Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየለውጥ ኃይሉ የመጣበትን መንገድ ይፈትሽ

የለውጥ ኃይሉ የመጣበትን መንገድ ይፈትሽ

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ     

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ከሞላ ጎደል በ‹‹ፈተና የተሞላ›› የሚባል ነው፡፡ በአንድ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ዋስትና ማጣት፣ ግጭቶች፣ ሥርዓት አልበኝነቶችና የተለያዩ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ድኅረ ጦርነት መልሶ መገንባትና ወደ ነባሩ ሁኔታ መመለስ የሚሹ በርካታ ፍርሥራሾችና የሥነ ልቦና ጉዳቶች እንደተዳፈኑ ነው፡፡

የመንግሥት ሕገወጥ ቤቶችን በየአካባቢው የማፍረሱ ዕርምጃና የኑሮ ውድነት መባባስ፣ መቼና እንዴት እንደፀደቁ የማይታወቁ የቋሚ ንብረት ግብር፣ የስም ማዞሪያ ክፍያዎችና መሰል ደንቦች በማኅበረሰቡ ላይ መጫንም ሌላ ፈተና ሆነዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ሰሞኑን የገዥው ፓርቲ ብልፅግና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጉባዔውን ያደረገው፡፡ እናም የአገር መሪዎች ያጤኑት ዘንድ ከትህትና ጋር አንዳንድ ጉዳዮችን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡

አሁን ያለው ደመና በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አገራዊ ለውጥ ከመጣ ወዲህ ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥም እየተደማመረ የመጣ ነው፡፡ እንደ አገር የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማኅበረ ባህላዊ ለውጥ እንደሚንፀባረቅበት የታሰበው አዲስ ምዕራፍ ሲመጣ፣ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ‹‹ይህ ዓይነት ደመና ይፈጠራል፣ ቢፈጠርም እየተባባሰ ይቀጥላል›› የሚል እምነት ያለ አይመስልም ነበር፡፡ ምንም እንኳን ለውጥ ሲመጣ ተከትሎ የሚመጣ ፈተናና የፖለቲካ ጥቅም ግጭት መኖሩ አይቀሬ ቢሆንም፡፡

ለውጡ ኢትዮጵያን ወደ ሦስት አሠርት ዓመታት ገደማ ያስተዳደረው ኢሕአዴግ በተሃድሶው ባካሄደው የአመራር መቀያየር ብቻ አልነበረም የመጣው፡፡ ይልቁንም ብዙኃኑ ሕዝብ፣ የተለያዩ ተቃዋሚ ኃይሎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችና ሚዲያዎች ጭምር የለውጥ መሻቱን በማቀጣጠላቸውና ዕውን እንዲሆን በመታገላቸውም ነበር፡፡ ያም ሆኖ በሒደቱ መመልከት እንደታቻለው፣ በለውጡ አስፈላጊነት ላይ የተሰባሰቡ ኃይሎች ሁሉ በቀጣዩ ሒደት ላይ ስምምነት ሊኖራቸው አልቻለም፡፡ እንዲያውም በመካረር ውስጥ የሚብሰከሰክ የጥቅም ግጭትና አለመደማመጥ ነው እያረበበ የመጣው ማለት ይቻላል፡፡

አዳዲሶቹ የፖለቲካ ኃይሎች በኢሕአዴግ ውስጥ ያረጀውን፣ ወደ ጥላቻና መገፋፋት የተለጠጠውን አስተሳሰብ ለመቀየር መሪ ሲጨብጡ ከጎናቸው የነበረው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡ ለዚህ ቅቡልነት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ከአብዛኛው የለውጥ ኃይሉና አመራሩ ምንም እንኳን ሲወቀስ በኖረው ኢሕአዴግ ውስጥ የቆዩ ቢሆንም የአገራዊ አንድነትን፣ የፍቅርንና የይቅር መባባልን ዓርማ በማንሳቱ ነበር ‹‹ለውጥማ አለ›› የሚለው ወገን እየበዛ የመጣው፡፡ በተግባር ግን አስተሳሰቡ ገፍቶ የተነገረውን ያህል መራመድ ባለመቻሉ በየቦታው ተገዳዳሪው እንደ አሸን መፍላቱን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

ቀደም ሲል በአገር ደረጃ የነበሩ ኢኮኖሚያውም ሆኑ ማኅበራዊ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ለውጡ በቀዳሚነት በሕዝብ የተፈለገው የፖለቲካ ጥያቄዎችን እንዲፈታ ነበር፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ ምኅዳሩና የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ የወደቀው ጫና እንዲነሳ፣ ጠንካራ አገረ መንግሥትና የሕዝቦች አንድነት እንዲመለስ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታና በአመለካከትም ሆነ በዕድሜ ያሉትን ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን እንዲያጠብ የሚረዱ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱም የብዙዎች ምኞት ነበር፡፡ የውስጥ ጥገኝነቱ የተመሠረተው በእነዚሁ ሳንካዎች ላይ በመሆኑ ግን ገደሉን መሻገር እያዳገተ መጥቷል፡፡

በአገር ደረጃ የተጀመሩ የኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በፍትሐዊ ሥርጭት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ እንዲሁም እንደ ኢፍትሐዊነት፣ አድሏዊነት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ብልሽቶች እንዲታረሙ ነበር፡፡

ለዚህም በሒደት ቅቡልነት ያለው አካታች፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ መንግሥታዊ ሥርዓት መፍጠርን ሕዝብ በጉጉት ሲጠብቅም ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን አሁንም መንግሥት የአገር ሰላም ማረጋጋጥ እንደተሳነው አካል በብሔርተኝነት፣ በፀረ ዴሞክራሲያዊነትና በመልካም አስተዳደር ብልሽት የሚተች ከመሆን አልዳነም፡፡ ቅቡልነቱም ላይ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል፡፡

በእርግጥም በለውጡ ጅማሮ ሰሞን የተስፋ ብርሃን ለመፈንጠቃቸውም ሆነ፣ ለሕዝቡ ተስፋና ጉጉት ከፍታ ሌሎች ምክንያቶችም ይኖራሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የለውጡ ኃይል በአመለካከት ልዩነት ሰበብ የታሰሩ ዜጎችን መፍታቱ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበራዊ አንቂዎች የሐሳብ ነፃነት እንዲያገኙ፣ የተጋጩ፣ ጫፍና ጫፍ የቆሙ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገራቸው እንዲገቡና እንዲቀራረቡ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ጉዳያቸውን እየመከሩ ከእነ ልዩነታቸው በነፃነት እየተንቀሳቀሱ፣ በአገራቸው ጉዳይ ያገባኛል የሚሉበት ጊዜ እንዲመጣ፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር አገርን የዘረፉ እንዲጠየቁና የሕዝብ ሀብትም እንዲመለስ ጥረቶች ተጀማምረው ነበር፡፡ ፋታ ተገኝቶ ዳር መድረስ የቻለ አንድም ተግባር ግን የለም፡፡

ሌላው ቀርቶ ከኤርትራ ሕዝብና መንግሥት ጋር የነበረውን ፍጥጫ በማስወገድ መቀራረብ መጀመሩ፣ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋርም በሰጥቶ መቀበል መርህና በመስማማት በጋራ ተጠቃሚ ለመሆን አዳዲስ ዕርምጃዎች ታይተው ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ የለውጡ አመራር አኅጉራዊ ህልሙን በማንፀባረቅ ብቻ ሳይወሰን፣ ለመላው ዓለም ዜጋ ተኮርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ እንደሚከተል አቋሙን ማንፀባረቁ ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን፣ ሌላው ዓለምም አጋርነትና ዕውቅና እንዲሰጠው ገፋፍቶታል (የጠቅላይ ሚኒስትሩን የኖቤል ሽልማት ያስታውሷል)፡፡

ከዚያ ወዲህ ግን እንደታሰበው የለውጡ ጉዞ አልጋ በአልጋ መሆን አልቻለም፡፡ በተለይ በርካታ ገለልተኛ ወገኖች እንደሚወቅሱት፣ መንግሥት በቀዳሚነት ወደ አገር ውስጥ የገቡትን የታጠቁም ሆነ ያልታጠቁ ፖለቲከኞች የሚመሩበት ደንብ ወይም ስምምነት ነድፎ አለመተግበሩ ቀዳሚው ችግር ነበር፡፡ ሲቀጥል ለውጡ የተፈለገበትን ምክንያት በፍላጎት ዳሰሳም ሆነ ሕዝቡን በየደረጃው በማነጋገር ለይቶ ፈጥኖ ወደ ውይይትና ምክክር አለመግባቱን በድክመት ያነሳሉ፡፡ ሲሰልስ ደግሞ በርካታ በእንጥልጥል የተያዙ ጉዳዮችን (የወሰን፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የማንነት፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን፣…) በይደር ወደ ራስ ፍላጎትና የአንድ ወገን ጥያቄ መመለስ ማዘንበሉ ቅሬታን ማባባሱ ይነገራል፡፡

በዚህ ላይ በሕዝብ ግፊትና በሥርዓቱ ውስጥ ባሉ ለውጥ ፈላጊዎች የተጀመረው አዲስ ዕርምጃ፣ ጥቅሙን ያሳጣውና ያልተዋጠለት ሕወሓት ዋነኛው ተገዳዳሪ እንደሚሆንና ከፍተኛ እስከሚባል አውዳሚ ጦርነት እንደሚገባ ተንብዮ በቂ ጥንቃቄ ባለመደረጉ ከፍተኛ ዋጋ መከፈሉ በአሉታዊነት ይነሳል፡፡ በአስከፊው ጦርነት በመቶ ሺዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተንገላተዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቃይና ለተረጂነት ተጋልጠዋል፡፡ በግርድፍ ግምት 1.5 ትሪሊዮን ብር የሚገመት የአገር ሀብት ለጦርነት ተማግዷል፡፡ ለስላሳና ሰላማዊ የተባለው ለውጥ ዛሬም ባልተረጋጋ አገራዊ ሁኔታ ውስጥ እንዲቃትት ተዳርጓል፡፡

ዛሬ ላይ ብዙዎች እንደሚናገሩት በርከት ባሉ የአገራችን ከባቢዎች ሰላምም ሆነ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ዋስትና የለም፡፡ እንደ ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ግሽበት (ዓለም አቀፍ ሁኔታውም የራሱ ጫና እንዳሳደረ ሳይካድ)፣ ተረጂነትና ተፈናቃይነት ተባብሰዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የሕዝቦች አብሮ የመኖር ባህል ተሟጦና ተሸርሽሮ ጫፍ ላይ የደረሰው ቀደም ባሉት ዓመታት በተነዙ ትርክቶች ቢሆንም፣ ከለውጡ ወዲህ ቀላል የማይባሉ የሕዝብ መከራና ሥቃዮች ተስተውለዋል፡፡ አንዱ ሕዝብ ከሌላው ጋር በጋራ አብሮ ለመኖር የተሳነው እርስ በርሱ የሚገፋፋ፣ የአንድ አገር ልጆች በሐሳባዊ ክልል ታጥረው የሚሳደዱ፣ ዜጎችም ከማንነት ፍጥጫ ያልወጡበት አስከፊ ንፍቀ ክበብ እንዳረበበ ነው፡፡ እንዴትና ለምን ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው፡፡

ይህንን አስቸጋሪና አስከፊ ሁኔታ በማስወገድ አገር በተረጋጋና ዋስትና ባለው ሰላምና ዴሞክራሲ እንድትቀጥል የለውጥ ኃይሉ ብቻ አልነበረም ኃላፊነት ያለበት፡፡ እንደ ሕዝብም ከዛገውና ከላሸቀው አስተሳሳብ ተላቆ በሕግና ሥርዓት እየተመሩ መኖር በተገባ ነበር፡፡ ፖለቲከኞቻችንና የማኅበራዊ አንቂዎች የዘውግ ትርክትና የብሔር ፉክክርን፣ በተለይም ከመጠራጠርና ከማጋጋል ይልቅ አብሮነትን፣ የግልጽነትና የተጠያቂነትን፣ ብሎም የፍትሐዊነት አጀንዳን ማራመድ በጀመሩ ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ በመግባባት መንፈስ ኢመደበኛ ኃይሎች በሁሉም አካባቢ ታጥቀው እንዲንቀሳቀሱ ሊፈቀድ አይገባም ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት የሕዝብ ደኅንነት ማረጋጋጥ ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ ሁሉም መተባበርና መተማመን በቻለ ነበር፡፡ ይህ አለመሆኑ ነው አሳሳቢው ችግር፡፡

እንደ አገር የመጣንበትን ክፉ ጊዜ ለመሻገር መንግሥትም ፈራ ተባ ሳይል ለሕዝቦች አብሮነት፣ ለብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ፣ ብሎም ፍቅርና አንድነት አቅሙን አሟጦ መትጋት ነበረበት፡፡ ገና ሰፊ ግንዛቤና የጋራ እምነት ያልተያዘበትን የመደመር አስተሳሳብ በጥቂት መሪዎች አንደበት ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ገዥው ፓርቲ (ብልፅግና) ሰዎች አፍና ልብ ውስጥ በማስረፅ ወደ ሕዝብ ከማውረድ በፊት በተግባርም የጋራ አገር ግንባታ ሒደቱን የሚያሳዩ ዕርምጃዎችም መጠናከር ነበረባቸው፡፡ አሁን እንደሚታየው ግን የብሔርና የሃይማኖት ፖለቲካ ነጋዴዎች መሳሳብና መምታታት ነው አየሩን ሞልቶት ያለው፡፡ ይህ አሉታዊ አካሄድ ካልተገታ ደግሞ ዘላቂ ሰላምም ሆነ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ዕውን መሆን አይችልም፡፡

ለውጡ ሲጀምር ሌላው ቀዳሚ አጀንዳ የነበረው አዲሱ ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ ኢሕአዴግም በተሃድሶው ይል እንደነበረው የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በየአካባቢው ያለው ሥራ አጥነትና ድህነት ትልቁ አገራዊ ፈተና ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ከ25 ቢሊዮን ዶላር (አሁን 28.5 ቢሊዮን መድረሱ ይነገራል) በላይ ዕዳ የሚያናጥጥባት፣ ዴሞክራሲ ከስም ውጪ አንዳች ትርጉም የለው አፈጻጸም ያልታየበት፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተጨፈለቁበት፣ በመጨረሻም ኢፍትሐዊነትና ምዝበራ እየነገሠባት የመጣች አገር እንደሆነች ቁልጭ አድርጎ መታየቱ በፍጥነት እንዲቃለል ነበር፡፡ እናም እንደ ገዥ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግሥት እነዚህ ወሳኝ ተግዳሮቶች ‹‹እንዴት በሌላ አጀንዳ ሊጠለፉ ቻሉ?›› ብሎ መፈተሽ ይገባል፡፡ ነቅቶ ማረምም ግድ ይላል፡፡

ወሳኝ የሆኑ አገር የማቆም መሠረቶች (በተለይ ሰላምና ደኅንነት) ከተጣሉ በኋላ/ወይም፣ ጎን ለጎን ደግሞ በአገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታውን ቢያንስ በሥራ ላይ ካለው ሕገ መንግሥት አንፃር መተግበርም አስፈላጊ ነው፡፡ እርግጥ እዚህ ላይ በርከት ያሉ መልካም ጥረቶችና ዋስትና የተሰጠቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ብቅ ብቅ ያሉ ቢሆንም፣ ስለምን የተገዳዳሪ ፖለቲከኞች የተፎካካሪነት ሥነ ልቦናና ብቃት ተዳክሞ ቀረ የሚለው ተጠየቅ አሁንም እንደተንሰራፋ ነው፡፡ የፖለቲካም ሆነ የለውጥ መሻት ቋንቋው መሣሪያና ኃይል ሆኖ የመቀጠሉ ዳፋስ የት ሊያደርስ ይችላል ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

እውነት ለመናገር በኢሕአዴግ 27 ዓመታት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ቢቀነቀንም፣ ሁሉም ሕዝብ የሚተማመንባቸው የምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶችና ገለልተኛ የፀጥታ ተቋማት ካለመኖራቸውም በላይ፣ ገዥው ፓርቲ በሁሉም መስክና መንግሥታዊ ክንፍ እጁን በሰፊው ጭኖ እንደነበር አይረሳም፡፡ በመሆኑም ስለዴሞክራሲ ቢያወራም ውጤት ሊያመጣ ካለመቻሉ ባሻገር፣ ጭራሽ ሥርዓቱ የደከመባቸውን አንዳንድ ሥራዎች ሁሉ ዋጋ የሚያሳጣ መጠልሸት ደርሶበት ነበር፡፡ ታዲያ አሁን ላይ ካለፈው ታሪካዊ ስህተት ትምህርት ተወስዶ የጋራና ዴሞክራሲ ባህል የሚታይባት አገር ለመገንባት ለምን አልተጀመረም? እግር መጎተቱንስ ምን አመጣው? ማለትም ይበጃል፡፡

እስካሁን እንደ አገር ተቃዋሚ ፓርቲ ሲባል ጥቂት ጉምቱና ዕድሜ ጠገብ ምሁራንን ብቻ ወይም የፓርቲ አመራሮችን እንጂ መዋቅራዊ ጥንካሬዎችን፣ የአባላት ብዛትና ቁርጠኝነትን፣ የጠራ የፓርቲ ስትራቴጂና ማኒፌስቶን ማግኘት እንደ ህልም የማይጨበጥ ሆኖ ነበር የቆየው፡፡ በምንገኝበት ሁኔታም መዳከም እንጂ፣ መሻሻል ስለመታየቱ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም፡፡ እንዲያውም የፖለቲካ ምኅዳሩን ፅንፈኞች፣ ገታራ የዩቲዩብ ፖለቲካ ነጋዴዎችና አፍራሽ ኃይሎች ናቸው የሚራወጡበት ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ይህንን ቀውስ አርሞና አዳክሞ ሕጋዊና የሠለጠነ ፖለቲካ ማዳበርም የሁሉም ድርሻ ነው፡፡

ለአብነት ያህል ከቅርብ ወቅት ወዲህ እንደምንመለከተው በትግራይና በምዕራብ ኦሮሚያ ካለማቋረጥ የቀጠለው ግጭትና የሰላም ዕጦት አንሶ፣ በአማራ ክልልም የግጭት መንፈስ እየታየ መሆኑ የአባባሉ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ዜጎች በየትኛውም መንገድ ሐሳባቸውንና ፍላጎታቸውን በተደራጀ፣ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲያራምዱ ሁኔታዎች መመቻቸት ያለባቸውን ያህል፣ ሕግና ሥርዓትን የማክበር ግዴታም አለባቸው፡፡ ይህን ወደ ጎን ብሎ ወደ ግጭትም ሆነ መተራመስ መግባት ግን ተያይዞ ከመጠፋፋት ያለፈ ፋይዳ የለውም፣ ውጤቱም እጅግ አደገኛ ነው፡፡ እናም መንግሥት ለቃሉ የሚታመንና ጠንካራ ሕዝብም አዳማጭና አገር ወዳድ ሆኖ መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡

በመሠረቱ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ የዓለም አገሮችም አንደሚታየው ለፓርቲ ፖለቲካ ተወዳዳሪነት መዳከምና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጨንገፍ፣ እንዲሁም ለጥላቻና ለተካረረ የፖለቲካ መስተጋብር መስፈን ዋነኛ ተጠያቂዎች አምባገነን መንግሥታት ናቸው፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የዕድገት ደረጃ አምባገነንነትንና የብዝበዛ መዋቅርን መቀየር መቻል፣ ወይም ትውልዱን የሚመጥን ለውጥ ማስመዝገብ ወሳኝ ዕርምጃ አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በአገራችን ለመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማበብ አዲሱ አመራር ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና እኛም እንደ ዜጋ የተናጠልም ሆነ የጋራ ርብርብ ማድረግ የታሪክ ግዴታችን መሆኑ ሊጤን ይገባል፡፡

መንግሥትም አገር በምትገኝበት ደረጃ ባለፉት አምስት ዓመታት ከታዩ መልካም ጎኖች በላይ ድክመቶችና የለውጥ መሻት እያንገዳገዳቸው ያሉ ሥራዎችን ለይቶ፣ የተጣመሙትን ማቃናት የሚያስፈልገው ለዚሁ ነው፡፡ መንግሥት ሁሉንም ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ መመለስ ባይችል እንኳን፣ የሕዝቡ መብቴ ይከበርልኝዋስትና ይሰጠኝጥርጣሬዬ ይገፈፍልኝ መሰል ትክክለኛ ጥያቄዎችን መመለስና አቅም በፈቀደ መጠን በጠንካራ የድርጅት ውስጠ ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ በማተኮር፣ በሁሉም አካባቢዎች ዋስትና መስጠት ይኖርበታል፡፡

ችግሮችን በፀጥታ ኃይልና በመሣሪያ ብቻ ለመፍታት መሞከርም ተደጋግሞ እንደታየው ኪሳራው ከባድና አደገኛ ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ተደማምጠውና ከመንግሥትም ጋር ተነጋግረው መዋል ማደር ካልቻሉ፣ እኳንስ ኢትዮጵያን ያህል ሰፊና ብዝኃነት የሞላበት አገር ጂቡቲንም በጥበቃ ማስተዳደር አይቻልም፡፡ ስለሆነም የትኛውንም የውስጥ ችግር ለመፍታት የሚያስፈልገው ውጫዊ ሰበብ መደርደር ወይም የፖለቲካ ሽኩቻ ማቀጣጠል ሳይሆን፣ ከሕዝብ ጋር በመሆን ዘላቂና ተከታታይ፣ እንዲሁም ትውልዱንና ወቅቱን የሚመጥን መፍትሔ ማፈላለግ ብቻ ነው፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ዘግይቶ ወይም በድሮ በሬ ለማረስ በመሞከሩ ተዳክሞ ለመቀጠል መሞከር ሕዝብ እንዲንገሸገሽና እንዲቆጣ ይገፋል፡፡ የአገርንም ጥቅምና ህልውና ለአደጋ ማጋለጥ ይከተላል፡፡ በተለይ በንግግር የሚፈጠረውን ግርግር ተጠቅመን፣ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አደፍርሰን፣ የዓረቡን ዓለም የመፍረስ አብዮት ወይም የአፍሪካውያንን ቀውስ በኢትዮጵያ ዕውን እናደርጋለን የሚሉ ተስፈኞች አገሪቱን እንዲፈነጩባት ያደርጋል፡፡

በአጠቃላይ እንደ መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ በአገሪቱ የተለያዩ ማዕዘናት የሚከሰቱ ተደጋጋሚ ችግሮችን ፈጥኖ ፖለቲካዊ መፍትሔ በመስጠት፣ አስተማማኝ ሥርዓት ለመገንባት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የወሰደውን ያህል ጊዜና ጉልበት ቢያባክንም፣ ሁሉን አቀፍ ውይይትና መተማመን ብሎም የለውጥ ዕርምጃ መውሰድም ብልህነት ነው፡፡

የአገሪቱ መንግሥት ጠንካራና ሁነኛ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ ነው ሊባል የሚችለው፣ ችግሮች ሲፈጠሩ በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት አቅም ያለው አስተዋይ መንግሥት በመሆኑ ወይም ሁሉንም የወከለ ነው በመባሉ ብቻ ሳይሆን፣ ከትናንት የተሻለች አገርን ወደ መገንባት መሸጋገር ሲችልም ነው፡፡ እናም ብልኃትና ጥንቃቄ ይቅደም እላለሁ፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...