነና አገርና መንግሥትን ሊያናጋ በሚችል ደረጃ ደርሷል ብለው ይሞግታሉ፡፡ ግሽበቱ በጣም ከፍተኛ (ሃይፐር ኢንፊሌሽን) ደረጃ የደረሰ እንደሆነና ይህም የኢኮኖሚ ቀውስ ክስተት ዋዜማን ማመላከቻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ግሽበቱ ተከማችቶ ከአንድ መቶ ፐርሰንት በላይ ደርሷል ከሚል መረጃ ላይ ተነስተው ‹‹ሃይፐር›› ግሽበት ላይ ስለመድረሱ ሞጋቾቹ  ሲሞግቱና ጉዳዩን መንግሥት ዕውቅና እንዲሰጠው ሲገፋፉ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታችን በዚህ ደረጃ  አልደረሰም፣ ሊገለጽም አይገባም ብለው ለመሞገት የሰጡትን ቃለ መጠይቅ በሳምንቱ መጨረሻ ግንቦት 12 እና 13 ቀን 2015 ዓ.ም. የወጡ ጋዜጦች አስነብበውናል፡፡

እኔ በዚህ ቴክኒካዊ በሆነ ‹‹ሃይፐር›› ግሽበት ደረጃ ደርሷል አልደረሰም ከሚል እሰጥ አገባ ውስጥ መግባቴን ገታ አድርጌ፣ ላለፉት አሠርት ዓመታት ኢኮኖሚያችን ትኩረት አጥቶ፣ ፖለቲከኞቻችን በፖለቲካ እሰጥ አገባ ዴሞክራሲ በሚባል ኳስ ጨዋታ ኢኮኖሚውን እየበሉ፣ እያቀጨጩና እየገደሉት ነው የምለውን ማስጠንቀቂያዬን በድጋሚ በተከታዩ ክፍል በማስገንዘቢያነት ካቀረብኩ በኋላ፣ በተለይ በፖለቲካ ውስጥ በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሸርሽሮ ገብቶ የኢኮኖሚ ፍላጎቱንና ጥቅሙን በማስጠበቅ ላይ ስላለው የውጭ ኃይሎች እንቅስቃሴና መሣሪያ ባንዳዎች መሰሪ ሥራ፣ ኢትዮጵያውያን ነቅተው ያውቁ ዘንድ ማብራሪያ አቅርቤያለሁ፡፡

የኢኮኖሚያችን ትኩረት ማጣት የጊዜ ፍሰት

እኔ ባለፉት አሠርት ዓመታት ውስጥ የብልፅግና መራሹ መንግሥት ከመከሰቱም አስቀድሞ፣ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትኩረት ተነፍጎታል፣ እየታመመ ነው፣ ካላከምነው የማንወጣው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምስቅልቅልና ቀውስ ውስጥ እንወድቃለን ብዬ ካለኝ የትምህርት መሠረትና መረጃ፣ የማማከር ሥራ ጥናታዊ ግኝት፣ ወዘተ. አኳያ በተለያዩ መድረኮች ጽሑፎችን በማቅረብ፣ መጻሕፍትን አዘጋጅቼ በማሳተምና ለአንባብያን በማቅረብ ግንዛቤ በመፍጠር የማንቂያ ደወል ለመደወል ሞክሬያለሁ፡፡

ኢኮኖሚያችን ከውስጣዊ ይዘቱ ጤና ማጣቱ ጋር ተዳብሎ ሁለንተናው ለውጭ ኃይሎች ፍላጎት ማሟያነት እየዋለ መምጣቱን፣ አለፍ ብሎም በእነዚህ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እየዋለ ስለመሆኑ በመጽሐፍ ደረጃ ጭምር ጽፌ ያቀረብኩት ነፍሱን ይማርና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት ባለበት ጊዜ ነበር፡፡ ይኸው ትኩረት ያላገኘው የኢኮኖሚያችን ጉዳይ፣ ዛሬ ላይ መጥፎ ሁኔታና ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል፡፡ የችግሩ ዋና መሠረቱ የተዛባ የፖለቲከኞቻችን የቅደም ተከተል ዕሳቤ ነው፡፡

ፖለቲከኞቻችን ያኔም ሆነ ዛሬ የሚያስቡት የኢኮኖሚ ችግሮቻችን የሚፈቱት በቅድሚያ ፖለቲካው ሲስተካከልና  ዴሞክራሲ ሲሰፍን ነው የሚል የተዛባ አንድምታ ያለው ዕሳቤን ሲያቀነቅኑ አዳምጣለሁ፣ እመለከታለሁም፡፡ በ2007 ዓ.ም. በእንግሊዝኛ በታተመው መጽሐፌ ውስጥ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጭምር ያለው ዕሳቤ የተዛባና መስተካከል ያለበት ስለመሆኑ አመላክቻአለሁ፡፡ የመንግሥት ትኩረት በቅድሚያ ኢኮኖሚው ላይ መሆን እንደሚገባው፣ ኢኮኖሚው በዘላቂነት በዜጎች በሚመራ የዕድገትና ብልፅግና ጎዳና ላይ እንዲገኝ፣ በዚህ ሒደትም ሲጠነክርና ሲጎለብት ፖለቲካውና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደሩ የተቃናና ውጤታማ ሊሆን እንደሚችልም በመጽሐፌ ውስጥ አብራርቻለሁ፡፡

ፖለቲካና ዴሞክራሲ በቅድሚያ መስተካከል አለበት የሚለው የተዛባው ኢሕአዴጋዊ ዕሳቤና ተጓዳኝ እንቅስቃሴዎች ግን ከለውጡም በኋላ ሳይስተካከሉ ቀጥለው፣ ዛሬ ወደ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ምስቅልቅልና ማኅበራዊ ቀውሶች ውስጥ እየከተቱን መጥተዋል፡፡

ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ በኋላም በ2012 ዓ.ም. በጻፍኩት ‹‹ኢኮኖሚው ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› በሚለው መጽሐፌ ውስጥ ይህንኑ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት የሚያሳጣ የፖለቲካ አካሄድ፣ ‹‹ዴሞክራሲን እንደ ኳስ፣ ኢትዮጵያ እንደ ኳስ ሜዳ›› በሚል ንዑስ ክፍል ማብራሪያ አቅርቤበታለሁ፡፡ በዚሁ ንዑስ ክፍል የአገሪቱ ኢኮኖሚ ምኅዳር እየተበላሸ እንደሆነ ለማሳወቅ ጥሬያለሁ፡፡ ይህን ላድርግ እንጂ የኢኮኖሚው ጉዳይ መሻሻል አለማሳየቱ ብቻ ሳይሆን፣ በውጭ ኃይሎች ሴራ ቀስ በቀስ ከዜጎች የኢኮኖሚ ልማት መሪነት እጅ እንዲወጣ እየተደረገ እንዳለ በመገንዘቤ፣ በተለያዩ ቃለ መጠይቆች ወቅትና መጣጥፎች ስለሴራው ለማሳወቅ ሞክሬያለሁ፡፡

በተለይ በኢኮኖሚ ባንዳዎች መሣሪያነት በሚተገበር የውጭ ኃይሎች ስትራቴጂ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሥውር ከርቀት በሚንቀሳቀሱ ቅኝ ገዥዎች (በእንግሊዝኛ ኮሎኒያሊስትስ ኢን አብሰንሺያ ብዬ በምገልጸው) እጅ ውስጥ እየገባ እንዳለ የሚጠቁም ጽሑፍ በ2013 ዓ.ም. ‹‹ኮርፖራቶክራሲ…›› በሚል ርዕስ በአሳተምኩት መጽሐፍ ውስጥ ማብራሪያ አቅርቤያለሁ፡፡ ማብራሪያው ከ28 ዓመታት በፊት ጽፌ በኅትመት ሰነዶች ውስጥ የሚገኘውን ኢትዮጵያ በርቀት የሥውር ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት (ኮሎኒያሊዝም ኢን አበሰንሺያ) አራማጆች ወጥመድ ውስጥ እየገባች ነው የሚለውን ትምህርታዊ ምልከታዬና መልዕክቴ ዕውን እየሆነ ስለመምጣቱ በሚያስረዳ ትንታኔም የተሞላ ነበር፡፡ የ2012 እና የ2013 ዓ.ም. መጻሕፍቶቼ በለገሃር ጃፋር፣ በአራት ኪሎ እነሆ መጽሐፍት መደብር ስለሚገኙ የራስዎ አድርገው ለተጨማሪ ማብራሪያ ግኝት አንብቧቸው፡፡

ከላይ ለማመላከት የሞከርኩትን ጥረቴንና ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ያደረጉትንና የሚያደርጉትን ጥረትም ሳጤን ለምን ዛሬ ላይ ጤንነቱ በተጓደለ፣ በችግር አረንቋ ውስጥ በወደቀ  ኢኮኖሚ ውስጥ ተዘፍቀን እንገኛለን ብዬ መጠየቄን ማቆም እንደሌለብኝ ተገንዝቤአለሁ፡፡

በእርግጥ በቅርቡ ባሳለፍነው የጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት ጊዜ በብዙ ሚዲያ አውታሮች ላይ ለቃለ መጠይቅ ቀርቤ በሰጠኋቸው ምላሾች፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከገጠመን ግጭትና የዜጎች መፈናቀል፣ በተለይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከገባንበት ጦርነት አንፃር የኢኮኖሚ ይዘታችን መጥፎ እንዳልሆነ የገለጽኩበትም ጊዜ ነበር፡፡ በጦርነትና በግጭቶች ወቅት የሚታዩ የኢኮኖሚ ችግሮች በተለይም የዋጋ ግሽበቱ፣ የሥራ አጥነቱ፣ ያለመረጋጋቱ፣ የመንግሥት በጀትና የንግድ ሚዛኑ መዛባት፣ ወዘተ.  ጦርነቱ ሲረግብ ይስተካከላል የሚል የተስፋ ምላሽ በቃለ መጠይቆቹ ወቅት እንድሰጥ አድርገውኛል፡፡ ይሁን እንጂ ከጦርነቱ ረገብ ማለት በኋላ፣ በተለይም ዛሬ ተስፋዬ ተሟጦ አልቋል ባልልም፣ ኢኮኖሚያችን ግን በከፍተኛ ደረጃ ስለመታመሙ ምልክቶቹ እየጎለበቱ መምጣታቸውን እያስተዋልኩ ሲሆን፣ ችግሮቹም ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳሰቡኝ ነው፡፡

የዋጋ ግሽበቱ በክምችትም ሆነ በወርኃዊ ይዘቱ በጣም ከፍተኛና ለኢኮኖሚ ቀውስ የሚዳርግ (ሃይፐር ኢንፍሌሽን) ደረጃ ደርሷል የሚለው አከራካሪ ቢሆንም፣ በጥቅሉ ግን በጣም ከፍተኛና ለኢትዮጵያውያን በተለይም በውጭ ኃይሎች ተካፋይ ላልሆኑና ተቀጥረው ለሚሠሩ ዜጎች ኑሮን መራርና አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ድብቅ ሥራ አጥነቱ ከመጎልበቱ በተጨማሪ የሥራ አጥ ቁጥር እየጨመረና ለዜጎች ኑሮ በማናቸውም ደረጃ አስቸጋሪነቱ እየጎለበት መጥቷል፡፡ ይህ በአንዳንድ አካባቢ ዲግሪ የያዙ፣ የተማሩ ግን በቡድን የተደረጁ ዘራፊዎችና ነጣቂዎች እንዲከሰቱ እያደረገ ስለመሆኑ ከኅትመትም ሆነ ከኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዘገባዎች መረዳት ይቻላል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ማኅበራዊ ቀውስን እያስከተለ እንደመጣ አመላካች ኩነቶች ይስተዋላሉ፡፡ የተማረው ወጣት በተናጠልም ሆነ በቡድን ዘረፋንና ንጥቂያን ተያይዞታል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ባለመኪኖች ለአፍታ በትራፊክ መብራት ሆነ በሌላ ምክንያት አነዳዳቸውን ቀዝቀዝ ባደረጉበት ወቅት እንኳ መዘረፍ የተለመደ ክስተት እየሆነ መጥቷል፡፡

በማምረት፣ በሥርጭትና በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በርካታ ሕገወጥነቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ አምራቹ ገበሬና መንግሥት ተጋግዘው ቢያንስ የምግብ እህሎች አቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር ቢሠሩም፣ ለምሳሌ ስንዴ በብዛት ተመርቶ ለኤክስፖርት ጭምር የሚሆን ቢመረትም፣ በአገር ውስጥ ዋጋው ንሮ የሕዝብን ሰቆቃና እሮሮ አስከትሏል፡፡ ከስንዴ የሚመረቱ የዳቦ፣ ማካሮኒና መሰል ምርቶችም ዋጋ አሻቅቦ የኢኮኖሚ ቀውስ ይከሰት ዘንድ የሚሠሩ እኩይ ሥራዎች እንዳሉ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡

በእርሻ ምርቶችና በሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች ዙሪያ የዋጋ ግሽበቱ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን፣ በአገር ደረጃም ንግድና በጀት ሚዛን መዛባቶች ቀውስ እንዳያስከትሉ የሚደረጉ ሸቀጥ ተኮር ድጎማዎችና ተጓዳኝ የዋጋ ፖሊሲ ዕርምጃዎች ተገቢውንና የሚጠበቅን ውጤት ከማስገኘት ይልቅ፣ ኢኮኖሚውን ወደ ባሰ አጣብቂኝ ውስጥ ሲከቱትም እየተስተዋለ ነው፡፡

ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ግዥ ላይም ኢኮኖሚው ባልተገባ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ ዶላር እንደ ብር መገበያያ ሆኖ በኢኮኖሚው ውስጥ ቢሠራጭም፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ፣ መንግሥትን በቁጥጥራቸው ውስጥ ሊያስገቡ በዓለም የገንዘብ ተቋማት በኩል የሚሠሩት የውጭ ኃይሎች ዕቅዳቸው እየሰመረላቸው እንደመጣ የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ አካሄዳቸው በኢኮኖሚው ውስጥ ቀውስ መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ በፖለቲካው ረገድ በሰሜኑ አገራችን በኩል አለን የሚሉትን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከብር መንግሥት እሰከ ማግኘት ድረስ የሚዘልቅ የግልበጣ ሴራ ያለው ሥራ የሚሠሩ ይመስላል፡፡ አብዛኛውንም ሕዝብ የውጮቹን ቅዱስ፣ ለጋሾች፣ ለችግራችን ደራሾች፣ የእኛ ፖለቲከኞችን በተለይም መንግሥትን ጥፋተኛ፣ ኢኮኖሚውን ለመምራት  አቅም የለሽ እንደሆነ አድርጎ እንዲያይ በአሉታዊ ዕሳቤ ውስጥ እንዲዋኝ እያደረጉትም ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሆይ እንንቃ፣ የውጭ ኃይሎች እንደ ጆን ፐርኪንስ አገላለጽ የኮርፖራቶክራሲው አካላትና በእነሱ በባንዳነት ተመልምለው በስለላም ሆነ በሰርጎ ገብነት በሚሠሩ ዜጎች አማካይነት ለዘመናት በጦርነትና በወረራ ያላገኟትን አገር በቀላሉ በኢኮኖሚ አሻጥርና ሴራ በሥውር በርቀት ቅኝ ሊገዟት በሚችሉበት ሁኔታና ይዘት ላይ ናቸው፣ እንጠንቀቅ፡፡ እንዴት የውስጥ ችግሮቻችንን እንደምንፈታ እየመከርን፣ እነሱንም  ከእኩይ ሥራቸው ልንገታቸው እንደምንችል የትግል ሥልታችንን እንፈትሽ፡፡

የውጭ ኃይሎች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የበላይነትን የመያዝ አዝማሚያቸው እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ከተራ ንግድ ጀምሮ እስከ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ድረሰ እየተቆጣጠሩት፣ ለዘመናት በተለያየ መንገድ ሊያንበረክኩትና ቅኝ ሊገዙት ያልቻሉትን ኢትዮጵያዊ ወደ ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት መረብ ውስጥ አስገብተው በዶላር ቁሌት እያሟሹት ነው፡፡

ዜጎች በግብርናና ማኑፋክቸሪነግ ኢንዱስትሪው፣ በትራንስፖርትና በሎጂስቲክስ፣ በኢንፎርሜሽንና በቴክኖሎጂ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ አናሳና ተገፊ እየሆኑ እንደመጡ የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ፡፡ በሰሞነኛው በኮንስትራክሽን ሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ውስጥ ባሉ ማኅበራት መሪዎች በኩል የሚሰጡ ማብራሪያዎች ይህንኑ ይጠቁማሉ፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሰርስረው በገቡ የውጭ ኃይሉ ዕገዛ ጭምር፣  በኢኮኖሚው ውስጥ ከሠራተኛው የኢኮኖሚ አቅም ጋር ተያይዞ እየተከሰተ ያለውን ቀውስ ለማሳወቅ የሠራተኛ ማኅበራት በሰላማዊ ሠልፍ እናሳውቅ ሲሉ ቢከለከሉም፣ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎቹ ግን ጉዳዩ ወደ ኢኮኖሚ ቀውስና ተገቢ ወዳልሆነ ፖለቲካዊ እንቀስቃሴ እንዳያመራ መንግሥትን በጉዳዩ ላይ እንምከርበት በማለት እየጎተጎቱ ነው፡፡

በእርግጥም በአጠቃላይ በኢኮኖሚያችን ዙሪያ ያለው ጤና ያጣ ይዘት ወደ ቀውስነት ሳይሸጋገር፣ አገራዊ መሠረት ያለው ምክክር ማድረግ ይገባል፡፡ የምክክር ኮሚሽኑ ሥራው ፖለቲካዊ ነውና ኢኮኖሚያዊ ምክክር ካልተደረገ፣ ሒደቱን እንደሚያቀጭጭበትና ውጤት አልባ እንደሚያደርግበት ተገንዝቦ ለኢኮኖሚው ምክክር ዕገዛ ቢያደርግ ይሻላል እላለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር የተቋማትን ሚና በሰፊው የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ፣ የፕሮግራምና የኢንስቲትዩሽን (ፖስፕኢ) ቀረፃ፣ ክለሳና አተገባበር ጋር አቆራኝቶ መፈተሸም ተገቢ ነው፡፡

ከላይ ከጠቃቀስኳቸው ከታማሚ ኢኮኖሚ ጠቋሚዎች ጋር ተያያዥነት ባለው ይዘትና ምክረ ሐሳባዊ አቀራረብ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ በእሑድ ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትሙ በርዕሰ አንቀጹ፣ ‹‹ጠንካራና አስተማማኝ ተቋማት በሌሉበት ውጤት መጠበቅ አይቻልም!›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ዘገባ፣ ‹‹…ሁሉንም ወገኖች የሚያግባቡ ጠንካራ ተቋማት መገንባት ከተቻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት አያቅትም፡፡ የጋራ ተጠቃሚነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ሲኖር የፖለቲካ ቀውሱን ማስቆም ይቻላል…›› ብሎ ምክር አዘል መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ርዕሰ አንቀጹ በይዘቱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በቀውስ ሒደት ላይ እንዳለ አመላክቶ፣ ይህ ሒደት እንዲኮለሽና ወደ ጤናማ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አቋም ላይ ይመለስ ዘንድ የተቋማት አደረጃጀትና አሠራር መሰተካካል አስፈላጊነትን የሚያመላክት ነው፡፡ ይህንን ርዕሰ አንቀጽ ተጠቃሽ ያደረግኩት ተቋም አንዱ የኢንስትቲዩሽን ጉዳይ አካል ሆኖ፣ ከኢንስትቲዩሽን ግንባታና አደረጃጀት አንፃር ከአገራዊ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም/ፕሮጀክት የተሰናሰለ ቀረፃና ትግበራ አስፈላጊነት ጋር ተካቶ መመርመር እንዳለበት ለማመላከት ነው፡፡

የፖስፕኢ ቀረፃና ትግበራን ከአጥፊዎች እጅ ማውጣት

በእኔ ትምህርታዊ ይዘትና ዕውቀት ምልከታና ክትትል ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖስፕኢ ቀረፃና ትግበራ፣ ከአጥፊነት (ባንዳነት) ነፃ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ቁጥጥር ውጪ እየሆነ መጥቷል፡፡ 

በበርካታ ትምህርታዊ መጽሔቶችና መጻሕፍቶቼ ላይ ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት የኢኮኖሚ ፖስፕኢ ቀረፃ፣ ግንባታና ትግበራችን መሠረት ማድረግ ያለበት ችግሮችን የመለየቱ፣ የመፍትሔ ሐሳቦችንና ዕርምጃዎችን የማፍለቁንና  አፈጻጸሙ መምራት ያለበት በባንዳነት በማናቸውም የውጭ ኃይል ባልተመለመሉ ኢትዮጵያውያን መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ የዛሬው የኢኮኖሚያችን ጤና ማጣት መንስዔና መጎልበት የኢኮኖሚ ፖስፕኢ ቀረፃና ትግበራ አመራር በውጭ ኃይሎች እጅ ውስጥ መውደቅ፣ ለዚህም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባንዳዎች መሣሪያነት ገዝፎ መገኘት ነው የሚል መላምታዊ ዕሳቤም አለኝ፡፡ ባንዳዎች ወረድ ብዬ በአኃዝ አስደግፌ በማብራራው የዶላር ክፍያ መጠን ተቅበዝብዘው የአገራቸውን ሉዓላዊነትና ደኅንነት ለውጭ ኃይሎች አሳልፈው ለመስጠት ደፋ ቀና እንደሚሉ ማስገንዘብ እሻለሁ፡፡

ስለኢትዮጵያውያን ፖለቲካ ባንዳዎች በበርካቶች ለበርካታ ዓመታት፣ በተለይም ከጣሊያን ተደጋጋሚ  ወረራ ጋር ተያይዞ ተጽፏል፡፡ በእኔ በኩል ስለኢኮኖሚና ፖለቲካ ባንዳዎች ቀደም ሲል በጻፍኳቸው መጽሐፍት ውስጥ ማብራሪያ ሰጥቼያለሁ፡፡ ወደኋላ ተመልሼ በማጣቀስ ስለባንዳ ትርጓሜና ማብራሪያ መስጠት የዚህ ጽሑፌ ዓላማ አይደለም፡፡ ለዚህኛው ጽሑፌ ግን በቅርቡ በዶ/ር ዓብይ ከተጻፈው መጽሐፍ ውስጥ የቀረበውን ትርጓሜ ለአንባብያን ማካፈሉን ተገቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ 

ዶ/ር ዓብይ በ2015 ዓ.ም. ባሳተመው ‹‹የመደመር ትውልድ›› መጽሐፍ በገጽ 79 ላይ ባንዳ ማለት ‹‹…በገንዘብ፣ በትርክት፣ በዕውቀት ወይም በሌላ ጉዳይ ተታሎ፣ አገሩንና ማንነቱን በክህደት አሳልፎ ለጠላት የሚሰጥ ማለት ነው፡፡ ባንዳነት ለራስ ክብር ያለመስጠት በሽታ ነው፤›› ብሎ ማብራሪያ አቅርቧል፡፡

የሦስቱ ካቢኔ ዓይነቶችና የባንዳዎች ሥራ

ዛሬ የውጭ ኃይሎችና ያሰማሯቸው ባንዳዎች የአገሪቱን ፖስፕኢ ቀረፃና ትግበራ ከመደበኛው ካቢኔ ቁጥጥር ውጪ ያደረጉት ይመስላል፡፡ መደበኛ ካቢኔውም ሆነ የግርዶሽ/ጥላ ካቢኔዎች የውጭ ኃይሎች መሣሪያና መጠቀሚያ ሆነዋል የሚል መላምታዊ ድምዳሜ ላይ እንድደርስም አድርገውኛል፡፡

የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖስፕኢ ቀራጮቹና አስተግባሪዎቹ የሥውር ካቤኒው አባለት ናቸው የሚል ትምህርታዊ ድምዳሜም ላይ ደርሻለሁ፡፡ የትምህርት ዝግጅቴ፣ የመማርና የማስተማር፣ እንዲሁም የማማከር ሥራ ልምዴ፣ እንዲሁም ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ከሚገኝ ጥበባዊ ግኝት አንፃር ለዚህ ድምዳሜ የሚያበቃ ይዘት ላይ ነኝ ብዬ ለማለትም እደፍራለሁ፡፡

ስለሦስቱ ካቢኔዎች ምንነትና መገለጫ አንባብያን በ2012 ዓ.ም.፣ ‹‹ኢኮኖሚው ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› በሚል ርዕስ ካሳተምኩት መጽሐፌ ከምዕራፍ አምስት ውስጥ ማብራሪያ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ይጠቅም ዘንድ በአጭሩ ግን ሦስቱ ፖለቲከኞች ያልኳቸውን ከሦስቱ ካቢኔዎች አደረጃጀት ጋር በማቆራኘት እንደሚከተለው አቅርቤአቸኋለሁ፡፡

አንደኛው በአገራችን የፖለቲካ ምኅዳር፣ ሥርዓትና ሕግ መሠረት በፓርቲነት ተደራጅተው በመንግሥታዊ ሥልጣንና የኃይል መንበር ላይ የተቀመጡ ፖለቲከኞችን የሚያመላክት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ የፖለቲካ ፓርቲ መንግሥት ሆኖ ያደራጀው የሚኒስትሮች ስብስብ ካቢኔ ‹‹መደበኛው ካቢኔ›› ነው ብዬ ገልጬዋለሁ፡፡

ሁለተኛው ከገዥው የፖለቲካ ፓርቲ ስብስብ ሌላ በተፎካካሪ ወይም ተቃዋሚ የፖለቲካ አደረጃጀት ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ቡድን/ፓርቲዎችን በጥቅሉ የሚገልጽ ነው፡፡ እነዚህ በቁጥር በርካቶች ሊሆኑ ቢችሉም፣ ከፖስፕኢ ይዘታቸው አንፃር ያለውን የመንግሥት ሥርዓትና የፖስፕኢ ይዘት በአብዛኛው የሚቃወሙና ሥልጣን ቢይዙ ጉድለትና ክፍተት አለባቸው የሚሉትን ፖስፕኢ ሊለውጡ ወይም ማሻሻያ ለማድረግ የሚሹ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለዚህ ሥራ ይበጀናል ብለውም በተለምዶ ‹‹የግርዶሽ/ጥላ ካቢኔ›› በእንግሊዝኛው አጠራር ‹‹ሻዶ ካቢኔ›› የሚባለውን ያደራጃሉ፣ የግርዶሽ ሚኒስትሮችንም ይሰይማሉ፡፡

ሦስተኛው ደግሞ በውጭ ኃይል፣ በዋነኛነት ፖለቲካዊ አሠራርን ለኢኮኖሚ ሥርዓት መቆጣጠሪያነትና የአገሪቱን ተፈጥሮአዊ ፀጋና ሀብት ለመበዝበዝ የሚደረግን ፖለቲካዊ አደረጃጀትንና አሠራርን የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ አደረጃጀት በውጭ አገሮች በተለይ በአደጉ ኢምፔሪያሊስት አገሮች፣ በእነሱ በሚዘወሩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና በድንበር ዘለል ኩባንያዎች የሚመራ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ያለው፣ በአብዛኛው ከአንድ አገር ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ውስጥ የተመለመሉና የሠለጠኑ የፖለቲካና  ኢኮኖሚ ባንዳዎችን ያቀፈ ስብስብ ነው፡፡ በአገር ውስጥም በሚሠራበት ጊዜ በርቀት በሥውር አገሮችን ቅኝ ለመግዛት በሚያስችለው አደረጃጀት፣ በህቡዕ፣ ወይም ‹‹ሥውር ካቢኔ›› አደረጃጀት የሚንቀሳቀስ ነው፡፡

በእኔ ግምትና እምነት ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ሥውሩ ካቢኔ›› እየጎለበተ፣ በሚከውናቸው ሴራዊ የፖለቲካ ሥራዎች አገር በቀል የሆኑትን የመደበኛውንና የግርዶሽ ካቢኔ አባላትን እንቀስቃሴ አኮለሽቶ፣ ሕዝቡ ትኩረቱን በውስጣዊ የፖለቲካ ትርምስና ግጭት ላይ እንዲያደርግ እየሠራ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አንዳንዴም የሃይማኖት ተቋማትም ለእሱ ፍላጎትና ጥቅም እንዲሠሩ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፖስፕኢ ቀረፃ፣ ክለሳና ትግበራ ለሥውር ቅኝ አገዛዝ እንዲያግዝ ማመቻቸት፣ ካልሆነም አገሪቷ እርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ትርምስ እንድትዳከም  በመሥራት ላይ ያለ ካቢኔም ነው፡፡

የውጭ ኃይል የዚህ ካቢኔ አባላቱ በተቻለው ሁሉ በመደበኛውም ሆነ በግርዶሽ ካቢኔ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ፣ አሊያም በአማካሪነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ በተለያዩ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችና ትልልቅ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተቋማት ውስጥ እንዲሰገሰጉ ተግቶ ይሠራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በግሉ ዘርፍ በግብርናና ማኑፋክቸሪነግ ኢንዱስትሪ፣ በአገለግሎት ዘርፍ በተለይም በንግዱ ኅብረተሰብ ውስጥ በኢንቬስተርነትና በአማካሪነት ስም የሚሰገሰጉ ከዳያስፖራው ኢትዮጵያዊ ክፍል የተመረጡ፣ የሠለጠኑና በፋይናንስ አቅርቦት የሚደገፉ አባላትን ያቀፈ ነው፡፡

በውጭ ኃይሎች በሥውር የሚደራጁ የካቢኔ አባላት በዓለማችን ባሉ ታዋቂ የአደጉ አገሮች የስለላ ድርጅቶች ጭምር ከፍተኛ ሥልጠና እንደሚያገኙ ከስለላ ጋር ተጎዳኝተው የሚጻፉ ጽሑፎች ያመላክታሉ፡፡ በዚህ መንገድ ከሠለጠኑ በርካታ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባንዳ ስብስብ መሀል የተመረጡና ወርኃዊ ክፍያቸውም በዶላር ሆኖ በብር ምንዛሪ ሲሰላ የትየለሌ የሆነ አባላት ብዛት በርካታ እንደሚሆን ይገመታል፡፡  ባንዳዎቹ በተነፃፃሪነት ከእነሱ ይበልጥ ዕውቀትና ልምድ ካላቸው ንፁህ ኢትዮጵያዊ  ሙያተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ከ30 እሰከ 50 እጥፍ በላይ ወርኃዊ ክፍያ የሚከፈላቸው ናቸው፡፡ በባንዳነት አገር ለመሸጥና ለማጥፋት የሚከፈላቸው ዋጋ ማለት ነው፡፡

ይህ ማለት በምሳሌያዊ አቀራረብ፣ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር የተጣራ ወርኃዊ ደመወዙ አሥር ሺሕ ብር ከሆነ፣ በአማካሪነት በዚያው ተቋም ውስጥ ያለ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል በውጭ ምንዛሪ በተሰላ የደመወዝ ምጣኔ በአማካሪነት የሚመደብ ባንዳ ቢያንስ ሦስት መቶ ሺሕ ብር በወር ይከፈለዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ፈጠራ ሳይሆን እውነት ነው፡፡ እንዲያውም በከፍተኛ ደረጃ በተቋማት አመራር ቦታ ላይ የሚቀመጡ በትውልድ ኢትዮጵያውያን በዜግነት የውጭ የሆኑ፣ አንዳንዶችም በዜግነትም ኢትዮጵያዊ ሆነው ከኢትዮጵያ መንግሥት ካዝና ሳይሆን፣ በዓለም የገንዘብና የመንግሥታቱ ድርጅቶች በኩል በፕሮጀክት ስም በሚዘጋጅ ፔሮል (የደመወዝ መክፈያ ሰነድ) የሚከፈላቸው የዶላር ክፍያ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የምንዛሪ ምጣኔ ሲሰላ ከስምንት መቶ ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ወርኃዊ ደመወዝ እንደሚሆን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አንዳንዶች ሲሾሙ ከእኛ፣ ማለት ከኢትዮጵያውያን ተቋማት ለምሳሌ ገንዘብ ሚኒስቴር ደመወዝ አልቀበልም ብለው ሲኩራሩ ይስተዋላል፡፡ 

እነዚህ ባንዳ አመራሮችና አማካሪዎች ከኢትዮጵያውያን የምርምር ተቋማት ሳይንቲስቶችና ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮቻችን ከሃያ ሰላሳ እጥፍ በላይ በሚሆን ክፍያ እየሠሩ፣ በሌላቸው ትምህርታዊ ዝግጁነትና ዕውቀት የአገሪቱን ፖስፕኢ ቀረፃ ሲመሩ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ መሰሉ ሥውር የባንዳዎች ስብስብና የካቢኔ አሠራር፣ ኮርፖራቶክራሲው እንደ ኢትዮጵያ ያሉትን፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ቅኝ ያልተገዙትን አገሮች ቅኝ ለማስደረግ ሌት ተቀን ይሠራል፡፡ ባንዳው እኔ ከሃያ ስምንት ዓመት በፊት ጀምሬ ለማሳወቅ እንደምጥርበትና እያብራራሁት ባለው በርቀት፣ በሥውር ቅኝ የመግዛት ሥርዓት ውስጥ ኢትዮጵያን ለማስገባት እየተከፈለው የሚሠራ ሥውር አገር አፍራሽ ኃይል ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ብዙ ለፍታ ያስተማረቻቸው የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ መሐንዲስ ይሁኑ ኢኮኖሚስት ወይም የማኅበረሰብ አገልጋይ ምሩቃን፣ በወረዳ ደረጃ ተመድበው በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሲሠሩ የሚከፈላቸው የተጣራ ወርኃዊ ደመወዝ አራት ሺሕ ብር ነው፡፡ በተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ ያለ በሥውር ቅኝ ገዥው የተመለመለና በዓለም አቀፍ ብዝኃና ሁለትዮሽ ድርጅቶች ከለላ ሥር የሚሠራ ባንዳ ግን፣ ከዚህ በመቶ እጥፍ የሚሆን ወርኃዊ ደመወዝ ሲከፈለው ይስተዋላል፡፡ የባንዳው ተልዕኮ ግን አገርን ማሳደግና ማልማት ሳይሆን፣ አገርን ማጥፋትና ለሁለንተናዊ ቀውስ መዳረግ ነው፡፡ ባለአራት ሺሕ ብር ደመወዝተኛው አገራዊ ፖስፕኢውን እንዲተገበር ደፋ ቀና ሲል፣ ባለ አራት መቶ ሺሕ ብር ደመወዝተኛው (አምስት ሺሕ ዶላር በወር) ተከፋዩ ባንዳ ደግሞ አገራዊ ፖስፕኢው እንዳይተገበር፣ የውጭ ኃይሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያደርገው አገራዊ ተቋማትን የማፍረስ፣ ዜጎች በአገሪቷ ልማት ዘላቂነት ላይ የመሪነት ሚና እንዳይኖራቸወ በሚያደርግ የሴራ ተልዕኮ ላይ ተጠምዶ ይንቀሳቀሳል፡፡

መደምደሚያ

በእኔ ሙያዊ ምልከታና የመረጃ ክትትል ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የገጠማት የኢኮኖሚ ጤና ችግር መንስዔዎቹና አጎልባች ተውሳኮቹ፣ በአገሪቱ ውስጥ የተሰገሰጉ እኩይ ተልዕኮ ያላቸው የውጭ ኃይሎች አገራችንን ለመግዛት በያዙት ዕቅድና በአተገባበሩ በሚከሰቱ ኩነቶች፣ እንዲሁም ከዳያስፖራው ኢትዮጵያዊ ሆነ በአገር ውስጥ ካለው የተመለመሉ፣ የሠለጠኑና የተሠራጩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ባንዳዎች መሰሪ ሥራ ላይ የተጠነሰሱና የሚተገበሩ ናቸው፡፡ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያለን ንፁህ ኢትዮጵያውያን ይህን ክስተት ተከታትለን ተገቢውን የእርምትና የማስተካከያ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ 

በተለይ አገራችን የገጠማትን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ችግር ከውጭ ኃይሎች እኩይ ሥራና ሴራ ብሎም ተጠቃሚነት አግልለን ችግሮቹ በራሳችን የእርስ በርስ አለመግባባትና ግጭቶች ምክንያት ብቻ የሚከሰቱ አድርገን የምናይ ከሆነ፣ ኢኮኖሚያዊ አወዳደቃችን አስከፊና ሰብዕናችንን ከሰውነት በታች አውርደን ለቅኝ ገዥዎች አሳልፈን የሚያሰጥ ይሆናል፡፡ ይህ በምግብ፣ በመታረዝና በመጠለያ ድህነት ውስጥም ሆነን በነፃነት አብስለን የምንበላትን ቂጣ ወይም የምንቆረጥማትን ቆሎ አሳጥቶን፣ ሰላማዊ እንቅልፍ እንዳንተኛ ወደሚያደርግ ደረጃ እንዳያደርሰን መጠንቀቅና ነቅተን መታገል አለብን፡፡

በተለይ ትምህርታዊ መሠረት ያለንና የሙያ ባለቤቶች የሆንን ዜጎች፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የተሰገሰጉ የኢኮኖሚ ባንዳዎችን ነቅተን እንከታተል፡፡ ከቢሯችን አካባቢም ሆነ ራቅ ብለው ባሉ ሆቴሎች በእጃቸው በገባ የዶላር ምንዛሪ ጋባዥ መስለው ሊያዘናጉን የሚፈልጉትን አማካሪ ባንዳዎች ሥራንም  በጥሞና እንከታተል፡፡ የአገሪቱን ፖስፕኢ ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያነት ብቻ አንዳያስደርጉብን ነቅተን እንታገላቸው፡፡ በዚህ ሒደትም የሚዲያው ዘርፍ ሚና ይስተካከል፡፡

የሚዲያ ተቋማት የባንዳዎችና የእነሱ ከፋይ የውጭ ድርጅቶች የሴራና እኩይ ተልዕኮ ሰለባ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ውስጣዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ስንታገል፣ ‹‹የሥውር ካቤኔውን›› ስትራቴጂካዊ አካሄድ በማጋለጥ አገርን ከኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጥፋትና ውድመት እንድትድን እናድርግ፡፡ ትኩረታችን በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዓውዶች ላይ ይሁን፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የግብርና ኢኮኖሚስት፣ ከ42 ዓመት በላይ በማስተማር፣ በምርምርና በማማከር ልምድና ተሞክሮ ያካበቱ፣ የተለያዩ አካዳሚያዊ ጽሑፎችንና መጻሕፍት የጻፉ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...