Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ ዛሬ ሥራ ይጀምራል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ ዛሬ በይፋ ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

ከስምንት ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን ይዞ የተቋቋመው ራሚስ ባንክ፣ ዛሬ ሥራ የሚጀምረው በስድስት ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታልና በሁለት ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ነው፡፡

ራሚስ ባንክ በይፋ አገልግሎቱን እንደሚጀምር በማስመልከት ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ባንኩ ከወለድ ነፃ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ይዞ እንደሚቀርብ አስታውቋል፡፡

ራሚስ ባንክ የሥራ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንከ ከወሰደበት ጊዜ ጀምሮ የተሟላ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን አደረጃጀትና አስፈላጊውን በሰው ኃይል ቅጥር፣ በፖሊሲና በአሠራሮች ዙሪያ ዝግጅት ሲያደርግ፣ ቅርንጫፎችን ሲያዘጋጅና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የራሚስ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብዱልጀዋድ መሐመድ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ቀልጣፋና ከጊዜው ጋር የሚሄድ የተሟላ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ኮር ባንኪንግ ሲስተም ከሸሪዓና የፋይናንሻል አካውንቲንግ መመዘኛ ደረጃ ጋር ተስማሚ መሆኑ ከተረጋገጠው የማል ኮር ባንኪንግ ሲስተምን ማዕከሉን ሲንጋፖር ካደረገው አዜንቲዮ ኩባንያ ግዥ በመፈጸም ለሥራ ዝግጁ መደረጉን ባንኩ አስታውቋል፡፡

ባንኩ ለዋና መሥሪያ ቤት የሚሆን ባለ ዘጠኝ ወለል ሕንፃ በቦሌ ዋናው መንገድ ፍላሚንጎ አካባቢ ከሚገኘው ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት ላይ ግዥ የፈጸመ ሲሆን፣ በዚሁ ሕንፃ ላይ አገልግሎቱን የሚጀምር መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ራሚስ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በምሥራቅ አፍሪካ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ማዕከል የመሆን ራዕይ አንግቦ የተነሳ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዓሊ መሐመድ ዓሊ፣ ይህንኑ ራዕይ ለማሳካት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ቀጣይነት ያለው የንግድ ዕድገት ላይ ትኩረት በማድረግ በሸሪዓ መርህ ላይ የተመሠረተ የተሟላ የባንክ አገልግሎት በመላው አገሪቷ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከባንኩ እሴቶች መካከል የዋስትና ማስያዣ የሌላቸውንና የመንቀሳቀሻ ካፒታል እጥረት ያለባቸውን ሰዎች ከንግድ ሥራ ጋር በሽርክና ማገናኘት የሚገኝበት ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የሀብት ክፍፍልና የገቢ አለመመጣጠን ለመፍታት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ተብሏል፡፡

ባንኩ ወደ ሥራ ሲገባ ዛሬ በሚመረቀው ዋና መሥሪያ ቤቱ ውስጥ የሚከፍተውን ቅርንጫፍ ጨምሮ በ20 ቅርንጫፎች ሥራውን በመጀመር በቀጣይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 50 ለማሳደግ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ መስጠት ከጀመሩበትና ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ከተቋቋሙ ወዲህ ከተቀማጭ ገንዘብ የሚያሰባስቡት ገንዘብ የጨመረ ቢሆንም፣ ፋይናንስ ያደረጉት ዝቅተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡

ከዚህ አንፃር ከወለድ ነፃ የሚሰበሰበውን ገንዘብ መጠን ያህል ፋይናንስ እየተደረገ ባልሆነበት ሁኔታ ራሚስ ባንክም እንዲህ ያለው ነገር እንዳያጋጥመው ምን የተለየ ነገር ያደርጋል? ለሚለው ጥያቄ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ዓሊ ለዚህ በተለየ መንገድ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ወደ ሥራ የገባነው ኢንዱስትሪውን በሚገባ በማጥናት በመሆኑ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚያስችል አሠራር ስለሚኖረን የምናሰባስበውን ተቀማጭ ገንዘብ በሚገባ ፋይናንስ ለማድረግ እንችላለን›› ብለዋል፡፡

‹‹የተዘጋጀንባቸው የተለያዩ አገልግሎቶች አሉን›› ያሉት የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብዱልጀዋድ በበኩላቸው፣ በወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ ማዕከል ለማድረግ እንደሚችሉ፣ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አሠራሮችን ቀርፀው ወደ ሥራ የሚገቡ በመሆኑና በኢንዱስትሪው ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚያስችሉ ዕድሎች እንዳሉም አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለአገርም ሆነ ለዓለም የአጭር ጊዜ ዕድሜ ያለው በመሆኑ፣ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ማግኘት ከባድ ስለመሆኑ በዚሁ መግለጫቸው ላይ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ይህንን ክፍተት ከመቅረፍ አኳያ ባንኩ እየሠራ ያለው ሥራ እደተጠበቀ ሆኖ አሁን ላይ ለታሰበው አገልግሎት በተቻላቸው መጠን ባለሙያዎችን አሰባስበው የሚጀምሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን ለማጎልበት መሠራት ካለባቸው ሥራዎች  መካከል በዋናነት ስለአገልግሎቱ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ በመሆኑ ከዚህ አንፃር ራሚስ ባንክ በምሥረታ ሒደት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሳይቀር ይህንን ሥራ ሲሠራ መቆየቱንና ብዙ ደንበኞችን ማፍራት የመቻል ዕድሉ ሰፊ እንደሚሆንም ተነግሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በመስኮት ደረጃ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ 14 ባንኮች ያሉ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ዘምዘም፣ ሒጅራና ሸበሌ ባንኮች ናቸው፡፡

ዛሬ ወደ ሥራ የሚገባው ራሚስ ባንክ፣ አራተኛው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ሲሆን፣ ከአራቱ ባንኮች ውስጥ ሸበሌ ባንክ ከሌሎች በተለየ ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ተደራጅቶ ወደ ሥራ የገባ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

እነዚህ በመስኮት ደረጃና ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡት ባንኮች በ2015 የሒሳብ ዓመት ዘጠነኛ ወር መጨረሻ ላይ ያሰባሰቡት አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ከ163.7 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች